ይሖዋ የእውነት አምላክ ነው
“የእውነት አምላክ አቤቱ፣ ተቤዥተኸኛል።”—መዝሙር 31:5
1. በአንድ ወቅት በሰማይና በምድር ላይ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
ሐሰት የሚባል ነገር ያልነበረበት ወቅት ነበር። በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ፍጹማን የሆኑ መንፈሳዊ ፍጡራን “የእውነት አምላክ” የሆነውን ፈጣሪያቸውን ያገለግሉ ነበር። (መዝሙር 31:5) ሐሰት የሚናገርም ሆነ የሚያታልል አልነበረም። ይሖዋ ለመንፈሳዊ ልጆቹ የሚነግራቸው በሙሉ እውነት ነበር። ይህን የሚያደርገው ስለሚወዳቸውና ስለ ደኅንነታቸው ከልብ ስለሚያስብላቸው ነው። በምድር ላይም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ከፈጠረ በኋላ ባዘጋጀው የመገናኛ መስመር አማካኝነት ግልጽ፣ ቀጥተኛና እውነተኛ የሆነ መልእክት ያስተላልፍላቸው ነበር። ይህ አስደሳች እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም!
2. የመጀመሪያው ውሸታም ማን ነው? ውሸት የተናገረውስ ለምንድን ነው?
2 ውሎ አድሮ ግን አንድ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ይሖዋን በመቃወም ራሱን አምላክ ለማድረግ በማን አለብኝነት ተነሳ። ሰይጣን ዲያብሎስ ተብሎ የተጠራው ይህ መንፈሳዊ ፍጡር በሌሎች የመመለክ ፍላጎት አደረበት። ሌሎችን በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ ይህን ፍላጎቱን ከግብ ለማድረስ ሲል ውሸት ፈጠረ። በዚህም ምክንያት “ሐሰተኛ የሐሰትም አባት” ተባለ።—ዮሐንስ 8:44
3. አዳምና ሔዋን የሰይጣንን ውሸት ሰምተው ምን አደረጉ? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ?
3 ሰይጣን ለመጀመሪያዋ ሴት ለሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ችላ ብላ ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ እንደማትሞት በእባብ አማካኝነት ነገራት። ይህ ዓይን ያወጣ ውሸት ነበር። በተጨማሪም ፍሬውን ብትበላ መልካሙንና ክፉውን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆን ነገራት። ይህም ቢሆን ውሸት ነው። ሔዋን ከዚያ በፊት ውሸት ሰምታ የማታውቅ ቢሆንም እባቡ የነገራት ነገር አምላክ ለባልዋ ለአዳም ከነገረው ጋር እንደሚጋጭ ተገንዝባ መሆን አለበት። ያም ሆኖ ግን ይሖዋን ሳይሆን ሰይጣንን አመነች። በተነገራት ውሸት ተታልላ ፍሬውን ቀጥፋ በላች። በኋላ አዳምም ከፍሬው በላ። (ዘፍጥረት 3:1-6) እንደ ሔዋን ሁሉ አዳምም ከዚያ በፊት ውሸት ሰምቶ አያውቅም ነበር፤ ሆኖም ፍሬውን የበላው እንደ ሚስቱ ተታልሎ አልነበረም። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) ይህ አድራጎቱ ለፈጣሪው ጀርባውን እንደሰጠ ያሳያል። ይህም በሰው ዘር ላይ መራራ ውጤት አስከትሏል። አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት ዘሮቹ በሙሉ ለኃጢአትና ለሞት እንዲሁም ለመከራና ለሥነ ምግባር ውድቀት ተዳርገዋል።—ሮሜ 5:12
