እምነት እንድንታገሥና በጸሎት እንድንተጋ ያደርገናል
“ታገሡ፣ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።” —ያዕቆብ 5:8
1. በያዕቆብ 5:7, 8 ቃላት ላይ ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?
ከረጅም ዘመን ጀምሮ ሲጠበቅ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ “መገኘት” [NW] ዛሬ እውን ሆኗል። (ማቴዎስ 24:3-14) ዛሬ በአምላክና በክርስቶስ ላይ እምነት አለን የሚሉ ሁሉ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በተናገራቸው በሚከተሉት ቃላት ላይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጥብቀው ማሰባቸው ተገቢ ይሆናል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ፣ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፣ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና።”—ያዕቆብ 5:7, 8
2. ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈላቸው ሰዎች ከገጠሟቸው ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ ምን ነበሩ?
2 ያዕቆብ በመንፈስ አነሳሽነት መልእክቱን የጻፈላቸው ክርስቲያኖች ትዕግሥት ማሳየትና ለተለያዩ ችግሮች እልባት መስጠት አስፈልጓቸው ነበር። የብዙዎቹ አካሄድ በአምላክ ላይ እምነት አለን ከሚሉ ሰዎች የሚጠበቅ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል በአንዳንዶቹ ልብ ውስጥ አቆጥቁጠው የነበሩትን ምኞቶች በሚመለከት አንድ ነገር መደረግ ነበረበት። በእነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች መካከል ሰላም መልሶ እንዲሰፍን ማድረግ አስፈልጎ ነበር። ትዕግሥተኞችና በጸሎት ትጉዎች በመሆን ረገድም ምክር አስፈልጓቸዋል። ያዕቆብ ለእነርሱ የጻፈላቸውን ሐሳብ ስንመረምር የተናገራቸውን ነገሮች እኛ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንደምንችል እናስተውል።
መጥፎ ምኞቶች አጥፊ ናቸው
3. በጉባኤ ውስጥ ለብጥብጥ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምን ነበሩ? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
3 ክርስቲያን ነን ይሉ በነበሩት አንዳንዶች ዘንድ ሰላም ጠፍቶ የነበረ ሲሆን ለዚህም ዋነኛ መንሥኤዎቹ መጥፎ ምኞቶች ነበሩ። (ያዕቆብ 4:1-3) ጠበኝነት ሰላማቸውን እያደፈረሰ የነበረ ሲሆን አንዳንዶችም ፍቅር በጎደለው መንገድ በሌሎች ወንድሞቻቸው ላይ ይፈርዱ ነበር። ይህም በብልቶቻቸው ከሚዋጉ ዓለማዊ ምኞቶች የመነጨ ነው። እኛም የጉባኤውን ሰላም የሚያደፈርስ ምንም ነገር ላለማድረግ ስንል ክብርና ሥልጣን የመፈለግ እንዲሁም ቁሳዊ ንብረት የማካበት ሥጋዊ ምኞት እንዳይጠናወተን መከላከል እንችል ዘንድ እርዳታ ለማግኘት መጸለይ ያስፈልገን ይሆናል። (ሮሜ 7:21-25፤ 1 ጴጥሮስ 2:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በውስጣቸው ያደረው የመጎምጀት ባሕርይ የጥላቻና የነፍሰ ገዳይነት መንፈስ ወደማንጸባረቅ መርቷቸው ነበር። አምላክ መጥፎ ምኞቶቻቸውን ስለማይፈጽምላቸው ግባቸውን ለማሳካት ሲሉ ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸውን ገፍተውበት ነበር። እኛም ተመሳሳይ የሆኑ መጥፎ ምኞቶች ካሉን እንዲሳኩልን እንጠይቅ ይሆናል ይሁን እንጂ አናገኝም፤ ምክንያቱም ቅዱስ የሆነው አምላካችን እንዲህ ያሉትን ጸሎቶች አይሰማም።—ሰቆቃው ኤርምያስ 3:44፤ 3 ዮሐንስ 9, 10
4. ያዕቆብ አንዳንዶቹን “አመንዝሮች” ሲል የጠራቸው ለምን ነበር? ይህስ እኛን እንዴት ሊነካን ይገባል?
