በደስታ እልል የምንልበት ምክንያት አለን
“ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።”—ኢሳይያስ 35:10
1. በዛሬው ጊዜ ለደስታ የሚሆን የተለየ ምክንያት ያላቸው እነማን ናቸው?
በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ደስታ ያላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት መሆናቸውን ሳታስተውል አትቀርም። ነገር ግን የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ደስተኞች ናቸው። በተጨማሪም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እየተባበሩ ባሉ ገና ባልተጠመቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ፊት እንዲህ ዓይነት ደስታ የማግኘት ተስፋ ተቀምጧል። በዚህ መጽሔት ውስጥ ያሉትን እነዚህን ቃላት እያነበብክ መሆንህ ይህንን ደስታ የራስህ እንዳደረግህ ወይም ልታገኘው እንደምትችል ያሳያል።
2. ክርስቲያኖች ያላቸው ደስታ አብዛኞቹ ሰዎች ካሉበት ሁኔታ ጋር እንዴት ይነጻጸራል?
2 ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው አንድ ነገር የጎደለው ሆኖ ይሰማቸዋል። አንተስ? ቁሳዊ ፍላጎትህ ሙሉ በሙሉ ላይሟላልህ እንደሚችል የታወቀ ነው። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሀብታሞችና ኃያላን ሰዎች እንኳ እነዚህ ነገሮች እንደማይሟሉላቸው የተረጋገጠ ነው። በተጨማሪም አሁን ካለህ የተሻለ ጤንነትና አካላዊ ጥንካሬ እንዲኖርህ ትፈልግ ይሆናል። ደስታን በተመለከተ ግን በምድር ላይ ከሚኖሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የበለጠ ሀብታምና ጤነኛ ነህ ለማለት ያስደፍራል። እንዴት እንዲህ ሊባል ይቻላል?
3. ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ቃላት የትኞቹ ናቸው? ለምንስ?
3 ኢየሱስ “ይህን የነገርሁአችሁ ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና የእናንተም ደስታ ፍጹም እንዲሆን ነው” በማለት የተናገራቸውን ቃላት አስታውስ። (ዮሐንስ 15:11 የ1980 ትርጉም) “የእናንተም ደስታ ፍጹም እንዲሆን” ብሏል። እንዴት ያለ ግሩም አባባል ነው! ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር ያደረግነው ጥልቅ ጥናት ደስታችን ፍጹም ወይም የተሟላ እንዲሆን የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሳይቶን ነበር። አሁን ግን ኢሳይያስ 35:10 ላይ የሚገኙትን ትልቅ ትርጉም ያላቸው ቃላት ልብ በል። እነዚህ ቃላት ትልቅ ትርጉም አላቸው የተባለው በዛሬው ጊዜ በእኛ ላይ እየተፈጸሙ ስለሆነ ነው። እንዲህ ይነበባል፦ “እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም [“ላልተወሰነ ጊዜ” አዓት] ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።”
4. በኢሳይያስ 35:10 ላይ የተጠቀሰው ምን ዓይነት ደስታ ነው? ለዚህ ደስታ ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?
4 “ላልተወሰነ ጊዜ መደሰት።” “ላልተወሰነ ጊዜ” የሚለው ሐረግ ኢሳይያስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ላሰፈረው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ነው። ሆኖም ሌሎች ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ይህ ጥቅስ የሚያስተላልፈው ጽንሰ ሐሳብ “ለዘላለም” የሚል ነው። (መዝሙር 45:6፤ 90:2፤ ኢሳይያስ 40:28) ስለዚህ ዘላለማዊ ደስታ በሚያስገኙ ሁኔታዎች ሥር ፍጻሜ የሌለው ደስታ ይኖራል። ይህ በጣም ደስ አያሰኝምን? ምናልባት ይህ ጥቅስ ሊጨበጥ ስለማይችል ረቂቅ ሁኔታ የሚናገር መስሎ ይታይህ ይሆናል። ‘ይህ ነገር የሚያጋጥሙኝን የዕለት ተዕለት ችግሮችና አሳሳቢ ጉዳዮች የሚመለከት አይደለም’ በማለት ታስብ ይሆናል። እውነታዎቹ የሚያሳዩት ግን ከዚህ የተለየ ነው። በኢሳይያስ 35:10 ላይ የተሰጠው ትንቢታዊ ተስፋ በዛሬው ጊዜ ለአንተም ትርጉም አለው። ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይህን ማራኪ የሆነ የኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ትንቢት በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ በማተኮር እንመርምር። የምንመለከተው ነገር በጣም እንደሚያስደስትህ እርግጠኛ ሁን።
መደሰት ያስፈለጋቸው ሕዝቦች
5. በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ የሚገኘው ትንቢት የተጻፈው በምን ዓይነት ትንቢታዊ መቼት ነው?
