አንደኛ ዜና መዋዕል
26 የበር ጠባቂዎቹ+ ምድብ እንደሚከተለው ነው፦ ከቆሬያውያን መካከል ከአሳፍ ልጆች አንዱ የሆነው የቆረ ልጅ መሺሌሚያህ።+ 2 መሺሌሚያህም ወንዶች ልጆች ነበሩት፦ የበኩር ልጁ ዘካርያስ፣ ሁለተኛው የዲአዔል፣ ሦስተኛው ዘባድያህ፣ አራተኛው ያትንኤል፣ 3 አምስተኛው ኤላም፣ ስድስተኛው የሆሃናን እና ሰባተኛው ኤሊየሆዔናይ። 4 ኦቤድዔዶምም ወንዶች ልጆች ነበሩት፦ የበኩር ልጁ ሸማያህ፣ ሁለተኛው የሆዛባድ፣ ሦስተኛው ዮአስ፣ አራተኛው ሳካር፣ አምስተኛው ናትናኤል፣ 5 ስድስተኛው አሚዔል፣ ሰባተኛው ይሳኮር እና ስምንተኛው ፐኡልታይ፤ አምላክ እነዚህን ልጆች በመስጠት ኦቤድዔዶምን ባረከው።
6 ልጁም ሸማያህ ልጆች ወለደ፤ እነሱም ብቃት ያላቸውና ኃያላን ነበሩ፤ የየቤተሰባቸውም መሪ ሆኑ። 7 የሸማያህ ወንዶች ልጆች ኦትኒ፣ ረፋኤል፣ ኢዮቤድ እና ኤልዛባድ ነበሩ፤ የኤልዛባድ ወንድሞች የሆኑት ኤሊሁ እና ሰማክያህም ብቃት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። 8 እነዚህ ሁሉ የኦቤድዔዶም ወንዶች ልጆች ነበሩ፤ እነሱም ሆኑ ወንዶች ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው አገልግሎቱን ለማከናወን ችሎታና ብቃት ያላቸው ሰዎች ነበሩ፤ ከኦቤድዔዶም ወገን 62 ነበሩ። 9 መሺሌሚያህም+ ብቃት ያላቸው ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ነበሩት፤ እነሱም 18 ነበሩ። 10 የሜራሪ ልጅ የሆነው ሆሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት። ሺምሪ የበኩር ልጅ ባይሆንም እንኳ አባቱ የቤተሰቡ መሪ አድርጎ ሾመው፤ 11 ሁለተኛው ኬልቅያስ፣ ሦስተኛው ተባልያህ እና አራተኛው ዘካርያስ ነበሩ። የሆሳ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች በአጠቃላይ 13 ነበሩ።
12 የበር ጠባቂዎቹ ምድብ መሪዎች ልክ እንደ ወንድሞቻቸው በይሖዋ ቤት በሚቀርበው አገልግሎት የሚያከናውኑት ሥራ ነበራቸው። 13 በመሆኑም ለእያንዳንዱ በር፣ ትንሽ ትልቅ ሳይባል ለሁሉም በየአባቶቻቸው ቤት ዕጣ+ ተጣለ። 14 ከዚያም የምሥራቁ በር ዕጣ ለሸሌምያህ ወጣ። አስተዋይ መካሪ ለሆነው ለልጁ ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ በዕጣውም መሠረት የሰሜን በር ደረሰው። 15 ኦቤድዔዶም በደቡብ በኩል ያለው በር ደረሰው፤ ወንዶች ልጆቹ+ ደግሞ ግምጃ ቤቶቹ ደረሷቸው። 16 ሹፒም እና ሆሳ+ በአቀበቱ መንገድ ባለው በሻለከት በር አቅራቢያ የሚገኘው የምዕራብ በር ደረሳቸው፤ የዘብ ጠባቂ ቡድኖቹ ጎን ለጎን ቆመው ይጠብቁ ነበር፤ 17 በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል በየቀኑ አራት፣ በደቡብ በኩል በየቀኑ አራት እንዲሁም ግምጃ ቤቶቹን+ ሁለት ሁለት ሆነው ይጠብቁ ነበር፤ 18 በምዕራብ በኩል ባለው መተላለፊያ በጎዳናው+ ላይ አራት፣ በመተላለፊያው ላይ ደግሞ ሁለት ሆነው ይጠብቁ ነበር። 19 የቆሬያውያንና የሜራራውያን ወንዶች ልጆች የበር ጥበቃ ምድብ ይህ ነበር።
