“በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ”
“እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።”—1 ጴጥሮስ 1:15, 16
1. ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ቅዱሳን እንዲሆኑ ያበረታታው ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ጴጥሮስ ከላይ ያለውን ምክር የሰጠው ለምን ነበር? ምክንያቱም እያንዳንዱ ክርስቲያን ሐሳቡንና ድርጊቱን ከይሖዋ ቅድስና ጋር አስማምቶ ለመቀጠል እንዲችል እነዚህኑ ነገሮች መቆጣጠር እንዳለበት ስለተገነዘበ ነው። በመሆኑም ከላይ ያሉትን ቃላት ከተናገረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፣ . . . እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።”—1 ጴጥሮስ 1:13, 14
2. እውነትን ከማወቃችን በፊት ምኞቶቻችን ቅዱስ ያልነበሩት ለምንድን ነው?
2 የቀድሞ ምኞቶቻችን ቅዱስ አልነበሩም። ለምን? ምክንያቱም ብዙዎቻችን የክርስትናን እውነት ከመቀበላችን በፊት ዓለማዊ አኗኗር የምንከተል ሰዎች ነበርን። ጴጥሮስ እንደሚከተለው ብሎ በግልጽ በጻፈ ጊዜ ይህን ነገር ተገንዝቦ ነበር፦ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።” እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስ ባለንበት ዘመናዊ ዓለም ውስጥ የሚታዩትን ርኩስ ተግባሮች አልዘረዘረም፤ ምክንያቱም በጊዜው አይታወቁም ነበር።—1 ጴጥሮስ 4:3, 4
3, 4. (ሀ) መጥፎ ምኞቶችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ስሜት የለሽ መሆን አለባቸውን? አብራራ።
3 እነዚህ ምኞቶች ሥጋን፣ የስሜት ሕዋሶቻችንንና ፍላጎቶቻችንን የሚማርኩ መሆናቸውን አስተውለሃልን? እነዚህ ነገሮች እንዲቆጣጠሩን ከፈቀድን ሐሳባችንና ድርጊታችን ሁሉ በቀላሉ ይረክሳል። ይህም ድርጊታችን በማመዛዘን ችሎታችን እንዲመራ መፍቀዳችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አጉልቶ ያሳያል። ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት አስቀምጦታል፦ “እንግዲህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ሰውነታችሁን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያውና ቅዱስ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም በማመዛዘን ችሎታችሁ ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።”—ሮሜ 12:1, 2 አዓት
4 ለአምላክ ቅዱስ መሥዋዕት ለማቅረብ ከፈለግን የላቀ ቦታ እንዲይዝ መፍቀድ ያለብን ለማመዛዘን ችሎታችን እንጂ ለስሜታችን መሆን አይኖርበትም። ስሜታቸው ድርጊታቸውን እንዲቆጣጠረው በመፍቀዳቸው ምክንያት በሥነ ምግባር ብልግና የወደቁት ምንኛ ብዙ ናቸው! ይህ ማለት ግን ስሜታችንን ማፈን አለብን ማለት አይደለም። ይህ ቢሆንማ ኖሮ ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት የምናገኘውን ደስታ እንዴት መግለጽ እንችል ነበር? ይሁን እንጂ የሥጋ ሥራዎችን ሳይሆን የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት የምንፈልግ ከሆነ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን አእምሮአችንን ማደስ ይኖርብናል።—ገላትያ 5:22, 23፤ ፊልጵስዩስ 2:5
ቅዱስ አኗኗር የሚጠይቅ ቅዱስ ዋጋ
5. ጴጥሮስ ቅዱስ የመሆን ጉዳይ ያሳሰበው ለምን ነበር?
