ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
“በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም።”—ሥራ 5:42
1, 2. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛው የስብከት ዘዴ ተለይተው ይታወቃሉ? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?
ጥሩ አለባበስ ያላቸው ሁለት ሰዎች ወደ አንድ ቤት በመሄድ ለቤቱ ባለቤት ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ አጠር ያለ መልእክት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይነግሩታል። ግለሰቡ ለመልእክቱ ፍላጎት ካሳየ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ካበረከቱለት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በነጻ ሊያስጠኑት እንደሚችሉ ይገልጹለታል። ከዚያም ወደሚቀጥለው ቤት በመሄድ ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። በምድር ላይ ባሉ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ማየት የተለመደ ነገር ነው። አንተም በዚህ ሥራ የምትካፈል ከሆነ ሰዎች ገና መናገር ከመጀመርህ በፊት የይሖዋ ምሥክር መሆንህን እንደሚያውቁ አስተውለህ ይሆናል። በእርግጥም ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው አገልግሎት መለያ ምልክታችን ሆኗል።
2 ኢየሱስ የሰጠንን የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልዕኮ ለመፈጸም በተለያዩ ዘዴዎች እንጠቀማለን። (ማቴ. 28:19, 20) በገበያ ቦታዎች፣ በመንገድ ላይ እንዲሁም ሰዎች በሚገኙባቸው ሌሎች ስፍራዎች ምሥራቹን እንሰብካለን። (ሥራ 17:17) በስልክ ወይም በደብዳቤ ተጠቅመን ለብዙ ሰዎች ለመመስከር እንጥራለን። በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ለምናገኛቸው ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች እናካፍላቸዋለን። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን ሊያገኙ የሚችሉበት ድረ ገጽ አለን።a እነዚህ ሁሉ ዘዴዎች ጥሩ ውጤቶች አስገኝተዋል። ያም ሆኖ በአብዛኞቹ አገሮች ምሥራቹን በዋነኝነት የምንሰብከው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ነው። በዚህ መንገድ እንድንሰብክ መሠረት የሆነን ምንድን ነው? በዘመናችን የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች ከቤት ወደ ቤት በሚከናወነው አገልግሎት በስፋት መካፈል የጀመሩት እንዴት ነበር? በአሁኑ ጊዜ በዚህ ዘዴ መጠቀም አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
ሐዋርያት የተጠቀሙበት ዘዴ
3. ኢየሱስ ስብከትን በተመለከተ ለሐዋርያቱ ምን መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር? ይህ መመሪያስ ስለሚሰብኩበት መንገድ ምን ይጠቁማል?
3 ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የመስበኩ ዘዴ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው። ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱን እንዲሰብኩ በላካቸው ጊዜ “ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው [ፈልጉ]” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። ሐዋርያቱ፣ ሊቀበላቸው ፈቃደኛ የሆነ ሰው የሚፈልጉት እንዴት ነበር? ኢየሱስ ይህን የሚያደርጉት ወደ ሰዎች ቤት በመሄድ እንደሆነ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ። ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው።” ሐዋርያቱ፣ ሰዎች ወደ ቤታቸው እስኪጠሯቸው ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው? ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረውን ልብ በል:- “ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።” (ማቴ. 10:11-14) ከዚህ መመሪያ በግልጽ መመልከት እንደምንችለው ሐዋርያቱ፣ ቅድሚያውን ወስደው ወደ ሰዎች ቤት በመሄድ “ወንጌልን እየሰበኩ . . . በየመንደሩ ያልፉ” ነበር።—ሉቃስ 9:6
4. ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተጠቀሰው የት ላይ ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሐዋርያት ከቤት ወደ ቤት ይሰብኩ እንደነበረ በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ በሐዋርያት ሥራ 5:42 ላይ ሐዋርያቱን በተመለከተ እንዲህ የሚል ዘገባ ሰፍሮ ነበር:- “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም።” ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ የሚገኙትን ሽማግሌዎች እንዲህ ብሏቸዋል:- “በአደባባይም ሆነ ከቤት ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም።” ጳውሎስ ወደ እነዚህ ሽማግሌዎች ቤት የሄደው አማኞች ከመሆናቸው በፊት ነበር? ሐዋርያው ‘በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ስለመመለስና በጌታችን በኢየሱስ ስለማመን’ እንዲሁም ስለሌሎች ነገሮች ስላስተማራቸው፣ አማኞች ከመሆናቸው በፊት ቤታቸው ሄዶ እንደነበር ግልጽ ነው። (ሥራ 20:20, 21) ሮበርትሰንስ ዎርድ ፒክቸርስ ኢን ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ የሐዋርያት ሥራ 20:20ን በተመለከተ እንዲህ ብሏል:- “ይህ ታላቅ ሰባኪ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ይሰብክ እንደነበር ልብ ማለት ያስፈልጋል።”
ዘመናዊ የአንበጣ ሠራዊት
5. የስብከቱ ሥራ በኢዩኤል ትንቢት ላይ የተገለጸው እንዴት ነው?