5 ይህን ትንቢት ለመገንዘብ እንዲረዳን ወደኋላ መለስ ብለን ትንቢቱ የተጻፈበትን መቼት እንመልከት። ዕብራዊው ነቢይ ኢሳይያስ ይህን መጽሐፍ የጻፈው በ732 ከዘአበ አካባቢ ነው። ይህም የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከማጥፋቱ በፊት በርከት ያሉ አሥርተ ዓመታት ቀደም ብሎ ነበር። ኢሳይያስ 34:1, 2 እንደሚያመለክተው አምላክ በኢሳይያስ 34:6 ላይ የተጠቀሰችውን ኤዶምን ጨምሮ በብሔራት ላይ በቀሉን እንደሚያወርድ ተንብዮ ነበር። ይህንንም ለመፈጸም የጥንት ባቢሎናውያንን መሣሪያ አድርጎ እንደተጠቀመባቸው ግልጽ ነው። በተመሳሳይም አይሁዳውያን ከሃዲዎች ሆነው ስለነበር አምላክ በባቢሎናውያን ተጠቅሞ ይሁዳን አጠፋት። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የአምላክ ሕዝቦች ተማርከው ከመወሰዳቸውም በተጨማሪ አገራቸው ለ70 ዓመታት ባድማ ሆነች።—2 ዜና መዋዕል 36:15-21
6. በኤዶማውያን ላይ በተፈጸመውና በአይሁዳውያን ላይ በተፈጸመው ትንቢት መካከል ምን ልዩነት አለ?
6 ይሁን እንጂ በኤዶማውያንና በአይሁዶች መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። በኤዶማውያን ላይ የተወሰደው የበቀል እርምጃ ዘላለማዊ ነው፤ ከጊዜ በኋላ ፈጽመው ከታሪክ መድረክ ጠፍተዋል። አዎን፣ በዛሬው ጊዜ ኤዶማውያን ይኖሩባቸው በነበሩባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ ባዶ ፍርስራሾችን መጎብኘት ትችላለህ። ከእነዚህም መካከል በዓለም ላይ ታዋቂ የሆነው የፔትራ ከተማ ፍርስራሽ ይገኝበታል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ‘ኤዶማዊ’ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ብሔር ወይም ሕዝብ የለም። ታዲያ ባቢሎናውያን በይሁዳ ላይ የሚያደርሱት ጥፋት ዘላለማዊ ሆኖ ምድሪቱ ለዘላለም ደስታ የማይታይባት ጠፍ ምድር ሆና ትቀር ይሆን?
7. በባቢሎን የሚኖሩ አይሁዳዊ ምርኮኞች ለኢሳይያስ ምዕራፍ 35 እንዴት ምላሽ ሰጥተው ሊሆን ይችላል?
7 በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ የሚገኘው ትንቢት በጣም አስደሳች መልእክት አለው። ትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱበት በ537 ከዘአበ ስለሆነ ይህ ትንቢት የተሐድሶ ትንቢት ሊባል ይቻላል። በባቢሎን በምርኮ ሥር የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ነፃነት አግኝተው ነበር። (ዕዝራ 1:1-11) ቢሆንም ይህንን መለኮታዊ ትንቢት የተመለከቱ አይሁዳዊ ምርኮኞች ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት በትውልድ አገራቸው በይሁዳ ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚጠብቃቸው ራሳቸውን ጠይቀው ሊሆን ይችላል። በምንስ ዓይነት ሁኔታ ይኖሩ ይሆን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ በደስታ እልል የምንልበትን ምክንያት ይጠቁመናል። እስቲ እንመልከት።
8. አይሁዶች ከባቢሎን ሲመለሱ ምን ዓይነት ሁኔታ ጠበቃቸው? (ከሕዝቅኤል 19:3-6፤ ሆሴዕ 13:8 ጋር አወዳድር።)
