ኢዮብ ጸንቷል፤ እኛም መጽናት እንችላለን!
“እነሆ፣ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] እንላቸዋለን።”—ያዕቆብ 5:11
1. አንድ በዕድሜ የገፋ ክርስቲያን በእርሱ ላይ ይደርሱ ስለነበሩ ፈተናዎች ምን ብሏል?
‘ዲያብሎስ እግር በእግር እየተከታተለኝ ነው! ልክ ኢዮብ የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማኛል!’ ኤ ኤች ማክሚላን በእነዚህ ቃላት በመጠቀም የሚሰማውን ስሜት በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለሚገኘው የቅርብ ጓደኛው ገልጾለታል። ወንድም ማክሚላን ምድራዊ ሕይወቱን በ89 ዓመቱ ነሐሴ 26, 1966 ፈጽሟል። እንደ እርሱ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የታማኝነት አገልግሎታቸው ዋጋ ‘ወዲያው እንደሚከተላቸው’ ያውቅ ነበር። (ራእይ 14:13 አዓት) በእርግጥም አለመሞትን ለብሰው ከሞት ስለሚነሡ ለይሖዋ የሚሰጡት አገልግሎት ሳይስተጓጎል ይቀጥላል። ወንድም ማክሚላን ይህን ሽልማት በማግኘቱ ጓደኞቹ ተደስተዋል። ይሁን እንጂ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ ላይ አቋሙን በማበላሸት አምላክን እንዲተው ሰይጣን የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች ይበልጥ እንዲገነዘብ ያደረገውን የጤና እክል ጨምሮ በተለያዩ ፈተናዎች ተንገላቷል።
2, 3. ኢዮብ ማን ነበር?
2 ወንድም ማክሚላን ልክ ኢዮብ የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማኛል ሲል ከባድ የእምነት ፈተናዎችን ጸንቶ የተቋቋመን አንድ ሰው መጥቀሱ ነበር። ኢዮብ በሰሜናዊ አረብያ “ዖፅ በሚባል አገር” ይኖር ነበር። የኖኅ ልጅ የሴም ዝርያ ሲሆን የይሖዋ አምላኪ ነበር። ፈተናዎቹ በኢዮብ ላይ የደረሱት ዮሴፍ በሞተበትና ሙሴ ጻድቅ መሆኑን ባስመሠከረበት ጊዜ መካከል ይመስላል። በዚያ ወቅት ለአምላክ ያደሩ በመሆን ረገድ በምድር ላይ ኢዮብን የሚተካከል ሰው አልነበረም። ይሖዋ ኢዮብን እንከን የሌለው፣ ጻድቅና አምላክን የሚፈራ ሰው እንደሆነ አድርጎ ተመልክቶታል።—ኢዮብ 1:1, 8
3 ኢዮብ “በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ” የነበረ ሰው እንደመሆኑ መጠን ብዙ አገልጋዮች ነበሩት፤ ከብቶቹም 11,500 ያክሉ ነበር። ሆኖም መንፈሳዊ ብልጽግና በእርሱ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ነበረው። በዛሬው ጊዜ እንዳሉት ለአምላክ አክብሮት እንዳላቸው አባቶች ኢዮብ ሰባቱን ወንዶች ልጆቹንና ሦስቱን ሴቶች ልጆቹን ስለ ይሖዋ ሳያስተምራቸው አልቀረም። ራሳቸውን ችለው መኖር ከጀመሩም በኋላ ምናልባት ኃጢአት ሠርተው ሊሆን ይችላል ብሎ በማሰብ ለእነርሱ መሥዋዕቶችን በማቅረብ የቤተሰቡ ካህን ሆኖ ይሠራ ነበር።—ኢዮብ 1:2–5
4. (ሀ) ስደት የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ኢዮብን ልብ ማለት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢዮብን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
4 ስደት የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች በትዕግሥት ለመጽናትና ራሳቸውን ለማጠንከር እንዲችሉ ኢዮብን ልብ ሊሉት ይገባል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “እነሆ፣ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።” (ያዕቆብ 5:11) ልክ እንደ ኢዮብ ሁሉ የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮችና በዘመናችን ያሉት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የእምነትን ፈተናዎች ለመቋቋም ጽናት ያስፈልጋቸዋል። (ራእይ 7:1–9) ታዲያ ኢዮብ ምን ዓይነት ፈተናዎችን ጸንቶ ተቋቁሟል? ፈተናዎቹ የተከሰቱት ለምንድን ነው? በእሱ ላይ ከደረሱት ሁኔታዎች ትምህርት ማግኘት የምንችለውስ እንዴት ነው?
