ሁልጊዜ የወንድማማችነት ፍቅር ይኑራችሁ!
“ሁልጊዜ የወንድማማችነት ፍቅር ይኑራችሁ።”—ዕብራውያን 13:1 የ1980 ትርጉም
1. ቀዝቃዛ በሆነ ምሽት እሳቱ መንደዱን እንዲቀጥል ምን ታደርጋላችሁ? ሁላችንም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ምን ኃላፊነት አለብን?
ውጭ ያለው ብርድ በጣም ኃይለኛ ነው፤ ቅዝቃዜው እየጨመረ ሄዷል። ቤታችሁን የሚያሞቀው በምድጃው ላይ እየነደደ ያለው እሳት ብቻ ነው። ሕይወታችሁን ማቆየት የምትችሉት እሳቱ እንዳይጠፋ ማድረግ ስትችሉ ብቻ ነው። ነበልባሉ ሲጠፋና ቀይ የነበረው ፍም እየከሰመ ሄዶ አመድ ሲሆን ዝም ብላችሁ ትመለከቱታላችሁን? አታደርጉትም። እሳቱ መንደዱን እንዲቀጥል ያለመታከት እንጨት መቆስቆሳችሁ አይቀርም። እኛም በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ሊንቦጎቦግ የሚገባውን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ “እሳት” ይኸውም ፍቅርን በተመለከተ ተመሳሳይ ተግባር ማከናወን ይጠበቅብናል።
2. (ሀ) በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ፍቅር እየቀዘቀዘ ሄዷል ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ ነገር ነው?
2 የምንኖረው ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች ዘንድ ፍቅር እየቀዘቀዘ ባለበት ዘመን ውስጥ ነው። (ማቴዎስ 24:12) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ከሁሉ ስለሚበልጠው የፍቅር ዓይነት ማለትም ለይሖዋ አምላክና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ስላለን ፍቅር ነው። ሌሎች የፍቅር ዓይነቶችም እየተመናመኑ ሄደዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻው ቀን” ብዙዎች “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 NW) ይህ ምንኛ እውነት ነው! ቤተሰብ ተፈጥሮአዊ ፍቅር የሚታይበት ቦታ ሊሆን ሲገባው ጠብና ድብድብ አንዳንድ ጊዜም የሚዘገንን የጭካኔ ድርጊት የሚፈጸምበት ቦታ ሆኗል። አዎን፣ ሰዎች ለሰዎች ያላቸው ስሜት ቀዝቃዛ በሆነበት በዚህ ዓለም ውስጥ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ከራሳቸው አብልጠው በማየት የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዲያሳዩ ታዝዘዋል። ይህ ፍቅር የእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ መለያ ምልክት መሆኑ ለሁሉም በጉልህ በሚታይበት መንገድ ሊንጸባረቅ ይገባዋል።—ዮሐንስ 13:34, 35
3. የወንድማማችነት ፍቅር ምንድን ነው? ይህ ፍቅር ሁልጊዜ መኖር አለበት ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተነሳስቶ “ሁልጊዜ የወንድማማችነት ፍቅር ይኑራችሁ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። (ዕብራውያን 13:1 የ1980 ትርጉም) አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳሠፈረው “የወንድማማችነት ፍቅር” (ፊላደልፊያ ) የሚለው የግሪክኛ ቃል “የሚያመለክተው የጠበቀ ፍቅርን፣ ደግነት ማሳየትን፣ የሌላውን ስሜት መረዳትንና እርዳታ መስጠትን” ነው። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ሁልጊዜ ይኑር ሲል ምን ማለቱ ነው? ይኸው ጽሑፍ “ፈጽሞ መቀዝቀዝ አይገባውም” ማለቱ ነው ብሏል። እንግዲያውስ ለወንድሞቻችን የጠበቀ የመውደድ ስሜት ስለተሰማን ብቻ መርካት አይገባንም፤ በግልጥ እንዲታይ ልናደርግ ይገባናል። ከዚህም ሌላ ይህ ፍቅር ቀስ በቀስ እንዳይቀዘቅዝ በመጠበቅ ዘላቂ ልናደርገው ይገባል። ይህን ማድረግ ፈታኝ ነውን? አዎን፣ ፈታኝ ነው፤ ይሁን እንጂ የይሖዋ መንፈስ የጠበቀ የወንድማማችነት ፍቅር እንድንኮተኩትና ይህንንም ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። በእሳት የተመሰለውን ፍቅርን በልባችን ውስጥ መቆስቆስ የምንችልባቸውን ሦስት መንገዶች እንመልከት።
የሌላውን ሰው ችግር እንደራሳችሁ አድርጋችሁ አስቡ
4. የሌሎችን ችግር እንደራስ መመልከት ማለት ምን ማለት ነው?