5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ በአሁኑ ጊዜ ታላቅ የስብከት ሥራ እንደሚከናወን የሚያመላክት ነበር። ነቢዩ ኢዩኤል፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን ሥራ፣ አጥፊ ከሆነ የነፍሳት መቅሰፍት ጋር ያመሳሰለው ሲሆን ከእነዚህ ነፍሳት መካከል አንበጦችም ይገኙበታል። (ኢዩ. 1:4) እንደ አንድ ጦር ሠራዊት የሚጓዙት እነዚህ አንበጦች ምንም ዓይነት መሰናክል ሳይበግራቸው ወደየቤቱ እየገቡ ያገኙትን ሁሉ ጥርግርግ አድርገው ይበላሉ። (ኢዩኤል 2:2, 7-9ን አንብብ።) በዘመናችን የአምላክ ሕዝቦች የስብከቱን ሥራ በጽናት እንዲሁም በተሟላ ሁኔታ እንደሚያከናውኑ በግልጽ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑት ባልንጀሮቻቸው ይህን ትንቢት ለመፈጸም ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች ዋነኛው ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነው አገልግሎት ነው። (ዮሐ. 10:16) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሐዋርያት ይጠቀሙበት የነበረውን ይህን ዘዴ መከተል የጀመሩት እንዴት ነበር?
6. በ1922 ከቤት ወደ ቤት መመስከርን በተመለከተ ምን ማበረታቻ ተሰጥቶ ነበር? ሆኖም የአንዳንዶች ምላሽ ምን ነበር?
6 ከ1919 ወዲህ ባሉት ዓመታት፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን ምሥራቹን የመስበክ ኃላፊነት እንዳለበት ጎላ ተደርጎ ሲገለጽ ቆይቷል። ለአብነት ያህል፣ በነሐሴ 15, 1922 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “አገልግሎት አስፈላጊ ነው” የሚለው ርዕስ፣ “ጽሑፎችን በቅንዓት ለሰዎች የማድረስን እንዲሁም ቤታቸው በመሄድ መንግሥተ ሰማያት መቅረቡን የመመስከርን” አስፈላጊነት ለቅቡዓን ክርስቲያኖች አስገንዝቧቸዋል። እንዴት መመስከር እንደሚቻል የሚያሳዩ የመግቢያ ሐሳቦች ቡሌቲን (አሁን የመንግሥት አገልግሎታችን) በተባለው ጽሑፍ ላይ ይወጡ ነበር። ያም ሆኖ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር መጀመሪያ ላይ አነስተኛ ነበር። አንዳንዶች በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ፈቃደኞች አልነበሩም። እነዚህ ግለሰቦች ሥራውን በተመለከተ የተለያዩ የተቃውሞ ሐሳቦችን ይሰነዝሩ የነበረ ቢሆንም ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የማይሰብኩበት ዋነኛ ምክንያት እንዲህ ማድረጋቸው ክብራቸውን እንደሚነካ ይሰማቸው ስለነበር ነው። ለመስክ አገልግሎት የሚሰጠው ትኩረት እየጨመረ ሲሄድ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ቀስ በቀስ ከይሖዋ ድርጅት ራሳቸውን ማግለል ጀመሩ።
7. በ1950ዎቹ ዓመታት ምን እንደሚያስፈልግ ግልጽ ሆኖ ነበር?
