ጊዜው አንተ ከምታስበው የበለጠ ወደፊት ገፍቷልን?
ኢየሱስ ከመሞቱ ከሦስት ቀን በፊት በኢየሩሳሌም ውስጥ ሥራ በጣም የበዛበት ቀን አሳልፎ ነበር። ያ ቀን አሁን ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ትልቅ ትርጉም ያለው ቀን ነበር። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ነበር፤ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እርሱን ለማጥመድ ያቀረቧቸውን ተንኮል ያዘሉ ጥያቄዎች መልሶአል። በመጨረሻም ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ ገሃነም የሚያመሩ ግብዞችና መርዘኛ እባቦች መሆናቸውን በመግለጽ አወገዛቸው።—ማቴዎስ ምዕራፍ 22, 23
የቤተ መቅደሱን አካባቢ ትቶ ሲሄድም ከደቀመዛሙርቱ አንዱ “መምህር ሆይ፣ እንዴት ያሉ ድንጋዮችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደሆኑ እይ አለው።” ኢየሱስም በዚህ ምንም ባለመደነቅ፦ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አለው። (ማርቆስ 13:1, 2) በዚያን ጊዜም ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ለመጨረሻ ጊዜ ትቶ በመሄድ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወርዶ ተሻገረና የደብረ ዘይትን ዳገት ወጣ።
ከሸለቆው ባሻገር ቤተ መቅደሱን በሞሪያ ተራራ ላይ ከፊት ለፊቱ እየተመለከተ በተራራው ላይ ቁጭ ብሎ ወደ ማምሻው ላይ የነበረውን ፀሐይ ይሞቃል። ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ለብቻቸው ወደ እርሱ መጡ። ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ የተናገራቸው ቃል አእምሮአቸውን አስጨንቆት ነበር። ስለዚህም እንዲህ ብለው ጠየቁት፦ “እነዚህ ነገሮች የሚሆኑት መቼ ነው? የመገኘትህና የነገሮች ስርዓት መደምደሚያ ዘመን ምልክት ምንድን ነው?” (ማቴዎስ 24:3፤ ማርቆስ 13:3, 4 አዓት) ያን ቀን ከሰዓት በኋላ በደብረ ዘይት ለጠየቁት ጥያቄ እርሱ የሰጣቸው መልስ ለእኛም በጣም አስፈላጊ ነው። ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን” ከማሰብ በጣም እንዳንዘገይ ሊጠብቀን ይችላል።
ጥያቄያቸው ሁለት ፍሬ ነገሮችን ያጠቃለለ ነበር። አንዱ ክፍል ስለ ቤተ መቅደሱና ስለ አይሁድ ሥርዓት መጨረሻ የሚገልጽ ሲሆን ሌላው ደግሞ ኢየሱስ ንጉሥ በመሆን ስለሚገኝበት የወደፊት ጊዜና ስለ አሁኑ የነገሮች ስርዓት መደምደሚያ ዘመን የሚገልጽ ነው። ሁለቱም ጥያቄዎች በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፣ በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ ኢየሱስ በሰጣቸው መልሶች ውስጥ ተሸፍነዋል። (በተጨማሪም ራእይ 6:1-8 ተመልከት) የዚህን የአሁኑን የዓለም ወይም የነገሮች ስርዓት መደምደሚያ በተመለከተ ኢየሱስ በአንድ ላይ ተጠቃለው የመጨረሻ ቀኖችን ለይተው የሚያሳውቁ በአንድ ወቅት የሚፈጸሙ ጥምር ምልክት የሚሆኑ አያሌ ገጽታዎችን ገልጿል። ይህ ብዙ ክፍሎችን ያጣመረ ምልክት እየተፈጸመ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተነገረላቸው የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንድንኖር አድርጓልን? የምልክቱስ መፈጸም ቀኑ ከምናስበው በላይ ገፍቶ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቀናልን?