4 ለክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ያለህን ፍቅር ማሳደግ የምትፈልግ ከሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ራስህን በእነርሱ ቦታ በማስቀመጥ በሕይወታቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ችግር ልትረዳላቸውና ልታዝንላቸው ያስፈልግ ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህንኑ ጉዳይ ጠቅሷል:- “በቀረውስ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ፤ የሌላውን ችግር እንደራሳችሁ አድርጋችሁ አስቡ፤ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ ደጎችና ትሑቶች ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8 የ1980 ትርጉም) “የሌላውን ችግር እንደራሳችሁ አድርጋችሁ” አስቡ በሚለው ፋንታ የገባው የግሪክኛ ቃል “መከራን መጋራት” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተሠራበት የግሪክኛ ቋንቋ ማብራሪያ የሚሰጥ አንድ መጽሐፍ ይህን ቃል በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “ቃሉ የሌሎችን ችግር እንደ ራሳችን ችግር አድርገን በማሰብ ስሜታቸውን በምንጋራበት ጊዜ የሚኖረንን ውስጣዊ ሁኔታ ያመለክታል።” በመሆኑም ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። አንድ በዕድሜ የገፋ የታመነ የይሖዋ አገልጋይ በአንድ ወቅት “ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ስቃያቸው በጥልቅ እንዲሰማን ማድረግ ነው” ሲል ተናግሯል።
5. ይሖዋ የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ እንደሚመለከት እንዴት እናውቃለን?
5 ይሖዋ በዚህ መንገድ የሌሎችን ችግር እንደራሱ ችግር አድርጎ ይመለከታልን? እንዴታ። ለምሳሌ ያህል በሕዝቡ በእስራኤል ላይ የደረሰውን መከራ በሚመለከት “በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ” የሚል እናነባለን። (ኢሳይያስ 63:9) ይሖዋ ችግራቸውን ከማየትም አልፎ አብሯቸው ተጨንቋል። በዘካርያስ 2:8 (NW) ላይ የሚገኙት ይሖዋ ራሱ የተናገራቸው “የሚነካችሁ የዓይኔን ብሌን የሚነካ ነው” የሚሉት ቃላት ምን ያህል በጥልቅ እንደሚነካ ይገልጻሉ።a አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ ይህንን ጥቅስ በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “ዓይን ከሰው ልጅ የአካል ክፍሎች ሁሉ በጣም ውስብስብ ከሆኑትና ጥንቃቄ ከሚጠይቁት መካከል አንዱ ነው፤ ከዚህ ይበልጥ ደግሞ ማየት እንችል ዘንድ የሰማይ ብርሃን ወደ ዓይናችን የሚገባበት ቀዳዳ ማለትም የዓይናችን ብሌን ከሁሉ ይበልጥ ጥንቃቄ የሚሻና በጣም ወሳኝ ክፍል ነው። ይሖዋ ለሚያፈቅራቸው ሕዝቦቹ ያለውን ጥልቅ አሳቢነት ከዚህ ይበልጥ ሊገልጽ የሚችል ምንም ነገር የለም።”
6. ኢየሱስ ክርስቶስ የሌሎችን ችግር እንደ ራሱ አድርጎ እንደሚመለከት ያሳየው እንዴት ነው?