5 የክርስቲያኖች ቅድስና ጴጥሮስን ይህን ያህል ያሳሰበው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ታዛዥ የሆኑትን የሰው ልጆች ለመቤዠት ስለተከፈለው ቅዱስ ዋጋ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፣ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ።” (1 ጴጥሮስ 1:18, 19) አዎን፣ የቅድስና ምንጭ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሰዎች ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርቱ የሚያስችላቸውን ቤዛ እንዲከፍል “ቅዱስ” የሆነውን አንድያ ልጁን ልኮታል።—ዮሐንስ 3:16፤ 6:69፤ ዘጸአት 28:36፤ ማቴዎስ 20:28
6. (ሀ) በቅዱስ ኑሮ መመላለስ ቀላል የማይሆንልን ለምንድን ነው? (ለ) ኑሯችን ቅዱስ እንዲሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
6 ይሁን እንጂ ብልሹ በሆነው የሰይጣን ዓለም ውስጥ እየኖርን ቅዱስ ኑሮ መምራት ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ሰይጣን እሱ በሚቆጣጠረው የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በንጽሕና ለመመላለስ በሚጥሩት እውነተኛ ክርስቲያኖች ፊት ወጥመዱን ይዘረጋል። (ኤፌሶን 6:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) አንድ ሰው ሰብዓዊ ሥራ፣ የቤተሰብ ተቃውሞ፣ በትምህርት ቤት የሚያጋጥመው ፌዝና የእኩዮች ተጽዕኖ የሚያሳድሩትን ግፊት ተቋቁሞ ቅዱስ ሆኖ ለመኖር የግድ ጠንካራ መንፈሳዊነት ያስፈልገዋል። ይህም የግል ጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና አጎልቶ የሚያሳይ ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንደሚከተለው ሲል መክሮታል፦ “በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር አድርገህ፣ ከእኔ የሰማኸውን ጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ።” (2 ጢሞቴዎስ 1:13) እነዚህን ጤና የሚሰጡ ቃላት በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ እንሰማቸዋለን እንዲሁም በግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አማካኝነት እናነባቸዋለን። በጣም ብዙ በሆኑ የተለያዩ የኑሯችን ዘርፎች በየዕለቱ ቅዱስ እንድንሆን ሊረዱን ይችላሉ።
ቅዱስ አኗኗር በቤተሰብ ውስጥ
7. ቅድስና በቤተሰብ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይገባል?
7 ጴጥሮስ ዘሌዋውያን 11:44ን ሲጠቅስ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ሃጊዮስ የሚል ሲሆን ትርጉሙም “ከኃጢአት የተለየ በመሆን ለአምላክ የተወሰነ፣ ክቡር” ማለት ነው። (በደብልዩ ኢ ቫይን የተዘጋጀው አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ) ይህ የክርስቲያናዊ ቤተሰብ ሕይወታችንን እንዴት ሊነካው ይገባል? ‘አምላክ ፍቅር በመሆኑ’ የቤተሰብ ሕይወታችን በፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ማለት እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። (1 ዮሐንስ 4:8) የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር በትዳር ጓደኛሞች እንዲሁም በወላጆችና በልጆች መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይሻክር የሚያለሰልስ ዘይት ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:4-8፤ ኤፌሶን 5:28, 29, 33፤ 6:4፤ ቆላስይስ 3:18, 21
8, 9. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያን ቤት ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታዎች ይከሰታሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ጥሩ ምክር ይሰጣል?
