ተጨማሪ ሐሳብ
1 ይሖዋ
የአምላክ ስም ይሖዋ ነው፤ ትርጉሙም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ነው። ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ሲሆን ሁሉንም ነገር የፈጠረው እሱ ነው። የፈለገውን ነገር ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው።
የአምላክ ስም በዕብራይስጥ የሚጻፈው በአራት ፊደሎች ነው። እነዚህ ፊደላት በአማርኛ ‘የሐወሐ’ በሚሉት ተነባቢ ፊደላት ይወከላሉ። የአምላክ ስም በመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰባት ሺህ ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች፣ በቋንቋቸው የተለመደውን አጠራር ስለሚጠቀሙ ይሖዋ የሚለውን ስም በተለያየ መንገድ ይጠሩታል።
▸ ምዕ. 1 አን. 15፣ ግርጌ
2 መጽሐፍ ቅዱስ “በአምላክ መንፈስ መሪነት” የተጻፈ ነው
የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት አምላክ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጻፍ በሰዎች ተጠቅሟል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሥራ አስኪያጅ ጸሐፊው ደብዳቤ እንድትጽፍለት ሊያደርግ ይችላል፤ ሆኖም ደብዳቤው የሥራ አስኪያጁን ሐሳብ የያዘ ነው። በተመሳሳይም አምላክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈስ ቅዱስ በመምራት የእሱን ሐሳብ እንዲጽፉ አድርጓል። የአምላክ መንፈስ እነዚህን ሰዎች የመራቸው በተለያየ መንገድ ነው፤ ለምሳሌ አንዳንዶች በራእይ ወይም በሕልም ያዩትን ነገር ጽፈዋል።
3 መሠረታዊ ሥርዓቶች
እነዚህ ሥርዓቶች፣ መሠረታዊ የሆነን እውነት የሚያብራሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጓደኛ አድርገን የምንመርጣቸው ሰዎች ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን እንደሚችሉ ያስገነዝበናል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ የምናደርገው ነገር ከሚያስከትለው ውጤት ልናመልጥ እንደማንችል ያሳያል።—ገላትያ 6:7
4 ትንቢት
ትንቢት ከአምላክ የተላከ መልእክት ነው። ትንቢቱ የሥነ ምግባር ትምህርት የያዘ አሊያም የአምላክን ፈቃድ፣ ትእዛዝ ወይም ፍርድ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል። ወደፊት ስለሚፈጸም ነገር የሚናገር መልእክትም ሊሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶች ይገኛሉ።
5 ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ስለ መሲሑ የተነገሩ በርካታ ትንቢቶች በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። “ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
▸ ምዕ. 2 አን. 17፣ ግርጌ
6 ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ
ይሖዋ፣ እሱን የሚወዱ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ ይፈልጋል፤ ምድርን የፈጠረውም ለዚህ ነው። የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። አምላክ በቅርቡ ክፋትን ሁሉ አስወግዶ ሕዝቦቹ ለዘላለም እንዲኖሩ ያደርጋል።
7 ሰይጣን ዲያብሎስ
በአምላክ ላይ ዓመፅ የቀሰቀሰው መልአክ ሰይጣን ተብሎ ይጠራል። ሰይጣን የሚለው ቃል “ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህ ስም የተሰጠው ይሖዋን ስለሚቃወም ነው። በተጨማሪም ዲያብሎስ ተብሎ ይጠራል፤ ይህ መጠሪያ ደግሞ “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ስም የተሰጠው ስለ አምላክ ውሸት ስለሚናገርና ሰዎችን ስለሚያታልል ነው።