4 በአንዳንዶቹ የጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ ዓለማዊ መንፈስ፣ ቅናትና ኩራት ይታይ ነበር። (ያዕቆብ 4:4-6) ያዕቆብ አንዳንዶቹ ከዓለም ጋር በመወዳጀት መንፈሳዊ ምንዝር በመፈጸማቸው “አመንዝሮች” ሲል ጠርቷቸዋል። (ሕዝቅኤል 16:15-19, 25-45) በአስተሳሰባችን፣ በንግግራችንና በድርጊታችን ዓለማዊ መንፈስ እንዲንጸባረቅ እንደማንፈልግ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም ይህ የአምላክ ጠላቶች እንድንሆን ያደርገናል። ከቃሉ እንደምንረዳው “ቅናት” ኃጢአት በወረሱት የሰው ልጆች ውስጥ ከሚታየው መጥፎ ዝንባሌ ወይም “መንፈስ” አንዱ ነው። (ዘፍጥረት 8:21፤ ዘኁልቁ 16:1-3፤ መዝሙር 106:16, 17፤ መክብብ 4:4) እንደ ቅናትና ኩራት ያሉትን ወይም ሌላ ዓይነት መጥፎ ዝንባሌዎች መዋጋት እንደሚያስፈልገን ከተገነዘብን የአምላክን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ለማግኘት እንጣር። ይገባናል በማንለው የአምላክ ደግነት የምናገኘው ይህ ኃይል ‘ከቅናት ዘንባሌ’ ይበልጥ ብርቱ ነው። ይሖዋ ኩራተኞችን የሚቃወም ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ የኃጢአት ዝንባሌዎችን የምንዋጋ ከሆነ ይገባናል የማንለውን ደግነቱን ይሰጠናል።
5. ይገባናል የማንለውን የአምላክ ደግነት ለማግኘት የትኞቹን ብቃቶች ማሟላት ይኖርብናል?
5 ይገባናል የማንለውን የአምላክ ደግነት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ያዕቆብ 4:7-10) ይገባናል የማንለውን የይሖዋ ደግነት ለማግኘት እርሱን መታዘዝ፣ ዝግጅቶቹን መቀበል እንዲሁም እንደፈቃዱ ለሆነው ነገር ሁሉ ተገዥ መሆን ይኖርብናል። (ሮሜ 8:28) እንዲሁም ዲያብሎስን ‘መቃወም’ ወይም ‘መቃረን’ ይኖርብናል። የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በመደገፍ ጸንተን ከቆምን ‘ከእኛ ይሸሻል።’ የዓለምን የክፋት ወኪሎች የሚገታው ኢየሱስ ዘላቂ የሆነ ጉዳት የሚያስከትል ነገር እንዳይደርስብን ይረዳናል። ደግሞም በጸሎት፣ ታዛዥ በመሆንና በእምነት ወደ አምላክ እንደምንቀርብና እርሱም ወደ እኛ እንደሚቀርብ ፈጽሞ አትዘንጉ።—2 ዜና መዋዕል 15:2
6. ያዕቆብ አንዳንዶቹን ክርስቲያኖች “ኃጢአተኞች” ሲል የጠራቸው ለምንድን ነው?
6 ያዕቆብ በአምላክ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚናገሩትን አንዳንድ ሰዎች “ኃጢአተኞች” ሲል የጠራቸው ለምንድን ነው? ለክርስቲያኖች በማይገባ አስተሳሰብ ይኸውም ‘በጦርና’ በመረረ ጥላቻ ተጠምደው ስለነበር ነው። (ቲቶ 3:3) በመጥፎ ሥራ የተሞሉት ‘እጆቻቸው’ መንጻት ነበረባቸው። በተጨማሪም የውስጣዊ ግፊት መቀመጫ የሆነውን ‘ልባቸውን’ ማጥራት አስፈልጓቸው ነበር። (ማቴዎስ 15:18, 19) ‘ሁለት ሀሳብ ያላቸው’ አንዳንዶች የአምላክም፣ የዓለምም ወዳጅ ለመሆን በመፈለግ እያመነቱ ይዋልሉ ነበር። ከእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ በመማር እንዲህ ያሉ ነገሮች እምነታችንን እንዳያጠፉብን ዘወትር ንቁዎች እንሁን።—ሮሜ 7:18-20
7. ያዕቆብ አንዳንዶቹን ‘እንዲያዝኑና እንዲያለቅሱ’ የነገራቸው ለምንድን ነው?
