ምዕራፍ አሥራ አምስት
እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
1. አምላክን እንዴት ልናመልከው እንደሚገባ ሊነግረን የሚችለው ማን ነው?
አብዛኞቹ ሃይማኖቶች ስለ አምላክ እውነቱን እንደሚያስተምሩ ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሃይማኖቶች ‘አምላክ ማን ነው?’ እንዲሁም ‘ሊመለክ የሚገባው እንዴት ነው?’ የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ የሚያስተምሩት ትምህርት በጣም የተለያየ ነው። አምላክ መመለክ የሚፈልገው እንዴት እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? እሱን እንዴት ልናመልከው እንደሚገባ ሊነግረን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።
2. አምላክን እንዴት ልናመልከው እንደሚገባ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
2 ይሖዋ እንዴት ልናመልከው እንደሚገባ ማወቅ እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን አጥና፤ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ ለአንተ በጣም ስለሚያስብ ከትምህርቶቹ ጥቅም ማግኘት እንድትችል ይረዳሃል።—ኢሳይያስ 48:17
3. አምላክ ምን እንድናደርግ ይፈልጋል?
3 አንዳንድ ሰዎች አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች እንደሚቀበል ይናገራሉ፤ ሆኖም ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አላስተማረም። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።” በመሆኑም አምላክ ፈቃዱ ምን እንደሆነ እንድናውቅ ከዚያም ተግባራዊ እንድናደርገው ይፈልጋል። ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የአምላክን ትእዛዝ የማያከብሩ ሰዎችን ከወንጀለኞች ወይም ‘ከዓመፀኞች’ ጋር አመሳስሏቸዋል።—ማቴዎስ 7:21-23
4. ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን በተመለከተ ምን ብሏል?
4 ኢየሱስ፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” (ማቴዎስ 7:13, 14) በቀጭኑ መንገድ መሄድ ማለትም አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለክ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። በሰፊው መንገድ መሄድ ይኸውም አምላክን እሱ በማይፈልገው መንገድ ማምለክ ደግሞ ሞት ያስከትላል። ይሁንና ይሖዋ ማንም ሰው እንዲሞት አይፈልግም። በመሆኑም ሰዎች ሁሉ ስለ እሱ ማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ያደርጋል።—2 ጴጥሮስ 3:9
እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
5. እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቅ እንደሚቻል ተናግሯል። የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች የሚያምኑባቸውን ነገሮችና ድርጊታቸውን በማየት ሃይማኖቱ እውነተኛ መሆን አለመሆኑን ማወቅ እንችላለን። ኢየሱስ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሏል። በተጨማሪም “ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:16, 17) እንዲህ ሲባል ግን የእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች ፍጹም ናቸው ማለት አይደለም። ሆኖም ምንጊዜም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ከዚህ ቀጥሎ እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎችን ለይተን ለማወቅ የሚረዱንን ነጥቦች እንመለከታለን።
6, 7. እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?
6 እምነታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “የአምላክን ቃል ከእኛ በሰማችሁ ጊዜ እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) እምነታችን የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን አለበት። በሰዎች ሐሳብ፣ ወግ አሊያም በሌላ ነገር ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም።
7 ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ነበር። (ዮሐንስ 17:17ን አንብብ።) በተደጋጋሚ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ይጠቅስ ነበር። (ማቴዎስ 4:4, 7, 10) እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችም የኢየሱስን ምሳሌ ስለሚከተሉ የሚያስተምሩት ትምህርት ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው።
8. ኢየሱስ ይሖዋን ማምለክን በተመለከተ ምን አስተምሯል?