4. (ሀ) ሰይጣን በዔድን ገነት የተናገራቸው ውሸቶች በይሖዋ እውነተኝነት ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በሰይጣን እንዳንታለል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 ከዚያም ውሸት ይበልጥ እየተስፋፋ ሄደ። በዔድን ገነት ውስጥ የተነገሩት እነዚህ ውሸቶች በይሖዋ እውነተኝነት ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች እንደሆኑ መገንዘብ ይኖርብናል። ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት አንድ ጥሩ ነገር አምላክ ነፍጓቸዋል በማለት ተከራከረ። ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ አልነበረም። አዳምና ሔዋን አለመታዘዛቸው ምንም አልጠቀማቸውም። ይሖዋ እንደተናገረው ሞተዋል። የሆነ ሆኖ ሰይጣን በይሖዋ ላይ የጀመረው የስም ማጥፋት ዘመቻ በዚህ አላበቃም። በመሆኑም ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት ሰይጣን ‘ዓለሙን ሁሉ እያሳተ’ እንደሆነ ጽፏል። (ራእይ 12:9) በሰይጣን ዲያብሎስ እንዳንታለል በይሖዋና በቃሉ እውነተኝነት ላይ ሙሉ ትምክህት ሊኖረን ይገባል። በይሖዋ ላይ ያለንን ትምክህት ማዳበርና ማጠናከር እንዲሁም ባላጋራው የሆነው ሰይጣን ከሚነዛው ውሸትና የማታለያ ድርጊት ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ እውነቱን ያውቃል
5, 6. (ሀ) የይሖዋን እውቀት እንዴት ትገልጸዋለህ? (ለ) የሰው ልጆች እውቀት ከይሖዋ ጋር ሲወዳደር ምን ያህል ልዩነት አለው?
5 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘ሁሉንም እንደፈጠረ’ በተደጋጋሚ ይናገራል። (ኤፌሶን 3:8, 9) “ሰማዩንና ምድሩን ባሕሩንም በእነርሱም የሚኖረውን ሁሉ” የፈጠረው እርሱ ነው። (ሥራ 4:24) በመሆኑም ስለ እያንዳንዱ ነገር እውነቱን ያውቃል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ፕላኑን ራሱ አውጥቶ ያለ ማንም እርዳታ ቤቱን የሠራን ሰው እንመልከት። ይህ ሰው ስለ ቤቱ እያንዳንዱን ዝርዝር ነገር የሚያውቅ ሲሆን ቤቱን በሚመለከት ከማንም የተሻለ ግንዛቤ እንደሚኖረው የታወቀ ነው። ሰዎች ራሳቸው ስለሠሯቸው ነገሮች ጠንቅቀው ያውቃሉ። በተመሳሳይም ፈጣሪ ስለፈጠራቸው ነገሮች በዝርዝር ያውቃል።
6 ነቢዩ ኢሳይያስ የይሖዋ እውቀት ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ግሩም በሆነ መንገድ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፣ ሰማይንም በስንዝር የለካ፣ የምድርንም አፈር በመስፈርያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው? የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፣ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?” (ኢሳይያስ 40:12-14) በእርግጥም ይሖዋ “አዋቂ” እንዲሁም “በእውቀትም ፍጹም የሆነ” አምላክ ነው። (1 ሳሙኤል 2:3፤ ኢዮብ 36:4፤ 37:16) ከእርሱ ጋር ሲወዳደር የእኛ እውቀት ምንኛ ኢምንት ነው! የሰው ልጅ የደረሰበት የእውቀት ደረጃ የቱንም ያህል የላቀ ቢሆን ስለ ተፈጥሮ ያለን ግንዛቤ ከአምላክ ጋር ሲነጻጸር “የመንገዱ ዳርቻ” ጋር እንኳ አይደርስም። ‘ሹክሹክታን ከኃይለኛ ነጎድጓድ’ [የ1980 ትርጉም] ጋር የማወዳደር ያህል ነው።—ኢዮብ 26:14
7. ዳዊት የይሖዋን እውቀት በሚመለከት ምን ተገንዝቦ ነበር? እኛስ ምንን አምነን መቀበል ይኖርብናል?