አንገብጋቢ ጥያቄ
5. ኢዮብ ሳያውቀው በሰማይ ምን እየተከናወነ ነበር?
5 በሰማይ አንድ ትልቅ አከራካሪ ጥያቄ ሊነሣ መሆኑን ኢዮብ አያውቅም ነበር። አንድ ቀን “የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ።” (ኢዮብ 1:6) ቃል ተብሎ የሚጠራው የአምላክ አንድያ ልጅ በቦታው ተገኝቶ ነበር። (ዮሐንስ 1:1–3) ጻድቃን የሆኑት መላእክትና ዓመፀኛ የሆኑት ‘የአምላክ መላእክታዊ ልጆችም’ ተገኝተው ነበር። (ዘፍጥረት 6:1–3) መንግሥቲቱ በ1914 እስከተቋቋመችበት ጊዜ ድረስ ከሰማይ ተባሮ ስላልነበር ሰይጣንም ተገኝቶ ነበር። (ራእይ 12:1–12) በኢዮብ ዘመን ሰይጣን አንድ አንገብጋቢ የሆነ አከራካሪ ጥያቄ አስነሣ። ይሖዋ በፍጥረታቱ ሁሉ ላይ ያለውን የሉዓላዊነት መብት አጠያያቂ ሊያደርገው ነው።
6. ሰይጣን ምን ለማድረግ እየጣረ ነበር? የይሖዋን ስም ያጠፋው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ሰይጣንም “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፣ በእርስዋም ተመላለስሁ” በማለት መለሰለት። (ኢዮብ 1:7) የሚውጠውን ፍለጋ ሲኳትን ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች ያላቸውን አቋም በማበላሸትና ከአምላክ በማለያየት ሰይጣን ማንም ሰው በፍቅር ተነሣስቶ አምላክን ሙሉ በሙሉ አይታዘዝም የሚል አባባሉን ለማረጋገጥ ይሞክራል። አከራካሪውን ጥያቄ በማንሣት ይሖዋ ሰይጣንን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፣ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፣ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም።” (ኢዮብ 1:8) ኢዮብ አለፍጽምናውን ግምት ውስጥ የሚያስገቡትን መለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ጠብቋል። (መዝሙር 103:10–14) ይሁን እንጂ ሰይጣን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፣ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል።” (ኢዮብ 1:9, 10) በዚህም መንገድ ዲያብሎስ ማንኛውም ሰው ይሖዋን የሚወደውና የሚያመልከው እርሱ ላሉት ባሕርያት ካለው አድናቆት ተነሣስቶ ሳይሆን አምላክ ፍጥረታቱ እሱን እንዲያገለግሉት መደለያ ስለሚያቀርብላቸው ነው በማለት ስሙን አጠፋው። ሰይጣን ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው በፍቅር ተገፋፍቶ ሳይሆን ለራሱ የስስት ጥቅም ሲል ነው አለ።
ሰይጣን ጥቃት ሰነዘረ!
7. ዲያብሎስ አምላክን የተገዳደረው በምን መንገድ ነው? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠ?
7 “ነገር ግን” አለ ሰይጣን፤ “እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” አምላክ ለዚህ ስድብ ለሆነ ግድድር ምን ምላሽ ሰጠ? ይሖዋ “እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፣ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው።” ዲያብሎስ ኢዮብ ያለው ጥሪት ሁሉ ተባርኳል፣ ተበራክቷል እንዲሁም ጥበቃ አግኝቷል ብሏል። አምላክ ኢዮብ መከራ እንዲደርስበት ቢፈቅድም በአካሉ ላይ ግን አንዳችም ዓይነት ጉዳት እንዲደርስበት አልፈቀደም። ሰይጣን ክፉ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ቆርጦ በመነሣት ስብሰባውን ጥሎ ወጣ።—ኢዮብ 1:11, 12
8. (ሀ) ኢዮብ ምን የቁሳዊ ንብረት ጥፋት ደርሶበታል? (ለ) ‘ከሰማይ የእግዚአብሔር እሳት ወረደ’ ቢባልም ሐቁ ምን ነበር?