7 ከዚያ በኋላ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ብዛት ያላቸው ሰዎች በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀመሩ። ሆኖም ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት በሚከናወነው አገልግሎት ረገድ በግለሰብ ደረጃ ተጨማሪ ሥልጠና እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የነበረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በ1950ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በዚያ አገር ከነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል 28 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት የስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶችን በማሠራጨት ወይም መጽሔቶችን ይዘው መንገድ ዳር በመቆም ብቻ ነበር። ከአስፋፊዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በስብከቱ ሥራ አዘውትረው አይካፈሉም ነበር፤ እነዚህ ወንድሞች ምንም ሳያገለግሉ የሚያሳልፏቸው ወራት ነበሩ። ታዲያ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች በሙሉ ከቤት ወደ ቤት እንዲሰብኩ ለመርዳት ምን ተደርጎ ይሆን?
8, 9. በ1953 ምን ዓይነት የሥልጠና ፕሮግራም ተጀመረ? ምንስ ውጤት አስገኝቷል?
8 በ1953 በኒው ዮርክ ሲቲ በተደረገ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የቀረበው ትምህርት ከቤት ወደ ቤት ለሚከናወነው አገልግሎት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነበር። በስብሰባው ላይ ወንድም ናታን ኖር፣ የሁሉም የበላይ ተመልካቶች ዋነኛ ሥራ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት አዘውትሮ እንዲያገለግል መርዳት ሊሆን እንደሚገባ ገልጾ ነበር። ወንድም ኖር “ሁሉም ሰው ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት መስበክ መቻል አለበት” በማለት ተናግሯል። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስም በዓለም ዙሪያ ሥልጠና መሰጠት ተጀመረ። ከቤት ወደ ቤት መስበክ ላልጀመሩት ወንድሞች፣ ሰዎችን ቤታቸው ሄደው ማነጋገርና ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሱ ማስረዳት እንዲሁም ለጥያቄዎቻቸው መልስ መስጠት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ሥልጠና ተሰጣቸው።
9 ይህ የሥልጠና ፕሮግራም በጣም ግሩም ውጤት አስገኝቷል። በአሥር ዓመት ውስጥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አስፋፊዎች ቁጥር በእጥፍ የጨመረ ሲሆን የተመላልሶ መጠየቆች ቁጥር 126 በመቶ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር 150 በመቶ እድገት አሳይቷል። በዛሬው ጊዜ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ነው። ይህ አስደናቂ እድገት ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ከቤት ወደ ቤት የሚያከናውኑትን ሥራ እንደባረከው የሚያሳይ አንድ ማስረጃ ነው።—ኢሳ. 60:22
ሰዎች ከጥፋቱ እንዲድኑ ምልክት ማድረግ
10, 11. (ሀ) በሕዝቅኤል ምዕራፍ 9 ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሕዝቅኤል ምን ዓይነት ራእይ ተመልክቶ ነበር? (ለ) ይህ ራእይ በዘመናችን እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው?
10 ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ነቢዩ ሕዝቅኤል ከተመለከተው ራእይ መገንዘብ ይቻላል። ነቢዩ በዚህ ራእይ ላይ በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ ስድስት ሰዎች እንዲሁም ቀጭን በፍታ የለበሰና በጎኑ የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበ ሰባተኛ ሰው ተመልክቶ ነበር። ሰባተኛው ሰው “በኢየሩሳሌም ከተማ ሁሉ ሂድና በውስጧ ስለ ተሠራው ጸያፍ ተግባር ሲያዝኑና ሲያለቅሱ በነበሩ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት አድርግ” የሚል መመሪያ ተሰጠው። የጦር መሣሪያ የያዙት ስድስቱ ሰዎች ደግሞ ሰባተኛውን ሰው በመከተል ምልክት ያልተደረገባቸውን በሙሉ እንዲገድሉ ትእዛዝ ተሰጣቸው።—ሕዝቅኤል 9:1-6ን አንብብ።
11 በዚህ ትንቢት ላይ “ቀጭን በፍታ የለበሰ” የተባለው ሰው ቅቡዓን ቀሪዎችን እንደሚያመለክት እናውቃለን። ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” አባላት በሚሆኑት ሰዎች ላይ በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አማካኝነት ምሳሌያዊ ምልክት ያደርጋሉ። (ዮሐ. 10:16) ይህ ምልክት ምንድን ነው? በምሳሌያዊ ሁኔታ በግምባራቸው ላይ የሚደረገው ይህ ምልክት፣ እነዚህ በጎች ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውንና አዲሱን ሰው መልበሳቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ኤፌ. 4:20-24) እነዚህ በግ መሰል ሰዎች ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር አንድ መንጋ የሚሆኑ ሲሆን በሌሎች ሰዎች ላይ ምልክት በማድረጉ ወሳኝ ሥራ ቅቡዓኑን ይረዷቸዋል።—ራእይ 22:17
12. በሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ስለማድረግ የሚገልጸው ሕዝቅኤል የተመለከተው ራእይ በግ መሰል ሰዎችን መፈለጋችንን መቀጠላችን አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎላው እንዴት ነው?