7 ያዕቆብ አንባቢዎቹን “ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም” ብሏቸዋል። አምላካዊ በሆነ መንገድ ማዘናቸው ንስሐ እንደገቡ የሚያሳይ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 7:10, 11) ዛሬ አንዳንዶች እምነት አለን ቢሉም በሌላ በኩል ግን ከዓለም ጋር ለመወዳጀት ይጥራሉ። እንዲህ ዓይነት ጎዳና የምንከተል ከሆነ ደካማ ስለሆነው መንፈሳዊ ሁኔታችን ልናዝንና ሁኔታውን ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ ልንወስድ አይገባንምን? አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ የአምላክን ይቅርታ ካገኘን ንጹሕ ሕሊናና አስደሳች የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ስለሚኖረን በፊቱ ከፍ ከፍ እንደተደረግን ሆኖ ይሰማናል።—መዝሙር 51:10-17፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
አንዳችሁ በሌላው ላይ አትፍረዱ
8, 9. አንዳችን ሌላውን መንቀፍ ወይም በሌላው ላይ መፍረድ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
8 የእምነት ወንድማችንን መንቀፍ ኃጢአት ነው። (ያዕቆብ 4:11, 12) ይሁንና አንዳንዶች ራሳቸውን የማመጻደቅ ባሕርይ ስላላቸው ወይም ደግሞ ሌሎችን በማጣጣል ራሳቸውን ማዋደድ ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል፣ መሰል ክርስቲያኖችን ይተቻሉ። (መዝሙር 50:20፤ ምሳሌ 3:29) ‘መንቀፍ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥላቻን የሚያንጸባርቅ ሲሆን የተጋነነ ወይም የሐሰት ክስ መሰንዘርን ያመለክታል። ይህም በአንድ ወንድም ላይ የተጣመመ ፍርድ ከማስተላለፍ ተለይቶ አይታይም። ይህስ ‘የአምላክን ሕግ መተቸትና በሕጉ ላይ መፍረድ’ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ጻፎችና ፈሪሳውያን ‘የአምላክን ትእዛዝ በብልሃት ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው’ በራሳቸው የአቋም ደረጃዎች መሠረት ይፈርዱ ነበር። (ማርቆስ 7:1-13) በተመሳሳይም ይሖዋ የማይኮንነውን ወንድም እኛ የምንኮንነው ከሆነ ‘በአምላክ ሕግ ላይ መፍረዳችንና’ ሕጉ ብቁ አይደለም ማለታችን አይሆንምን? ወንድማችንን አግባብነት በሌለው መንገድ የምንተች ከሆነ የፍቅርን ሕግ ፈጽመናል ማለት አንችልም።—ሮሜ 13:8-10
9 አንድ ነገር እናስታውስ:- “ሕግን የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ነው፤” እርሱም ይሖዋ ነው። ‘ሕጉ ፍጹም ነው፤’ የሚጎድለውም ነገር የለም። (መዝሙር 19:7፤ ኢሳይያስ 33:22) ለመዳን የሚያበቁትን የአቋም ደረጃዎችና ሕጎች የመደንገግ መብት ያለው አምላክ ብቻ ነው። (ሉቃስ 12:5) በመሆኑም ያዕቆብ “በሌላው ግን የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” ሲል ጠይቋል። በሌሎች ላይ የመፍረድና ሌሎችን የመኮነን ሥልጣን የለንም። (ማቴዎስ 7:1-5፤ ሮሜ 14:4, 10) አምላክ የማያዳላና ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን፣ እኛ ደግሞ ኃጢአተኞች መሆናችንን ቆም ብለን ማሰባችን ራሳችንን በማመጻደቅ በሌሎች ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ሊረዳን ይገባል።
በኩራት ተገፋፍታችሁ በራሳችሁ ከመታመን ራቁ
10. በዕለታዊ ሕይወታችን ይሖዋን ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
10 በማንኛውም ጊዜ ይሖዋንና ሕጎቹን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። (ያዕቆብ 4:13-17) በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች አምላክን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን” ይላሉ። ‘ለራሳችን ገንዘብ ብናከማችና በአምላክ ዘንድ ግን ባለጠጋ ባንሆን’ ሕይወታችን ነገ ሊቀጭና ይሖዋን ማገልገል የምንችልበትን አጋጣሚ ልናጣ እንችላለን። (ሉቃስ 12:16-21) ያዕቆብ እንዳለው “ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ” የጠዋት እንፍዋለት ነን። (1 ዜና መዋዕል 29:15) ዘላቂ ደስታና የዘላለም ሕይወት እናገኛለን ብለን ተስፋ ማድረግ የምንችለው በይሖዋ በማመን ብቻ ነው።
11. “ይሖዋ ቢፈቅድ” ማለት ምን ማለት ነው?