6 ኢየሱስም ዘወትር የሌሎችን ችግር እንደራሱ አድርጎ ይመለከት ነበር። የታመሙትንም ሆነ ችግር የደረሰባቸውን ሌሎች ሰዎች መከራ ሲመለከት በተደጋጋሚ ጊዜ ‘ሐዘን’ ተሰምቶታል። (ማርቆስ 1:41፤ 6:34) ለቅቡዓን ተከታዮቹ ደግነት የማያሳዩ ሰዎችንም በሚመለከት በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ አድርጎ እንደሚቆጥረው ገልጿል። (ማቴዎስ 25:41-46) ዛሬ ሰማያዊው ‘ሊቀ ካህናችን’ እርሱ በመሆኑ ‘በድካማችን ሊራራልን የሚችል’ ሊቀ ካህን አግኝተናል።—ዕብራውያን 4:15
7. አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቢያበሳጩን የሌሎችን ችግር እንደራሳችን አድርገን መመልከታችን የሚረዳን እንዴት ነው?
7 ‘በድካማችን ሊራራልን የሚችል’ የሚለው አነጋገር የሚያጽናና አይደለም? እንግዲያውስ እርስ በርሳችንም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ መጣር ይገባናል። እርግጥ የሌሎችን ድክመት መልቀም በጣም ቀላል ነው። (ማቴዎስ 7:3-5) ይሁን እንጂ ሌላ ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚያስቆጣ ነገር ሲፈጽሙብህ ለምን እንደዚህ ለማድረግ አትሞክርም? ራስህን በእነርሱ ቦታ አስቀምጠህ ማለትም የእነርሱ ዓይነት አስተዳደግና ባሕርይ ኖሮህ ተመሳሳይ ችግር ቢገጥምህ ምን ታደርግ እንደነበር አስብ። ተመሳሳይ ስህተት ምናልባትም ከዚህ የከፋ ስህተት እንደማትፈጽም እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? ከሌሎች ብዙ ከመጠበቅ ይልቅ የሌላውን ሰው ችግር እንደራሳችን አድርገን ልናስብ ይገባል፤ ይህም ‘አፈር መሆናችንን እንደሚያስበው’ እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ እንድንሆን ይረዳናል። (መዝሙር 103:14፤ ያዕቆብ 3:17) እርሱ ያለብንን የአቅም ገደብ ያውቃል። ልናደርገው ከምንችለው ነገር በላይ ፈጽሞ አይጠብቅብንም። (ከ1 ነገሥት 19:5-7 ጋር አወዳድር።) ሁላችንም የሌሎችን ችግር እንደራሳችን እንመልከት።
8. አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት አንዳንድ መከራዎች ሲደርሱባቸው ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይገባናል?
8 ጳውሎስ ጉባኤው በአንድነት ተባብረው የሚሠሩ የተለያዩ ብልቶች እንዳሉት አንድ አካል መሆኑን ገልጿል። በመቀጠልም:- “አንድም ብልት ቢሠቃይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሠቃያሉ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 12:12-26) አንዳንድ መከራ ከሚደርስባቸው ጋር መከራቸውን ልንጋራቸው ወይም ራሳችንን በእነርሱ ቦታ አስቀምጠን ችግራቸውን ልንረዳላቸው ይገባል። በዚህ ረገድ ሽማግሌዎች ቀዳሚ ሆነው ይገኛሉ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጨምሮ ጽፏል:- “የሚደክም ማን ነው፣ እኔም አልደክምምን? የሚሰናከል ማን ነው፣ እኔም አልናደድምን?” (2 ቆሮንቶስ 11:29) በዚህ ረገድ ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የጳውሎስን ምሳሌ ይከተላሉ። በሚያቀርቡት ንግግር፣ በእረኝነት ሥራቸውና የፍርድ ጉዳዮችን በሚያዩበት ጊዜ ሳይቀር የሌላውን ሰው ችግር እንደራሳቸው አድርገው ለመመልከት ይጥራሉ። ጳውሎስ “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” ሲል መክሯል። (ሮሜ 12:15) እረኞቹ ስሜታቸውን እንደሚረዱላቸው፣ ያሉባቸውን የአቅም ገደቦች እንደሚገነዘቡላቸው እንዲሁም በእነርሱ ላይ የሚደርሰው መከራ እንደሚያሳዝናቸው ሲያውቁ በጎቹ የሚሰጣቸውን ምክር፣ መመሪያና ተግሳጽ ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኛ ይሆናሉ። ‘ለነፍሳቸው እረፍት እንደሚያገኙ’ እርግጠኞች በመሆን በጉጉት በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።—ማቴዎስ 11:29
