ሕዝቅኤል
37 የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ነበረች፤ ይሖዋም በመንፈሱ ወሰደኝ፤ በሸለቋማው ሜዳ መካከልም አኖረኝ፤+ ስፍራውም በአጥንቶች ተሞልቶ ነበር። 2 እሱም በዙሪያቸው እንዳልፍ አደረገኝ፤ በሸለቋማው ሜዳ ላይ በጣም ብዙ አጥንቶች ወድቀው አየሁ፤ አጥንቶቹም በጣም ደርቀው ነበር።+ 3 እሱም “የሰው ልጅ ሆይ፣ እነዚህ አጥንቶች ሕያው ሊሆኑ ይችላሉ?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ የምታውቀው አንተ ነህ” አልኩ።+ 4 እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ስለ እነዚህ አጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘እናንተ ደረቅ አጥንቶች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ፦
5 “‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ “እስትንፋስ እንዲገባባችሁ አደርጋለሁ፤ እናንተም ሕያው ትሆናላችሁ።+ 6 ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋም አለብሳችኋለሁ፤ በቆዳም እሸፍናችኋለሁ፤ እስትንፋስም አስገባባችኋለሁ፤ እናንተም ሕያው ትሆናላችሁ፤ እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።”’”
7 ከዚያም በታዘዝኩት መሠረት ትንቢት ተናገርኩ። ትንቢቱን እንደተናገርኩ የሚንኮሻኮሽ ድምፅ ተሰማ፤ አጥንቶቹም እርስ በርስ መገጣጠም ጀመሩ። 8 ከዚያም አጥንቶቹ ጅማትና ሥጋ ሲለብሱ አየሁ፤ በቆዳም ተሸፈኑ። ሆኖም በውስጣቸው ገና እስትንፋስ አልነበረም።
9 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ለነፋሱ ትንቢት ተናገር። የሰው ልጅ ሆይ፣ ትንቢት ተናገር፤ ነፋሱንም እንዲህ በለው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ነፋስ* ሆይ፣ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ ሕያው እንዲሆኑም በእነዚህ በተገደሉት ሰዎች ላይ ንፈስ።”’”
10 ስለዚህ ባዘዘኝ መሠረት ትንቢት ተናገርኩ፤ እስትንፋስም* ገባባቸው፤ እነሱም ሕያው ሆነው በእግራቸው ቆሙ፤+ እጅግ ታላቅ ሠራዊትም ሆኑ።
11 ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ፣ እነዚህ አጥንቶች መላው የእስራኤል ቤት ናቸው።+ እነሱ ‘አጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋችንም ጨልሟል።+ ከሌሎች ጋር ሙሉ በሙሉ ተቆራርጠናል’ ይላሉ። 12 ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ መቃብሮቻችሁን እከፍታለሁ፤+ ከመቃብሮቻችሁም ውስጥ አስነሳችኋለሁ፤ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣችኋለሁ።+ 13 ሕዝቤ ሆይ፣ መቃብሮቻችሁን ስከፍትና ከመቃብሮቻችሁ ውስጥ ሳስነሳችሁ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።”’+ 14 ‘መንፈሴን በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ እናንተም ሕያው ትሆናላችሁ፤+ በምድራችሁም ላይ አሰፍራችኋለሁ፤ እናንተም እኔ ይሖዋ ራሴ እንደተናገርኩና ይህን እንዳደረግኩ ታውቃላችሁ’ ይላል ይሖዋ።”
15 የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 16 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፣ በትር ወስደህ ‘ለይሁዳና ከእሱ ጋር ላሉት* የእስራኤል ሰዎች’+ ብለህ ጻፍበት። ከዚያም ሌላ በትር ወስደህ ‘ለዮሴፍ ይኸውም ኤፍሬምን ለሚወክለው በትርና ከእሱ ጋር ላሉት* የእስራኤል ቤት ሰዎች ሁሉ’+ ብለህ ጻፍበት። 17 ከዚያም በእጅህ ውስጥ አንድ በትር ይሆኑ ዘንድ ሁለቱንም አንድ ላይ ያዛቸው።+ 18 ወገኖችህ* ‘የእነዚህ ነገሮች ትርጉም ምን እንደሆነ አትነግረንም?’ ብለው ሲጠይቁህ፣ 19 እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በኤፍሬም እጅ ውስጥ ያለውን የዮሴፍንና ከእሱ ጋር ያሉትን የእስራኤልን ነገዶች በትር ወስጄ ከይሁዳ በትር ጋር አያይዘዋለሁ፤ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፤+ እነሱም በእጄ ላይ አንድ በትር ይሆናሉ።”’ 20 የጻፍክባቸውን በትሮች ማየት እንዲችሉ በእጅህ ያዝ።
21 “ከዚያም እንዲህ በላቸው፦ ‘ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያንን ከሄዱባቸው ብሔራት መካከል አመጣቸዋለሁ፤ ከየአቅጣጫውም ሰብስቤ ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።+ 22 በምድሪቱ፣ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ብሔር አደርጋቸዋለሁ፤+ በሁሉም ላይ አንድ ንጉሥ ይገዛል፤+ ከእንግዲህ ሁለት ብሔራት አይሆኑም፤ ደግሞም ተከፍለው ሁለት መንግሥታት አይሆኑም።+ 23 ከእንግዲህ ወዲህ አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻቸው፣* ጸያፍ በሆኑት ልማዶቻቸውና በሚፈጽሟቸው በደሎች ሁሉ ራሳቸውን አያረክሱም።+ ታማኝነት በማጉደል ከሠሩት ኃጢአት ሁሉ እታደጋቸዋለሁ፤ ደግሞም አነጻቸዋለሁ። እነሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔ ራሴም አምላካቸው እሆናለሁ።+
24 “‘“አገልጋዬ ዳዊት ንጉሣቸው ይሆናል፤+ ሁሉም አንድ እረኛ ይኖራቸዋል።+ ድንጋጌዎቼን አክብረው ይመላለሳሉ፤ ደንቦቼንም በጥንቃቄ ይጠብቃሉ።+ 25 አባቶቻችሁ በኖሩባት፣ ለአገልጋዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይቀመጣሉ፤+ እነሱና ልጆቻቸው* እንዲሁም የልጅ ልጆቻቸው በእሷ ላይ ለዘላለም ይኖራሉ፤+ አገልጋዬም ዳዊት ለዘላለም አለቃቸው* ይሆናል።+
26 “‘“ከእነሱም ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤+ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ዘላለማዊ ይሆናል። እነሱንም አጸናቸዋለሁ፤ አበዛቸዋለሁ+ እንዲሁም መቅደሴን በመካከላቸው ለዘላለም አኖራለሁ። 27 ድንኳኔ* ከእነሱ ጋር* ይሆናል፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።+ 28 መቅደሴም ለዘላለም በመካከላቸው በሚሆንበት ጊዜ፣ ብሔራት እስራኤልን የቀደስኩት እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።”’”+