11 በኩራት አምላክን ቸል ከማለት ይልቅ “ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” የሚል ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል። ‘ይሖዋ ቢፈቅድ’ ማለታችን ከእርሱ ፈቃድ ጋር ተስማምተን ለመሄድ እንደምንፈልግ የሚያሳይ ነው። ቤተሰባችንን ለመርዳት መነገድ፣ ለመንግሥቱ ሥራ ስንል ወደ ሌላ ቦታ መጓዝና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። ይሁን እንጂ መኩራራት አይገባንም። “እንዲህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው፤” ምክንያቱም በአምላክ እንዳንመካ ያደርገናል።—መዝሙር 37:5፤ ምሳሌ 21:4፤ ኤርምያስ 9:23, 24
12. በያዕቆብ 4:17 ላይ የሚገኙት ቃላት ትርጉም ምንድን ነው?
12 ያዕቆብ በራስ ስለ መመካትና ስለ ኩራት የተናገረውን ሐሳብ ለመቋጨት ይመስላል እንዲህ ብሏል:- “እንግዲህ በጎ ለማድረግ አውቆ ለማይሠራው ኃጢአት ነው።” እያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወቱ በአምላክ ላይ የተመካ መሆኑን በትሕትና አምኖ መቀበል ይኖርበታል። ይህን አለማድረጉ “ኃጢአት” ይሆንበታል። እርግጥ ነው፣ በአምላክ ላይ ያለን እምነት የሚጠይቅብንን ማንኛውንም ሌላ ነገር ሳናደርግም ብንቀር ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል።—ሉቃስ 12:47, 48
ባለጠጎችን አስመልክቶ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
13. ሀብታቸውን አላግባብ ስለሚጠቀሙበት ሰዎች ያዕቆብ ምን ብሏል?
13 አንዳንዶቹ የጥንት ክርስቲያኖች በፍቅረ ነዋይ ተጠምደው ስለነበር ወይም ባለጠጎችን ያሞካሹ ስለነበር ያዕቆብ አንዳንድ ባለጠጋ ሰዎችን አስመልክቶ ጠንከር ያለ ሐሳብ ሰጥቷል። (ያዕቆብ 5:1-6) ሃብታቸውን አላግባብ የሚጠቀሙ ዓለማዊ ሰዎች አምላክ የእጃቸውን በሚያስረክባቸው ጊዜ ‘በሚደርስባቸው ጭንቅ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ።’ በዚያ ዘመን የብዙዎቹ ሰዎች ሀብት በአብዛኛው ልብስ፣ እህልና ወይን ነበር። (ኢዩኤል 2:19፤ ማቴዎስ 11:8) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ነገሮች ሊበሰብሱ ወይም ‘ብል ሊበላቸው’ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ያዕቆብ ማጉላት የፈለገው ሀብት ሊበላሽ የሚችል ነገር መሆኑን ሳይሆን ከንቱ መሆኑን ነው። ወርቅና ብር ባይዝጉም እነዚህን ነገሮች የምናከማች ከሆነ እንደ ዛገ ነገር ዋጋ ቢስ ይሆናሉ። ‘ዝገት’ አንድ ቁሳዊ ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ አለመዋሉን የሚጠቁም ነገር ነው። እንግዲያውስ በቁሳዊ ንብረታቸው የሚታመኑ ሰዎች የአምላክ ቁጣ በእነርሱ ላይ ለሚወርድበት ‘ለኋለኛው ቀን’ “እንደ እሳት” ያለ ነገር እያከማቹ መሆናቸውን ሁላችንም ልንዘነጋው አይገባም። ዛሬ የምንኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ በመሆኑ እንዲህ ያሉት ቃላት ለእኛ ልዩ ትርጉም አላቸው።—ዳንኤል 12:4፤ ሮሜ 2:5
14. ብዙውን ጊዜ ባለጠጎች ምን ያደርጋሉ? እኛስ ይህንን በሚመለከት ምን ማድረግ ይገባናል?