አድናቆት ማሳየት
9. ይሖዋ መልካም ጎናችንን እንደሚያደንቅ የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 የወንድማማችነትን ፍቅር ማቀጣጠል የምንችልበት ሁለተኛው መንገድ አድናቆት ማሳየት ነው። ሌሎችን ለማድነቅ በመልካም ባሕርይዎቻቸው ላይ ማተኮርና ለሚያደርጓቸው ጥረቶች ትልቅ ግምት መስጠት ይኖርብናል። ይህንን ስናደርግ ይሖዋን ራሱን እንመስለዋለን። (ኤፌሶን 5:1 NW) እርሱ በየዕለቱ ብዙ ጥቃቅን ኃጢአቶቻችንን ይቅር ይለናል። እውነተኛ ንስሐ እስከገባን ድረስ ከባድ ኃጢአቶችን ሳይቀር ይቅር ይለናል። አንድ ጊዜ ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በኋላ ዳግመኛ ስለዚያ አያውጠነጥንም። (ሕዝቅኤል 33:14-16) መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” ሲል ጠይቋል። (መዝሙር 130:3) ይሖዋ የሚያተኩረው እርሱን በማገልገል በምናከናውናቸው መልካም ነገሮች ላይ ነው።—ዕብራውያን 6:10
10. (ሀ) የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን አድናቆት ማጣታቸው አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ለትዳር ጓደኛው ያለውን አድናቆት እያጣ ያለ አንድ ሰው ምን ማድረግ ይገባዋል?
10 በተለይ ይህንን ምሳሌ በቤተሰብ ውስጥ መከተል በጣም አስፈላጊ ነው። ወላጆች አንዳቸው ሌላውን የሚያደንቁ ከሆነ ለቤተሰባቸው ምሳሌ ይሆናሉ። ትዳር መቅኖ ባጣበት በአሁኑ ዘመን የትዳር ጓደኛን ችላ ማለትና የእርሱን ወይም የእርሷን መልካም ባሕርይዎች በመዘንጋት ስህተቶቹን ወይም ስህተቶቿን ማጉላት በጣም ቀላል ነው። እንዲህ ያለው አሉታዊ አስተሳሰብ ትዳርን በመሸርሸር ደስታ የሌለበት ሸክም እንዲሆን ያደርጋል። ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁ አድናቆት እየተመናመነ ከመጣ ‘በእርግጥ የትዳር ጓደኛዬ ምንም መልካም ባሕርያት የላትምን/የለውምን?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። በመጀመሪያ እንድትወዱትና እንድታገቡት ስላደረጓችሁ ምክንያቶች መለስ ብላችሁ አስቡ። ይህንን ልዩ ሰው እንድትወዱት ያደረጓችሁ ምክንያቶች ሁሉ ጠፍተዋልን? እንደዚያ እንደማይሆን ግልጽ ነው፤ እንግዲያውስ የትዳር ጓደኛችሁን መልካም ባሕርያት ለማድነቅ ተጣጣሩ፤ አድናቆታችሁንም በቃላት ግለጹ።—ምሳሌ 31:28
11. በትዳር ጓደኛሞች መካከል ያለው ፍቅር ከግብዝነት ነፃ እንዲሆን ካስፈለገ ሊወገድ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
11 በተጨማሪም አድናቆት የትዳር ጓደኛሞች ፍቅራቸው ከግብዝነት ነፃ እንዲሆን ይረዳቸዋል። (ከ2 ቆሮንቶስ 6:6፤ 1 ጴጥሮስ 1:22 ጋር አወዳድር።) ከልብ በመነጨ አድናቆት ላይ የተመሠረተ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ባለበት ትዳር ውስጥ ከተዘጋ በር በስተኋላ የሚፈጸም የጭካኔ ድርጊትም ሆነ የሚጎዱና የሚያዋርዱ ቃላት ቦታ የላቸውም። በተጨማሪም ምንም ዓይነት የደግነትና የትህትና ቃላት ሳይለዋወጡ የተኮራረፉ ያህል ሆነው የሚኖሩበት አልፎ ተርፎም ድብድብ ያለበት ትዳር አይሆንም። (ኤፌሶን 5:28, 29) አንዳቸው ሌላውን ከልብ የሚያደንቁ ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው ይከባበራሉ። ይህን የሚያደርጉት በሰው ፊት ሲሆኑ ብቻ ሳይሆን በይሖዋ እይታ ውስጥ እስካሉ ድረስ በሌላ አባባል በማንኛውም ጊዜ ሁሉ ነው።—ምሳሌ 5:21
12. ወላጆች ልጆቻቸው ላላቸው መልካም ጎን አድናቆታቸውን መግለጽ የሚገባቸው ለምንድን ነው?