8 እንዲህ የመሰለውን ፍቅር ማሳየት በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ሁልጊዜ መኖሩ እንደማይቀር አድርገን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ክርስቲያን ቤቶች ውስጥ መገኘት የሚገባውን ያህል ፍቅር ሁልጊዜ አለመገኘቱ አይካድም። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ፍቅር እንዳለን እናሳይ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ቤታችን ስንመለስ ቅድስናችን ሙልጭ ብሎ ይጠፋ ይሆናል። ሚስት ክርስቲያን እህታችን መሆኗ ወይም ባል በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የምናከብረው ወንድም (ምናልባትም የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ) መሆኑ ከመቅጽበት ተረስቶ በቁጣ መጯጯህ ልንጀምር እንችላለን። ሁለት ዓይነት ኑሮም በሕይወታችን ውስጥ ሊያቆጠቁጥ ይችላል። የክርስቶስን ዓይነት ባሕርይ የሚያንጸባርቁ ባልና ሚስት መሆናቸው ይቀርና እርስ በርስ የሚነታረኩ ወንድና ሴት ይሆናሉ። በቤት ውስጥ መስፈን ያለበት ሁኔታ ቅዱስ መሆን እንደሚገባው ይዘነጋሉ። ምናልባትም እንደ ዓለማዊ ሰዎች መናገር ይጀምሩ ይሆናል። ጸያፍና የሽሙጥ ንግግሮች ከአፋችን በቀላሉ ሊወጡ ይችላሉ!—ምሳሌ 12:18፤ ከሥራ 15:37-39 ጋር አወዳድር።
9 ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምክር ሰጥቷል፦ “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል [በግሪክኛ ሎጎስ ሳፕሮስ “የሚያረክስ ንግግር” ወይም በሌላ አባባል ቅዱስ ያልሆነ ነገር] ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ።” ለሚሰሙት ብሎ የሚጠቅሰው ልጆችን ጨምሮ በቤት ውስጥ ያሉትን ሁሉ ነው።—ኤፌሶን 4:29፤ ያዕቆብ 3:8-10
10. ስለ ቅድስና የተሰጠው ምክር ለልጆች የሚሠራው እንዴት ነው?
10 ይህ የቅድስና መመሪያ በክርስቲያን ቤት ውስጥ ለሚገኙ ልጆችም እኩል ይሠራል። ከትምህርት ቤት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ከዓለማዊ እኩዮቻቸው የሰሙትን የዓመፀኝነትና አክብሮት የጎደለው ንግግር በቀላሉ ማንጸባረቅ ሊጀምሩ ይችላሉ! ልጆች የይሖዋን ነቢይ የተሳደቡት ስድ ልጆች ያሳዩት ዝንባሌ አይማርካቸውም፤ ዛሬም እንደነርሱ ባለጌና ተሳዳቢ የሆኑ ልጆች አሉ። (2 ነገሥት 2:23, 24) ሥርዓታማ ነገር መናገር የማይቀናቸው ወይም ለሌሎች አሳቢነት የሚጎድላቸው ሰዎች የሚናገሩት የዱርዬ ቋንቋ ንግግራችሁን ሊያጎድፈው አይገባም። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ንግግራችን ቅዱስ፣ ደስ የሚል፣ የሚያንጽ፣ ደግነት ያለበትና “በጨው የተቀመመ” መሆን ይኖርበታል። ከሌሎች ሰዎች የተለየን መሆናችንን የሚያሳውቅ መሆን ይገባዋል።—ቆላስይስ 3:8-10፤ 4:6
ቅድስናና የማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻችን
11. ቅዱስ መሆን ማለት ራስን ማመጻደቅ ማለት ያልሆነው ለምንድን ነው?
11 ቅዱስ የሆነውን ነገር ለማድረግ ስንጣጣር በተለይ በማያምኑ የቤተሰባችን አባሎች ዘንድ ራሳችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ወይም ራሳችንን ማመጻደቅ አይገባንም። ደግነት የተሞላው ክርስቲያናዊ ባሕርያችን አዎንታዊ በሆነ መልኩ ከሌሎች የተለየን መሆናችንን እንዲሁም በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ እንደተጠቀሰው ደግ ሳምራዊ ፍቅርንና ርኅራኄን ማሳየት የምንችል መሆናችንን እንዲያስተውሉ ሊረዳቸው ይገባል።—ሉቃስ 10:30-37
12. ክርስቲያን ባለ ትዳሮች የትዳር ጓደኞቻቸው በእውነት እንዲማረኩ ለማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
12 ጴጥሮስ ለክርስቲያን ሚስቶች እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ የማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻችን በተገቢው መንገድ መያዝ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል፦ “እንዲሁም፣ እናንተ ሚስቶች ሆይ፣ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው።” አንዲት ክርስቲያን ሚስት (ባልም ሊሆን ይችላል) ንጹህ፣ አሳቢና ሰው አክባሪ ከሆነች የማያምነው ባሏ በእውነት ሊማረክ ይችላል። ይህም ማለት የማያምነው የትዳር ጓደኛዋ ችላ እንደተባለ ወይም እንደተተወ ሆኖ እንዳይሰማው ቲኦክራሲያዊ ፕሮግራሟን እንደ ሁኔታው ማስተካከል ይኖርባታል።a—1 ጴጥሮስ 3:1, 2
13. አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች አንድ የማያምን ባል እውነትን እንዲያደንቅ ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው?