14 ባለጠጋዎቹ ብዙውን ጊዜ የእርሻቸውን አጫጆች ያጭበረብሯቸዋል፤ እነዚህ ሠራተኞች የተከለከሉት ደመወዝ ለበቀል “ይጮኻል።” (ከዘፍጥረት 4:9, 10 ጋር አወዳድር።) ባለጠጋ የሆኑ ዓለማዊ ሰዎች ‘ተቀማጥለው’ ኖረዋል። ሥጋዊ ምኞታቸውን ለማርካት በመሯሯጥ ስብ የሸፈነው ደንዳና ልብ አፍርተዋል፤ ለእርድ በሚዘጋጁበት ‘ቀንም’ ቢሆን እንዲህ ከማድረግ አይመለሱም። ‘ጻድቁን ይኮንናሉ ይገድሉማል።’ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “እርሱ እናንተን የሚቃወም አይደለምን?” [NW] ይሁን እንጂ በሌላ አባባል “ጻድቁ አይቃወማችሁም” ማለት ነው። በዚህም ሆነ በዚያ ለባለጠጎች የምናደላ መሆን አይገባንም። በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባናል።—ማቴዎስ 6:25-33
እምነት እንድንታገሥ ይረዳናል
15, 16. ትዕግሥተኛ መሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ያዕቆብ ጨቋኝ ስለሆኑ በዓለም ያሉ ባለጠጋ ሰዎች ከገለጸ በኋላ ጭቆና የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች እንዲታገሡ አበረታቷል። (ያዕቆብ 5:7, 8) አማኞች የሚደርስባቸውን መከራ በትዕግሥት ቢቋቋሙ ኢየሱስ በሥልጣኑ ተገኝቶ በሚጨቁኗቸው ሰዎች ላይ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው ወሮታውን ያገኛሉ። (ማቴዎስ 24:37-41) እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ዘሩን ለመዝራት የበልግ መባቻ ዝናብ እንዲሁም ፍሬ ለማግኘት የሚረዳውን የመከር ማብቂያ ዝናብ በትዕግሥት እንደሚጠባበቅ ገበሬ መሆን አስፈልጓቸው ነበር። (ኢዩኤል 2:23) በተለይ በአሁኑ ጊዜ ‘ጌታ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በሥልጣኑ ላይ የተገኘ በመሆኑ’ መታገሥና ልባችንን ማጽናት ያስፈልገናል!
16 መታገሥ የሚገባን ለምንድን ነው? (ያዕቆብ 5:9-12) ትዕግሥት የእምነት ወንድሞቻችን ቢያበሳጩን ከልክ በላይ እንዳናዝን ወይም እንዳንተክዝ ይረዳናል። በውስጣችን መጥፎ ስሜት በመያዝ “አንዳችን በሌላው የምናዝን ከሆነ” [NW] በፈራጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንኮነናለን። (ዮሐንስ 5:22) የክርስቶስ ‘መገኘት’ በመጀመሩ ምክንያት “በደጅ ፊት ቆሟል” ለማለት በሚቻልበት በዛሬው ጊዜ ብዙ የእምነት ፈተናዎች የሚገጥሟቸውን ወንድሞቻችን በመታገሥ በመካከላችን ሰላም እንፍጠር። ኢዮብ ፈተናዎች ሲደርሱበት በትዕግሥት በመጽናቱ ምክንያት አምላክ ወሮታውን እንደከፈለው ስናስታውስ የእኛም እምነት ይጠነክራል። (ኢዮብ 42:10-17) እምነትና ትዕግሥት ካለን ‘ይሖዋ እጅግ የሚምር የሚራራም’ እንደሆነ መመልከት እንችላለን።—ሚክያስ 7:18, 19
17. ያዕቆብ “አትማሉ” ያለው ለምንድን ነው?
