‘ቃሉን በደስታ የሚያደርጉ’ ሰዎች
“ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።”—ያዕቆብ 1:21, 22
1. የ1996 የዓመት ጥቅሳችን እንዴት ሊታይ ይገባል?
“ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ።” ይህ አጭር አነጋገር ኃይለኛ መልእክት ይዟል። ይህ ጥቅስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው “የያዕቆብ መልእክት” የተወሰደ ሲሆን የ1996 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ በመሆን ዓመቱን በሙሉ በመንግሥት አዳራሾች ውስጥ ተሰቅሎ ይታያል።
2, 3. ያዕቆብ በስሙ የተሰየመ ደብዳቤ መጻፉ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
2 የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የነበረው ያዕቆብ በጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጎላ ያለ ቦታ ነበረው። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ አንድ ጊዜ ለያዕቆብ በግል ተገልጦለት ነበር፤ ከዚያም ለሁሉም ሐዋርያት ተገለጠላቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:7) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ በተአምር ከእስር ቤት ሲፈታ ተሰብስበው ለነበሩት ክርስቲያኖች “ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሩ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 12:17) ያዕቆብ ሐዋርያ ባይሆንም እንኳ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የአይሁድን እምነት መከተል የጀመሩ አሕዛብ መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው የሚገልጽ ውሳኔ ባስተላለፉበት የአስተዳደር አካል ስብሰባ ላይ በሊቀ መንበርነት የመራ ይመስላል። ያዕቆብ ጉዳዩን በተመለከተ አጠቃላይ ሐሳብ ካቀረበ በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ያገኘው ውሳኔ ለሁሉም ጉባኤዎች ተላለፈ።—ሥራ 15:1–29
3 ያዕቆብ ያቀረበው የበሰለ ሐሳብ ከፍተኛ ክብደት ተሰጥቶት እንደነበረ ግልጽ ነው። ሆኖም “የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ” እንደሆነ ራሱ በትሕትና ተናግሯል። (ያዕቆብ 1:1) በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈው መልእክቱ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ብዙ አስተማማኝ ምክርና ማበረታቻ ይዟል። መልእክቱ ተጽፎ ያለቀው ሮም በጄኔራል ሴስቲየስ ጋለስ አማካኝነት በኢየሩሳሌም ላይ ካደረገችው የመጀመሪያ ወረራ አራት ዓመት ያህል ቀደም ብሎ ሲሆን በዚህ ጊዜ ምሥራቹ ‘ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ ተሰብኮ’ ነበር። (ቆላስይስ 1:23) ጊዜው አስጨናቂ የነበረ ሲሆን የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ በአይሁድ ብሔር ላይ ሊፈርድ እንደተዘጋጀ አሳምረው ያውቁ ነበር።
4. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡ እንደነበረ የሚጠቁመው ምንድን ነው?
4 በዚያን ጊዜ የነበሩ ክርስቲያኖች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሙሉ እንዲሁም አብዛኞቹ የግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ነበሯቸው። ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አስቀድሞ ከተጻፉት ጽሑፎች ብዙ መጥቀሳቸው በአምላክ ቃል ላይ ከፍተኛ እምነት እንደነበራቸው ያሳያል። እኛም ልክ እንደዚሁ የአምላክን ቃል ክብደት ሰጥቶ ማጥናትና በተግባር ማዋል ያስፈልገናል። ለመጽናት ከፈለግን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ማጠናከሪያና ማበረታቻ ያስፈልገናል።—መዝሙር 119:97፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13
5. በዛሬው ጊዜ ልዩ መመሪያ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህንንስ መመሪያ የምናገኘው ከየት ነው?