13 አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች የማያምነውን ባል ወዳጃዊ ሆነው በመቅረብ ሊረዱት ይችላሉ። በዚህ መንገድ የይሖዋ ምሥክሮች ጨርሶ ከሰው የማይገጥሙ ሰዎች አለመሆናቸውን እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ለሌሎች ነገሮችም ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዳላቸው ሊያስተውል ይችላል። በአንድ ወቅት አንድ ሽማግሌ አንድ የማያምን ባል በነበረው በትርፍ ጊዜ ዓሣ የማጥመድ ልማድ መካፈል ጀመረ። ጋሬጣውን ለማለፍ ይህን ማድረጉ ብቻ በቂ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ባል የተጠመቀ ወንድም ሆነ። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ለካናሪ ወፎች ፍቅር የነበረው አንድ የማያምን ባል ነበር። ሽማግሌዎች እርሱን ለመርዳት አልታከቱም። ከሽማግሌዎች መካከል አንዱ በሚቀጥለው ጊዜ ባልየውን ሲያገኘው በሚወደው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ለመጀመር ስለ እነዚህ ወፎች አጠና! እንግዲያውስ ቅዱስ መሆን ማለት ግትር መሆን ወይም እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከት ማለት አይደለም።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23
በጉባኤ ውስጥ ቅዱስ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
14. (ሀ) ሰይጣን ጉባኤውን ለመሸርሸር ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱ ምንድን ነው? (ለ) የሰይጣንን ወጥመዶች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
14 ዲያብሎስ ለሚለው መጠሪያ የሚሠራበት ዲያቦሎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉም “ከሳሽ” ወይም “ስም አጥፊ” የሚል በመሆኑ ሰይጣን ዲያብሎስ ስም አጥፊ ነው። ስም ማጥፋት የተካነበት አንዱ መስክ ሲሆን በጉባኤ ውስጥም ሊጠቀምበት ይሞክራል። በጣም የሚወደው ዘዴው ሐሜት ነው። በዚህ ቅዱስ ያልሆነ ተግባር እንዲያጠምደን እንፈቅድለታለንን? ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ራሳችን የሐሜት ቆስቋሽ በመሆን፣ የሰማነውን በማውራት ወይም ሲነገር በማዳመጥ ነው። ጥበብ የተሞላበቱ ምሳሌ እንዲህ ይላል፦ “ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል ጆሮ ጠቢ [“ስም አጥፊ፣” አዓት] ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል።” (ምሳሌ 16:28) ለሐሜትና ለስም ማጥፋት ማርከሻው ምንድን ነው? ንግግራችን ሁልጊዜ የሚያንጽና በፍቅር ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። የወንድሞቻችንን መጥፎ ነው ብለን ያሰብነውን ጎን ሳይሆን ጥሩ ጥሩ ባሕርያቸውን ለማየት የምንጥር ከሆነ ንግግራችን ሁልጊዜ አስደሳችና መንፈሳዊ ይሆናል። ሌሎችን መንቀፍ ቀላል እንደሆነ አትዘንጉ። ሌሎች ሰዎችን የሚያማላችሁ ሰው እናንተንም በሌሎች ዘንድ ሊያማችሁ ይችላል!—1 ጢሞቴዎስ 5:13፤ ቲቶ 2:3
15. በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ ቅዱሳን ሆነው እንዲኖሩ የሚረዳቸው የትኛው የክርስቶስ ባሕርይ ነው?