7 ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ በደንብ ያውቀናል ቢባል ምክንያታዊ ነው። ይህን የተገነዘበው ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ መረመርኸኝ፣ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፣ የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 139:1-5) እርግጥ ዳዊት የሰው ልጆች የፈለጉትን የመምረጥ ነጻነት እንዳላቸው ያውቅ ነበር። አምላክ እርሱን ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ ምርጫውን ለእኛ ትቶልናል። (ዘዳግም 30:19, 20፤ ኢያሱ 24:15) ቢሆንም ይሖዋ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል። የተሻለውን የሚመኝልን ከመሆኑም በላይ አካሄዳችንን በተሻለ መንገድ ለመምራት ችሎታው አለው። (ኤርምያስ 10:23) አዎን፣ እውነቱን በማስተማር እንዲሁም አስተዋዮችና ደስተኞች እንድንሆን በመርዳት ረገድ ከእርሱ ጋር የሚተካከል ችሎታ ያለው አስተማሪ፣ ሊቅ ወይም አማካሪ የለም።
ይሖዋ እውነተኛ ነው
8. ይሖዋ እውነተኛ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
8 እውነትን ማወቅና ሁልጊዜ እውነትን መናገር ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ ያህል ዲያብሎስ ‘በእውነት ላለመቆም’ መርጧል። (ዮሐንስ 8:44) በአንጻሩ ግን ይሖዋ “ባለ ብዙ . . . እውነት” ነው። (ዘጸአት 34:6) ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋ እውነተኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሊዋሽ የማይቻለው’ እና “የማይዋሽ” አምላክ በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል። (ዕብራውያን 6:17፤ ቲቶ 1:2) እውነተኝነት ከይሖዋ ባሕርያት መካከል ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው። ይሖዋ እውነተኛ ስለሆነና ታማኝ አገልጋዮቹን ፈጽሞ ስለማያታልላቸው ልንመካበትና ልንተማመንበት እንችላለን።
9. ይሖዋ የሚለው ስም ለእውነተኝነቱ ማረጋገጫ የሚሰጠን እንዴት ነው?
9 ይሖዋ የሚለው ስም ራሱ ለእውነተኝነቱ ማረጋገጫ ይሆናል። መለኮታዊው ስም “ይሆናል” የሚል ትርጉም አለው። ይህም ቃል የገባቸውን ነገሮች በሙሉ ፈጻሚ ሆኖ እንደሚገኝ ያመለክታል። ማንም ቢሆን እንዲህ መሆን አይችልም። ይሖዋ የሁሉም የበላይ ስለሆነ ዓላማውን እንዳያሳካ ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም። ይሖዋ እውነተኛ ከመሆኑም በላይ የተናገራቸውን ነገሮች በሙሉ ለመፈጸም የሚያስችል ጥበብና ኃይል አለው።
10. (ሀ) ኢያሱ የይሖዋን እውነተኝነት የተመለከተው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የገባቸው የትኞቹ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ተመልክተሃል?
10 የይሖዋን እውነተኝነት የሚያሳዩ አስደናቂ ክንውኖችን ከተመለከቱት በርካታ ሰዎች መካከል ኢያሱ ይገኝበታል። ይሖዋ በግብፅ ላይ የሚያመጣቸውን አሥሩን መቅሰፍቶች አስቀድሞ ሲናገርና በተግባር ሲያሳይ ኢያሱ የዓይን ምሥክር ነበር። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነጻ አውጥቶ የሚቃወሟቸውን ኃያላን የከነዓን መንግሥታት ከፊታቸው እየጠራረገ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንደሚያስገባቸው የገባውን ቃል ሲፈጽም ተመልክቷል። ኢያሱ በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሰብስቦ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እነሆም፣ ዛሬ የምድርን ሁሉ መንገድ እሄዳለሁ፤ እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።” (ኢያሱ 23:14) ኢያሱ የተመለከታቸውን ተአምራት በቦታው ተገኝተህ ባታይም አምላክ የገባቸው የትኞቹ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ተመልክተሃል?
ይሖዋ እውነትን ይገልጣል
11. ይሖዋ ለሰዎች እውነትን ማስተማር እንደሚፈልግ የሚያሳየው ምንድን ነው?