5 በዛሬው ጊዜ የሰው ዘር ‘ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባልሆነ ወደፊትም ከቶ በማይሆን ታላቅ መከራ’ ደፍ ላይ ይገኛል። (ማቴዎስ 24:21) በሕይወት መትረፋችን የተመካው መለኮታዊ መመሪያ በማግኘታችን ላይ ነው። ይህንን መመሪያ እንዴት ማግኘት እንችላለን? በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ለያዛቸው ትምህርቶች ልባችንን በመክፈት ነው። ይህም ባለፉት ጊዜያት እንደኖሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ‘ቃሉን የምናደርግ እንድንሆን’ ያስችለናል። የአምላክን ቃል በትጋት ማንበብና ማጥናት እንዲሁም ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ መጠቀም አለብን።—2 ጢሞቴዎስ 2:15፤ 3:16, 17
በደስታ መጽናት
6. ፈተናዎችን ስንጋፈጥ ደስተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
6 ያዕቆብ በመልእክቱ መክፈቻ ላይ ሁለተኛውን የመንፈስ ፍሬ ይኸውም ደስታን ጠቅሷል። እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት። ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።” (ያዕቆብ 1:2–4፤ ገላትያ 5:22, 23) ልዩ ልዩ ፈተናዎችን መጋፈጥ “ሙሉ ደስታ” ነው ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው? ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:11, 12) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደባረከው ማየቱ ደስታ ያስገኛል።—ዮሐንስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8፤ ዕብራውያን 11:8–10, 26, 35
7. (ሀ) ለመጽናት የሚያስችል ምን እርዳታ አለልን? (ለ) ልክ እንደ ኢዮብ ልንካስ የምንችለው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ራሱ “ወደ ፊት በሚያገኘው ደስታ ምክንያት” ጸንቷል። (ዕብራውያን 12:1, 2 የ1980 ትርጉም) እኛም ብንሆን የኢየሱስን የድፍረት ምሳሌ አተኩረን በመመልከት መጽናት እንችላለን! ያዕቆብ በመልእክቱ መደምደሚያ አካባቢ እንደጠቀሰው ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ የዘለቁትን ሰዎች ይሖዋ አብዝቶ ይክሳቸዋል። ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “እነሆ፣ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።” (ያዕቆብ 5:11) ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ በመኖሩ ጤንነቱንና ሀብቱን መልሶ በማግኘት እንዲሁም ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር ደስታ አግኝቶ በመኖር እንደተካሰ አስታውስ። ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ መጽናትህ አምላክ አመጣለሁ ብሎ ቃል በገባው በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሚኖረው ገነት ይህንን የመሰለ ደስታ ያስገኝልሃል፤ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል የምታገኘው ደስታ በዚያን ጊዜ እጥፍ ድርብ ይሆናል።
ጥበብን መሻት
8. እውነተኛ የሆነ በሥራ ላይ ሊውል የሚችል ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ጸሎት ምን ሚና ይጫወታል?
8 የአምላክን ቃልና ቃሉ እንዴት በሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል በትጋት ማጥናታችን እያጣጣረ ባለው በዚህ ብልሹ የሰይጣን ዓለም ውስጥ የሚደርስብንን መከራ ለመቋቋም የሚያስችል አምላካዊ ጥበብ ያስገኝልናል። ይህንን ጥበብ እንደምናገኝ ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶናል? ያዕቆብ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።” (ያዕቆብ 1:5, 6) ይሖዋ ልመናችንን ሰምቶ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ መልስ እንደሚሰጥ ተማምነን ከልብ መጸለይ አለብን።
9. ያዕቆብ ስለ አምላካዊ ጥበብና ይህን ጥበብ ማግኘት ስላለው ውጤት የገለጸው እንዴት ነው?
9 አምላካዊ ጥበብ ከይሖዋ የሚገኝ ስጦታ ነው። ይህንን ጥበብ በተመለከተ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህም የሚመጣው እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት የብርሃን ሁሉ አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር ነው።” ከጊዜ በኋላ በደብዳቤው ላይ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ እውነተኛ ጥበብ ማግኘት ምን ውጤት እንዳለው አመልክቷል፦ “ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። . . . ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፣ በኋላም ታራቂ፣ ገር [“ምክንያታዊ” አዓት]፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።”—ያዕቆብ 1:17 የ1980 ትርጉም፤ 3:13–17
10. የሐሰት ሃይማኖት ከእውነተኛው ሃይማኖት ጋር ምን ልዩነት አለው?