8 ብዙም ሳይቆይ ሰይጣናዊው ጥቃት ጀመረ። ከኢዮብ አገልጋዮች አንዱ የሚከተለውን መርዶ አሰማው፦ “በሬዎች እርሻ ያርሱ፣ በአጠገባቸውም አህዮች ይሰማሩ ነበር፤ የሳባም ሰዎች አደጋ ጣሉ፣ ወሰዱአቸውም፣ ብላቴኖቹንም በሰይፍ ስለት ገደሉ።” (ኢዮብ 1:13–15) በኢዮብ ንብረት ዙሪያ የነበረው አጥር ተነሥቶ ነበር። ወዲያውኑ ማለት ይቻላል አጋንንታዊ ኃይል ቀጥተኛ እርምጃ ወሰደ። ምክንያቱም ሌላ አገልጋይ የሚከተለውን ሪፖርት አድርጓል፦ “የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወደቀች፣ በጎቹንም አቃጠለች፣ ጠባቂዎችንም በላች።” (ኢዮብ 1:16) አምላክ ሌላው ቀርቶ በራሱ አገልጋይ ላይ ለደረሰው ለእንዲህ ዓይነቱ ታላቅ ጥፋት እንኳ ተጠያቂ እንደሆነ የሚያስመስል እንዴት ያለ ዲያብሎሳዊ ሥራ ነው! መብረቅ የሚወርደው ከሰማይ ስለሆነ ይሖዋ በቀላሉ ተወቃሽ ሊሆን ይችል ነበር። እሳቱን ያወረደው ግን አጋንንታዊ ኃይል ነበር።
9. የኢኮኖሚው ጥፋት ኢዮብ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና የነካው እንዴት ነው?
9 ሰይጣን ጥቃቱን ሲቀጥል ሌላ አገልጋይ ከለዳውያን የኢዮብን ግመሎች እንደወሰዱና ሌሎቹን ጠባቂዎች እንደገደሏቸው ተናገረ። (ኢዮብ 1:17) ምንም እንኳ ኢዮብ በዚህ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ውድመት ቢደርስበትም ይህ ሁኔታ ከአምላክ ጋር አላቆራረጠውም። አንተ ብትሆን ኖሮ አቋምህን ሳታጎድፍና አምላክን ሳትተው በቁሳዊ ንብረትህ ላይ የሚደርሰውን ታላቅ ጥፋት ጸንተህ ትቋቋም ነበርን?
ይበልጥ አሳዛኝ የሆኑ ጥቃቶች
10, 11. (ሀ) የኢዮብ አሥር ልጆች ምን ደረሰባቸው? (ለ) ኢዮብ በልጆቹ ላይ አሳዛኝ ሞት ከደረሰ በኋላ በይሖዋ ላይ ምን አመለካከት አደረበት?
10 ዲያብሎስ ኢዮብን ማጥቃቱን አላበቃም ነበር። አሁንም ሌላ አገልጋይ የሚከተለውን ሪፖርት አሰማው፦ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤ እነሆም፣ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጥቶ የቤቱን አራቱን ማዕዘን መታው፣ በብላቴኖቹም ላይ ወደቀ፣ ሞቱም፤ እኔም እነግርህ ዘንድ ብቻዬን አመለጥሁ አለው።” (ኢዮብ 1:18, 19) ሁኔታውን በትክክል ያልተረዳ ሰው ዐውሎ ነፋሱ ያስከተለውን ጥፋት ይህ ‘የአምላክ ሥራ ነው’ ሊል ይችላል። ይሁን እንጂ አጋንንታዊ ኃይል ኢዮብ በጣም በሚነካበት አቅጣጫ መጣበት።
11 በድንገት በሐዘን ጦር የተወጋው ኢዮብ “መጎናጸፊያውን ቀደደ፣ ራሱንም ተላጨ፣ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ።” ያም ሆኖ ግን ምን እንዳለ ተመልከት። “እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን።” ዘገባው እንዲህ በማለት አክሎ ይናገራል፦ “በዚህ ሁሉ ኢዮብ አልበደለም፣ ለእግዚአብሔርም ስንፍናን አልሰጠም።” (ኢዮብ 1:20–22) ሰይጣን እንደገና ተሸነፈ። አምላክን እያገለገልን ስንኖር በጣም የምናቀርበው ሰው ቢሞትብን ምን እናደርጋለን? ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ከይሖዋ ጋር መጣበቃችንና በእርሱ መታመናችን ልክ ኢዮብ እንዳደረገው አቋማችንን ሳናበላሽ እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ባልደረቦቻቸው ስለ ኢዮብ ጽናት ከሚተርከው ከዚህ ዘገባ መጽናኛና ብርታት ማግኘት እንደሚችሉ አያጠራጥርም።
ክርክሩ ተጋጋለ
12, 13. በሰማይ በተደረገ ሌላ ስብሰባ ላይ ሰይጣን ምን ጥያቄ አቀረበ? አምላክስ ምን ምላሽ ሰጠ?
