የሉቃስ ወንጌል
1 ብዙዎች እኛ ሙሉ እምነት የጣልንባቸውን መረጃዎች ለማጠናቀር የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል፤+ 2 ደግሞም ከመጀመሪያው አንስቶ የዓይን ምሥክሮች የነበሩ ሰዎችና+ መልእክቱን የሚያውጁ አገልጋዮች+ እነዚህን መረጃዎች ለእኛ አስተላልፈዋል። 3 ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፣+ እኔም በበኩሌ ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ ስለመረመርኩ ታሪኩን በቅደም ተከተል ልጽፍልህ ወሰንኩ። 4 ይህን ያደረግኩት በቃል የተማርካቸው ነገሮች እርግጠኛ መሆናቸውን በሚገባ እንድታውቅ ነው።+
5 በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ* ዘመን፣+ በአቢያህ+ የክህነት ምድብ ውስጥ የሚያገለግል ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበር። ሚስቱ የአሮን ዘር ስትሆን ስሟም ኤልሳቤጥ ነበር። 6 ሁለቱም በአምላክ ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ የይሖዋን* ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ እየጠበቁ ያለነቀፋ ይኖሩ ነበር። 7 ይሁን እንጂ ኤልሳቤጥ መሃን በመሆኗ ልጅ አልነበራቸውም፤ እንዲሁም ሁለቱም በዕድሜ የገፉ ነበሩ።
8 አንድ ቀን ዘካርያስ እሱ ያለበት ምድብ+ ተራው ደርሶ በአምላክ ፊት በክህነት እያገለገለ ሳለ 9 በክህነት ሥርዓቱ* መሠረት ወደ ይሖዋ* ቤተ መቅደስ+ ገብቶ ዕጣን+ የሚያጥንበት ተራ ደረሰው። 10 ዕጣን በሚቀርብበትም ሰዓት ሕዝቡ ሁሉ በውጭ ሆነው ይጸልዩ ነበር። 11 የይሖዋም* መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። 12 ዘካርያስም መልአኩን ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሃትም ተዋጠ። 13 መልአኩ ግን እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ፣ አትፍራ፤ ምክንያቱም አምላክ ያቀረብከውን ምልጃ ሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።+ 14 አንተም ደስ ይልሃል፤ ሐሴትም ታደርጋለህ፤ ብዙዎችም በእሱ መወለድ ደስ ይላቸዋል፤+ 15 በይሖዋ* ፊት ታላቅ ይሆናልና።+ ይሁንና የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ ፈጽሞ መጠጣት የለበትም፤+ ከመወለዱ በፊት እንኳ* በመንፈስ ቅዱስ ይሞላል፤+ 16 ከእስራኤል ልጆች መካከልም ብዙዎቹን ወደ አምላካቸው ወደ ይሖዋ* ይመልሳል።+ 17 በተጨማሪም ሰዎችን ለይሖዋ * ያዘጋጅ ዘንድ የአባቶችን ልብ እንደ ልጆች ልብ ለማድረግ፣*+ የማይታዘዙትንም ሰዎች ወደ ጻድቃን ጥበብ ለመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል+ በአምላክ ፊት ይሄዳል።”+
18 ዘካርያስ መልአኩን “ይህ እንደሚሆን እንዴት እርግጠኛ መሆን እችላለሁ? እኔ እንደሆነ አርጅቻለሁ፤ ሚስቴም ዕድሜዋ ገፍቷል” አለው። 19 መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፦ “እኔ በአምላክ አጠገብ በፊቱ የምቆመው+ ገብርኤል+ ነኝ፤ አንተን እንዳነጋግርህና ይህን ምሥራች እንዳበስርህ ተልኬአለሁ። 20 ሆኖም የተወሰነለትን ጊዜ ጠብቆ የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንክ ይህ ነገር እስኪፈጸም ድረስ ዱዳ ትሆናለህ! መናገርም አትችልም።” 21 ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕዝቡ ዘካርያስን በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፤ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ብዙ በመቆየቱም ግራ ተጋቡ። 22 በወጣ ጊዜም ሊያናግራቸው አልቻለም፤ እነሱም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አንድ ራእይ እንዳየ ተገነዘቡ። ከዚያ በኋላ ዱዳ ስለሆነ በምልክት ብቻ ያናግራቸው ነበር። 23 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ቅዱስ አገልግሎት* የሚያቀርብባቸው ቀናት ሲያበቁ ወደ ቤቱ ሄደ።