8 ሊመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው። መዝሙር 83:18 “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል [ነህ]” ይላል። ኢየሱስ፣ ሰዎች የእውነተኛውን አምላክ ማንነት እንዲያውቁ ይፈልግ ስለነበር የአምላክን ስም ለሰዎች አስተምሯል። (ዮሐንስ 17:6ን አንብብ።) በተጨማሪም “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:10) የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንከተላለን። ይሖዋን ብቻ እናመልካለን፤ ስሙን እንጠቀማለን፤ እንዲሁም የአምላክን ስምና ወደፊት የሚያደርግልንን ነገር ለሌሎች እናስተምራለን።
9, 10. እርስ በርሳችን እንደምንዋደድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 እርስ በርስ ከልብ ልንዋደድ ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እርስ በርስ እንዲዋደዱ አስተምሯቸዋል። (ዮሐንስ 13:35ን አንብብ።) ሰዎች የተወለዱበት ቦታ፣ ባሕላቸው እንዲሁም የኑሮ ደረጃቸው ለእነሱ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን አይገባም። እርስ በርስ ያለን ፍቅር እንደ ወንድማማቾችና እህትማማቾች አንድ ሊያደርገን ይገባል። (ቆላስይስ 3:14) በመሆኑም በጦርነት በመካፈል ሰዎችን አንገድልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ በግልጽ ይታወቃሉ፦ በጽድቅ ጎዳና የማይመላለስ ሁሉ የአምላክ ወገን አይደለም፤ ወንድሙን የማይወድም የአምላክ ወገን አይደለም።” በተጨማሪም “እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን፤ . . . ከክፉው ወገን እንደሆነውና ወንድሙን በጭካኔ እንደገደለው እንደ ቃየን መሆን የለብንም” ይላል።—1 ዮሐንስ 3:10-12፤ 4:20, 21
10 ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን ሌሎችን ለመርዳት እንዲሁም ለማበረታታት ልንጠቀምበት ይገባል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ‘ለሁሉም መልካም እናደርጋለን።’—ገላትያ 6:10
11. ኢየሱስ ወደ አምላክ የሚያደርስ መንገድ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
11 ኢየሱስ ወደ አምላክ የሚያደርስ መንገድ ስለሆነ እሱን መታዘዝ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መዳን በሌላ በማንም አይገኝም፤ ምክንያቱም ልንድንበት የምንችል ከሰማይ በታች ለሰዎች የተሰጠ ሌላ ስም የለም።” (የሐዋርያት ሥራ 4:12) በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 5 ላይ ኢየሱስ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዲሰጥ ይሖዋ እንደላከው ተምረናል። (ማቴዎስ 20:28) ይሖዋ፣ ኢየሱስን በምድር ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም መኖር ከፈለግን ኢየሱስን መታዘዝ እንዳለብን የሚናገረው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 3:36ን አንብብ።
12. በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የማንገባው ለምንድን ነው?
12 በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባት የለብንም። ኢየሱስ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም። በሮማዊው ገዢ በጲላጦስ ፊት ተከስሶ በቀረበበት ጊዜ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሎት ነበር። (ዮሐንስ 18:36ን አንብብ።) ልክ እንደ ኢየሱስ በሰማይ ላለው የአምላክ መንግሥት ታማኞች ነን፤ በዚህም ምክንያት የትም እንኑር የት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አንገባም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ለበላይ ባለሥልጣናት” ማለትም ለመንግሥታት እንድንገዛ ያዝዘናል። (ሮም 13:1) በመሆኑም የምንኖርበትን አገር ሕጎች እንታዘዛለን። ሆኖም አንድ ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ሐዋርያት የተዉትን ምሳሌ እንከተላለን፤ እነሱ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” ብለዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:29፤ ማርቆስ 12:17
13. የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ምን እንሰብካለን?
13 በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እናምናለን። ኢየሱስ “የመንግሥቱ ምሥራች” በመላው ዓለም እንደሚሰበክ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14ን አንብብ።) የአምላክ መንግሥት ወደፊት የሚያደርግልንን ነገር የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ሊያደርግ አይችልም። (መዝሙር 146:3) ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብላችሁ ጸልዩ በማለት ስለ አምላክ መንግሥት እንድንጸልይ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ አጥፍቶ ‘እሱ ብቻውን ለዘላለም እንደሚቆም’ ይናገራል።—ዳንኤል 2:44
14. አምላክን በትክክለኛው መንገድ የሚያመልኩት እነማን ናቸው ትላለህ?
14 እነዚህን ነጥቦች በሚገባ ካሰብክባቸው በኋላ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት የሚያስተምሩት እነማን ናቸው? የአምላክን ስም ለሌሎች የሚያሳውቁት እነማን ናቸው? እርስ በርስ ከልብ የሚዋደዱትና አምላክ እኛን ለማዳን ኢየሱስን እንደላከ የሚያምኑት እነማን ናቸው? ፖለቲካ ውስጥ የማይገቡት እነማን ናቸው? ችግሮቻችንን የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ የሚሰብኩት እነማን ናቸው?’ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።—ኢሳይያስ 43:10-12
ምን ለማድረግ አስበሃል?