8 መላእክት
ይሖዋ መላእክትን የፈጠረው ምድርን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። መላእክት የተፈጠሩት በሰማይ እንዲኖሩ ነው። ቁጥራቸው ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነው። (ዳንኤል 7:10) እነዚህ መላእክት የግል መጠሪያና የየራሳቸው ባሕርያት አሏቸው፤ ይሁንና ትሑት ስለሆኑ የሰው ልጆች እንዲያመልኳቸው አይፈልጉም። መላእክት የተለያየ ማዕረግና የሥራ ምድብ አላቸው። ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች መካከል በይሖዋ ዙፋን ፊት ማገልገል፣ ከእሱ መልእክት ተቀብለው ማስተላለፍ፣ በምድር ላይ ለሚገኙት የአምላክ አገልጋዮች ጥበቃ ማድረግና አመራር መስጠት፣ የአምላክን ፍርድ ማስፈጸምና የስብከቱን ሥራ መደገፍ ይገኙበታል። (መዝሙር 34:7፤ ራእይ 14:6፤ 22:8, 9) ወደፊት ደግሞ በአርማጌዶን ጦርነት ከኢየሱስ ጎን ተሰልፈው ይዋጋሉ።—ራእይ 16:14, 16፤ 19:14, 15
9 ኃጢአት
ከይሖዋ ወይም ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ማንኛውም ስሜት፣ አስተሳሰብ ወይም ድርጊት ኃጢአት ነው። ኃጢአት ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ያበላሽብናል፤ በመሆኑም አምላክ ሆን ብለን ኃጢአት ከመፈጸም እንድንርቅ የሚረዱ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። መጀመሪያ ላይ ይሖዋ ሁሉንም ነገር የፈጠረው ፍጹም አድርጎ ነው፤ ይሁንና አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት ሲሠሩ ፍጽምናቸውን አጡ። በመሆኑም የተወሰነ ዕድሜ ከኖሩ በኋላ አርጅተው ሞቱ፤ እኛም ከአዳም ኃጢአት ስለወረስን እናረጃለን እንዲሁም እንሞታለን።
10 አርማጌዶን
አምላክ የሰይጣንን ዓለምና ክፋትን ጠራርጎ ለማጥፋት የሚያደርገው ጦርነት አርማጌዶን ይባላል።
11 የአምላክ መንግሥት
የአምላክ መንግሥት፣ ይሖዋ በሰማይ ያቋቋመው መስተዳድር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ ነው። ወደፊት ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት ክፋትን ሁሉ ያስወግዳል። የአምላክ መንግሥት ምድርን ይገዛል።
12 ኢየሱስ ክርስቶስ
አምላክ ከሁሉም ነገር አስቀድሞ የፈጠረው ኢየሱስን ነው። ይሖዋ፣ ለሰው ልጆች ሲል እንዲሞት ኢየሱስን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ ከተገደለ በኋላ ይሖዋ ከሞት አስነስቶታል። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሰማይ እየገዛ ነው።
13 ስለ 70ዎቹ ሳምንታት የተነገረው ትንቢት
መጽሐፍ ቅዱስ፣ መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ አስቀድሞ ተናግሯል። ይህ የሚሆነው በትንቢቱ ላይ በተጠቀሱት 69 ሳምንታት መጨረሻ ላይ ነው፤ እነዚህ ሳምንታት መቆጠር የሚጀምሩት ከ455 ዓ.ዓ. ሲሆን የሚያበቁት ደግሞ በ29 ዓ.ም. ነው።
ሳምንታቱ የሚያበቁት በ29 ዓ.ም. እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ 69 ሳምንታት መቆጠር የጀመሩት ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ከተማዋን ዳግመኛ መገንባት ከጀመረበት ዓመት ማለትም ከ455 ዓ.