12 ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በሰማይ አደባባዮች ሌላ ስብሰባ ጠራ። ኢዮብ ልጅ አልባና ያጣ የነጣ ድሃ ሆኖ ነበር። በአምላክ ክርን የተደቆሰ መስሎ ነበር። ያም ሆኖ ግን አቋሙን ሳያጎድፍ ከአምላክ ጋር እንደተጣበቀ ቀጥሎ ነበር። እርግጥ፣ ሰይጣን በአምላክና በኢዮብ ላይ የሰነዘራቸው ክሶች ሐሰት መሆናቸውን አምኖ መቀበል አይፈልግም። ‘የአምላክ ልጆች’ ይሖዋ አከራካሪውን ጉዳይ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ዲያብሎስን በዘዴ እሱ ወደፈለገው ነጥብ ሲመራው የሚካሄደውን ክርክርና አጸፋዊ መልስ ሊሰሙ ተዘጋጅተዋል።
13 ይሖዋ ሰይጣን ስሌት እንዲያቀርብ በመፈለግ “ከወዴት መጣህ?” የሚል ጥያቄ አቀረበለት። የሰጠው መልስ ምን ነበር? “በምድር ላይ ዞርሁ፣ በእርስዋም ተመላለስሁ።” ይሖዋ ከእርሱ ጋር እንደተጣበቀ የቀጠለውን እንከን የለሹን፣ ጻድቁንና ፈሪሃ አምላክ ያለውን አገልጋዩን ኢዮብን እንደገና ጠቀሰ። ዲያብሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል። ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” ስለዚህ አምላክ “ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፣ እርሱ በእጅህ ነው” አለ። (ኢዮብ 2:2–6) ሰይጣን ይሖዋ ለኢዮብ የሚያደርገውን ጥበቃ ሙሉ በሙሉ እንዳላነሣ በመጠቆም የኢዮብን አጥንትና ሥጋ መጉዳት እንዲችል ጥያቄ አቀረበ። ዲያብሎስ ኢዮብን ኢንዲገድለው አልተፈቀደለትም። ሆኖም አካላዊ ሕመም ኢዮብን እንደሚያሠቃየውና ድብቅ በሆኑ ኃጢአቶች ሳቢያ አምላክ እየቀጣው እንዳለ እንደሚያስመስል ሰይጣን ያውቅ ነበር።
14. ሰይጣን ኢዮብን በምን መታው? ማንኛውም ሰው ኢዮብን ከሥቃዩ ሊገላግለው ያልቻለው ለምንድን ነው?
14 ሰይጣን ከስብሰባው ወጥቶ በመሄድ በጭካኔያዊ ተግባር መደሰቱን ቀጠለ። ኢዮብን “ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው።” ኢዮብ በአመድ ላይ ተቀምጦ በገል ገላውን ሲፍቅ እንዴት ያለ ሥቃይ ችሎ አሳልፏል! (ኢዮብ 2:7, 8) ችግሩ የደረሰበት በሰይጣናዊ ኃይል በመሆኑ ማንኛውም ሰብዓዊ ሐኪም ከዚህ ከሚያንገበግብና ከሚዘገንን አሳፋሪ ሥቃይ ሊገላግለው አልቻለም። ኢዮብን ሊፈውሰው ይችል የነበረው ይሖዋ ብቻ ነበር። በሕመም የምትሠቃይ የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ አምላክ በሽታህን እንድትችለው ሊረዳህ እንደሚችልና ከበሽታ ነፃ በሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ ሕይወት ሊሰጥህ እንደሚችል ፈጽሞ አትዘንጋ።—መዝሙር 41:1–3፤ ኢሳይያስ 33:24
15. ኢዮብ ሚስቱ ምን እንዲያደርግ ወተወተችው? የኢዮብ ምላሽስ ምን ነበር?