15. አምላክ የምናቀርበውን አምልኮ እንዲቀበለን ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 አምላክ መኖሩን ማመን ብቻ በቂ አይደለም። አጋንንትም እንኳ አምላክ እንዳለ ያምናሉ፤ ሆኖም እሱን አይታዘዙም። (ያዕቆብ 2:19) አምላክ የምናቀርበውን አምልኮ እንዲቀበለን የምንፈልግ ከሆነ እሱ እንዳለ ማመን ብቻ ሳይሆን ትእዛዙንም መፈጸም ይኖርብናል።
16. ከሐሰት ሃይማኖት መራቅ ያለብን ለምንድን ነው?
16 አምላክ የምናቀርበውን አምልኮ እንዲቀበለን ከፈለግን ከሐሰት ሃይማኖት መራቅ አለብን። ነቢዩ ኢሳይያስ “ከመካከሏ ውጡ፤ ንጽሕናችሁን ጠብቁ” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 52:11፤ 2 ቆሮንቶስ 6:17) በመሆኑም ከሐሰት አምልኮ ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል።
17, 18. “ታላቂቱ ባቢሎን” ምንን ታመለክታለች? ከእሷ መውጣት በጣም አጣዳፊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
17 የሐሰት ሃይማኖት ሲባል ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው በተለየ መንገድ አምላክን እንድናመልክ የሚያስተምር የትኛውም ሃይማኖት የሐሰት ሃይማኖት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ “ታላቂቱ ባቢሎን” በማለት ይጠራቸዋል። (ራእይ 17:5) ለምን? በኖኅ ዘመን ከተከሰተው የጥፋት ውኃ በኋላ በባቢሎን ከተማ ውስጥ በርካታ የሐሰት ትምህርቶች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ ትምህርቶች በዓለም ዙሪያ እየተስፋፉ ሄዱ። ለምሳሌ ያህል፣ በባቢሎን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሦስት ሦስት አማልክትን ያመልኩ ነበር። ዛሬም ብዙ ሃይማኖቶች አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ያስተምራሉ፤ ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው አምላክ አንድ ይኸውም ይሖዋ እንደሆነና ኢየሱስ ደግሞ ልጁ እንደሆነ በግልጽ ያስተምራል። (ዮሐንስ 17:3) ከዚህም ሌላ በባቢሎን የነበሩ ሰዎች አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከእሱ ተለይታ መኖሯን የምትቀጥል ነገር እንዳለችና ይህች ነገር ሲኦል ገብታ ልትሠቃይ እንደምትችል ያምኑ ነበር። ይህም ቢሆን እውነት አይደለም።—ተጨማሪ ሐሳብ 14, 17 እና 18ን ተመልከት።
18 አምላክ፣ የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ በቅርቡ እንደሚጠፉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 18:8) የሐሰት ሃይማኖትን ለቆ መውጣት በጣም አጣዳፊ የሆነው ለምን እንደሆነ ተገነዘብክ? ይሖዋ አምላክ ይህ ጥፋት ከመምጣቱ በፊት እርምጃ እንድትወስድ ይፈልጋል።—ራእይ 18:4
19. ይሖዋን ለማገልገል ስትወስን እሱ አይተውህም የምንለው ለምንድን ነው?
19 ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተህ ይሖዋን ለማገልገል ስትወስን አንዳንድ ጓደኞችህ ወይም ቤተሰቦችህ ያደረግከውን ውሳኔ ላይደግፉ፣ ከባድ ተቃውሞ ሊያደርሱብህ እንዲሁም ሊያገሉህ ይችላሉ። ሆኖም ይሖዋ አይተውህም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙና እርስ በርስ የሚዋደዱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ ትልቅ ቤተሰብ አባል ትሆናለህ፤ እንዲሁም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖርሃል። (ማርቆስ 10:28-30) ምናልባትም ይሖዋን ለማገልገል ያደረግከውን ውሳኔ ከተቃወሙ ጓደኞችህ ወይም ቤተሰቦችህ መካከል አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይወስኑ ይሆናል።
20. እውነተኛውን ሃይማኖት መከተል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
20 አምላክ በቅርቡ ክፋትን ሁሉ ያስወግዳል፤ የእሱ መንግሥትም ምድርን ማስተዳደር ይጀምራል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 13) ያ ጊዜ በጣም አስደሳች እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰው ይሖዋን እሱ በሚፈልገው መንገድ ያመልከዋል። በዚያ ጊዜ መገኘት ከፈለግክ አሁኑኑ እርምጃ መውሰድህና እውነተኛውን ሃይማኖት መከተልህ አስፈላጊ ነው።