ዓ. ነው። (ዳንኤል 9:25፤ ነህምያ 2:1, 5-8) “ደርዘን” የሚለው ቃል 12 ቁጥርን እንደሚያስታውሰን ሁሉ “ሳምንት” የሚለው ቃልም 7 ቁጥርን ያስታውሰናል። በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት ሳምንታት፣ ሰባት ቀናትን የያዙ ሳምንታት ሳይሆኑ ሰባት ዓመታትን የያዙ ሳምንታት ናቸው፤ ይህ የሆነው “አንዱ ቀን እንደ አንድ ዓመት [ይቆጠር]” በሚለው ትንቢት ላይ በተገለጸው ደንብ መሠረት ነው። (ዘኁልቁ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6) ስለዚህ እያንዳንዱ ሳምንት የሰባት ዓመት ርዝማኔ አለው ማለት ነው፤ አንድ ሳምንት ሰባት ዓመት ከሆነ 69 ሳምንት ደግሞ 483 ዓመት ይሆናል (69 x 7)። ከ455 ዓ.ዓ ጀምረን 483 ዓመታትን ስንቆጥር 29 ዓ.ም. ላይ እንደርሳለን (ዜሮ የሚባል ዓመት የለም)። ኢየሱስ የተጠመቀውና መሲሕ የሆነው በዚህ ዓመት ላይ ነው!—ሉቃስ 3:1, 2, 21, 22
ይኸው ትንቢት፣ ስለ አንድ ሌላ ሳምንት ማለትም ስለ ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ይናገራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ይኸውም በ33 ዓ.ም. መሲሑ ይገደላል፤ ከ36 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ምሥራች ለአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ብሔራት ይሰበካል።—ዳንኤል 9:24-27
14 የሐሰት ትምህርት የሆነው ሥላሴ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ ፈጣሪ እንደሆነ እንዲሁም ኢየሱስን ከሁሉ አስቀድሞ እንደፈጠረው ይናገራል። (ቆላስይስ 1:15, 16) ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ አይደለም። እሱም ቢሆን ከአምላክ ጋር እኩል እንደሆነ ተናግሮ አያውቅም። እንዲያውም “ከእኔ አብ ይበልጣል” ብሏል። (ዮሐንስ 14:28፤ 1 ቆሮንቶስ 15:28) አንዳንድ ሃይማኖቶች ግን የሥላሴን ትምህርት ይኸውም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሦስት አካል ሆኖም አንድ አምላክ እንደሆኑ የሚገልጽ ትምህርት ያስተምራሉ። “ሥላሴ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ሥላሴ የሐሰት ትምህርት ነው።
መንፈስ ቅዱስ፣ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል ሲሆን አምላክ ይህን በዓይን የማይታይ ኃይሉን ፈቃዱን ለመፈጸም ይጠቀምበታል። መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ‘በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ’ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ” በማለት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 17
15 መስቀል
እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን ለማምለክ በመስቀል አይጠቀሙም። ለምን?
መስቀል፣ በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ለአምልኮ ሲያገለግል ቆይቷል። በጥንት ዘመን የኖሩ የጣዖት አምላኪዎች መስቀልን የተለያዩ ፍጥረታትን እንዲሁም የመራባት አምላክን ለማምለክ ይጠቀሙበት ነበር። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በነበሩት 300 ዓመታት ውስጥ ክርስቲያኖች መስቀልን ለአምልኮ አይጠቀሙም ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን የሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረው ቆስጠንጢኖስ መስቀል የክርስትና መለያ ምልክት እንዲሆን አደረገ። ይህን ያደረገው ክርስትና በሰዎች ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ነበር። ይሁንና መስቀልን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም። ዘ ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “መስቀል ከክርስትና ዘመን በፊት በነበሩትም ሆነ ከክርስትና ውጭ ባሉት ባሕሎች ውስጥ የነበረ ነገር ነው” በማለት ይገልጻል።
ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ አይደለም። “መስቀል” ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛ ቃላት “ቀጥ ያለ እንጨት፣” “አጣና” ወይም “ዛፍ” የሚል ትርጉም አላቸው። ዘ ከምፓንየን ባይብል እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በግሪክኛ በተጻፈው [አዲስ ኪዳን] ውስጥ ሁለት እንጨቶችን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ዘገባ አይገኝም።” ኢየሱስ የተሰቀለው ቀጥ ባለ እንጨት ላይ ነው።
ይሖዋ፣ እሱን ለማምለክ ምስሎችን ወይም ቅርጾችን እንድንጠቀም አይፈልግም።—ዘፀአት 20:4, 5፤ 1 ቆሮንቶስ 10:14
16 የመታሰቢያው በዓል
ኢየሱስ፣ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ ተከታዮቹን አዟቸዋል። በመሆኑም በየዓመቱ ኒሳን 14 ቀን፣ ይኸውም እስራኤላውያን የፋሲካ በዓልን ያከብሩ በነበሩበት ዕለት የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ያከብራሉ። በመታሰቢያው በዓል ላይ፣ የኢየሱስን ሥጋ የሚወክለው ቂጣ እንዲሁም ደሙን የሚወክለው የወይን ጠጅ በእያንዳንዱ ሰው ፊት እንዲዞር ይደረጋል። ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙ ሰዎች ቂጣውን ይበላሉ፤ እንዲሁም የወይን ጠጁን ይጠጣሉ። በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ደግሞ በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘት አክብሮታቸውን የሚያሳዩ ቢሆንም ቂጣውን አይበሉም፤ እንዲሁም የወይን ጠጁን አይጠጡም።
17 ነፍስ
አዲስ ዓለም ትርጉም “ነፍስ” የሚለውን ቃል (1) ሰውን፣ (2) እንስሳን ወይም (3) የአንድን ሰው ወይም እንስሳ ሕይወት ለማመልከት ተጠቅሞበታል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
ሰው። “በኖኅ ዘመን ጥቂት ሰዎች ይኸውም ስምንት ነፍሳት በውኃው መካከል አልፈው [ዳኑ]።” (1 ጴጥሮስ 3:20) እዚህ ላይ “ነፍሳት” የሚለው ቃል ሰዎችን ማለትም ኖኅንና ሚስቱን እንዲሁም ሦስት ልጆቻቸውንና የልጆቻቸውን ሚስቶች የሚያመለክት ነው።
እንስሳ። “አምላክ ‘ውኃዎቹ በሚርመሰመሱ ሕያዋን ፍጥረታት [“ነፍሳት” የግርጌ ማስታወሻ] ይሞሉ፤ እንዲሁም የሚበርሩ ፍጥረታት ከምድር በላይ በሰማያት ጠፈር ላይ ይብረሩ’ አለ። ቀጥሎም አምላክ ‘ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን [“ነፍሳትን” የግርጌ ማስታወሻ] እንደየወገናቸው እንዲሁም የቤት እንስሳትን፣ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው ታውጣ’ አለ። እንዳለውም ሆነ።”—ዘፍጥረት 1:20, 24
የአንድ ሰው ወይም እንስሳ ሕይወት። ይሖዋ፣ “ነፍስህን ለማጥፋት የሚፈልጉት ሰዎች በሙሉ ሞተዋል” በማለት ለሙሴ ነግሮት ነበር። (ዘፀአት 4:19) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤ ጥሩ እረኛ ሕይወቱን [“ነፍሱን” የግርጌ ማስታወሻ] ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል።”—ዮሐንስ 10:11
በሌላ በኩል ደግሞ አንድን ነገር “በሙሉ ነፍስ” ማድረግ፣ ሥራውን በራስ ተነሳሽነትና በሙሉ አቅም ማከናወንን ያመለክታል። (ማቴዎስ 22:37፤ ዘዳግም 6:5) በተጨማሪም “ነፍስ” የሚለው ቃል፣ የአንድን ሕያው ፍጡር ምኞት ወይም ፍላጎት ለማመልከት ተሠርቶበታል። ከዚህም ሌላ የሞተ ነፍስ የሚለው አገላለጽ የሞተን ሰው ወይም አስከሬንን ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል።—ዘኁልቁ 6:6፤ ምሳሌ 23:2፤ ኢሳይያስ 56:11፤ ሐጌ 2:13