17 ትዕግሥት ከሌለን ውጥረት ውስጥ በምንገባበት ጊዜ አንደበታችንን አላግባብ ልንጠቀምበት እንችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በነገሩ ብዙም ሳናስብበት መሐላ እንፈጽም ይሆናል። ያዕቆብ ያልታሰበበት ቃለ መሐላ እንዳናደርግ ሲያስጠነቅቅ “አትማሉ” ብሏል። ሁልጊዜ የተናገሩትን ነገር በመሐላ ማረጋገጥም ግብዝነት ይመስላል። በመሆኑም፣ ቃላችን አዎን፣ አዎን ወይም ደግሞ አይደለም፣ አይደለም እንዲሆን በማድረግ እውነቱን ብቻ መናገር ይገባናል። (ማቴዎስ 5:33-37) እርግጥ ያዕቆብ በፍርድ ቤት እውነቱን ለመናገር ቃለ መሐላ መፈጸም ስህተት ነው ማለቱ አይደለም።
እምነትና ጸሎቶቻችን
18. ‘መጸለይና’ ‘መዝሙራትን መዘመር’ የሚገባን በምን ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ነው?
18 ንግግራችንን ለመቆጣጠር፣ ታጋሾች ለመሆንና በአምላክ ላይ ያለንን ጤናማ እምነት ጠብቀን ለመቆየት ከፈለግን ጸሎት በሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ሚና ሊጫወት ይገባል። (ያዕቆብ 5:13-20) በተለይ ፈተና በሚደርስብን ጊዜ ‘ልንጸልይ’ ይገባናል። ደስ ሲለን ደግሞ ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ባቋቋመበት ጊዜ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ እንዳደረጉት ‘መዝሙራትን እንዘምር።’ (ማርቆስ 14:26 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) አንዳንድ ጊዜ ለአምላክ ባለን የአመስጋኝነት ስሜት ተሞልተን በልባችን የውዳሴ መዝሙር የምናሰማበት ጊዜ ይኖራል። (1 ቆሮንቶስ 14:15፤ ኤፌሶን 5:19) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ ይሖዋን በመዝሙር ማወደስ እንዴት የሚያስደስት ነው!
19. በመንፈሳዊ ከታመምን ምን ማድረግ ይገባናል? እንዲህ የምናደርገውስ ለምንድን ነው?
19 አንድ ዓይነት መጥፎ አድራጎት በመፈጸማችን ወይም ደግሞ ከይሖዋ ማዕድ አዘውትረን ሳንመገብ በመቅረታችን ምክንያት በመንፈሳዊ ከታመምን የመዘመር ውስጣዊ ስሜቱ አይኖረን ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምንገኝ ከሆነ ‘እንዲጸልዩልን’ ሽማግሌዎችን በትሕትና ወደ እኛ እንጥራ። (ምሳሌ 15:29) ከዚህም ሌላ ‘በይሖዋ ስም ዘይት ይቀቡናል።’ በቁስል ላይ እንደሚደረግ እረፍት የሚሰጥ ዘይት የሚያጽናኑት ቃሎቻቸውና ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክራቸው የመንፈስ ጭንቀትን፣ ጥርጣሬንና ፍርሃትን ለማሸነፍ ይረዳሉ። የእኛ እምነት ከታከለበት ‘የእምነት ጸሎት ድውዩን ያድናል።’ ሽማግሌዎቹ በመንፈሳዊ የታመምነው አንድ ከባድ ኃጢአት በመፈጸማችን ምክንያት መሆኑን ከተረዱ በደግነት ኃጢአታችን ምን እንደሆነ ግልጽ አድርገው በማስረዳት ሊረዱን ይሞክራሉ። (መዝሙር 141:5) ንስሐ የምንገባ ከሆነ አምላክ የእነርሱን ጸሎት ሰምቶ ይቅር እንደሚለን እምነት ሊኖረን ይችላል።
20. ኃጢአታችንን እርስ በርሳችን የምንናዘዘውና አንዳችን ለሌላው የምንጸልየው ለምንድን ነው?