24 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ፀነሰች፤ ለአምስት ወርም ከቤት ሳትወጣ ቆየች፤ እንዲህም አለች፦ 25 “ይሖዋ* በዚህ ወቅት ይህን አደረገልኝ። በሰዎች መካከል ይደርስብኝ የነበረውን ነቀፋ ለማስወገድ ፊቱን ወደ እኔ መለሰ።”+
26 ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛ ወሯ አምላክ መልአኩ ገብርኤልን+ በገሊላ ወደምትገኝ ናዝሬት ወደተባለች ከተማ ላከው፤ 27 የተላከውም ከዳዊት ቤት ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች አንዲት ድንግል+ ሲሆን የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበር።+ 28 መልአኩም ገብቶ “እጅግ የተባረክሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ* ከአንቺ ጋር ነው” አላት። 29 እሷ ግን በንግግሩ በጣም ደንግጣ ይህ ሰላምታ ምን ትርጉም እንዳለው ለመረዳት በውስጧ ታስብ ጀመር። 30 ስለዚህ መልአኩ እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ፣ በአምላክ ፊት ሞገስ ስላገኘሽ አትፍሪ። 31 እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤+ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።+ 32 እሱም ታላቅ ይሆናል፤+ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል፤+ ይሖዋ* አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤+ 33 በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”+
34 ማርያም ግን መልአኩን “እኔ ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽሜ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለችው።+ 35 መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤+ የልዑሉም ኃይል በአንቺ ላይ ያርፋል። ስለሆነም የሚወለደው ልጅ ቅዱስና+ የአምላክ ልጅ+ ይባላል። 36 እነሆ፣ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፤ መሃን ትባል የነበረ ቢሆንም ይኸው ስድስተኛ ወሯን ይዛለች፤ 37 አምላክ የተናገረው ቃል ሳይፈጸም አይቀርምና።”*+ 38 በዚህ ጊዜ ማርያም “እነሆ፣ እኔ የይሖዋ* ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። ከዚያም መልአኩ ተለይቷት ሄደ።
39 ማርያምም በዚያው ሰሞን ተነስታ በተራራማው አገር ወደምትገኝ አንዲት የይሁዳ ከተማ በፍጥነት ሄደች፤ 40 ወደ ዘካርያስ ቤት ገብታም ኤልሳቤጥን ሰላም አለቻት። 41 ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ በማህፀኗ ውስጥ ያለው ፅንስ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች፤ 42 ድምፅዋንም ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች፦ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማህፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው! 43 የጌታዬ እናት ወደ እኔ መምጣቷ ለእኔ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው! 44 እነሆ፣ የሰላምታሽን ድምፅ እንደሰማሁ በማህፀኔ ያለው ፅንስ በደስታ ዘሏልና። 45 ይሖዋ* የነገራት ነገር ሙሉ በሙሉ የሚፈጸም በመሆኑ ይህን ያመነች ደስተኛ ነች።”