▸ ምዕ. 6 አን. 5፣ ግርጌ፤ ምዕ. 15 አን. 17
18 መንፈስ
በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጡም ሆነ የግሪክኛው ቃላት የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። ይሁንና በጥቅሉ ሲታይ እንደ ነፋስ ወይም የሰዎችና የእንስሳት ትንፋሽ ያሉ በሰው ዓይን የማይታዩ ነገሮችን ያመለክታሉ። በተጨማሪም እነዚህ ቃላት መንፈሳዊ አካላትን እንዲሁም የአምላክ ኃይል የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ሊያመለክቱ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከእሱ ተለይታ መኖሯን የምትቀጥል ነገር እንዳለች አያስተምርም።—ዘፀአት 35:21፤ መዝሙር 104:29፤ ማቴዎስ 12:43፤ ሉቃስ 11:13
▸ ምዕ. 6 አን. 5፣ ግርጌ፤ ምዕ. 15 አን. 17
19 ገሃነም
ገሃነም፣ በጥንቷ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ይገኝ የነበረ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ሸለቆ መጠሪያ ነው። በኢየሱስ ዘመን፣ እንስሳት ወይም ሰዎች ወደዚህ ሸለቆ ተጥለው ይሠቃዩ አሊያም በሕይወት እያሉ በእሳት ይቃጠሉ እንደነበር የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም። በመሆኑም ገሃነም የሞቱ ሰዎች የሚሠቃዩበትና ለዘላለም የሚቃጠሉበት በዓይን የማይታይ ቦታ አይደለም። ኢየሱስ ወደ ገሃነም ስለሚጣሉ ሰዎች ሲናገር እነዚህ ሰዎች ለዘላለም እንደሚጠፉ ማመልከቱ ነበር።—ማቴዎስ 5:22፤ 10:28
20 የጌታ ጸሎት
ይህ ጸሎት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ብለው መጸለይ እንዳለባቸው ባስተማራቸው ጊዜ የተናገረው ጸሎት ነው። ‘አቡነ ዘበሰማያት’ ወይም ‘አባታችን ሆይ’ በመባልም ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት እንድንጸልይ አስተምሮናል፦
“ስምህ ይቀደስ”
በይሖዋ ላይ የውሸት ክስ ተሰንዝሯል፤ በመሆኑም ስሙን እንዲያነፃ መጸለይ ይኖርብናል። እንዲህ ብለን የምንጸልየው፣ በሰማይና በምድር ያሉ ሁሉ የአምላክን ስም እንዲያከብሩና ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ ስለምንፈልግ ነው።
“መንግሥትህ ይምጣ”
የአምላክ መንግሥት የሰይጣንን ክፉ ዓለም እንዲያጠፋ እንዲሁም ምድርን እንዲገዛትና ወደ ገነትነት እንዲለውጣት እንጸልያለን።
“ፈቃድህ . . . በምድርም ላይ ይፈጸም”
የአምላክ ዓላማ በምድር ላይ እንዲፈጸም የምንጸልየው ታዛዥና ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ስለምንፈልግ ነው፤ አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር ዓላማው ይህ ነበር።
21 ቤዛው
ይሖዋ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ሲል ቤዛ አዘጋጅቷል። ይህ ቤዛ፣ የመጀመሪያው ሰው አዳም ያጣውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መልሶ ለመግዛት እንዲሁም በሰው ልጆችና በይሖዋ መካከል ያለውን የተበላሸ ዝምድና ለማስተካከል የተከፈለ ዋጋ ነው። አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው ለኃጢአተኞች ሁሉ እንዲሞት ሲል ነው። በኢየሱስ ሞት ምክንያት የሰው ልጆች ሁሉ ለዘላለም የመኖርና ፍጹም የመሆን አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል።
22 በ1914 ምን ታሪካዊ ክንውን ተፈጽሟል?
በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ አምላክ መንግሥቱን በ1914 እንደሚያቋቁም ይጠቁማል።
ትንቢቱ፦ ይሖዋ፣ ንጉሥ ናቡከደነጾር ወደፊት የሚፈጸምን ነገር በሕልም እንዲያይ አድርጎ ነበር፤ ናቡከደነጾር በሕልሙ ላይ አንድ ትልቅ ዛፍ የተመለከተ ሲሆን ዛፉ በኋላ ላይ ተቆረጠ። ከዚያም ዛፉ እንዳያድግ ሲባል ጉቶው ዙሪያውን በብረትና በመዳብ ታስሮ “ሰባት ዘመናት” እንዲቆይ ተደረገ። ይህ ጊዜ ሲያበቃ ዛፉ እንደገና ያድጋል።—ዳንኤል 4:1, 10-16
ይህ ትንቢት ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ዛፉ የአምላክን አገዛዝ ይወክላል። ለበርካታ ዓመታት ይሖዋ፣ የእስራኤልን ብሔር ለመምራት በኢየሩሳሌም ተቀምጠው የሚገዙ ነገሥታትን ይጠቀም ነበር። (1 ዜና መዋዕል 29:23) ሆኖም እነዚህ ነገሥታት ታማኝ ሳይሆኑ በመቅረታቸው የእነሱ አገዛዝ አበቃ። ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. ጠፋች። ‘ሰባቱ ዘመናት’ መቆጠር የሚጀምሩት ከዚህ ዓመት ነው። (2 ነገሥት 25:1, 8-10፤ ሕዝቅኤል 21:25-27) ኢየሱስ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም በአሕዛብ ትረገጣለች” በማለት ሲናገር ‘ሰባቱን ዘመናት’ ማመልከቱ ነበር። (ሉቃስ 21:24) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ‘ሰባቱ ዘመናት’ ገና አላበቁም ነበር። ‘ሰባቱ ዘመናት’ ሲያበቁ ይሖዋ ንጉሥ እንደሚሾም ቃል ገብቷል። የአዲሱ ንጉሥ ማለትም የኢየሱስ አገዛዝ በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ ሕዝቦች ዘላለማዊ በረከት ያስገኛል።—ሉቃስ 1:30-33
‘የሰባቱ ዘመናት’ ርዝማኔ፦ ‘ሰባቱ ዘመናት’ የ2,520 ዓመታት ርዝማኔ አላቸው። ከ607 ዓ.ዓ. ጀምረን 2,520 ዓመታት ስንቆጥር 1914 ላይ እንደርሳለን። ይሖዋ መሲሑን ማለትም ኢየሱስን የአምላክ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ የሾመው በዚህ ዓመት ነው።
ይሁንና ‘ሰባቱ ዘመናት’ 2,520 ዓመታት እንደሆኑ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሦስት ከግማሽ ዘመናት 1,260 ቀናት እንደሆኑ ይናገራል። (ራእይ 12:6, 14) በመሆኑም ‘ሰባቱ ዘመናት’ የዚህ ቁጥር እጥፍ ማለትም 2,520 ቀናት ይሆናሉ ማለት ነው። “አንዱ ቀን እንደ አንድ ዓመት [ይቆጠር]” በሚለው ትንቢት ላይ በተገለጸው ደንብ መሠረት 2,520 ቀናት 2,520 ዓመታት ይሆናሉ።—ዘኁልቁ 14:34፤ ሕዝቅኤል 4:6
23 የመላእክት አለቃ ሚካኤል
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘው አንድ የመላእክት አለቃ ብቻ ሲሆን እሱም ሚካኤል ተብሎ ይጠራል።—ዳንኤል 12:1፤ ይሁዳ 9
ሚካኤል ታማኝ መላእክትን ያቀፈው የአምላክ ሠራዊት መሪ ነው። ራእይ 12:7 ‘ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶውና ከመላእክቱ ጋር እንደተዋጉ’ ይናገራል። የራእይ መጽሐፍ የአምላክ ሠራዊት መሪ ኢየሱስ እንደሆነ ይገልጻል፤ በመሆኑም ሚካኤል የሚለው ስም የኢየሱስ ሌላ መጠሪያ ነው።—ራእይ 19:14-16
▸ ምዕ. 9 አን. 4፣ ግርጌ
24 የመጨረሻዎቹ ቀናት