20 ‘እርስ በእርስ ኃጢአትን በግልጽ መናዘዝ’ ተጨማሪ ኃጢአት ከመፈጸም ሊገታን ይገባል። አንዳችን ለሌላው ርኅራኄ እንድናሳይ የሚያበረታታ መሆን ይኖርበታል፤ ይህም ‘አንዳችን ስለ ሌላው እንድንጸልይ’ ያነሳሳናል። ይህን ማድረጋችን ጠቃሚ እንደሚሆን እምነት ሊኖረን ይችላል፤ ምክንያቱም ‘ጻድቅ ሰው’ ማለትም እምነት ያለውና በአምላክ ፊት ቅን የሆነ ሰው የሚያቀርበው ጸሎት በይሖዋ ፊት ብዙ ነገር ያከናውናል። (1 ጴጥሮስ 3:12) ነቢዩ ኤልያስ እንደኛው ድክመት የነበረበት ሰው ቢሆንም ጸሎቱ ውጤታማ ነበር። እርሱ በመጸለዩ ምክንያት ለሦስት ዓመት ተኩል ያክል ዝናብ ሳይዘንብ ቀርቷል። እንደገና በጸለየ ጊዜ ደግሞ ዝናብ መዝነብ ጀምሯል።—1 ነገሥት 17:1፤ 18:1, 42-45፤ ሉቃስ 4:25
21. አንድ ክርስቲያን ‘ከእውነት ቢስት’ ምን ማድረግ እንችል ይሆናል?
21 አንድ የጉባኤው አባል ከትክክለኛው ትምህርትና አኗኗር በመውጣት ‘ከእውነት ቢስትስ?’ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር፣ በጸሎትና በሌሎች እርዳታዎች አማካኝነት ከስህተቱ ልንመልሰው እንችል ይሆናል። በዚህ መንገድ ለመርዳት ከተሳካልን በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጥላ ሥር ገብቶ ከመንፈሳዊ ሞትና ከጥፋት ፍርድ ይድናል። አንድን የተሳሳተ ሰው በመርዳት የኃጢአቱን ብዛት እንሸፍንለታለን። ተግሳጽ የተሰጠው ኃጢአተኛ ከኃጢአት ጎዳናው ሲመለስ፣ ንስሐ ሲገባና ይቅርታ ለማግኘት ሲጥር የእርሱን ኃጢአት ለመሸፈን ባደረግነው ጥረት እንደሰታለን።—መዝሙር 32:1, 2፤ ይሁዳ 22, 23
ለሁላችንም የሚሆን ትምህርት
22, 23. የያዕቆብ ቃላት እኛን እንዴት ሊነኩን ይገባል?
22 የያዕቆብ መልእክት ለሁላችንም የሚጠቅም ነገር እንደያዘ ግልጽ ነው። ፈተናዎችን እንዴት መወጣት እንደምንችል ይገልጽልናል፣ አድሏዊ እንዳንሆን ይመክረናል፣ በመልካም ሥራዎችም እንድንካፈል አጥብቆ ያሳስበናል። ያዕቆብ አንደበታችንን እንድንቆጣጠር፣ የዓለምን ተጽዕኖ እንድንቋቋምና ሰላምን እንድንከተል አጥብቆ ያሳስበናል። እንዲሁም የተናገረው ነገር ትዕግሥተኞች እንድንሆንና በጸሎት እንድንተጋ ይረዳናል።
23 የያዕቆብ መልእክት በመጀመሪያ የተላከው ለጥንቶቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደነበር አይካድም። ይሁንና ሁላችንም፣ ምክሩ እምነታችንን አጥብቀን ለመያዝ እንዲረዳን ልንፈቅድለት ይገባል። የያዕቆብ ቃላት በአምላክ አገልግሎት ቁርጥ ያለ እርምጃ እንድንወስድ የሚያንቀሳቅስ እምነት እንድናዳብር ኃይል ይሰጡናል። በተጨማሪም ይህ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መልእክት ታጋሾች እንዲሁም ‘ጌታ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በሥልጣኑ ላይ በተገኘበት’ በዛሬው ጊዜ በጸሎት የምንተጋ የይሖዋ ምሥክሮች እንድንሆን የሚያስችል ዘላቂ የሆነ እምነት ይገነባልናል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አንዳንዶቹ የጥንት ክርስቲያኖች አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን መለወጥ ያስፈለጋቸው ለምን ነበር?
◻ ያዕቆብ ለባለጠጋ ሰዎች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
◻ ትዕግሥተኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ዘወትር መጸለይ የሚገባን ለምንድን ነው?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች ከእምነት ወንድሞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ይበልጥ ታጋሾች መሆን አስፈልጓቸው ነበር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ትዕግሥተኞች፣ አፍቃሪዎችና በጸሎት የሚተጉ መሆን ይኖርባቸዋል