12 ልጆችም እንደምታደንቋቸው ሊሰማቸው ይገባል። ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያው በከንቱ ሊያወድሷቸው ይገባል ማለት ሳይሆን የሚያስመሰግኑ ባሕርይዎቻቸውንና ያደረጉትን መልካም ነገር በማንሳት ሊያመሰግኗቸው ይገባል። ይሖዋ በኢየሱስ ደስ መሰኘቱን በመግለጽ ያሳየውን ምሳሌ አስታውሱ። (ማርቆስ 1:11) እንዲሁም ኢየሱስ እንደ “ጌታ” ተደርጎ በተጠቀሰበት ምሳሌ ውስጥ ያሳየውን አርዓያም አስታውሱ። እያንዳንዳቸው በተሰጣቸውና ባፈሩት ነገር ረገድ ልዩነት የነበረ ቢሆንም ሁለቱንም “አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ” በማለት እኩል አመስግኗቸዋል። (ማቴዎስ 25:20-23፤ ከማቴዎስ 13:23 ጋር አወዳድር።) ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ ስላለው ለየት ያለ ባሕርይ፣ ችሎታና ስላገኘው ውጤት አድናቆታቸውን የሚገልጹበትን መንገድ ይፈልጋሉ። በአንፃሩ ደግሞ ያከናወኑትን ነገር ከልክ በላይ በማጋነን ልጆቻቸው ከሌሎች ልቀው የመታየት ስሜት እንዲያድርባቸው ላለማድረግ ይጠነቀቃሉ። ልጆቻቸው ተበሳጭተው እንዲያድጉ ወይም ልባቸው እንዲዝል አይፈልጉም።—ኤፌሶን 6:4፤ ቆላስይስ 3:21
13. እያንዳንዱን የጉባኤ አባል በማድነቅ ረገድ ቀዳሚ ሆነው የሚገኙት እነማን ናቸው?
13 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ለእያንዳንዱ የአምላክ መንጋ አባል አድናቆት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ ሆነው ይገኛሉ። በጽድቅ የመገሰጽ፣ ኃጢአት የፈጸሙትን በየዋሕነት የማቅናት እንዲሁም ሲያስፈልግ ለአንዳንዶች ጠንከር ያለ ምክር የመስጠት ከባድ ኃላፊነት ስላለባቸው ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። እነዚህን ሁለት የተለያዩ ኃላፊነቶች በሚዛናዊነት ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው?—ገላትያ 6:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
14, 15. (ሀ) ጳውሎስ ጠንከር ያለ ምክር በመስጠት ረገድ ሚዛናዊነትን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሁንና ክርስቲያን ሽማግሌዎች ስህተትን የማረምንና የማመስገንን አስፈላጊነት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
14 የጳውሎስ ምሳሌ ትልቅ እገዛ ይሆናቸዋል። ግሩም አስተማሪ፣ ሽማግሌና እረኛ ነበር። ከባድ ችግር የነበረባቸው ጉባኤዎች ገጥመውት ስለነበር አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጠንከር ያለ ምክር ከመስጠት ወደኋላ አላለም። (2 ቆሮንቶስ 7:8-11) የጳውሎስን አገልግሎት መለስ ብለን ስንቃኝ ሁልጊዜ ተግሳጽ ይሰጥ እንዳልነበር እንረዳለን፤ ይህንን የሚያደርገው ከሁኔታው አንጻር አስፈላጊና ተገቢ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ነበር። ይህን በማድረጉ አምላካዊ ጥበብ እንዳለው አሳይቷል።