ብዙ ክፍሎችን አጣምሮ የያዘው የኢየሱስ ምልክት አንዱ ገጽታ፦ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና” ይላል። (ማቴዎስ 24:7) በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚያን ጊዜ የነበሩት የይሖዋ ምስክሮች ወዲያውኑ ነቅተው ዝግጁ ሆኑ። ለምን? ከ35 ዓመታት ቀደም ብሎ በታህሣሥ ወር 1879 ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ላይ በመመስረት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት 1914 በሰው ታሪክ ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ መክፈቻ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። 28 ብሔራት በመጨረሻው ተካፋይ የሆኑበትና 14 ሚልዮን ሰዎች የተገደሉበት ዓለም አቀፍ ስፋት በመያዝም አንደኛ የሆነው ይህ ጦርነት ኢየሱስ ስለ ፍጻሜው በሰጠው ብዙ ክፍሎችን ባጣመረው ምልክት ውስጥ ከሚፈጸሙት ነገሮች የመጀመሪያው ሊሆን የሚችል ነበርን? ሌሎቹስ የምልክቱ ገጽታዎች ከዚህ ተከትለው ይመጡ ይሆንን?
‘ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ራእይ’ ውስጥም ይኸው የደም መፋሰስ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር። እዚህ ላይ ዳማ ፈረስና ጋላቢው ‘ከምድር ሰላምን እንደሚወስዱ’ ተገልጿል። (ራእይ 1:1፤ 6:4) ይህ ሁኔታ ከ1914 እስከ 1918 ባለው ጊዜ በትክክል ተፈጽሟል። አንደኛው የዓለም ጦርነት የመጀመሪያው ብቻ ነበር። በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ቀጠለ። ሃምሳ ዘጠኝ ብሔራት በዚያ ጦርነት ውስጥ ገቡ፤ 50 ሚልዮን ሰዎችም ተገደሉ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት 45 ዓመታት ውስጥ ከ125 በላይ የሆኑ ጦርነቶች ተደርገው ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ገድለዋል።
ሌላው የምልክቱ ገጽታ፦ “የምግብ እጥረት” እንደሚኖር የሚገልጸው ነው። (ማቴዎስ 24:7) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና ከጦርነቱ በኋላ ረሃብ ተስፋፍቶ ነበር። አንድ ዘገባ ከ1914 ወዲህ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ 60 ከፍተኛ የረሃብ አደጋዎች እንደደረሱ በዝርዝር ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ዛሬም እንኳን ቢሆን በየቀኑ በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና በሕክምና መከላከል በሚችሉ በሽታዎች ወደ 40,000 የሚሆኑ ሕፃናት ይሞታሉ።
“ብዙ የመሬት መንቀጥቀጥ ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11 አዓት) አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላ ምድር በብዙ የመሬት መንቀጥቀጥ ተናግታለች። በ1915 በጣልያን ውስጥ የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የ32,610 ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል። በ1920 በቻይና የደረሰው ደግሞ 200,000 ሰዎችን ገድሎአል። በ1923 በጃፓን በደረሰው አደጋ 99,300 ሰዎች ሞተዋል። በ1935 ዛሬ ፓኪስታን ተብላ በምትጠራው አገር 25,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በ1939 በቱርክ ውስጥ 32,700 ሰዎች፣ በ1970 በፔሩ ውስጥ 66,800 ሰዎች ሞተዋል። በ1976 በቻይና ውስጥ 240,000 ሰዎች (አንዳንዶች 800,000 እንደሆኑ ይናገራሉ) ሞተዋል። በ1988 ደግሞ በአርሜንያ 25,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በእርግጥም ከ1914 ወዲህ ታላላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ደርሷል!
“በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) በ1918 እና በ1919 ወደ 1,000,000,000 የሚሆኑ ሰዎች ስፓኒሽ ኢንፍሉኤንዛ በሚባል ተላላፊ በሽታ ታመው ነበር፤ በዚህም በሽታ ምክንያት ከ20,000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሞተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ገና የመጀመሪያው ብቻ ነበር። በማደግ ላይ በሚገኙት አገሮች ውስጥ ወባ፣ ቢልሃርዝያ፣ የሚያሳውር በሽታ፣ የማያቋርጥ ተቅማጥና ሌሎች በሽታዎች በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አካለ ጎዶሎ ማድረግና መግደላቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም የልብ ሕመምና ካንሰር በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሕይወቶችን በማጥፋት ላይ ናቸው። በጾታ የሚተላለፉ በሽታዎች የሰውን ዘር በመጨረስ ላይ ናቸው። በዛሬው ጊዜ በሰዎች ልብ ውስጥ ሽብር የሚፈጥረው ገዳዩ የኤድስ መቅሰፍት በየደቂቃው አንድን አዲስ ሰው እንደሚበክል ተገምቷል፤ እስካሁንም መድኃኒት አልተገኘለትም።
“የአመጻ ብዛት።” (ማቴዎስ 24:12) ከ1914 ወዲህ አመጸኝነት እየተስፋፋ መጥቷል፣ ዛሬ ደግሞ ይብሱኑ ፈንድቷል። የነፍስ ግድያ፣ ሴትን አስገድዶ ማስነወር፣ ዝርፊያ፣ የወሮበሎች የእርስ በርስ ውጊያ፤ እነዚህ ሁሉ የጋዜጣና የራዲዮ እንዲሁም የቴሌቪዥን ዜና ዋና ርዕሶች ሆነዋል። ትርጉም የለሽ የሆነ አመጽ ከቁጥጥር ውጭ በመሆን ተስፋፍቷል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ሰው መቶ ጥይት በሚጎርስ ፈጣን አውቶማቲክ መሣሪያ ተሰብስበው በነበሩ ተማሪዎች ላይ በማርከፍከፍ 5 ልጆችን ሲገድል 29 አቆሰለ። በእንግሊዝ ውስጥ አንድ ወፈፌ AK-47 በተባለ የጦር መሣሪያ 16 ሰዎችን ረፈረፈ። በካናዳ ውስጥ ሴቶችን የሚጠላ አንድ ሰው ወደ ሞንትሪያል ዩንቨርስቲ በመሄድ 14 ሴቶችን ገደለ። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ልክ ተኩላ፣ እንደ አንበሳና የዱር አውሬ ናቸው፤ ተይዘው እንደሚጠፉ አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት ናቸው።—ከሕዝቅኤል 22:27፤ ሶፎንያስ 3:3፤ 2 ጴጥሮስ 2:12 ጋር አወዳድር።
“ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ።” (ሉቃስ 21:26) የመጀመሪያው የአቶም ቦምብ ከፈነዳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአቶሚክ ሳይንቲስት የሆኑት ሃሮልድ ሲ ዩሬይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ፦ “ፍርሃትን እንበላለን፣ በፍርሃት እንተኛለን፣ በፍርሃት እንኖራለን፣ በፍርሃትም እንሞታለን” ብለው ነበር። የኑክሌር ጦርነት ካስከተለው ፍርሃት በተጨማሪ የወንጀል፣ የረሃብ፣ የኤኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የስነ ምግባር መውደቅ፣ የቤተሰብ መንኮታኮት፣ የምድር መበላሸት ፍርሃትም አለ። እንዲያውም በዕለታዊ ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ዜናዎች ላይ ከፊታችን የሚደቀነው ክፉ ጊዜ በየትም ስፍራ ፍርሃት የሚለቅ ነው።
በዚህ የነገሮች ስርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ስለሚከሰቱት ሁኔታዎች ሐዋርያው ጳውሎስም ጽፎአል። እርሱ የጻፋቸውን ቃላት ማንበብ ዕለታዊ ዜናን እንደማንበብ ያህል ነው። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ሁሉም ነገር “ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ” እንደነበረ ቀጥሎአልን?
ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጨረሻዎቹን ቀኖች ሌላ ገጽታ ሲገልጽ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ” ብሏል።—2 ጴጥሮስ 3:3, 4
ዛሬ የመጨረሻዎቹ ቀኖች ጉዳይ ሲነሣ ብዙ ሰዎች ‘እነዚህ ነገሮችማ ቀደም ብለው ደርሰዋል። ታሪክ ራሱን በመድገም ላይ ነው ያለው’ እያሉ በማሾፋቸውና በመናገራቸው የጴጥሮስን ትንቢታዊ ቃላት ይፈጽማሉ። ስለዚህ ማስጠንቀቂያውን ከምንም ባለመቁጠር ‘እንደ ራሳቸው ምኞት ይመላለሳሉ።’ የመጨረሻዎቹን ቀኖች በጣም ግልጽ በሆነ መንገድ ለይተው የሚያሳውቁትን ትንቢቶች መፈጸም ወደ ጎን የሚተውትም ‘እንደ ራሳቸው ፍላጎት’ ነው።—2 ጴጥሮስ 3:5
ሆኖም ኢየሱስ የተነበያቸው የጥምሩ ምልክት የተለያዩ ገጽታዎች በአንድነት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥና በዚህን ያህል ስፋት ሁሉንም አካባቢ የሚያዳርሱ ውጤቶችን በማስከተል የተፈጸሙበት ጊዜ ከዛሬ በፊት አልነበረም። (ለምሳሌ ማቴዎስ 24:3-12፤ ማርቆስ 13:3-8፤ ሉቃስ 21:10, 11, 25, 26ን እንደገና ተመልከት) ነገር ግን አሁንም ትኩረትህን በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ወደተተነበየው ሌላ ገጽታ ለመመለስ እንፈልጋለን።
እስቲ ወደ ራእይ 11:18 እንሂድ። ጥቅሱ የክርስቶስ መንግሥት መግዛት በምትጀምርበት፣ ብሔራት በሚቆጡበትና የፍርድ ሰዓት በሚደርስበት ጊዜ ይሖዋ ‘ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ’ ይናገራል። በአሁኑ ጊዜ የአየሩ፣ የውኃውና የመሬቱ መበከል አካባቢውን እያበላሸው አይደለምን? እርግጥ ነው፤ ሰዎች ለራሳቸው ብልጽግና ሲሉ የምድርን ሀብት ሲበዘብዙ ኖረዋል። ይሁን እንጂ ይህን ሲያደርጉ መኖሪያ እስከማትሆን ድረስ ሊያጠፏት በሚችሉበት ደረጃ ደርሰው አያውቁም ነበር። አሁን ግን ከ1914 ወዲህ ሳይንሳዊ ቴክኖሎጂ እያደገ በመምጣቱ ሰዎች ያንን ኃይል አግኝተዋል፤ ሀብት ለማግኘት ስለሚስገበገቡም ምድርን እያጠፏት፣ አካባቢውን እየበከሉትና ምድር ሕይወትን ለማኖር ያላትን ችሎታ አስጊ ደረጃ ላይ እያደረሱት ነው።
በአሁኑ ጊዜ ስግብግብ የሆነውና በፍቅረ ነዋይ የተጠመደው ኅብረተሰብ በአደገኛ ሁኔታ ይህንን በማድረግ ላይ ነው። በዚህ ምክንያት ከመጡት አሳዛኝ ውጤቶች ውስጥ አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ የአሲድ ዝናብ፣ የመላው ዓለም ከባቢ አየር ሙቀት መጨመር፣ የኦዞን ንብርብር መሸንቆር፣ የተጠራቀመ ቆሻሻ መብዛት፣ መርዛማ ዝቃጮች፣ አደገኛ የሆኑ የተባይ ማጥፊያ መድሃኒቶች፣ የኑክሌር ዝቃጭ፣ በባሕር ላይ የሚፈስ ዘይት፣ የከተማ ፍሳሽ፣ የእንስሳት ዝርያ ለመጥፋት አደጋ መጋለጡ፣ የደረቁ ሐይቆች፣ የጉድጓድ ውሃ መበከል፣ የደኖች መውደም፣ የተበከለ አፈር፣ ለም አፈር ተሸርሽሮ መሄዱ፣ ዛፎችን ሰብልን፣ እንዲሁም የሰውን ጤንነት የሚጎዳ የፋብሪካ ጭስ ናቸው።
ፕሮፌሰር ባሪ ኮሞኖር እንዲህ አሉ፦ “ምድርን የማበላሸቱ ሁኔታ ቁጥጥር ሳይደረግበት ከቀጠለ በመጨረሻ ይህች ፕላኔት ለሰው ሕይወት መኖሪያነት ያላትን ብቃት ሊያሳጣት ይችላል ብዬ አምናለሁ። . . . ችግሩ ሳይንሳዊ እውቀት ስለጠፋ ሳይሆን ሆን ተብሎ የሚደረግ ስግብግብነት ነው።” የዓለም ሁኔታ 1987 የተባለው መጽሐፍ በገጽ 5 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ሰው በልዩ ልዩ መስክ የሚያደርገው መራወጥ ምድር መኖሪያ ለመሆን ያላትን ችሎታ አስጊ እያደረገው መጥቷል።” በ1990 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለሕዝብ ቴሌቪዥን የቀረበው ዋና ተከታታይ ፕሮግራም “ፕላኔትዋን ምድር ለማዳን የሚደረግ ሩጫ” የሚል ነበር።
