የጥንቱ ክርስትናና ፖለቲካዊ መንግሥት
ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ደቀ መዛሙርቱን “እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:19) ሆኖም ይህ ማለት ክርስቲያኖች የዚህን ዓለም ባለ ሥልጣናት በጥላቻ ዓይን ይመለከቷቸዋል ማለት ነውን?
የዓለም ክፍል ባይሆኑም የጠላትነት አቋም የላቸውም
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ” ብሏቸው ነበር። (ሮሜ 13:1) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፣ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ።” (1 ጴጥሮስ 2:13, 14) ለመንግሥትና መንግሥት ለሾማቸው ባለ ሥልጣኖች መገዛት እንደሚገባ የሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት እንደ ነበረው ግልጽ ነው። ሕግ አክባሪ ዜጎች ለመሆንና ከሁሉም ሰው ጋር በሰላም ለመኖር ይጥሩ ነበር።—ሮሜ 12:18
ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን “ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት” በሚል ርዕስ ሥር እንዲህ ብሏል፦ “ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ቤተ ክርስቲያን ከሮማ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ጋር ምንም ግንኙነት አልነበራትም። ሆኖም የክርስትና መሪዎች . . . የክርስትና እምነት እስከሚፈቅደው ደረጃ ድረስ ለሮማ ሕግ የመታዘዝንና ለንጉሠ ነገሥቱ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ያስተምሩ ነበር።”
አክብሮትን እንጂ አምልኮን አልሰጡም
ክርስቲያኖች የሮማን ንጉሠ ነገሥት በጥላቻ የሚመለከቱ አልነበሩም። ሥልጣኑን ያከብሩ ነበር፤ ለሥልጣኑ የሚገባውን አክብሮትም ይሰጡ ነበር። በንጉሠ ነገሥት ኔሮ የግዛት ዘመን ሐዋርያው ጴጥሮስ በተለያዩ የሮማ ግዛት ክፍሎች ውስጥ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች “ሁሉን አክብሩ፣ . . . ንጉሥን አክብሩ” ሲል ጽፎላቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ግሪክኛ ይናገሩ የነበሩ ሰዎች “ንጉሥ” የሚለውን ቃል የአገራቸውን ነገሥታት ብቻ ሳይሆን የሮማውን ንጉሠ ነገሥትም ለማመልከት ይጠቀሙበት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮማ ግዛት ዋና ከተማ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ . . . ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ሲል መክሯቸዋል። (ሮሜ 13:7) የሮማው ንጉሠ ነገሥት ክብር እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ እንዲመለክም ፈልጎ ነበር። እዚህ ላይ የጥንት ክርስቲያኖች ገደብ አበጅተው ነበር።
ፖሊካርፕ በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ በአንድ የሮማ ገዥ ፊት ቀርቦ በነበረበት ወቅት እንዲህ ብሎ እንደነበረ ይነገራል፦ “እኔ ክርስቲያን ነኝ። . . . በአምላክ ለተሾሙ መንግሥታትና ባለ ሥልጣናት . . . ክብር መስጠት እንዳለብን ተምረናል።” ይሁን እንጂ ፖሊካርፕ ንጉሠ ነገሥቱን ከማምለክ ሞትን መርጧል። በሁለተኛው መቶ ዘመን በአንጾኪያ ይኖር የነበረውና ክርስትናን ደግፎ የተናገረው ቴዎፍሎስ “ንጉሠ ነገሥቱን አከብረዋለሁ፤ እጸልይለታለሁ እንጂ አላመልከውም። እኔ የማመልከው ሕያውና እውነተኛ የሆነውን አምላክ ነው” ሲል ጽፏል።
ንጉሠ ነገሥቱን በተመለከተ የሚቀርቡ ተገቢ ጸሎቶች ለንጉሠ ነገሥቱ ከሚቀርበው አምልኮ ወይም ከብሔራዊ ስሜት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የላቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ የእነዚህን ጸሎቶች ዓላማ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፣ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2
“ከኅብረተሰቡ አመለካከት ጋር አይገጥምም ነበር”
የጥንት ክርስቲያኖች ያሳዩት የነበረው አክብሮት የተሞላበት ምግባር ይኖሩበት የነበረውን ዓለም ወዳጅነት አላተረፈላቸውም። ፈረንሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ኤ አሞን የጥንት ክርስቲያኖች አኗኗራቸው “ከኅብረተሰቡ አመለካከት ጋር አይገጥምም ነበር” ሲሉ ገልጸዋል። በእርግጥም አኗኗራቸው ከሁለቱም ኅብረተሰቦች ማለትም ከአይሁዳውያንም ሆነ ከሮማውያን አመለካከት አይገጥምም ነበር። ሁለቱም ኅብረተሰቦች በብዙ ነገር አድልዎ ይፈጽሙባቸው ነበር፤ ስለ እነርሱም የተሳሳተ አመለካከት ነበራቸው።
ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ከአይሁድ መሪዎች የሐሰት ክስ በተመሠረተበት ጊዜ በሮማው ገዥ ፊት ክሱን በመቃወም “የአይሁድን ሕግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሣርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም . . . ወደ ቄሣር ይግባኝ ብዬአለሁ” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 25:8, 11) ጳውሎስ አይሁዳውያን ሊገድሉት እያሴሩ እንዳሉ ስላወቀ ወደ ኔሮ ይግባኝ ብሏል፤ ይህም ለሮማ ንጉሠ ነገሥት ሥልጣን እውቅና መስጠቱን ያሳያል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በሮም ችሎት ፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በቀረበበት ወቅት በነፃ ተለቅቆ ነበር። ሆኖም በኋላ እንደገና ታስሮ በኔሮ ትእዛዝ እንደተገደለ አፈ ታሪክ ይናገራል።