15 አንድ ሽማግሌ የሚያከናውነውን አገልግሎት ከሙዚቃ ጋር ብናወዳድረው ተግሳጽና ወቀሳ በሙዚቃ ውስጥ እንደሚሰማ አንድ ኖታ ብቻ ይሆናል። ይህ ኖታ በቦታው ሲሰማ ደስ ይላል። (ሉቃስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2) ይህ አንድ ኖታ ብቻ በተደጋጋሚ የሚሰማበት ሙዚቃ ምን እንደሚመስል እስቲ አስበው። ወዲያው ለጆሮ ይሰለቻል። በተመሳሳይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ትምህርታቸው ሁሉንም የሚያቅፍና ኅብር ያለው እንዲሆን ይጥራሉ። ችግሮችን በማስተካከል ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ የትምህርታቸው አጠቃላይ መልእክት የሚያንጽ ይሆናል። ልክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎችም አስቀድመው የሚነቅፉበትን ስህተት ሳይሆን የሚያመሰግኑበትን በጎ ጎን ይፈልጋሉ። መሰል ክርስቲያኖች የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት ያደንቃሉ። አነሰም በዛ እያንዳንዱ ይሖዋን ለማገልገል የተቻለውን ሁሉ እያደረገ እንዳለ እርግጠኞች ናቸው። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ይህንን ስሜታቸውን በቃላት ከመግለጽ ወደ ኋላ አይሉም።—ከ2 ተሰሎንቄ 3:4 ጋር አወዳድር።
16. ጳውሎስ አድናቂና ራሱን በሌሎች ቦታ የሚያስቀምጥ ሰው መሆኑ በመሰል ክርስቲያኖች ላይ ያመጣው ውጤት ምንድን ነው?
16 ጳውሎስ ካገለገላቸው ክርስቲያኖች መካከል አብዛኞቹ እንደሚያደንቃቸውና ችግራቸውን እንደራሱ ችግር በመመልከት እንደሚያስብላቸው ሆኖ ይሰማቸው እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ይህንን እንዴት እናውቃለን? ስለ ጳውሎስ እንዴት ይሰማቸው እንደነበር ተመልከት። ትልቅ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም እንኳን አይፈሩትም ነበር። አዎን፣ የሚወደድና የሚቀረብ ሰው ነበር። እንዲያውም ከአንድ አካባቢ ለቆ ሲሄድ ሽማግሌዎቹ ‘አንገቱ ላይ ተጠምጥመው ስመውታል’! (ሥራ 20:17, 37) ሽማግሌዎችም ሆኑ ሁላችንም የጳውሎስን ምሳሌነት በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል! አዎን፣ አንዳችን ለሌላው አድናቆት እንዳለን እናሳይ።
የፍቅራዊ ደግነት መግለጫዎች
17. በጉባኤ ውስጥ የደግነት መግለጫ የሆኑ ድርጊቶችን ከማከናወን የሚገኙ አንዳንድ መልካም ውጤቶች ምንድን ናቸው?
17 የጋለ የወንድማማችነት ፍቅር እንዲኖር ከሚረዱን ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ነገሮች መካከል አንዱ ብዙም ነገር የማይጠይቅ የደግነት ድርጊት ነው። ኢየሱስ እንዳለው “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው።” (ሥራ 20:35) የምንሰጠው ነገር መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ወይም ደግሞ ጊዜያችንንም ሆነ ጉልበታችንን ሌሎችን ደስ ከማሰኘታችንም በላይ እኛ ራሳችን እንደሰታለን። ደግነት በጉባኤ ውስጥ ከአንዱ ወደሌላው የሚተላለፍ ባሕርይ ነው። አንድ የደግነት ድርጊት ሌላ ተመሳሳይ የደግነት ድርጊት እንዲታይ ምክንያት ይሆናል። ከዚያ ወዲያ የወንድማማች መዋደድ ያብባል!—ሉቃስ 6:38
18. በሚክያስ 6:8 ላይ የተገለጸው “ደግነት” ትርጉም ምንድን ነው?
