ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ
5 ምድራዊ ቤታችን* የሆነው ይህ ድንኳን ቢፈርስ+ በሰው እጅ የተሠራ ቤት ሳይሆን በሰማይ ዘላለማዊ የሆነ ሕንፃ ከአምላክ እንደምናገኝ እናውቃለን።+ 2 ከሰማይ የሆነውን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን በዚህ ቤት* ውስጥ ሆነን እንቃትታለን፤+ 3 ስለዚህ ይህን ስንለብስ ራቁታችንን ሆነን አንገኝም። 4 እንዲያውም በዚህ ድንኳን ውስጥ ያለነው እኛ ከባድ ሸክም ተጭኖን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ዘላለማዊው ሕይወት ሟች የሆነውን አካል እንዲተካ+ ይህን ድንኳን ማውለቅ ሳይሆን ሰማያዊውን መኖሪያ መልበስ እንፈልጋለን።+ 5 ለዚህ ነገር ያዘጋጀን አምላክ ነው፤+ ለሚመጣው ነገር ማረጋገጫ* አድርጎ መንፈሱን የሰጠን እሱ ነው።+
6 በመሆኑም ስለዚህ ጉዳይ ምንጊዜም እርግጠኞች ነን፤ በተጨማሪም መኖሪያችን በሆነው በዚህ አካል እስካለን ድረስ ከጌታ ጋር አብረን እንዳልሆን እናውቃለን፤+ 7 የምንመላለሰው በእምነት እንጂ በማየት አይደለምና። 8 ሆኖም እኛ እርግጠኞች ነን፤ ደግሞም ከዚህ አካል ተለይተን መኖሪያችንን ከጌታ ጋር ብናደርግ እንመርጣለን።+ 9 ስለዚህ ከእሱ ጋር አብረን ብንኖርም ሆነ ባንኖር ዓላማችን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ነው። 10 ምክንያቱም እያንዳንዱ በሥጋ እያለ ላደረገው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር፣ እንደ ሥራው ብድራት እንዲቀበል ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ልንቀርብ* ይገባል።+
11 እንግዲህ ጌታን መፍራት እንደሚገባን ስለምናውቅ ሰዎች የምንናገረውን እንዲቀበሉ ለማሳመን ምንጊዜም እንጥራለን፤ ሆኖም አምላክ በሚገባ ያውቀናል።* የእናንተም ሕሊና እኛን በሚገባ እንድታውቁ እንደረዳችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። 12 እኛ ብቃታችንን ለእናንተ እንደ አዲስ ማቅረባችን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ሳይሆን በውጫዊ መልክ ለሚኩራሩ+ መልስ መስጠት ትችሉ ዘንድ በእኛ እንድትኮሩ እያነሳሳናችሁ ነው። 13 አእምሯችንን ብንስት+ ለአምላክ ብለን ነውና፤ ጤናማ አእምሮ ቢኖረን ደግሞ ለእናንተ ብለን ነው። 14 አንድ ሰው ለሁሉም መሞቱን+ ስለተረዳን ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም ሁሉም ቀድሞውኑ ሞተዋል። 15 በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።+
16 ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ሰዎችን የምናውቀው ከሥጋዊ አመለካከት አንጻር አይደለም።*+ ክርስቶስን በሥጋዊ ሁኔታ እናውቀው የነበረ ቢሆንም ከዚህ በኋላ በዚህ መንገድ አናውቀውም።+ 17 በመሆኑም ማንም ከክርስቶስ ጋር አንድነት ካለው አዲስ ፍጥረት ነው፤+ አሮጌዎቹ ነገሮች አልፈዋል፤ እነሆ፣ አዳዲስ ነገሮች ወደ ሕልውና መጥተዋል! 18 ሆኖም ሁሉም ነገሮች የተገኙት በክርስቶስ አማካኝነት ከራሱ ጋር ካስታረቀንና+ የማስታረቅ አገልግሎት ከሰጠን አምላክ ነው።+ 19 ይህም፣ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ዓለምን ከራሱ ጋር ከማስታረቁም በላይ+ በደላቸውን አልቆጠረባቸውም ማለት ነው፤+ ለእኛ ደግሞ የእርቁን መልእክት በአደራ ሰጥቶናል።+
20 ስለዚህ እኛ ክርስቶስን ተክተን+ የምንሠራ አምባሳደሮች ነን፤+ አምላክ በእኛ አማካኝነት እየተማጸነ ያለ ያህል ነው። ክርስቶስን ተክተን የምንሠራ እንደመሆናችን መጠን “ከአምላክ ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። 21 እኛ በእሱ አማካኝነት በአምላክ ፊት ጻድቅ እንድንሆን+ ኃጢአት የማያውቀው+ እሱ ለእኛ የኃጢአት መባ ተደረገ።