የያዕቆብ ደብዳቤ
5 እናንተ ሀብታሞች እንግዲህ ስሙ፤ እየመጣባችሁ ባለው መከራ አልቅሱ እንዲሁም ዋይ ዋይ በሉ።+ 2 ሀብታችሁ በስብሷል፤ ልብሳችሁንም ብል በልቶታል።+ 3 ወርቃችሁና ብራችሁ ሙሉ በሙሉ ዝጓል፤ ዝገቱም በእናንተ ላይ ይመሠክራል፤ ሥጋችሁንም ይበላል። ያከማቻችሁት ነገር በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደ እሳት ይሆናል።*+ 4 እነሆ፣ በእርሻችሁ ላይ ያለውን ሰብል ለሰበሰቡት ሠራተኞች ሳትከፍሏቸው የቀራችሁት ደሞዝ ይጮኻል፤ አጫጆቹም ለእርዳታ የሚያሰሙት ጥሪ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ ይሖዋ* ጆሮ ደርሷል።+ 5 በምድር ላይ በቅንጦት ኖራችኋል፤ የራሳችሁንም ፍላጎት ለማርካት ትጥሩ ነበር። በእርድ ቀን ልባችሁን አወፍራችኋል።+ 6 ጻድቁን ኮነናችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት። እሱ እየተቃወማችሁ አይደለም?*
7 እንግዲህ ወንድሞች፣ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ+ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ። እነሆ፣ ገበሬ የመጀመሪያውና የኋለኛው ዝናብ እስኪመጣ ድረስ በመታገሥ የምድርን መልካም ፍሬ ይጠባበቃል።+ 8 እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ፤+ ጌታ የሚገኝበት ጊዜ ስለተቃረበ ልባችሁን አጽኑ።+
9 ወንድሞች፣ እንዳይፈረድባችሁ አንዳችሁ በሌላው ላይ አታጉረምርሙ።*+ እነሆ፣ ፈራጁ ደጃፍ ላይ ቆሟል። 10 ወንድሞች፣ በይሖዋ* ስም የተናገሩትን ነቢያት+ መከራ በመቀበልና ትዕግሥት በማሳየት+ ረገድ አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው።+ 11 እነሆ፣ የጸኑትን ደስተኞች* እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን።+ ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤+ በውጤቱም ይሖዋ* ያደረገለትን አይታችኋል፤+ በዚህም ይሖዋ* እጅግ አፍቃሪና* መሐሪ እንደሆነ ተመልክታችኋል።+
12 ከሁሉም በላይ ወንድሞቼ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ወይም በሌላ መሐላ መማላችሁን ተዉ። ከዚህ ይልቅ “አዎ” ካላችሁ አዎ ይሁን፤ “አይደለም” ካላችሁ አይደለም ይሁን፤+ አለዚያ ለፍርድ ትዳረጋላችሁ።
13 ከእናንተ መካከል መከራ እየደረሰበት ያለ ሰው አለ? መጸለዩን ይቀጥል።+ ደስ የተሰኘ አለ? የምስጋና መዝሙር ይዘምር።+ 14 ከእናንተ መካከል የታመመ ሰው አለ? የጉባኤ ሽማግሌዎችን ወደ እሱ ይጥራ፤+ እነሱም በይሖዋ* ስም ዘይት ቀብተው+ ይጸልዩለት። 15 በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን* ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም* ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባላል።
16 ስለዚህ ፈውስ ማግኘት እንድትችሉ አንዳችሁ ለሌላው ኃጢአታችሁን በግልጽ ተናዘዙ፤+ እንዲሁም አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ። ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።+ 17 ኤልያስ እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር፤ ያም ሆኖ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ በጸለየ ጊዜ በምድሩ ላይ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናብ አልዘነበም።+ 18 ከዚያም እንደገና ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብ ሰጠ፤ ምድሩም ፍሬ አፈራ።+
19 ወንድሞቼ፣ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው ከእውነት መንገድ ስቶ ቢወጣና ሌላ ሰው ቢመልሰው፣ 20 ኃጢአተኛን ከስህተት ጎዳናው የሚመልስ ማንኛውም ሰው+ ኃጢአተኛውን* ከሞት እንደሚያድንና ብዙ ኃጢአትን እንደሚሸፍን እወቁ።+