11 ከእሴይ+ ጉቶ፣ ቅርንጫፍ ይወጣል፤
ከሥሮቹም የሚወጣው ቀንበጥ ፍሬ ያፈራል።+
2 በእሱም ላይ የይሖዋ መንፈስ፣+
የጥበብና+ የማስተዋል መንፈስ፣
የምክርና የኃይል+ መንፈስ፣
የእውቀትና ይሖዋን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።
3 ይሖዋን በመፍራትም ደስ ይሰኛል።+
ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም
ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም።+
4 ለችግረኞች በትክክል ይፈርዳል፤
በምድር ላሉ የዋሆች ጥቅም ሲል ሌሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይወቅሳል።
በአፉም በትር ምድርን ይመታል፤+
በከንፈሩም እስትንፋስ ክፉዎችን ይገድላል።+
5 ጽድቅ የወገቡ መታጠቂያ፣
ታማኝነትም የጎኑ መታጠቂያ ይሆናል።+
6 ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር የሚቀመጥበት ጊዜ ይኖራል፤+
ነብርም ከፍየል ግልገል ጋር ይተኛል፤
ጥጃ፣ አንበሳና የሰባ ከብት አብረው ይሆናሉ፤+
ትንሽ ልጅም ይመራቸዋል።
7 ላምና ድብ አብረው ይበላሉ፤
ልጆቻቸውም አብረው ይተኛሉ።
አንበሳ እንደ በሬ ገለባ ይበላል።+
8 ጡት የሚጠባ ሕፃንም በእባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፤
ጡት የጣለውም ሕፃን እጁን በመርዘኛ እባብ ጎሬ ላይ ያደርጋል።
9 በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ
ምንም ዓይነት ጉዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤+
ምክንያቱም ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን
ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።+
10 በዚያን ቀን የእሴይ ሥር+ ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል።+
ብሔራት ከእሱ መመሪያ ይሻሉ፤+
ማረፊያ ስፍራውም እጅግ የከበረ ይሆናል።
11 በዚያን ቀን ይሖዋ ዳግመኛ እጁን ዘርግቶ የተረፉትን የሕዝቡን ቀሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ ከአሦር፣+ ከግብፅ፣+ ከጳትሮስ፣+ ከኢትዮጵያ፣+ ከኤላም፣+ ከሰናኦር፣ ከሃማትና ከባሕር ደሴቶች+ መልሶ ይሰበስባል። 12 ለብሔራት ምልክት ያቆማል፤ በየቦታው የተሰራጩትን እስራኤላውያንም መልሶ ያመጣቸዋል፤+ እንዲሁም የተበታተኑትን የይሁዳ ሰዎች ከአራቱም የምድር ማዕዘኖች ይሰበስባል።+
13 የኤፍሬም ቅናት ይወገዳል፤+
ይሁዳንም የሚጠሉ ይጠፋሉ።
ኤፍሬም በይሁዳ አይቀናም፤
ይሁዳም ኤፍሬምን አይጠላውም።+
14 በምዕራብ በኩል በፍልስጤም ተረተር ላይ በድንገት ይወርዳሉ፤
ግንባር ፈጥረው በምሥራቅ የሚኖሩ ሕዝቦችን ይዘርፋሉ።
በኤዶምና+ በሞዓብ+ ላይ እጃቸውን ይዘረጋሉ፤
አሞናውያንም ተገዢዎቻቸው ይሆናሉ።+
15 ይሖዋ የግብፅን ባሕረ ሰላጤ ይከፍላል፤+
በወንዙም+ ላይ እጁን በዛቻ ያወዛውዛል።
በሚያቃጥል እስትንፋሱ የወንዙን ሰባት ጅረቶች ይመታል፤
ሰዎችም ከነጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋል።
16 እስራኤል ከግብፅ ምድር በወጣበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ፣
ከሕዝቡ የተረፉት ቀሪዎችም+ ከአሦር የሚወጡበት ጎዳና+ ይኖራል።