18 ይሖዋ ሕዝቡ እስራኤል ደግነትን እንዲያሳይ አሳስቧል። በሚክያስ 6:8 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ሰው ሆይ፣ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም [“ደግነትንም፣” NW] ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ‘ደግነትን መውደድ’ ማለት ምን ማለት ነው? እዚህ ላይ ደግነት የሚለውን ቃል ወክሎ የገባው (ቼሴድ ) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል በአማርኛ ‘ምሕረት’ ተብሎም ተተርጉሟል። ዘ ሶንሲኖ ቡክስ ኦቭ ዘ ባይበል የተባለው መጽሐፍ እንዳሰፈረው ይህ ቃል “ምሕረት እንደሚለው ቃል የማይጨበጥን ነገር ከማመልከት እጅግ የሚበልጥ ከመሆኑም ሌላ በተግባር የሚገለጽን ባሕርይ የሚያመለክት ነው። ቼሴድ ‘በተግባር የሚገለጽ ምሕረት’ ማለት ሲሆን ለድኻና ለችግረኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች የፍቅራዊ ደግነት መግለጫ የሆኑ ነገሮችን ማድረግን ይጠይቃል።” ሌላ አንድ ምሁርም ቼሴድ ማለት “በተግባር የተገለጸ ፍቅር” ማለት ነው ብለዋል።
19. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ለሌሎች ደግነት በማሳየት ረገድ በየትኞቹ መንገዶች ቀዳሚ ሆነን ልንገኝ እንችላለን? (ለ) ሌሎች ለአንተ የወንድማማችነት ፍቅር ያሳዩበትን አጋጣሚ ጥቀስ።
19 የወንድማማችነት ፍቅራችን እንዲያው በአፍ ብቻ የሚገለጽ ምናባዊ ነገር አይደለም። ተጨባጭ እውነታ ነው። እንግዲያውስ ለወንድሞችህና ለእህቶችህ ደግነት ማሳየት የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ። ሰዎች ለእርዳታ ወደ እርሱ እንዲመጡ ሳይጠብቅ ብዙውን ጊዜ ራሱ ቀዳሚ ሆኖ ይገኝ የነበረውን የኢየሱስን ምሳሌ ተከተል። (ሉቃስ 7:12-16) በተለይ ይበልጥ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አስብ። ሊጠየቅ የሚገባው ወይም የሚላላከው ሰው የሚያስፈልገው በዕድሜ የገፋ ወይም የአካል ጉዳተኛ የሆነ ሰው ይኖር ይሆን? የአንተን ጊዜና ትኩረት የሚሻ ‘አባት የሌለው ልጅ’ አለን? ችግሩን የሚያዳምጠው ወይም ጥቂት የሚያጽናኑ ቃላትን የሚያካፍለው ሰው የሚፈልግ የተጨነቀ ነፍስ ይኖራልን? የሚቻለን ሲሆን እንዲህ ላሉት ደግነት ለማሳየት ጊዜ እንመድብ። (ኢዮብ 29:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14፤ ያዕቆብ 1:27) ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች በሞሉበት ጉባኤ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የደግነት ድርጊቶች አንዱ ይቅር ባይነት እንደሆነ አትዘንጋ፤ ይህም የምንነቅፈው ነገር ቢኖረን እንኳ ቅሬታውን በነጻ መተውን ይጠይቃል። (ቆላስይስ 3:13 NW) ይቅር ባይ መሆን በእሳት የተመሰለውን የወንድማማችነት ፍቅር እንደ እርጥብ ብርድ ልብስ ከሚያዳፍኑት መከፋፈል፣ ቂምና ጠብ ጉባኤውን ለመጠበቅ ይረዳል።
20. ሁላችንም ምን እያልን ራሳችንን መመርመራችንን መቀጠል ይገባናል?