15 የጉባኤውን ቅድስና ለመጠበቅ ሁላችንም የክርስቶስ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል፤ የእርሱ ዐቢይ ባሕርይ ደግሞ ፍቅር እንደሆነ እናውቃለን። በመሆኑም ጳውሎስ የቆላስይስ ሰዎች እንደ ክርስቶስ ርኅሩኅ እንዲሆኑ እንዲህ ሲል መክሯቸዋል፦ “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ . . . ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፤ . . . በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።” በመቀጠልም “የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ” ብሏል። ይህን የመሰለ የይቅር ባይነት መንፈስ ከያዝን የጉባኤውን አንድነትና ቅድስና መጠበቅ እንደምንችል ምንም አያጠራጥርም።—ቆላስይስ 3:12-15
ቅድስናችን በጎረቤቶቻችን ዘንድ ይታያልን?
16. ቅዱስ አምልኮአችን ደስታ የሚገኝበት አምልኮ መሆን የሚኖርበት ለምንድን ነው?
16 ጎረቤቶቻችንስ? እንዴት ያዩናል? ከእውነት የሚገኘው ደስታ ይንጸባረቅብናል ወይስ ሸክም የሆነብን መስሎ እንዲታይ እናደርጋለን? ይሖዋ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እኛም ቅዱሳን ከሆንን በንግግራችንና በጠባያችን ግልጥ ሆኖ መታየት ይኖርበታል። ቅዱስ አምልኮአችን ደስታ የሚገኝበት አምልኮ መሆኑ በግልጽ መታየት ይኖርበታል። እንዲህ መሆን ያለበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም አምላካችን ይሖዋ አገልጋዮቹ ሁሉ እንዲደሰቱ የሚፈልግ ደስተኛ አምላክ ነው። በዚህም ምክንያት መዝሙራዊው ጥንት ስለነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” ብሎ ለመናገር ችሎ ነበር። ይህ ዓይነቱ ደስታ ይንጸባረቅብናልን? ልጆቻችን ጭምር በመንግሥት አዳራሽና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል በመገኘታቸው እርካታ ይሰማቸዋልን?—መዝሙር 89:15, 16፤ 144:15ለ አዓት
17. ሚዛኑን የጠበቀ ቅድስና ለማሳየት ምን ተግባራዊ ነገር ማድረግ እንችላለን?
17 ለጎረቤቶቻችን የትብብር መንፈስና ደግነት በማሳየት ቅድስናችንን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ አካባቢውን ለማጽዳት ወይም ደግሞ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ እንደሚደረገው መንገዶችንና አውራ ጎዳናዎችን ለመጠገን በጉርብትና መተባበር ያስፈልግ ይሆናል። በዚህ ረገድ ለአትክልት ቦታችን፣ ለግቢያችን ወይም ለሌሎች ንብረቶቻችን በምናደርገው እንክብካቤም ቅድስናችን ሊገለጽ ይችላል። ቆሻሻ በየቦታው የምንጥል ከሆነ ወይም የግቢያችን ንጽሕና ያልተጠበቀና እንክብካቤ የሚጎድለው ከሆነ አለዚያም አሮጌና የወላለቀ መኪና ወድቆ የሚታይ ከሆነ ለጎረቤቶቻችን አክብሮት አለን ማለት እንችላለንን?—ራእይ 11:18
በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት ቅዱስ መሆን
18. (ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች የሚገጥማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) ከዓለም የተለየን መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
18 ሐዋርያው ጳውሎስ ርኩሰት በሞላው የቆሮንቶስ ከተማ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፣ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፣ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር።” (1 ቆሮንቶስ 5:9, 10) በየዕለቱ ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ሰዎች ጋር የሚያገናኛቸው ጉዳይ ላላቸው ክርስቲያኖች ይህ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህ በተለይ ጾታዊ ጥቃት፣ ሙስና እና እምነት ማጉደል በሚወደሱባቸው ወይም ቸል ተብለው በሚታለፉባቸው ባሕሎች ውስጥ ንጹሕ አቋምን በጣም የሚፈታተን ነው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲኖር ‘ከሰው የማይገጥም ባሕርይ እንደሌለን’ ለማሳየት ስንል የአቋም ደረጃዎቻችንን አናላላም። ከዚህ ይልቅ ደግነት የተላበሰው ነገር ግን ከሌሎች የተለየው ክርስቲያናዊ ባሕርያችን የሚጎድላቸው መንፈሳዊ ነገር እንዳለ በሚታወቃቸውና የተሻለ ነገር ለማግኘት በሚፈልጉ አስተዋይ ሰዎች ዘንድ ለይቶ የሚያሳውቀን መሆን ይኖርበታል።—ማቴዎስ 5:3፤ 1 ጴጥሮስ 3:16, 17