የጥንት ክርስቲያኖች በሮማ ኅብረተሰብ ውስጥ የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በተመለከተ የማኅበራዊ ጉዳዮችና የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ኧርንስት ትሮልች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ከጣዖት አምልኮ፣ ወይም ለንጉሠ ነገሥቱ ከሚሰጠው አምልኮ፣ ወይም ደግሞ ከደም መፋሰስ ወይም ወንጀለኛን በሞት ከመቅጣት ጋር ግንኙነት ያለውን፣ እንዲሁም ክርስቲያኖች በአረማውያን ብልሹ ሥነ ምግባር ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ማንኛውም ዓይነት ሹመትም ሆነ ሥራ አይቀበሉም ነበር።” ይህ አቋም በክርስቲያኖችና በመንግሥት መካከል ምንም ዓይነት ሰላማዊና አክብሮት የተሞላበት ግንኙነት እንዳይኖር ያግዳልን?
ለቄሣር ‘የሚገባውን’ መስጠት
ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” የሚል ደንብ በማውጣት ክርስቲያኖች ከሮማ መንግሥትም ጋር ሆነ ከማንኛውም ሌላ መንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት ሊያሳዩት የሚገባውን ምግባር ገልጿል። (ማቴዎስ 22:21) ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጠው ይህ ምክር የሮማን አገዛዝ ይቃወሙ የነበሩትና ለውጪ ኃይል ቀረጥ መክፈል ሕገ ወጥ ድርጊት ነው ብለው ይከራከሩ የነበሩት የብሔረተኝነት ስሜት የነበራቸው ብዙ አይሁዳውያን ከነበራቸው አመለካከት በጣም የተለየ ነው።
ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በሮም ይኖሩ የነበሩትን ክርስቲያኖች እንዲህ አላቸው፦ “ስለዚህ ስለ ቊጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ . . . ስጡ።” (ሮሜ 13:5-7) ምንም እንኳ ክርስቲያኖች የዚህ ዓለም ክፍል ባይሆኑም ሐቀኞችና ቀረጥ የሚከፍሉ ዜጎች እንዲሁም መንግሥት ለሚሰጣቸው አገልግሎት ተገቢውን ዋጋ የሚከፍሉ መሆን አለባቸው።—ዮሐንስ 17:16
ይሁን እንጂ ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ቀረጥ መክፈልን ብቻ የሚመለከቱ ናቸውን? ኢየሱስ ለቄሣር መሰጠት የሚገባው ምን እንደሆነና ለአምላክ መሰጠት የሚገባው ምን እንደሆነ በቀጥታ ለይቶ ስላላመለከተ ሁኔታውን በማመዛዘንና ከመላው መጽሐፍ ቅዱስ ባገኘነው እውቀት በመንተራስ ውሳኔ ልንሰጥባቸው የሚገቡ አሻሚ የሆኑ ሁኔታዎች ይኖራሉ። በሌላ አነጋገር አንድ ክርስቲያን የትኞቹን ነገሮች ለቄሣር ሊሰጥ እንደሚችል ለመወሰን አንዳንድ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሠለጠነ ክርስቲያናዊ ሕሊና መጠቀም ሊያስፈልገው ይችላል።
ፍጹም ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለሁለቱም መገዛት
ብዙ ሰዎች ኢየሱስ የቄሣርን ለቄሣር ስጡ ብሎ ከተናገረ በኋላ “የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት አክሎ መናገሩን ይዘነጉታል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለየትኛው ቅድሚያ እንደሚሰጡ ገልጿል። ጴጥሮስ “ለንጉሥ” ወይም ለንጉሠ ነገሥቱና ‘ለመኳንንቱ’ መገዛት እንደሚገባ ምክር ከሰጠ በኋላ ከዚያ ትንሽ ዝቅ ብሎ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ። ሁሉን አክብሩ፣ ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ።” (1 ጴጥሮስ 2:16, 17) ሐዋርያው ክርስቲያኖች የአምላክ ባሪያዎች እንጂ የሰብዓዊ ገዥ ባሪያዎች እንዳልሆኑ አመልክቷል። ለመንግሥት ወኪሎች ተገቢ አክብሮት ማሳየት ያለባቸው ቢሆንም እንኳ ይህን ማድረግ ያለባቸው ከእነርሱ የላቀ ሕግጋት ያሉትን አምላክ በመፍራት መሆን ይኖርበታል።
ጴጥሮስ ይህን ከመጻፉ ከበርካታ ዓመታት በፊት የአምላክ ሕግ ከሰው የላቀ መሆኑን በግልጽ ተናግሮ ነበር። የአይሁዳውያን ሳንሄድሪን ሮማውያን ሕዝባዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ሥልጣን የሰጡት የአስተዳደር አካል ነበር። ሳንሄድሪን የተባለው ይህ አካል የኢየሱስ ተከታዮች በክርስቶስ ስም ማስተማራቸውን እንዲያቆሙ ባዘዛቸው ጊዜ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት ያላቸውን ጠንካራ አቋም ገልጸዋል። (ሥራ 5:29) በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የጥንት ክርስቲያኖች ለአምላክ በመታዘዝና ለሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት ተገቢውን አክብሮት በመስጠት ረገድ ሚዛናዊ መሆን ነበረባቸው። ተርቱሊያን ከረጅም ጊዜ በፊት በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንዲህ በማለት ነጥቡን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፦ “ሁሉ ነገር ለቄሣር ከተሰጠ ለአምላክ የሚቀር ምን ነገር ይኖራል?”
