ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። ከቤርሳቤህ ጋር ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ ነቢዩ ናታን መጥቶ ባነጋገረው ጊዜ ዳዊት ያቀረበው ማህሌት።+
51 አምላክ ሆይ፣ እንደ ታማኝ ፍቅርህ መጠን ሞገስ አሳየኝ።+
እንደ ታላቅ ምሕረትህ መተላለፌን ደምስስ።+
2 ከበደሌ ሙሉ በሙሉ እጠበኝ፤+
ከኃጢአቴም አንጻኝ።+
3 መተላለፌን በሚገባ አውቃለሁና፤
ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነው።+
4 አንተን፣ አዎ ከማንም በላይ አንተን በደልኩ፤+
በአንተ ዓይን ክፉ የሆነውን ነገር ፈጸምኩ።+
ስለዚህ አንተ በምትናገርበት ጊዜ ጻድቅ ነህ፤
በምትፈርድበት ጊዜም ትክክል ነህ።+
5 እነሆ፣ በደለኛ ሆኜ ተወለድኩ፤
እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ።+
6 ከልብ የመነጨ እውነት ደስ ያሰኝሃል፤+
ልቤን እውነተኛ ጥበብ አስተምረው።
7 ንጹሕ እሆን ዘንድ በሂሶጵ ከኃጢአቴ አንጻኝ፤+
ከበረዶም የበለጠ እነጣ ዘንድ እጠበኝ።+
8 ያደቀቅካቸው አጥንቶች ደስ እንዲላቸው፣+
የደስታንና የሐሴትን ድምፅ አሰማኝ።
9 ፊትህን ከኃጢአቴ መልስ፤+
የፈጸምኳቸውንም ስህተቶች ሁሉ አስወግድ።+
10 አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤+
በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር።+
11 ከፊትህ አትጣለኝ፤
ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ አትውሰድ።
12 የአንተ ማዳን የሚያስገኘውን ደስታ መልስልኝ፤+
አንተን የመታዘዝ ፍላጎት በውስጤ እንዲቀሰቀስ አድርግ።
13 ኃጢአተኞች ወደ አንተ እንዲመለሱ፣
ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ።+
14 አምላክ ሆይ፣ የመዳኔ አምላክ፣+ አንደበቴ ጽድቅህን በደስታ ያስታውቅ ዘንድ+
የደም ባለዕዳ ከመሆን አድነኝ።+
15 ይሖዋ ሆይ፣ አፌ ምስጋናህን እንዲያውጅ
ከንፈሮቼን ክፈት።+
16 መሥዋዕት እንዲቀርብልህ አትፈልግምና፤ ቢሆንማ ኖሮ ባቀረብኩልህ ነበር፤+
ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ አያስደስትህም።+
17 አምላክን የሚያስደስተው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤
አምላክ ሆይ፣ የተሰበረንና የተደቆሰን ልብ ችላ አትልም።+
18 በበጎ ፈቃድህ ለጽዮን መልካም ነገር አድርግላት፤
የኢየሩሳሌምን ግንቦች ገንባ።
19 በዚያን ጊዜ የጽድቅ መሥዋዕቶች፣
የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችና ሙሉ በሙሉ የሚቀርቡ መባዎች ደስ ያሰኙሃል፤
በዚያን ጊዜ ኮርማዎች በመሠዊያህ ላይ ይቀርባሉ።+