19. (ሀ) ልጆቻችሁ በትምህርት ቤት ምን ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸውንና ቅዱስ አኗኗራቸውን ለመደገፍ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
19 በተመሳሳይም ልጆቻችን በትምህርት ቤት ብዙ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። እናንተ ወላጆች ልጆቻችሁ የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ሄዳችሁ ታያላችሁን? በዚያ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለ ታውቃላችሁን? ከአስተማሪዎቹ ጋር ትነጋገራላችሁን? እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዓለም ዙሪያ ባሉ ብዙ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ዕፅ የሚዘዋወርባቸው፣ ዓመፅ እና የጾታ ብልግና የሚፈጸምባቸው ዋሻዎች ሆነዋል። ልጆቻችሁ እናንተ ወላጆቻቸው ችግራቸውን ተረድታችሁ ሙሉ ድጋፋችሁን ካልሰጣችኋቸው እንዴት ንጹሕ አቋማቸውን ሊጠብቁና በቅዱስ ኑሮ ሊገኙ ይችላሉ? ጳውሎስ “አባቶች ሆይ፣ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” የሚል ምክር ለወላጆች መስጠቱ ተገቢ ነው። (ቆላስይስ 3:21) ልጆችን የሚያበሳጫቸው አንዱ ነገር በየዕለቱ የሚገጥሟቸውን ችግሮችና ፈተናዎች ሳትረዱላቸው መቅረታችሁ ነው። በትምህርት ቤት ያሉትን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም ዝግጅት የሚጀመረው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲሰፍን በማድረግ ነው።—ዘዳግም 6:6-9፤ ምሳሌ 22:6
20. ቅድስና ለሁላችንም የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
20 ለማጠቃለል ያህል ቅዱስ መሆን ለሁላችንም የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የሰይጣን ዓለም እንዳይሸረሽረንና አስተሳሰቡም እንዳይጋባብን ስለሚጠብቀን ነው። አሁንም ሆነ ወደ ፊት በረከት ያስገኝልናል። ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚገኘውን እውነተኛ ሕይወት ለመውረስ ዋስትና ይሆነናል። ሚዛናዊ፣ በቀላሉ የምንቀረብ፣ ተግባቢ ክርስቲያኖች እንድንሆን ይረዳናል፤ ግትሮች አንሆንም። ባጭሩ ክርስቶስን እንድንመስል ያደርገናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:19
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከማያምን የትዳር ጓደኛ ጋር ሊኖር ስለሚገባው ጥበብ የተሞላበት ግንኙነት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት መጠበቂያ ግንብ 16-111 ላይ የወጣውን “የትዳር ጓደኛችሁን ችላ አትበሉ” የሚለውን ርዕስ ገጽ 20-2ና መጠበቂያ ግንብ 21-109 ገጽ 19-20 አንቀጽ 20-2ን ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን ስለ ቅድስና መምከሩን አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው ለምን ነበር?
◻ ቅዱስ ኑሮ መኖር ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?
◻ በቤተሰባችን ውስጥ ቅድስና ይበልጥ እንዲሰፍን ሁላችንም ምን ማድረግ እንችላለን?
◻ ጉባኤው በቅድስና እንዲመላለስ ሊወገድ የሚገባው ቅዱስ ያልሆነ ተግባር ምንድን ነው?
◻ በሥራ ቦታና በትምህርት ቤት ቅዱስ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎትና በሌሎች ሥራዎቻችን ሁሉ ደስተኞች መሆን ይገባናል