11 አንድ ወላጅ ከፍተኛ እውቀት እያለው ለልጆቹ ምንም የማይነግራቸው ቢሆን አያሳዝንም? ይሖዋ እንዲህ ዓይነት አምላክ ባለመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል። ይሖዋ እውቀቱን ሳይቆጥብ የሰው ልጆችን በፍቅር ተነሳስቶ ያስተምራቸዋል። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ‘ታላቁ አስተማሪ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ኢሳይያስ 30:20) በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ እርሱን መስማት ለማይፈልጉ ሰዎች እንኳን መልእክቱ እንዲነገር ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ሕዝቅኤልን ፈጽሞ መስማት ለማይፈልጉ ሰዎች እንዲሰብክ ልኮት ነበር። “የሰው ልጅ ሆይ፣ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፣ ቃሌንም ተናገራቸው” በማለት አዘዘው። ከዚያም “የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፣ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም” በማለት አስጠነቀቀው። ይህ ከባድ ኃላፊነት ቢሆንም ሕዝቅኤል በታማኝነት ተወጥቶታል። እንዲህ በማድረጉም የይሖዋን ርኅራኄ አንጸባርቋል። አንተም አስቸጋሪ በሆነ የአገልግሎት ክልል ውስጥ የምትሠራ ከሆነና በይሖዋ ከተማመንህ ነቢዩ ሕዝቅኤልን እንዳበረታታው ሁሉ አንተንም እንደሚያበረታታህ ሙሉ ትምክህት ሊኖርህ ይገባል።—ሕዝቅኤል 3:4, 7-9
12, 13. አምላክ ሰዎችን ለማስተማር በየትኞቹ መንገዶች ተጠቅሟል?
12 ይሖዋ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በነቢያት፣ በመላእክት አልፎ ተርፎም በሚወደው ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተናግሯል። (ዕብራውያን 1:1, 2፤ 2:2) ኢየሱስ ጲላጦስን “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” ብሎት ነበር። ጲላጦስ ይሖዋ የሰው ልጆችን ለማዳን ስላደረገው ዝግጅት ከአምላክ ልጅ በቀጥታ በመስማት እውነትን የመማር ግሩም አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ይሁን እንጂ ለእውነት የቆመ ባለመሆኑ ከኢየሱስ ለመማር አልፈለገም። በመሆኑም “እውነት ምንድን ነው?” ሲል በምጸት ጠየቀ። (ዮሐንስ 18:37, 38) ጲላጦስ ይህንን አጋጣሚ አለመጠቀሙ በጣም የሚያሳዝን ነው! ሆኖም ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ያስተማረውን እውነት አዳምጠዋል። ለደቀ መዛሙርቱ “የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው” ብሏቸው ነበር።—ማቴዎስ 13:16
13 ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እውነትን ያቆየልን ከመሆኑም በላይ ይህን እውነት በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ነገሮች በሙሉ እውነት ናቸው። ስለ አምላክ ባሕርያት፣ ዓላማዎችና ትእዛዛት እንዲሁም የሰው ልጆች ስለሚገኙበት ትክክለኛ ሁኔታ ይገልጻል። ኢየሱስ ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:17) በዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል። ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር ሁሉን በሚያውቀው አምላክ የተጻፈ መጽሐፍ የለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ለሰው ዘር ከተሰጡት ውድ ስጦታዎች መካከል አንዱ ሲሆን የአምላክ አገልጋዮች ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበቡ አስተዋይነት ነው።
እውነትን አጥብቃችሁ ያዙ
14. ይሖዋ አደርጋለሁ ካላቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? ልናምነው የሚገባንስ ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚነግረንን በቁም ነገር ልንይዘው ይገባል። ስለ ራሱ የሚነግረን በሙሉ እውነት ነው፤ እንዲሁም አደርጋለሁ ያለውን ሁሉ ያደርጋል። በእርግጥም በአምላክ ለመታመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን። ‘እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን እበቀላለሁ’ ሲለን ልናምነው ይገባል። (2 ተሰሎንቄ 1:8) ከዚህም በላይ ይሖዋ ጽድቅን የሚሹትን እንደሚወድ፣ እርሱ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው እንዲሁም ሐዘንንና ስቃይን ሌላው ቀርቶ ሞትን እንደሚያስቀር ሲናገር ልናምነው ይገባል። ይሖዋ በተለይ ሐዘንን፣ ስቃይንና ሞትን እንደሚያስቀር የተናገረው ተስፋ አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል ለሐዋርያው ዮሐንስ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ” ብሎታል።—ራእይ 21:4, 5፤ ምሳሌ 15:9፤ ዮሐንስ 3:36
15. ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ።
15 ሰይጣን የይሖዋ ፍጹም ተቃራኒ ነው። ለሰዎች የእውቀት ብርሃን ከመፈንጠቅ ይልቅ ያታልላቸዋል። ሰዎችን ከንጹሕ አምልኮ ለማራቅ ያለውን ግብ ለማሳካት ውሸትን ያስፋፋል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ከእኛ በጣም የራቀ እንደሆነና በምድር ላይ ስላለው መከራና ሥቃይ ደንታ እንደማይሰጠው ሊያሳምነን ይሞክራል። ሆኖም ይሖዋ ለፍጡራኖቹ ከልብ እንደሚያስብላቸውና የሚደርስባቸው ሥቃይና መከራ እንደሚሰማው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 17:24-30) ከዚህም በላይ ሰይጣን መንፈሳዊ ግቦችን መከተል ጊዜ ማባከን እንደሆነ ለማሳመን ይፈልጋል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ቅዱሳን ጽሑፎች “እግዚአብሔር . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣሉ። እንዲሁም ይሖዋ ‘ለሚፈልጉት ዋጋ የሚሰጥ’ አምላክ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ።—ዕብራውያን 6:10፤ 11:6
16. ክርስቲያኖች ልባሞች መሆንና እውነትን አጥብቀው መያዝ ያለባቸው ለምንድን ነው?
16 ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣንን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።” (2 ቆሮንቶስ 4:4) አንዳንዶች እንደ ሔዋን በሰይጣን ዲያብሎስ ይታለላሉ። ሌሎች ግን ተታልለው ሳይሆን ልክ እንደ አዳም የአምላክን ትእዛዛት ሆን ብለው ይጥሳሉ። (ይሁዳ 5, 11) ስለሆነም ክርስቲያኖች ልባሞች መሆንና እውነትን አጥብቀው መያዝ ያስፈልጋቸዋል።
ይሖዋ ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ ይፈልጋል
17. የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 ይሖዋ በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ እውነተኛ በመሆኑ አምላኪዎቹም እውነተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ፣ በልቡም እውነትን የሚናገር” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 15:1, 2) ይህን መዝሙር የሚዘምሩ አይሁዳውያን ‘የተቀደሰው ተራራህ’ የሚለው ሐረግ ንጉሥ ዳዊት ለቃል ኪዳኑ ታቦት ማረፊያ ድንኳን የተከለበትን የጽዮን ተራራ እንደሚያስታውሳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ሳሙኤል 6:12, 17) ተራራውና ድንኳኑ ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚኖርበትን ሥፍራ ያስታውሳቸዋል። በዚህ ቦታ ሰዎች ወደ አምላክ ቀርበው የእርሱን ሞገስ መለመን ይችላሉ።
18. (ሀ) የአምላክ ወዳጅ መሆን ምን ነገሮችን ይጠይቃል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
18 የይሖዋ ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በከንፈሩ ብቻ ሳይሆን “በልቡም” እውነትን መናገር ይኖርበታል። የእውነት ድርጊቶች የሚመነጩት ከልብ ስለሆነ እውነተኛ የአምላክ ወዳጆች ልባቸው ንጹሕ መሆን ይኖርበታል፤ እንዲሁም ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ እንዳላቸው ማሳየት አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 1:5፤ ማቴዎስ 12:34, 35) ይሖዋ ‘ሸንጋዩን ሰው ስለሚጸየፍ’ የእርሱ ወዳጅ የሆነ ሰው ሌሎችን አያታልልም ወይም አይሸነግልም። (መዝሙር 5:6) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አምላካቸውን በመከተል እውነተኛ ለመሆን ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋ ስለ ሁሉም ነገር እውነቱን ያውቃል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
• ይሖዋ እውነተኛ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
• ይሖዋ እውነትን ለሰዎች የገለጠው እንዴት ነው?
• እውነትን በተመለከተ ከእኛ የሚፈለገው ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእውነት አምላክ ስለፈጠራቸው ነገሮች ጠንቅቆ ያውቃል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ የገባቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