10 በሕዝበ ክርስትናም ሆነ በአጠቃላይ በሐሰት ሃይማኖት ግዛት ሥር ባሉ በሌሎች አገሮች ውስጥ በሚገኙ ሃይማኖተኞች ዘንድ አንዳንድ መዝሙሮችን መዘመር፣ ጸሎቶች ሲደገሙ መስማትና ምናልባትም ንግግር ማዳመጥ የተለመደ ነው። አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ብሩህ ተስፋ ስለሌላቸው አባሎቻቸው ተስፋ ያለው መልእክት እንዲያውጁ ማበረታቻ አይሰጡም። የአምላክን መሲሐዊ መንግሥት ታላቅ ተስፋ ጨርሶ አያነሱትም አለዚያም ፈጽሞ የተሳሳተ ፍቺ ሰጥተውታል። ይሖዋ የሕዝበ ክርስትናን ተከታዮች በተመለከት እንዲህ በማለት ተንብዮአል፦ “ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፣ የተቀደዱትንም ጉድጓዶች፣ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች፣ ለራሳቸው ቆፍረዋል።” (ኤርምያስ 2:13) የእውነት ውኃ የላቸውም። ሰማያዊውን ጥበብ አጥተዋል።
11, 12. (ሀ) መለኮታዊ ጥበብ ለምን ነገር ሊያነሳሳን ይገባል? (ለ) መለኮታዊ ጥበብ ከምን ነገር እንድንጠበቅ ያስጠነቅቀናል?
11 በዛሬው ጊዜ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ምንኛ የተለዩ ናቸው! የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ በሚሰጠው ከፍተኛ ኃይል በመታገዝ ስለ መጪው የይሖዋ መንግሥት በሚናገረው ምሥራች ምድርን እያጥለቀለቋት ነው። የሚናገሩት ጥበብ በአምላክ ቃል ላይ በጽኑ የተመሠረተ ነው። (ከምሳሌ 1:20ና ከኢሳይያስ 40:29–31 ጋር አወዳድር።) በእርግጥም የፈጣሪ አምላካችንን ታላላቅ ዓላማዎች በማወጅ ረገድ እውነተኛውን እውቀትና ማስተዋል በሚገባ ይጠቀሙበታል። በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ “በአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት፣ በመንፈሳዊ ጥበብና በማስተዋል እንዲሞሉ” የሁላችንም ምኞት መሆን አለበት። (ቆላስይስ 1:9) ይህ መሠረት ከተጣለ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ሁልጊዜ ‘ቃሉን የሚያደርጉ ለመሆን’ ይገፋፋሉ።
12 ‘አምላካዊ ጥበብ’ መለኮታዊ ተቀባይነት ከሚያሳጡን ኃጢአቶች እንድንጠበቅ ያስጠነቅቀናል። ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።” አዎን፣ መለኮታዊ ምክር ለመስማትና በሥራ ላይ ለማዋል ፈጣኖችና ዝግጁዎች መሆን አለብን። ቢሆንም “ትንሽ ብልት” በሆነው ምላስ አለአግባብ እንዳንጠቀም መጠንቀቅ አለብን። ምላስ ጉራ በሚነዛ፣ በሐሜት ወይም እኔ ያልኩት ይሁን በሚል ንግግር በምሳሌያዊ አባባል “ትልቅ ጫካ” ሊያቃጥል ይችላል። በዚህ የተነሳ ከሌሎች ጋር ባለን ማንኛውም ግንኙነት ረገድ ተግባቢነትንና ራስን መግዛትን ማዳበር አለብን።—ያዕቆብ 1:19, 20፤ 3:5
13. ‘ቃሉ በውስጣችን እንዲተከል’ መፍቀዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ያዕቆብ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለዚህ ርኩሰትን ሁሉ አላስፈላጊ ነገሮችንና ክፋትን አስወግዳችሁ፣ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለው ቃል በውስጣችሁ እንዲተከል በየዋህነት ፍቀዱ።” (ያዕቆብ 1:21 አዓት) ይህ ስግብግብ ዓለምም ሆነ በውስጡ የሚንጸባረቀው ወራዳ ሥነ ምግባር እንዲሁም በፍቅረ ነዋይ፣ ከሁሉ በፊት እኔ በሚል ዝንባሌና ይታይልኝ በሚል መንፈስ ላይ የተመሠረተው የአኗኗር ዘይቤ በቅርቡ ይጠፋል። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:15–17) ‘ቃሉ በውስጣችን እንዲተከል’ መፍቀዳችን ምንኛ አንገብጋቢ ነው! በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ከዚህ እያጣጣረ ካለው ዓለም ክፋት ጋር ሲወዳደር ልዩነቱ በማያሻማ ሁኔታ ቁልጭ ብሎ ይታያል። ይህንን ክፋት ማስወገድ እንፈልጋለን። (1 ጴጥሮስ 2:1, 2) ከይሖዋ የጽድቅ ጎዳናዎች ላለማፈንገጥ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ከፈለግን ለእውነት ፍቅር ሊኖረንና በልባችን ውስጥ ጠንካራ እምነት ሊተከል ያስፈልጋል። ነገር ግን የአምላክን ቃል መስማት ብቻ ይበቃልን?