ሰው አካባቢውን መበከሉን በፍጹም አያቆምም። ይህን እርምጃ የሚወስደው አምላክ ራሱ ሲሆን ምድርን የሚያጠፉትን በሚያጠፋበት ጊዜ ያንን ያደርጋል። አምላክና ሰማያዊው የጦር አዝማች ክርስቶስ ኢየሱስ በፍቅረ ንዋይ በተጠመዱት ብሔራት ላይ በመጨረሻው የአርማጌዶን ጦርነት በማምጣት ይህን ለውጥ ያመጣሉ።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:11-21
በመጨረሻም ስለ መጨረሻው ቀን የተነገረውን የሚከተለውን አስደናቂ የኢየሱስ ትንቢት ገጽታ ተመልከት፦ “ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህ የምሥራች የአምላክ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በሰማይ በመግዛት ላይ እንዳለችና በቅርቡም ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋትና ምድርን እንደገና ገነት ለማድረግ እርምጃ እንደምትወስድ የሚገልጽ ነው። ምሥራቹ ድሮም ተሰብኮ ነበር፤ ነገር ግን ሰው የሚኖርባትን መላዋን ምድር የሚሸፍን አልነበረም። ከ1914 ወዲህ የይሖዋ ምስክሮች ኢየሱስ የተነበየው ስደት ይኸውም፣ የመንግሥት ዕገዳ፣ የአድመኞች ድብደባ፣ እስር፣ ሥቃይ የደረሰባቸውና ብዙዎቹ የተገደሉ ቢሆንም እንኳን ይህንን ሥራ አከናውነዋል።
በ1919 ይህንን ምሥራች የሚሰብኩ 4,000 የይሖዋ ምስክሮች በምድር ላይ ነበሩ። ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣት ባለፈው ዓመት በ212 አገሮች ውስጥ በ200 ቋንቋዎች ከ4,000,000 በላይ የሚያክሉት የይሖዋ ምስክሮች በስብከቱ ተሳትፈዋል፤ በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትንና መጽሔቶችን አሰራጭተዋል፤ በሰዎች መኖሪያ ቤቶችም ውስጥ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል፤ በሁሉም የምድር ክፍሎች በሚገኙ ትላልቅ ስታዲየሞች ትላልቅ ስብሰባዎችን አድርገዋል። ይህንን የሚያክል ከፍተኛ ስፋት ያለው የወንጌል ስብከት ከ1914 በፊት በፍጹም ተከናውኖ አያውቅም። ክንውኑ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያስቻሉት ዘመናዊ ፈጣን የማተሚያ መሣሪያዎች፣ ዘመናዊ መጓጓዣ፣ ኮምፒተሮች፣ የፋክስ ማሽኖችና በተለይ በዘመናችን ብቻ የሚገኙት የዕቃ አላላክና መገናኛ ዘዴዎች ናቸው።
በኤርምያስ ዘመን የነበረችው ኢየሩሳሌም ጥፋት እየመጣባት እንዳለ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአት ነበር፤ ነዋሪዎችዋ ግን ያሾፉ ነበር፤ ሆኖም ጥፋት የመጣው እነርሱ ካሰቡት ጊዜ ቀድሞ ነው። በዛሬውም ጊዜ በአርማጌዶን ስለሚሆነው ጥፋት ከብዙ ድጋፍ ከሚሆን ማስረጃ ጋር ከፍተኛ የሆነ ማስጠንቀቂያ እያስተጋባ ነው። (ራእይ 14:6, 7, 17-20) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጆሮአቸውን ደፍነዋል። ጊዜው ግን እያለቀ ነው፤ እነርሱ ከሚያስቡት በላይ ወደፊት ገፍቷል። አንተስ ከምታስበው በላይ ጊዜው ወደፊት ገፍቷልን?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኤርምያስ ዘመን ቀኑ እነርሱ ከሚያስቡት በላይ አልቆ ነበር