አቋምን በማላላት ከመንግሥት ጋር የተፈጠረ ትስስር
ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከመንግሥት ጋር በነበራቸው ግንኙነት ይዘውት የነበረው አቋም ቀስ በቀስ እየላላ ሄደ። ኢየሱስና ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩለት ክህደት በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመናት እዘአ ተስፋፋ። (ማቴዎስ 13:37, 38፤ ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3-12፤ 2 ጴጥሮስ 2:1-3) ከሃዲ ክርስቲያኖች ከሮም ኅብረተሰብ ጋር ተስማምተው ለመኖር አቋማቸውን በማላላት የእነሱን አረማዊ በዓላት ማክበርና የእነሱን ፍልስፍና ማመን ጀመሩ፤ እንዲሁም የመንግሥት ባለ ሥልጣን ሆኖ መሥራት ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ አገልግሎትም መስጠት ጀመሩ።
ፕሮፌሰር ትሮልች እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ከፍተኛ ሥልጣን የያዙ፣ በታላላቅ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ እንዲሁም በጦር ሠራዊትና በሥልጣን ቦታዎች ላይ የሚሠሩ ክርስቲያኖች ቁጥር በጣም በመጨመሩ ከሦስተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ሁኔታው ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ ሄዷል። [መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ] የክርስትና ጽሑፎች በርካታ ክፍሎች ላይ በእነዚህ ነገሮች መሳተፍን በጥብቅ የሚያወግዙ ሐሳቦች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አቋምን ለማላላት የተደረጉ ጥረቶችንና ይህ ሁኔታ ሕሊናቸውን የሚረብሻቸውን ሰዎች መንፈስ ለማረጋጋት ተብለው የቀረቡ የመከራከሪያ ሐሳቦችም እናገኛለን . . . ከቆስጠንጢኖስ ዘመን ጀምሮ እነዚህ ችግሮች ጠፉ፤ በክርስቲያኖችና በአረማውያን መካከል የነበረው ግጭት ተወገደ፤ የመንግሥት የሥልጣን ቦታዎችም ክርስቲያን ነን ለሚሉት ሰዎችም ክፍት ሆነ።”
በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃ ላይ ይህ የተበረዘውና አቋሙን ያላላው ክርስትና የሮማ ግዛት መንግሥታዊ ሃይማኖት ሆነ።
በካቶሊክ፣ በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የተወከለችው ሕዝበ ክርስትና ባሳለፈችው የታሪክ ዘመን በመንግሥታት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግና የሚያካሄዷቸውን ጦርነቶች በመደገፍ ከመንግሥት ጋር ተስማምታ ለመኖር አቋሟን ስታላላ ኖራለች። የቤተ ክርስቲያን አባላት የነበሩና በዚህ ሁኔታ የተደናገጡ ብዙ ቅን ሰዎች በዛሬው ጊዜ ከመንግሥት ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የነበራቸው ዓይነት አቋም ያላቸው ክርስቲያኖች እንዳሉ ቢያውቁ ኖሮ እንደሚደሰቱ ምንም አያጠራጥርም። የሚቀጥሉት ሁለት ርዕሶች ይህን ጉዳይ ይበልጥ በዝርዝር ያብራሩታል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጴጥሮስ ‘ንጉሡን አክብሩ’ሲል የተናገረለት ቄሣር ኔሮ
[ምንጭ]
Musei Capitolini, Roma
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፖሊካርፕ ንጉሠ ነገሥቱን ከማምለክ ሞትን መርጧል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንት ክርስቲያኖች ሰላማውያን፣ሐቀኞችና ቀረጥ የሚከፍሉ ዜጎች ነበሩ