15 በመጨረሻ የኢዮብ ሚስት “እስከ አሁን ፍጹምነትህን [በእንግሊዝኛ ኢንተግሪቲ] ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለች። “ኢንተግሪቲ” የሚለው ቃል አቋምን ሳያበላሹ ወይም ሳያጎድፉ መቆምን ያመለክታል። እሷም ኢዮብ አምላክን እንዲሰድብ በአሽሙር ተናግራ ሊሆን ይችላል። እሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፣ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” ይኸኛውም የሰይጣን ዘዴ እንደታለመው አልሆነም። ምክንያቱም “በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም” ተብለናል። (ኢዮብ 2:9, 10) ለምሳሌ ያህል የሚቃወሙ የቤተሰብ አባላት በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የምትደክሙት ሞኝ ሆናችሁ ነው፤ ይሖዋ አምላክን ብትተዉት ይሻላችኋል ብለው መከሩን እንበል። ይሖዋን ስለምንወደውና ቅዱስ ስሙን ለማወደስ ስለምንፈልግ ልክ እንደ ኢዮብ እንዲህ ዓይነቱን ፈተና ጸንተን መቋቋም እንችላለን።—መዝሙር 145:1, 2፤ ዕብራውያን 13:15
በኩራት የተወጠሩ ሦስት አስመሳዮች
16. ኢዮብን ለማጽናናት በሚል ወደ እሱ ዘንድ የመጡት እነማን ናቸው? ይሁን እንጂ ሰይጣን እሱ በፈለገው መንገድ የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?
16 ሌላው የሰይጣን ውጥን ኢዮብን ለማጽናናት በሚል ወደ እሱ ዘንድ በመጡት ሦስት “ጓደኞቹ” ላይ ያነጣጠረ ነበር። አንዱ ኤልፋዝ ነበር። ኤለፋዝ በኤሳው በኩል የአብርሃም ዝርያ ሳይሆን አይቀርም። ኤልፋዝ በመናገር ረገድ ቀዳሚ ስለሆነ ከሁሉም በዕድሜ ላቅ የሚለው እርሱ መሆን አለበት። በልዳዶስም በቦታው ከነበሩት አንዱ ነው። አብርሃም ከኬጡራ ከወለዳቸው ልጆች መካከል አንዱ የሆነው የስዌሕ ዝርያ ነው። ሦስተኛው ሰው ሶፋር ነው። ትውልዱን ወይም የመኖሪያ ስፍራውን ለማመልከት ነዕማታዊ ተብሏል። ይኖርበት የነበረው ቦታ ሰሜናዊ ምዕራብ አረብያ ሳይሆን አይቀርም። (ኢዮብ 2:11፤ ዘፍጥረት 25:1, 2፤ 36:4, 11) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን እንዲተዉ ለማድረግ እንደሚሞክሩት ሰዎች እነዚህ ሦስት ሰዎች ኢዮብ የቀረቡለትን የሐሰት ክሶች ተቀብሎ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ እንዲያምንና አቋሙ ተበላሽቶ አምላክን እንዲተው ለማድረግ እንዲጥሩ ሰይጣን በፈለገው መንገድ ይመራቸው ነበር።
17. ኢዮብን ሊጠይቁት የመጡት ሦስቱ ሰዎች ምን አደረጉ? ለሰባት ቀናትና ለሰባት ሌሊቶች ምን ሳያደርጉ ቆይተው ነበር?
17 ሦስቱ ሰዎች በማልቀስ፣ ልብሳቸውን በመቅደድና በራሳቸው ላይ ትቢያ በመነስነስ ከፍተኛ የአዘኔታ መግለጫ ትዕይንት ሠሩ። ከዚያ በኋላ ግን አንድም የማጽናኛ ቃል ሳይተነፍሱ ከኢዮብ ጋር ሰባት ቀናትና ሰባት ሌሊቶች ተቀመጡ! (ኢዮብ 2:12, 13፤ ሉቃስ 18:10–14) እነዚህ በኩራት የተወጠሩ ሦስት አስመሳዮች በመንፈሳዊ ድሆች ስለነበሩ ስለ ይሖዋና ስለ ተስፋዎቹ የሚናገሩት የማጽናኛ ቃል አልነበራቸውም። ሆኖም የተሳሳቱ ድምዳሜዎች ላይ ደርሰው ነበር። እንደ ደንብ ተቆጥሮ የሚደረገውን ማኅበረሰቡ የሚጠቀምበትን የሐዘን መግለጫ ካከናወኑ በኋላ ወዲያውኑ የደረሱባቸውን የተሳሳቱ ድምዳሜዎች በኢዮብ ላይ ለማዥጎድጎድ ተዘጋጁ። ዝምታ የሰፈነባቸው ሰባት ቀናት ከማብቃታቸው በፊት ወጣቱ ኤሊሁ ውይይታቸውን ሊሰማ በሚችልበት ርቀት ተቀምጦ ነበር።
18. ኢዮብ በሞት አማካኝነት ለመገላገል የተመኘው ለምንድን ነው?