‘ቃሉን የምናደርግ’ መሆን
14. ቃሉን ‘የምንሰማ’ እና ‘የምናደርግ’ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
14 ያዕቆብ 1:22 ላይ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” የሚል እናነባለን። “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ”! በያዕቆብ መልእክት ላይ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ጭብጥ ይህ ነው። መጀመሪያ መስማት ከዚያም ‘ልክ እንደታዘዝነው’ ማድረግ አለብን! (ዘፍጥረት 6:22) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች አልፎ አልፎ ወደ አምልኮ ቦታዎች በመሄድ የሚሰጠውን ስብከት መስማት ወይም አንዳንድ የይስሙላ አምልኮቶችን ማከናወን በቂ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ አልፈው ምንም ነገር አያደርጉም። ራሳቸው ባወጧቸው የአቋም ደረጃዎች መሠረት ‘ጥሩ ኑሮ’ ከኖሩ በቂ ይመስላቸዋል። ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም [“የመከራውን እንጨት” አዓት] ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 16:24) እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ የኢየሱስን ፈለግ በመከተል የራስን ጥቅም መሠዋትና መጽናት ይጠይቅባቸዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ ባዘዘበት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአምላክ ፈቃድ አሁንም እንዳልተለወጠ ያውቃሉ። (ማቴዎስ 28:19) አንተስ በዚህ ረገድ እንዴት ነህ?
15. (ሀ) ያዕቆብ ‘ቃሉን በማድረግ’ ደስተኞች መሆን እንደምንችል ለማሳየት የሰጠው ምሳሌ ምንድን ነው? (ለ) የይስሙላ አምልኮ ብቻ በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው?
15 የአምላክን ቃል በትኩረት መመልከታችንን የምንቀጥል ከሆነ ምን እንደምንመስል የሚያሳይ መስተዋት ሊሆንልን ይችላል። ያዕቆብ እንዲህ ይላል፦ “ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ ይሆናል።” (ያዕቆብ 1:23–25) አዎን፣ ደስተኛ ‘የቃሉ አድራጊ’ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በእያንዳንዱ የክርስትና ኑሯችን ዘርፍ ‘አድራጊ’ መሆናችን አስፈላጊ ነው። የይስሙላ አምልኮ ማከናወን ብቻ ይበቃል በማለት ፈጽሞ ራሳችንን ማሞኘት የለብንም። ያዕቆብ ቀናተኛ ክርስቲያኖች እንኳ ችላ ብለዋቸው ሊሆኑ የሚችሉ ነገር ግን እውነተኛው አምልኮ ሊያሟላቸው ስለሚገቡ ነገሮች መክሮናል። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፣ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።”—ያዕቆብ 1:27
16. አብርሃም “የእግዚአብሔር ወዳጅ” የሆነው በምን መንገዶች ነው? እኛስ የይሖዋን ወዳጅነት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
