የማቴዎስ ወንጌል
7 “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤*+ 2 በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤+ በምትሰፍሩበት መስፈሪያም ይሰፍሩላችኋል።+ 3 ታዲያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ ትተህ በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ?+ 4 ወይም በራስህ ዓይን ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን ‘ዓይንህ ውስጥ ያለውን ጉድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? 5 አንተ ግብዝ! መጀመሪያ በራስህ ዓይን ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ማየት ትችላለህ።
6 “ቅዱስ የሆነውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በአሳማ ፊት አትጣሉ።+ አለዚያ ዕንቁዎቹን በእግራቸው ይረጋግጧቸዋል፤ ተመልሰውም ይጎዷችኋል።
7 “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤+ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።+ 8 የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤+ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል። 9 ደግሞስ ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው አለ? 10 ወይስ ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋል? 11 ታዲያ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት+ መልካም ነገር እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!+
12 “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።+ ሕጉም ሆነ የነቢያት ቃል የሚሉት ይህንኑ ነው።+
13 “በጠባቡ በር ግቡ፤+ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው፤ 14 ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ግን ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።+
15 “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች+ ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው+ ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።+ 16 ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?+ 17 በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል።+ 18 ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፤ የበሰበሰም ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም።+ 19 መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ ወደ እሳት ይጣላል።+ 20 በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።+
21 “‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገባው በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ብቻ ነው።+ 22 በዚያ ቀን ብዙዎች እንዲህ ይሉኛል፦ ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣+ በስምህ ትንቢት አልተናገርንም? በስምህ አጋንንትን አላወጣንም? በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንም?’+ 23 እኔም በዚያ ጊዜ ‘ቀድሞውንም አላውቃችሁም! እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ!’ እላቸዋለሁ።+
24 “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራን አስተዋይ ሰው ይመስላል።+ 25 ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤ ሆኖም ቤቱ በዓለት ላይ ስለተመሠረተ አልተደረመሰም። 26 ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውል ሁሉ ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል።+ 27 ዶፍ ወረደ፤ ጎርፍ ጎረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ቤቱንም በኃይል መታው፤+ ቤቱም ተደረመሰ፤ እንዳልነበረም ሆነ።”
28 ኢየሱስ ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ፤+ 29 የሚያስተምራቸው እንደ እነሱ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ነበርና።+