12 የሕዝቅኤል ራእይ ‘የሚያዝኑና የሚያለቅሱ’ ሰዎችን የመፈለጉ ሥራ አጣዳፊ የሆነበትን አንዱን ምክንያት ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ ነው። የጦር መሣሪያ በያዙት ስድስት ሰዎች የተመሰሉት በሰማይ የሚገኙት የይሖዋ ፍርድ አስፈጻሚ ኃይላት ምሳሌያዊው ምልክት ያልተደረገባቸውን ሰዎች በቅርቡ ያጠፋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ መጪውን ፍርድ በተመለከተ በጻፈው ሐሳብ ላይ ጌታ ኢየሱስ “ከኀያላን መላእክት” ጋር እንደሚመጣ እንዲሁም “እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን [እንደሚበቀል]” ገልጿል። (2 ተሰ. 1:7, 8) ሰዎች የሚፈረድባቸው ለወንጌሉ በሚሰጡት ምላሽ መሠረት እንደሆነ ልብ በል። በመሆኑም የአምላክ መልእክት እስከ መጨረሻው ድረስ ያለማቋረጥ መሰበክ አለበት። (ራእይ 14:6, 7) ስለዚህ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።—ሕዝቅኤል 3:17-19ን አንብብ።
13. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ኃላፊነት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር? እንዲህ የተሰማውስ ለምን ነበር? (ለ) አንተስ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለብህ?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ ምሥራቹን ለሌሎች የመስበክ ኃላፊነት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። “ግሪኮች ለሆኑትና ላልሆኑት፣ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉ፣ ዕዳ አለብኝ፤ በሮም ለምትኖሩ፣ ለእናንተም ወንጌልን ለመስበክ የምጓጓው ለዚህ ነው” በማለት ጽፏል። (ሮሜ 1:14, 15) ጳውሎስ ለተደረገለት ምሕረት ያለው አድናቆት፣ እሱ ከአምላክ ጸጋ እንደተጠቀመ ሁሉ ሌሎችም ከዚህ ጸጋ እንዲጠቀሙ መርዳት እንዳለበት እንዲሰማው አድርጎታል። (1 ጢሞ. 1:12-16) ጳውሎስ ለሰዎች ሁሉ ዕዳ እንዳለበትና ይህን ዕዳ የሚከፍለውም ምሥራቹን በመናገር እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። አንተስ በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የመስበክ ዕዳ እንዳለብህ ይሰማሃል?—የሐዋርያት ሥራ 20:26, 27ን አንብብ።
14. ሰዎች በሚገኙባቸው ቦታዎችም ሆነ ከቤት ወደ ቤት የምንሰብክበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?