20 ከሌዋውያን መካከል አኪያህ በእውነተኛው አምላክ ቤት የሚገኙት ግምጃ ቤቶችና ቅዱስ የሆኑ ነገሮች* ያሉባቸው ግምጃ ቤቶች ኃላፊ ነበር።+ 21 የላዳን ወንዶች ልጆች፦ የላዳን ወገን ከሆኑት ከጌድሶናውያን ወንዶች ልጆች ማለትም የጌድሶናዊው የላዳን ወገን ከሆኑት የየአባቶቻቸው ቤቶች መሪዎች መካከል የሂኤሊ+ 22 እንዲሁም የየሂኤሊ ወንዶች ልጆች ዜታምና ወንድሙ ኢዩኤል ነበሩ። እነሱም በይሖዋ ቤት የሚገኙት ግምጃ ቤቶች+ ኃላፊዎች ነበሩ። 23 ከአምራማውያን፣ ከይጽሃራውያን፣ ከኬብሮናውያን እና ከዑዚኤላውያን+ መካከል፣ 24 የሙሴ ልጅ፣ የጌርሳም ልጅ ሸቡኤል የግምጃ ቤቶቹ ኃላፊ ነበር። 25 የኤሊዔዘር+ ዘሮች የሆኑት ወንድሞቹ ረሃቢያህ፣+ የሻያህ፣ ዮራም፣ ዚክሪ እና ሸሎሞት ነበሩ። 26 ሸሎሞትና ወንድሞቹ ንጉሥ ዳዊት፣+ የአባቶች ቤት መሪዎች፣+ የሺህ አለቆቹ፣ የመቶ አለቆቹና የሠራዊቱ አለቆች የቀደሷቸው ቅዱስ ነገሮች+ የሚገኙባቸው ግምጃ ቤቶች ሁሉ ኃላፊዎች ነበሩ። 27 የይሖዋን ቤት ለማደስ በጦርነት+ ከተገኘው ምርኮ+ ውስጥ የተወሰነውን ቀደሱ፤ 28 በተጨማሪም ባለ ራእዩ+ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር+ እና የጽሩያ+ ልጅ ኢዮዓብ+ የቀደሷቸውን ነገሮች ሁሉ በኃላፊነት ይይዙ ነበር። ማንኛውም ሰው የቀደሰው ነገር በሸሎሚት* እና በወንድሞቹ እጅ ይሆን ነበር።
29 ከይጽሃራውያን+ መካከል ኬናንያ እና ወንዶች ልጆቹ ከአምላክ ቤት ውጭ ባለው የአስተዳደር ሥራ ላይ በእስራኤል አለቆችና ዳኞች+ ሆነው ተመደቡ።
30 ከኬብሮናውያን+ መካከል ብቁ የሆኑት ሃሻብያህ እና ወንድሞቹ 1,700 ነበሩ፤ እነሱም ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ባለው የእስራኤል ምድር ከይሖዋ ሥራ ሁሉና ከንጉሡ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። 31 የሪያህ+ የኬብሮናውያን አባቶች ቤቶችና ቤተሰቦች መሪ ነበር። በዳዊት ዘመነ መንግሥት 40ኛ ዓመት+ ምርመራ ተካሄደ፤ በእነሱም መካከል በጊልያድ፣ ያዜር+ በተባለ ቦታ ኃያላን የሆኑና ብቃት ያላቸው ሰዎች ተገኙ። 32 የአባቶች ቤቶች መሪዎች የሆኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞቹ 2,700 ነበሩ። በመሆኑም ንጉሥ ዳዊት ከእውነተኛው አምላክና ከንጉሡ ጉዳዮች ሁሉ ጋር በተያያዘ በሮቤላውያን፣ በጋዳውያንና በምናሴያውያን ነገድ እኩሌታ ላይ ሾማቸው።