16 ‘በአምላክ አምናለሁ’ ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ብቻ አይበቃም። ያዕቆብ 2:19 “እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል” በማለት ይናገራል። ያዕቆብ “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ” እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ከገለጸ በኋላ “እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን?” በማለት ስለ አብርሃም ይናገራል። (ያዕቆብ 2:17, 20–22) የአብርሃም ሥራ ዘመዶቹን መርዳትን፣ እንግዳ ተቀባይ መሆንን፣ ይስሐቅን ለመሥዋዕትነት ማቅረብንና አምላክ አመጣለሁ ብሎ ቃል በገባው ‘መሠረት ባላት ከተማ’ ማለትም ወደፊት በሚመጣው መሲሐዊ መንግሥት ላይ ያለውን የማይናወጥ እምነት ‘በግልጽ ማሳወቅን’ ያጠቃልል ነበር። (ዘፍጥረት 14:16፤ 18:1–5፤ 22:1–18፤ ዕብራውያን 11:8–10, 13, 14 አዓት፤ 13:2) አብርሃም ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ ተብሎ’ መጠራቱ ተስማሚ ነው። (ያዕቆብ 2:23) እኛም ወደፊት በሚመጣው የይሖዋ የጽድቅ መንግሥት ላይ ያለንን እምነትና ተስፋ በቅንዓት ካወጅን ‘የይሖዋ ወዳጆች’ ተብለን ልንጠራ እንችላለን።
17. (ሀ) ረዓብ ‘የጸደቀችው’ በምን ነበር? እንዴትስ ተካሰች? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ‘ቃሉን የሚያደርጉ’ የብዙ ሰዎች ዝርዝር የትኛው ነው? (ሐ) ኢዮብ የተካሰው እንዴት ነበር? ለምንስ?
17 ‘የቃሉ አድራጊዎች’ የሆኑ ሰዎች ‘በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጸድቀዋል።’ (ያዕቆብ 2:24) ረዓብ ስለ ይሖዋ ታላላቅ ሥራዎች በሰማችው ‘ቃል’ ላይ የነበራትን እምነት በሥራ የገለጸች ሴት ነበረች። እስራኤላውያን የሆኑትን ሰላዮች ከመደበቋም በላይ እንዲያመልጡ ከረዳቻቸው በኋላ የአባቷን ቤተሰብ ከጥፋት ለማዳን አንድ ላይ ሰብስባለች። ወደ ፊት ከሞት በምትነሳበት ጊዜ በሥራ የተደገፈው እምነቷ የመሲሑ ቅድመ አያት ለመሆን እንዳስቻላት ስትመለከት እንዴት ትደሰት ይሆን! (ኢያሱ 2:11፤ 6:25፤ ማቴዎስ 1:5 የ1980 ትርጉም) ዕብራውያን ምዕራፍ 11 እምነትን በተግባር በማሳየት ‘የቃሉ አድራጊዎች የሆኑ’ ሌሎች ብዙ ሰዎችን ይዘረዝራል። እነዚህም ቢሆኑ ከፍተኛ ወሮታ ይከፈላቸዋል። በከባድ መከራ ሥር ሳለ “የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን” በማለት የተናገረውን ኢዮብንም መርሳት የለብንም። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው እምነቱና ሥራው ታላቅ ሽልማት አስገኝቶለታል። (ኢዮብ 1:21፤ 31:6፤ 42:10፤ ያዕቆብ 5:11) እኛም በተመሳሳይ ‘ቃሉን የምናደርግ’ በመሆን መጽናታችን በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያስገኝልናል።
18, 19. ለረጅም ጊዜ ነፃነታቸው ተገፎ የነበሩ ወንድሞች ‘ቃሉን የሚያደርጉ የሆኑት’ እንዴት ነው? ጥረታቸው ምን በረከት አስገኝቷል?