20 ሁላችንም ይህን በጣም ወሳኝ የሆነ የፍቅር እሳት በልባችን ውስጥ መቀጣጠሉን እንዲቀጥል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ሁልጊዜ ራሳችንን እንመርምር። የሌሎች ሰዎችን ችግር እንደራሳችን አድርገን እንመለከታለንን? ለሌሎች አድናቆት አለንን? ለሌሎች ደግነት እናደርጋለንን? ይህንን እስካደረግን ድረስ ይህ ዓለም የቱንም ያህል አጥንት የሚሰብር ቅዝቃዜ ቢኖረው የፍቅራችን እሳት ወንድማማችነታችንን ያሞቀዋል። እንግዲያውስ በማንኛውም ዘርፍ አሁንም ሆነ ለዘላለም “የወንድማማችነት ፍቅር ይኑራችሁ!”—ዕብራውያን 13:1 የ1980 ትርጉም
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ትርጉሞች የአምላክን ሕዝቦች የሚነካ የአምላክን ዓይን እንደሚነካ ሳይሆን የእስራኤልን ወይም የራሱን ዓይን እንደሚነካ አስመስለው ተርጉመውታል። ይህ ስህተት የተፈጠረው በመካከለኛው ዘመን በኖሩትና ተቃራኒ ሐሳብ ያስተላልፋሉ ያሏቸውን ጥቅሶች በራሳቸው መንገድ በስህተት ለማስተካከል በሞከሩት ጸሐፊዎች አማካኝነት ነው። ይህን ማድረጋቸው ይሖዋ ያለው የአዛኝነት ስሜት እንዲሠወር አድርጓል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ የወንድማማችነት ፍቅር ምንድን ነው? ይህ ፍቅር ምን ጊዜም እንዳይጠፋ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
◻ የሌሎች ሰዎችን ችግር እንደራሳችን አድርገን መመልከት የወንድማማችነት ፍቅራችን ምንጊዜም እንዳይጠፋ የሚረዳን እንዴት ነው?
◻ አድናቆት በወንድማማችነት ፍቅራችን ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?
◻ የደግነት ድርጊቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የወንድማማችነት ፍቅራችን እንዲያብብ የሚያደርጉት እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍቅር በተግባር ሲገለጽ
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለጥቂት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና አንድ ሰው ስለ ወንድማማችነት ፍቅር አንዳንድ ጥርጣሬዎች ያድሩበታል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ሲል እንደተናገረ ያውቃል። (ዮሐንስ 13:35) ይሁን እንጂ ይህን ነገር ለማመን ተቸግሮ ነበር። አንድ ቀን ግን ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ተመለከተ።
ይህ ሰው ከተሽከርካሪ ወንበር የማይለይ ቢሆንም እንኳ ከመኖሪያ ቤቱ ራቅ ወዳለ ቦታ ይሄዳል። በእስራኤል ቤተ ልሔም ውስጥ በአንድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ይገኛል። በዚህ ጉባኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ የአረብ ተወላጅ የሆነ ምሥክር ከሌላ አገር ለጉብኝት የመጣ አንድ ወንድም እቤቱ እንዲያድር ጋብዞ ነበር። በዚህ ጊዜ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪም አብሮ ይጋብዘዋል። ማታ ወደ መኝታቸው ከመሄዳቸው በፊት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሚቀጥለው ቀን ጠዋት ተነስቶ በበረንዳው በኩል ሆኖ ፀሐይ ስትወጣ ማየት ይችል እንደሆነ የጋበዘውን ወንድም ፈቃድ ይጠይቃል። ጋባዡ እንደዚያ ማድረግ እንደማይኖርበት አጥብቆ ያሳስበዋል። በሚቀጥለው ቀን ይህ አረብ ወንድም ለምን እንደከለከለው ምክንያቱን በአስተርጓሚ ያስረዳዋል። ጎረቤቶቹ የአይሁድ ተወላጅ የሆነ ሰው (እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ያለ ማለት ነው) በእንግድነት እንደተቀበለ ቢያውቁ ቤቱን ከነቤተሰቡ በእሳት ያጋዩት እንደነበር ገለጸ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ይህን ሲሰማ በግራ መጋባት ስሜት ተውጦ “ታዲያ ይህን እያወቅህ እንዴት ጋበዝከን?” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ይህ የአረብ ተወላጅ የሆነ ወንድም ያለ አስተርጓሚ ዓይን ዓይኑን እያየ “ዮሐንስ 13:35” ብቻ ብሎ ዝም አለ።
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የወንድማማችነት ፍቅር እውን ሆኖ በማየቱ በጣም ተነካ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ ተግባቢና አድናቂ መሆኑ የሚቀረብ ሰው አድርጎታል