14 ከቤት ወደ ቤት የምናከናውነው አገልግሎት ሰዎች እንዲድኑ የሚረዳ ቢሆንም በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንድንካፈል የሚገፋፋን ከዚህ የበለጠ ምክንያት አለን። በሚልክያስ 1:11 ላይ ይሖዋ እንዲህ የሚል ትንቢት ተናግሯል:- “ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ . . . ለስሜ . . . ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና።” በዚህ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አምላኪዎቹ አገልግሎታቸውን በትሕትና በማከናወን በምድር ዙሪያ ስሙን ለሕዝብ ሁሉ እያወጁ ነው። (መዝ. 109:30፤ ዘፀ. 6:3 የ1879 ትርጉም፤ ማቴ. 24:14) ሰዎች በሚገኙባቸው ቦታዎችም ሆነ ከቤት ወደ ቤት የምንሰብክበት ዋነኛ ምክንያት ለይሖዋ ‘የምስጋና መሥዋዕት’ ለማቅረብ ነው።—ዕብ. 13:15
ታላቅ ትርጉም ያላቸው ክንውኖች ይጠብቁናል
15. (ሀ) እስራኤላውያን በሰባተኛው ቀን ኢያሪኮን ሲዞሩ ከሌሎቹ ቀናት የበለጠ እንቅስቃሴ ያደረጉት እንዴት ነበር? (ለ) ይህስ ስለ ስብከቱ ሥራ ምን ይጠቁመናል?
15 ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ወደፊት ምን ሁኔታዎች ይከናወናሉ? በኢያሱ መጽሐፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ስለ ኢያሪኮ መከበብ የሚገልጸው ታሪክ ሁኔታውን ግልጽ ያደርግልናል። አምላክ ኢያሪኮን ከማጥፋቱ በፊት እስራኤላውያን ከተማዋን ለስድስት ቀናት ያህል በቀን አንድ ጊዜ እንዲዞሯት ትእዛዝ ሰጥቷቸው እንደነበር አስታውስ። በሰባተኛው ቀን ያደረጉት እንቅስቃሴ ግን ከሌሎቹ ቀናት የበለጠ ነበር። ይሖዋ፣ ኢያሱን እንዲህ ብሎት ነበር:- “ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፣ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፣ . . . ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል።” (ኢያሱ 6:2-5 የ1954 ትርጉም) በተመሳሳይም በምናከናውነው የስብከት እንቅስቃሴ ረገድ ከአሁኑ የበለጠ ተሳትፎ ሊኖር ይችላል። ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት ወቅት፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስለ አምላክ ስምና ስለ መንግሥቱ ታላቅ ምሥክርነት መሰጠቱን እንደምናስተውል ምንም ጥርጥር የለውም።
16, 17. (ሀ) ‘ታላቁ መከራ’ ከማብቃቱ በፊት ምን ይከናወናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
16 እኛም የምናውጀው መልእክት እንደ “ታላቅ ጩኸት” የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ፣ ኃይለኛ የፍርድ መልእክቶች ‘እያንዳንዱ አርባ አምስት ኪሎ ግራም ከሚሆን ታላቅ በረዶ’ ጋር ተመሳስለዋል። ራእይ 16:21 ‘መቅሠፍቱ እጅግ አሠቃቂ እንደነበር’ ይገልጻል። ከቤት ወደ ቤት የምናከናውነው አገልግሎት እነዚህን ወሳኝ የፍርድ መልእክቶች በማወጅ ረገድ ምን ሚና እንደሚኖረው ወደፊት የምናየው ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘ታላቁ መከራ’ ከማብቃቱ በፊት የይሖዋ ስም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ መንገድ ለሕዝብ ሁሉ እንደሚታወቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ራእይ 7:14፤ ሕዝ. 38:23 NW
17 እንግዲያው ወደ ፊት የሚፈጸሙትን ታላቅ ትርጉም ያላቸው ክንውኖች እየተጠባበቅን ስለ መንግሥቱ ምሥራች በቅንዓት መስበካችንን እንቀጥል። ይህንን ኃላፊነታችንን ለመወጣት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል? እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች መቋቋም የምንችለውስ እንዴት ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ጥያቄዎች እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የይሖዋ ምሥክሮች ድረ ገጽ www.watchtower.org. ነው።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት አለን?
• በዘመናችን ከቤት ወደ ቤት ለሚከናወነው አገልግሎት ትኩረት የተሰጠው እንዴት ነው?
• ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አገልጋዮቹ የመስበክ ኃላፊነት ያለባቸው ለምንድን ነው?
• ወደ ፊት ምን ታላቅ ትርጉም ያላቸው ክንውኖች ይፈጸማሉ?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንተም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሌሎች የመስበክ ኃላፊነት እንዳለብህ ይሰማሃል?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድም ኖር በ1953