ይህ አገላለጽ የአምላክ መንግሥት የሰይጣንን ዓለም ከማጥፋቱ በፊት በምድር ላይ ታላላቅ ክንውኖች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” እና “የሰው ልጅ መገኘት” የሚሉት አገላለጾችም ተመሳሳይ ጊዜን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ማቴዎስ 24:3, 27, 37) ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ የጀመሩት የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ መግዛት በጀመረበት ጊዜ ሲሆን የሚያበቁት ደግሞ የሰይጣን ዓለም በአርማጌዶን ጦርነት ሲጠፋ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ 2 ጴጥሮስ 3:3
25 ትንሣኤ
አምላክ የሞቱ ሰዎችን አስነስቶ ዳግመኛ በሕይወት እንዲኖሩ የሚያደርግበት ዝግጅት ትንሣኤ ይባላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች ከሞት እንደተነሱ ተገልጿል። ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንዲሁም ጳውሎስ የሞቱ ሰዎችን አስነስተዋል። ይህን ተአምር መፈጸም የሚቻለው በአምላክ ኃይል ብቻ ነው። ይሖዋ ‘ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት ተነስተው’ በምድር ላይ እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ከተነሱ በኋላ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች እንዳሉም ይናገራል። አምላክ የመረጣቸው ወይም የቀባቸው ሰዎች ትንሣኤ አግኝተው ከኢየሱስ ጋር በሰማይ አብረው ይሆናሉ።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 11:25፤ ፊልጵስዩስ 3:11፤ ራእይ 20:5, 6
26 አጋንንታዊ (መናፍስታዊ) ድርጊት
በቀጥታም ሆነ በጠንቋዮች ወይም ምትሃታዊ ኃይል አላቸው በሚባሉ ሰዎች አማካኝነት ከመናፍስት ጋር ለመገናኘት የሚደረገው ጥረት አጋንንታዊ ወይም መናፍስታዊ ድርጊት ይባላል። ሰዎች እንዲህ ባለው ድርጊት የሚካፈሉት፣ የሞቱ ሰዎች መንፈስ በሕይወት መኖሯን እንደምትቀጥልና እነዚህ ሰዎች ኃያል መንፈሳዊ አካል እንደሚሆኑ ስለሚያምኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አጋንንት የሰው ልጆች የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ ለማድረግ ይሞክራሉ። ኮከብ ቆጠራ፣ ሟርት፣ አስማት፣ ጥንቆላ፣ በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱ ልማዶች እንዲሁም ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች የሚከናወኑ ነገሮች መናፍስታዊ ድርጊቶች ናቸው። በርካታ መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ሆሮስኮፕ፣ ፊልሞች፣ ፖስተሮችና ዘፈኖችም ጭምር አስማትንና አጋንንትን ምንም ጉዳት እንደማያመጡ ወይም አስደሳች እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ። በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚካሄድ ጭፈራ፣ ተዝካር፣ ሙት ዓመት፣ ለሙታን መሥዋዕት ማቅረብና እነዚህን የመሳሰሉ ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ልማዶችም ከአጋንንት ጋር ንክኪ ያላቸው ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ለመገናኘት ሲሞክሩ ዕፆችን ይጠቀማሉ።—ገላትያ 5:20, 21፤ ራእይ 21:8