8 አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ቢነገራቸውም እንኳ ወደዚያ የመመለሱ ጉዳይ የሚያጓጓ ሆኖ እንደማይታያቸው የታወቀ ነው። አገራቸው የአንድ ሰው ዕድሜ ለሚያክል ጊዜ ማለትም ለሰባት አሥርተ ዓመታት ባድማ ሆኖ ነበር። አገሩ ምን ዓይነት ሁኔታ ደርሶበት ነበር? እርሻ፣ የወይን ወይም ሌሎች ተክሎች የነበሩበት ቦታ ሁሉ ምድረ በዳ ሆኗል። በመስኖ ይጠጡ የነበሩ የአትክልት ቦታዎችና ማሳዎች ጠፍ ወይም በረሃ ሆነዋል። (ኢሳይያስ 24:1, 4፤ 33:9፤ ሕዝቅኤል 6:14) በጣም ተራብተው የሚርመሰመሱትን አራዊት በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ። ይህም እንደ አንበሳና ነብር የመሳሰሉትን ሥጋ በል አራዊት ይጨምር ነበር። (1 ነገሥት 13:24-28፤ 2 ነገሥት 17:25, 26፤ መኃልየ መኃልይ 4:8) ወንዶችን፣ ሴቶችን ወይም ልጆችን ሊገድሉ የሚችሉት ድቦች እንዲያው በዋዛ የሚታዩ አልነበሩም። (1 ሳሙኤል 17:34-37፤ 2 ነገሥት 2:24፤ ምሳሌ 17:12) እፉኝቶችንና ሌሎች መርዘኛ እባቦችን ወይም ጊንጦችን እንጥቀስ ካልንማ ዘርዝረን አንጨርሰውም። (ዘፍጥረት 49:17፤ ዘዳግም 32:33፤ ኢዮብ 20:16፤ መዝሙር 58:4፤ 140:3፤ ሉቃስ 10:19) በ537 ከዘአበ ከባቢሎን ከተመለሱት አይሁዶች ጋር አብረህ ኖረህ ቢሆን እንዲህ ባለው አካባቢ ወዲያ ወዲህ ለማለት ትፈራ ነበር። ከምርኮ የተመለሱ አይሁዶች እዚያ ሲደርሱ አገራቸው ገነት ሆኖ እንዳልጠበቃቸው ግልጽ ነው።
9. ከምርኮ የተመለሱ አይሁዳውያን ተስፋና እምነት ሊኖራቸው የሚችለው ለምን ነበር?
9 ቢሆንም አምላኪዎቹን ወደ አገራቸው የመለሰው ይሖዋ ነበር። እርሱ ደግሞ በምድራቸው የነበረውን ጠፍነትና ባድማነት ፈጽሞ ሊለውጥ ይችላል። ፈጣሪ ይህን ማድረግ እንደሚችል አታምንምን? (ኢዮብ 42:2፤ ኤርምያስ 32:17, 21, 27, 37, 41) ታዲያ ይሖዋ ከስደት ለተመለሱት አይሁዳውያንና ለአገራቸው ምን ያደርግላቸው ይሆን? ምንስ አደረገላቸው? ይህስ በዘመናችን ለሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች ምን ትርጉም አለው? የአሁኑንም ሆነ የወደፊት ሕይወትህንስ የሚነካው እንዴት ነው? በመጀመሪያ በዚያ ዘመን የሆነውን እንመልከት።
በለውጡ ተደሰቱ
10. በኢሳይያስ 35:1, 2 ላይ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚኖር ተተንብዮአል?
10 ቂሮስ አይሁዳውያን በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ወደሚገኘው አገራቸው እንዲመለሱ በሚያደርግበት ጊዜ ምን ይሆናል? በኢሳይያስ 35:1, 2 ላይ የሚገኘውን አስደሳች ትንቢት አንብብ፦ “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። እጅግ ያብባል በደስታና በዝማሬ ሐሤትን ያደርጋል፤ የሊባኖስ ክብር፣ የቀርሜሎስና የሳሮን ግርማ ይሰጠዋል፤ የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።”
11. ኢሳይያስ ስለ ምድሩ የተናገረው ምንድን ነው?
11 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሊባኖስ፣ ቀርሜሎስና ሳሮን በልምላሜያቸውና በውበታቸው የታወቁ ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 5:16፤ 27:29፤ 2 ዜና መዋዕል 26:10፤ መኃልየ መኃልይ 2:1፤ 4:15፤ ሆሴዕ 14:5-7) ኢሳይያስ እነዚህን ምሳሌዎች የጠቀሰው በአምላክ እርዳታ የሚታደሰው ምድር ምን እንደሚመስል ለማሳየት ነው። ይሁን እንጂ ለውጡ በምድሪቱ አፈር ላይ ብቻ የተወሰነ ነበርን? በፍጹም አይደለም!
12. በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ላይ የሚገኘው ትንቢት በሰዎች ላይ ያተኩራል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
12 ኢሳይያስ 35:2 ምድሩ “በደስታና በዝማሬ ሐሤትን” እንደሚያደርግ ይናገራል። አፈሩና ዕፅዋቱ “በደስታና በዝማሬ ሐሤት” እንዳላደረጉ እናውቃለን። ሆኖም ወደ ለምነትና ፍሬያማነት መታደሳቸው ሰዎች ሐሤት እንዲያደርጉና እንዲደሰቱ ሊያደርግ ይችላል። (ዘሌዋውያን 23:37-40፤ ዘዳግም 16:15፤ መዝሙር 126:5, 6፤ ኢሳይያስ 16:10፤ ኤርምያስ 25:30፤ 48:33) ይህ ትንቢት የሚያተኩረው በሰዎች ላይ ስለሆነ በምድሪቱ ላይ ከደረሰው ለውጥ ጋር የሚመጣጠን ለውጥ በሰዎችም ላይ ይኖራል። ስለዚህ ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱ አይሁዶች ላይ በተፈጠረው ለውጥ፣ በተለይም ባገኙት ደስታ ላይ በማተኮር የኢሳይያስን ቃላት የምንመረምርበት ምክንያት አለን።
13, 14. ኢሳይያስ 35:3, 4 በሰዎች ላይ ስለሚኖረው ስለ የትኛው ለውጥ ይተነብያል?
13 በዚህ መሠረት አይሁዶች ነፃ ወጥተው ከባቢሎን ከተመለሱ በኋላ ይህ ትንቢት እንዴት እንደተፈጸመ ለመመልከት የዚህን አበረታች ትንቢት አብዛኛውን ክፍል እንመርምር። ኢሳይያስ በቁጥር 3 እና 4 ላይ ከስደት በተመለሱት ሰዎች ላይ ስለሚኖሩ ሌሎች ለውጦች እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “የደከሙትን እጆች አበርቱ፣ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ። ፈሪ ልብ ላላቸው፦ እነሆ፣ አምላካችሁ በበቀል በእግዚአብሔርም ብድራት ይመጣልና፣ መጥቶ ያድናችኋልና በርቱ፣ አትፍሩ በሉአቸው።”
14 የምድርን ባድማነት ለመለወጥ የሚችለው አምላካችን ይበልጥ የሚያስበው ስለ እኛ ስለ አምላኪዎቹ መሆኑን ማሰብ አያጽናናምን? ግዞተኞቹ አይሁዳውያን ወደፊት ስለሚያጋጥማቸው ሁኔታ እንዲጨነቁ፣ እንዲፈሩ ወይም ተስፋ እንዲቆርጡ አልፈለገም። (ዕብራውያን 12:12) ግዞተኞቹ አይሁዶች የነበሩበትን ሁኔታ አስብ። አምላክ ከተናገራቸው ትንቢቶች ተስፋ ሊያገኙ ቢችሉም ስለ ወደፊቱ ሕይወታቸው ብሩሕ አመለካከት ሊኖራቸው አይችልም ነበር። እንደልባቸው ወዲያ ወዲህ ለማለትና ይሖዋን ለማገልገል ነፃነት ስላልነበራቸው ምንም ዓይነት ብርሃን በማይታይበት ጨለማ ቤት ውስጥ የነበሩ ይመስላሉ።—ከዘዳግም 28:29 እና ከኢሳይያስ 59:10 ጋር አወዳድር።
15, 16. (ሀ) ይሖዋ ከምርኮ ለተመለሱት አይሁዳውያን ስላደረገላቸው ነገር ምን ብለን መደምደም እንችላለን? (ለ) ከምርኮ የተመለሱት አይሁዳውያን በተአምር አካላዊ ፈውስ ለማግኘት ያልጠበቁት ለምን ነበር? ቢሆንም አምላክ ከኢሳይያስ 35:5, 6 ጋር በሚስማማ መንገድ ምን አድርጓል?