18 ለረጅም ዓመታት ከጸኑት መካከል በምሥራቅ አውሮፓ የሚኖሩ ወንድሞቻችን ይገኙበታል። በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው እገዳ ስለተነሳላቸው ባገኙት አዲስ አጋጣሚ ‘ቃሉን የሚያደርጉ’ ሆነዋል። በአጎራባች አገሮች የሚገኙ ሚስዮናውያንና አቅኚዎች የማስተማሩንና የማደራጀቱን ሥራ ለማገዝ ወደዚያ ሄደዋል። የፊንላንድና ሌሎች በአቅራቢያው ያሉ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፎች የግንባታ ሥራ ባለሙያዎችን ልከዋል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞች ያደረጉት ልግስና አዳዲስ ቅርንጫፍ ቢሮዎችንና የመንግሥት አዳራሾችን ለመሥራት የሚያስፈልገውን ወጪ ሸፍኗል።—ከ2 ቆሮንቶስ 8:14, 15 ጋር አወዳድር።
19 ለረጅም ጊዜ ነፃነት አጥተው የኖሩ ወንድሞቻችን በአገልግሎቱ እንዴት ያለ ቀና ምላሽ እየሰጡ ነው! ‘ጠንክረው እየሠሩ’ ከመሆናቸውም በላይ ‘በአስቸጋሪው ጊዜ’ ባልነበሯቸው አጋጣሚዎች ለመጠቀም ‘ጥረት እያደረጉ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2) ለምሳሌ ከባድ እገዳ በነበረባት አልባኒያ ውስጥ ባለፈው ሚያዝያ “የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?” የተባለው የመንግሥት ዜና ተሰራጭቶ ያለቀው በሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ነበር። ይህም በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ ለተገኙት ከ538 አስፋፊዎቻቸው እጅግ ለሚበልጡት 3,491 ሰዎች ጥሩ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ያስቻለ ነበር።
20. በቅርቡ ያሳለፍናቸው ዓመታት የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ምን ይጠቁማል? ብዙዎች ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
20 ሌሎች አገሮችም ቢሆኑ በቅርቡ ባሳለፍናቸው ዓመታት በጌታ ራት ላይ የተገኙት ሰዎች ቁጥር ከ10,000,000 ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ አድርገዋል። በብዙ ቦታዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው በመመልከት እምነታቸው የተጠናከረ ሰዎች ‘ቃሉን የሚያደርጉ እየሆኑ’ ነው። በስብስባ ላይ ከሚገኙ አዳዲስ ሰዎች አብዛኞቹ ቃሉን የሚያደርጉ እንዲሆኑ ልናበረታታቸው እንችላለንን?
21. ከዓመት ጥቅሳችን ጋር በመስማማት ምን ማድረግ አለብን? ግባችንስ ምን መሆን አለበት?
21 ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ በመጀመሪያው መቶ ዘመንና ከዚያ ወዲህ እንደነበሩት አያሌ ቀናተኛ ክርስቲያኖች ‘በፊታችን ወዳለው’ የዘላለም ሕይወት ‘ግብ ለመሮጥ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ፊልጵስዩስ 3:12–14 የ1980 ትርጉም) እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ማንኛውንም ዓይነት ጥረት ብናደርግ አያስቆጭም። ጊዜው ወደ ኋላ የምንመለስበትና ሰሚዎች ብቻ የምንሆንበት ሳይሆን ከመቼውም ይልቅ ‘በርትተን የምንሠራበት’ ጊዜ ነው። (ሐጌ 2:4፤ ዕብራውያን 6:11, 12) ‘ቃሉ በውስጣችን እንዲተከል በመፍቀድ’ አሁንም ሆነ ለዘላለም ‘ቃሉን በደስታ የምናደርግ’ እንሁን።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በደስታ መጽናት የምንችለው እንዴት ነው?
◻ “ላይኛይቱ ጥበብ” ምንድን ናት? እንዴትስ ማግኘት እንችላለን?
◻ ‘ቃሉን ከመስማት አልፈን የምናደርግ መሆን’ ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ‘የቃሉ አድራጊዎች’ እንድንሆን ሊያነሳሱን የሚገቡ የትኞቹ ሪፖርቶች ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኛም ለመለኮታዊ ትምህርት ልባችንን እንክፈት
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ በመኖሩ ከሚወዳቸው ሰዎች ጋር ደስታ አግኝቶ በመኖር ተክሷል