18 በመጨረሻ ኢዮብ ዝምታው እንዲያበቃ አደረገ። ሊጠይቁት ከመጡት ሦስት ሰዎች ምንም ማጽናኛ ባለማግኘቱ የተወለደበትን ቀን ረገመ። በመንገላታት ያሳለፋቸው ጊዜያትም ለምን እንደረዘሙበት በመገረም ተናገረ። ከመሞቴ በፊት ዳግመኛ እውነተኛ ደስታ አገኛለሁ ብሎ ስላልገመተ በሞት ለመገላገል ተመኘ። ኢዮብ በዚህ ወቅት ያጣ የነጣ ድሃ ሆኖ ነበር፤ እንዲሁም የሚያፈቅራቸው ልጆቹ በሞት ተለይተውትና በጠና ታሞ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ ኢዮብ ለሞት እስኪደርስ ድረስ ጉዳት እንዲደርስበት አልተወውም።—ኢዮብ 3:1–26
የኢዮብ ከሳሾች የሰነዘሩት ጥቃት
19. ኤልፋዝ ኢዮብን በሐሰት የወነጀለው በምን በምን ረገድ ነው?
19 የኢዮብን የአቋም ጽናት ይበልጥ በተፈታተነው ለሦስት ዙር በተካሄደው እሰጥ አገባ መጀመሪያ የተናገረው ኤልፋዝ ነበር። በመጀመሪያው ንግግሩ ኤልፋዝ “ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ኢዮብ የአምላክ ቅጣት እንዲደርስበት ያደረገው አንድ መጥፎ ነገር ሠርቶ መሆን አለበት ብሎ ደምድሞ ነበር። (ኢዮብ፣ ምዕራፍ 4, 5) ኤልፋዝ በሁለተኛው ንግግሩ ላይ የኢዮብን ጥበብ በማጣጣል “እኛ የማናውቀውን አንተ የምታውቀው ምንድር ነው?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። ኢዮብ ራሱን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ በላይ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል በማለት ኤልፋዝ ተናገረ። ኢዮብ በከሃዲነት፣ በጉቦና በአታላይነት ጥፋተኛ እንደሆነ አድርጎ በመግለጽ ሁለተኛውን ዙር ትችቱን ደመደመ። (ኢዮብ፣ ምዕራፍ 15) ኤልፋዝ በመጨረሻው ንግግሩ በሐሰት ኢዮብን የብዙ ወንጀሎች ተጠያቂ አደረገው። ሌላውን አስፈራርቶ በመዝረፍ፣ ለችግረኞች እንጀራና ውኃ በመከልከል እንዲሁም መበለቶችንና ወላጆች የሌሏቸውን በመጨቆን ወንጀል ሠርተሃል አለው።—ኢዮብ፣ ምዕራፍ 22
20. በልዳዶስ በኢዮብ ላይ የሰነዘረው ጥቃት ምን መልክ ነበረው?
20 ለሦስት ዙር በተካሄደው እሰጥ አገባ በእያንዳንዱ ዙር በሁለተኛነት የተናገረው በልዳዶስ ብዙውን ጊዜ ኤልፋዝ የተናገረውን ሐሳብ ተከትሏል። የበልዳዶስ ንግግሮች አጠር ያሉ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ እንደ ጭንቁር ይዋጉ ነበር። አልፎ ተርፎም የኢዮብን ልጆች መጥፎ ነገር ሠርተዋል ብሎ ከሰሳቸው። በመሆኑም ሞት የሚበዛባቸው አልነበረም አለ። በተዛባ አስተሳሰብ የሚከተለውን ምሳሌ ተጠቀመ፦ ደንገልና ሸምበቆ ውኃ ካላገኙ እንደሚደርቁና እንደሚረግፉ ሁሉ “እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜያቸው እንዲሁ ነው።” ይህ አባባል እውነት ነው፤ ነገር ግን በኢዮብ ላይ የሚሠራ አልነበረም። (ኢዮብ፣ ምዕራፍ 8) በልዳዶስ በኢዮብ ላይ የደረሱትን መከራዎች በክፉዎች ላይ ከሚደርሱባቸው ነገሮች ጋር መድቧቸዋል። (ኢዮብ፣ ምዕራፍ 18) በልዳዶስ አጭር በሆነው በሦስተኛው ንግግሩ ላይ ሰው “እንደ ትንኝ” እና “እንደ ትል [የ1980 ትርጉም]” ስለሆነ በአምላክ ፊት ንጹሕ አይደለም ሲል ተከራከረ።—ኢዮብ፣ ምዕራፍ 25
21. ሶፋር ኢዮብን የወነጀለው በምን ነበር?