46 ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ይሖዋን* ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤*+ 47 መንፈሴም አዳኜ በሆነው አምላክ እጅግ ደስ ይሰኛል፤+ 48 ምክንያቱም የባሪያውን መዋረድ* ተመልክቷል።+ እነሆ፣ ከአሁን ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ደስተኛ ይሉኛል፤+ 49 ምክንያቱም ኃያል የሆነው አምላክ ታላላቅ ነገሮች አድርጎልኛል፤ ስሙም ቅዱስ ነው፤+ 50 ምሕረቱም በሚፈሩት ሁሉ ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።+ 51 በክንዱም ታላላቅ ሥራዎች አከናውኗል፤ በልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋል።+ 52 ኃያላን ሰዎችን ከዙፋናቸው አውርዷል፤+ ዝቅ ያሉትንም ከፍ አድርጓል፤+ 53 የተራቡትን በመልካም ነገሮች አጥግቧል፤+ ሀብታሞችንም ባዶ እጃቸውን ሰዷቸዋል። 54 ምሕረቱን በማስታወስ አገልጋዩን እስራኤልን ረድቷል፤+ 55 ይህን ያደረገው ለአባቶቻችን በገባው ቃል መሠረት ለአብርሃምና ለዘሩ+ ለዘላለም ምሕረት ለማሳየት ነው።” 56 ማርያምም ከኤልሳቤጥ ጋር ሦስት ወር ያህል ከቆየች በኋላ ወደ ቤቷ ተመለሰች።
57 ኤልሳቤጥ የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰና ወንድ ልጅ ወለደች። 58 ጎረቤቶቿና ዘመዶቿም ይሖዋ* ታላቅ ምሕረት እንዳደረገላት ሰምተው የደስታዋ ተካፋዮች ሆኑ።+ 59 በስምንተኛው ቀን ሕፃኑን ሊገርዙት መጡ፤+ በአባቱም ስም ዘካርያስ ብለው ሊጠሩት ፈልገው ነበር። 60 እናትየው ግን መልሳ “አይሆንም! ዮሐንስ ይባል” አለች። 61 በዚህ ጊዜ “ከዘመዶችሽ መካከል በዚህ ስም የተጠራ ማንም የለም” አሏት። 62 ከዚያም አባቱን ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ በምልክት ጠየቁት። 63 እሱም የእንጨት ጽላት እንዲያመጡለት ጠየቀና “ስሙ ዮሐንስ ነው” ብሎ ጻፈ።+ በዚህ ጊዜ ሁሉም ተደነቁ። 64 ወዲያውም አፉ ተከፈተ፤ ምላሱም ተፈቶ መናገር ጀመረ፤+ አምላክንም አወደሰ። 65 ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በፍርሃት ተዋጡ፤ የሆነውም ነገር ሁሉ በተራራማው የይሁዳ አገር በሙሉ ይወራ ጀመር። 66 ይህን የሰሙም ሁሉ “የዚህ ሕፃን መጨረሻ ምን ይሆን?” በማለት ነገሩን በልባቸው ያዙ። የይሖዋ* እጅ ከእሱ ጋር እንደሆነ በግልጽ ይታይ ነበርና።
67 ከዚያም አባቱ ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፦ 68 “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ* ፊቱን ወደ ሕዝቡ ስለመለሰና ሕዝቡን ስላዳነ+ ውዳሴ ይድረሰው።+ 69 ደግሞም በአገልጋዩ በዳዊት ቤት+ የመዳን ቀንድ* አስነስቶልናል፤+ 70 ይህም ከጥንት ዘመን ጀምሮ በነበሩት ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ በተናገረው መሠረት ነው።+ 71 ከባላጋራዎቻችንና ከሚጠሉን ሰዎች ሁሉ እጅ እንደሚያድነን ቃል ገብቷል።+ 72 ለአባቶቻችን በሰጠው ተስፋ መሠረት ምሕረት ያሳየናል፤ ቅዱስ ቃል ኪዳኑንም ያስታውሳል።+ 73 ይህም ቃል ኪዳን ለአባታችን ለአብርሃም የማለው መሐላ ነው፤+ 74 በመሐላው መሠረትም ከጠላቶቻችን እጅ ነፃ ካወጣን በኋላ ለእሱ ያለፍርሃት ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ይሰጠናል፤ 75 ይህም ታማኝ እንድንሆንና በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ጽድቅ የሆነውን ነገር እንድናደርግ ነው። 76 ደግሞም አንተ ሕፃን፣ መንገዱን ለማዘጋጀት ቀድመህ በይሖዋ* ፊት ስለምትሄድ የልዑሉ ነቢይ ትባላለህ፤+ 77 ለሕዝቡም ኃጢአታቸው ይቅር ተብሎላቸው መዳን እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን እውቀት ትሰጣቸዋለህ፤+ 78 ይህም የሆነው አምላካችን ከአንጀት ስለራራልን ነው። ከዚህ ርኅራኄም የተነሳ እንደ ንጋት ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ከላይ ይወጣልናል፤ 79 ይኸውም በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ+ ለተቀመጡት ብርሃን ለመስጠት እንዲሁም እግሮቻችንን በሰላም መንገድ ለመምራት ነው።”
80 ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤልም በይፋ እስከታየበት ቀን ድረስ በበረሃ ኖረ።