27 የይሖዋ ሉዓላዊነት
ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ሲሆን መላውን ጽንፈ ዓለም የፈጠረው እሱ ነው። (ራእይ 15:3) በመሆኑም የሁሉም ነገር ባለቤትና ሉዓላዊ ገዢ ነው፤ ፍጥረታቱን የመግዛት ሙሉ ሥልጣን አለው። (መዝሙር 24:1፤ ኢሳይያስ 40:21-23፤ ራእይ 4:11) ለፈጠራቸው ነገሮች በሙሉ ሕግ አውጥቷል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሌሎች ገዢ እንዲሆኑ የመሾም ሥልጣን አለው። አምላክን በመውደድና በመታዘዝ የእሱን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት እንችላለን።—1 ዜና መዋዕል 29:11
28 ፅንስ ማስወረድ
ፅንስ ማስወረድ፣ ያልተወለደን ልጅ ሕይወት ለማቋረጥ ሆን ተብሎ የሚወሰድ እርምጃ ነው። በአደጋ ወይም በሰውነት ላይ በተፈጠረ ለውጥ የተነሳ በማህፀን ውስጥ ያለ ሕፃን ሕይወት ቢያልፍ ፅንስ ማስወረድ አይባልም። አንድ ሕፃን ከተጸነሰበት ጊዜ አንስቶ ራሱን የቻለ ሰው ነው እንጂ የእናቱ አካል ክፍል አይደለም። ስለዚህ ፅንስ ማስወረድ እንደ ነፍስ ግድያ ይቆጠራል።
29 ደም መውሰድ
አንድ ሰው ለሕክምና ሲባል የሌላን ሰው ደም ወይም ቀደም ሲል ከሰውነቱ ወጥቶ የተቀመጠን ደም አሊያም ከአራቱ ዋና ዋና የደም ክፍልፋዮች አንዱን እንዲወስድ ሊደረግ ይችላል። አራቱ ዋና ዋና የደም ክፍልፋዮች ቀይ የደም ሕዋሳት፣ ነጭ የደም ሕዋሳት፣ ፕሌትሌትና ፕላዝማ ናቸው።
30 ተግሣጽ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተግሣጽ” የሚለው ቃል የተሠራበት ቅጣትን ብቻ ለማመልከት አይደለም። ተግሣጽ ትምህርት፣ ሥልጠናና እርማት መስጠትንም ያመለክታል። ይሖዋ የሚሰጠን ተግሣጽ የሚጎዳ ወይም ጭካኔ የተሞላበት አይደለም። (ምሳሌ 4:1, 2) ይሖዋ ለወላጆች ግሩም ምሳሌ ትቷል። እሱ የሚሰጠው ተግሣጽ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ ግለሰቡ ተግሣጽን እንዲወድ ሊያነሳሳው ይችላል። (ምሳሌ 12:1) ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚወድ ከመሆኑም ሌላ ያሠለጥናቸዋል። እሱ የሚሰጣቸው ትምህርት የተሳሳተ አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ፣ ጥሩ አስተሳሰብ እንዲያዳብሩና እሱን በሚያስደስት መንገድ እንዲኖሩ ይረዳቸዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው ተግሣጽ በሚሰጡበት ወቅት ታዛዥ መሆን ያለባቸው ለምን እንደሆነ ሊያስረዷቸው ይገባል። በተጨማሪም ልጆቻቸው ይሖዋን፣ ቃሉን እንዲሁም በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲወዱ ማስተማር አለባቸው።
31 አጋንንት
ከሰው በላይ ኃይል ያላቸው በዓይን የማይታዩ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን ናቸው። አጋንንት ክፉ መላእክት ናቸው። እነዚህ ክፉ መላእክት የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ የእሱ ጠላቶች ሆነዋል። (ዘፍጥረት 6:2፤ ይሁዳ 6) ሰይጣን በይሖዋ ላይ ባስነሳው ዓመፅ ተባባሪ ሆነዋል።—ዘዳግም 32:17፤ ሉቃስ 8:30፤ የሐዋርያት ሥራ 16:16፤ ያዕቆብ 2:19