21 በተካሄደው እሰጥ አገባ በሦስተኛነት የተናገረው ሶፋር ነበር። በጥቅሉ ያቀረባቸው ሐሳቦች ኤልፋዝና በልዳዶስ ካቀረቧቸው ሐሳቦች ጋር የሚመሳሰሉ ነበሩ። ሶፋር ኢዮብን በክፋት ድርጊት በመወንጀል የኃጢአት ልማዶቹን እንዲያስወግድ አሳሰበው። (ኢዮብ፣ ምዕራፍ 11, 20) ከሁለት ዙር ንግግር በኋላ ሶፋር መናገሩን አቆመ። በሦስተኛው ዙር ላይ ምንም የሚያክለው ነገር አልነበረውም። ይሁን እንጂ ኢዮብ እሰጥ አገባው ተጀምሮ እስኪያልቅ በድፍረት ለከሳሾቹ መልስ ሰጥቷል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ነጥብ ላይ “እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ። በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን?” ብሎ ነበር።—ኢዮብ 16:2, 3
መጽናት እንችላለን
22, 23. (ሀ) በኢዮብ ላይ እንደታየው ዲያብሎስ ለይሖዋ አምላክ የምናሳየውን የጸና አቋም ለማበላሸት የሚጥረው እንዴት ሊሆን ይችላል? (ለ) ኢዮብ የተለያዩ ፈተናዎችን ጸንቶ ቢቋቋምም እንኳ አመለካከቱን በተመለከተ ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?
22 ልክ እንደ ኢዮብ እኛም በአንዴ ከአንድ በላይ የሆኑ ፈተናዎች ሊደርሱብን ይችላሉ፤ ሰይጣን ደግሞ ጽኑ አቋማችንን ለማበላሸት በሚያደርገው ጥረት ተስፋ መቁረጥን ወይም ሌሎች ነገሮችን ሊጠቀም ይችላል። ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ካሉብን እኛን ከይሖዋ ጋር ለማለያየት ሊሞክር ይችላል። የምናፈቅረው ሰው ቢሞት ወይም የጤና እክል ቢደርስብን ሰይጣን አምላክን እንድናማርር ለመገፋፋት ጥረት ሊያደርግ ይችላል። ልክ እንደ ኢዮብ ወዳጆች አንድ ሰው በሐሰት ሊወነጅለንም ይችላል። ወንድም ማክሚላን እንዳለው ሰይጣን ‘እግር በግር እየተከታተለን’ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ልንጸና እንችላለን።
23 እስከ አሁን እንደተመለከትነው ኢዮብ የደረሱበትን የተለያዩ ፈተናዎች ጸንቶ ተቋቁሟል። ይሁን እንጂ ኢዮብ የጸናው እንዲሁ ነበርን? በእርግጥ ኢዮብ የተሰበረ መንፈስ ነበረውን? ኢዮብ ተስፋው ሁሉ ተሟጦ እንደነበረና እንዳልነበረ እስቲ እንመልከት።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ሰይጣን በኢዮብ ዘመን ምን ትልቅ አከራካሪ ጥያቄ አስነሣ?
◻ ኢዮብ እስከ አቅሙ ወሰን ድረስ የተፈተነው በምንድን ነው?
◻ ሦስቱ የኢዮብ “ወዳጆች” በምን ወነ ጀሉት?
◻ በኢዮብ ላይ እንደታየው ሰይጣን አቋማችንን በማበላሸት እኛን ከይሖዋ ጋር ለማለያየት የሚሞክረው እንዴት ሊሆን ይችላል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤ ኤች ማክሚላን