15 ይሖዋ ቂሮስ ነፃ እንዲያወጣቸውና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባደረገ ጊዜ ግን ይህ ሁኔታ ተለወጠ! አምላክ ዕውር የነበረ አይሁዳዊ በተአምር ዓይኑን እንደከፈተ ወይም የደንቆሮ ጆሮ እንደከፈተ ወይም የትኛውንም ሽባ እንዳዳነ የሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ነገር አድርጓል። በውድ አገራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና ብርሃንና ነጻነት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
16 ወደ አገራቸው የተመለሱ አይሁዳውያን ይሖዋ እንደዚህ ያለ አካላዊ ፈውስ ይፈጽማል ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር የሚጠቁም ማስረጃ የለም። አምላክ ለይስሐቅ፣ ለሳምሶን ወይም ለዔሊ እንዲህ እንዳላደረገላቸው መገንዘብ አለባቸው። (ዘፍጥረት 27:1፤ መሳፍንት 16:21, 26-30፤ 1 ሳሙኤል 3:2-8፤ 4:15) ነገር ግን አምላክ ሁኔታቸውን የሚለውጠው በምሳሌያዊ ሁኔታ መሆኑን ተስፋ አድርገው ከነበረ ያሰቡት ሳይሳካ ቀርቶ አያዝኑም ነበር። በቁጥር 5 እና 6 ላይ ያለው ትንቢት በምሳሌያዊ ሁኔታ ተፈጽሟል። ኢሳይያስ እንደሚከተለው በማለት በትክክል ተንብዮአል፦ “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።”
ምድሪቱን ገነት ማድረግ
17. ይሖዋ የትኞቹ ለውጦች እንዲከናወኑ አድርጓል?
17 ወደ አገራቸው የተመለሱ አይሁዶች ኢሳይያስ ቀጥሎ እንደጠቀሳቸው ባሉ ሁኔታዎች በደስታ እልል ይሉ ነበር፦ “በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፣ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች፤ ቀበሮ የተኛበት መኖሪያ ልምላሜና ሸምበቆ ደንገልም ይሆንበታል።” (ኢሳይያስ 35:6, 7) በዛሬው ጊዜ በመላው እስራኤል ማየት ባንችልም ይሁዳ ትገኝበት የነበረው ቦታ ከጊዜ በፊት “ገነት” እንደነበረ ማስረጃዎች ያሳያሉ።a
18. ከምርኮ የተመለሱ አይሁዶች አምላክ ለሰጣቸው በረከቶች ምን ምላሽ ሰጥተው ሊሆን ይችላል?
18 አይሁዳዊ ቀሪዎች ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመለሱ ምን ተሰምቷቸው መሆን እንዳለበት አስብ! ይህም የሚደሰቱበት ምክንያት ነበር። የቀበሮና የሌሎች አራዊት መኖሪያ ሆኖ የነበረውን ጠፍ ምድር ማልማት ሊችሉ ነው። አንተስ እንዲህ ባለው ሥራ ብትካፈልና በተለይ ደግሞ አምላክ ጥረትህን ሲባርክ ብትመለከት ደስ አይልህምን?
19. ከባቢሎን ምርኮ መመለሱ በሁኔታዎች ላይ የተመካው እንዴት ነው?
19 ይሁን እንጂ እያንዳንዱ አይሁዳዊ ግዞተኛ ስለፈለገና ስለመሰለው ብቻ ተመልሶ በዚያ አስደሳች መልሶ የማቋቋም ሥራ ለመካፈል ይችላል ማለት አይደለም። አምላክ ለመመለስ የሚያስፈልገውን ብቃት ወስኖ ነበር። በባቢሎናዊና በአረመኔያዊ ሃይማኖት ልማዶች የተበከለ ሰው የመመለስ መብት አያገኝም ነበር። (ዳንኤል 5:1, 4, 22, 23፤ ኢሳይያስ 52:11) ጥበብ በጎደለው አካሄድ የተጠመደ ማንኛውም ሰው የመመለስ መብት አያገኝም። ይህን የመሰለ ሰው ለመመለስ ብቃት አይኖረውም። በሌላ በኩል ደግሞ የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች ያሟሉና በአንጻራዊ ሁኔታ አምላክ ቅዱሳን አድርጎ የሚመለከታቸው ሰዎች ወደ አገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ። በቅድስና ጎዳና መጓዝ ይችላሉ። ኢሳይያስ በቁጥር 8 ላይ ይህንን ግልጽ አድርጎታል፦ “በዚያም ጎዳናና መንገድ ይሆናል እርሱም የተቀደሰ መንገድ ይባላል፤ ንጹሐንም ያልሆኑ አያልፉበትም፣ ለንጹሐን ግን ይሆናል፤ ተላላፊዎችና ሰነፎች እንኳ አይስቱበትም።”
20. አይሁዳውያን ሲመለሱ ምን ነገር መፍራት አያስፈልጋቸውም ነበር? ይህስ ምን ያስከትላል?
20 ከምርኮ የተመለሱት አይሁዳውያን በመንገዳቸው ላይ ጨካኝ የሆኑ ሰዎች ወይም ወንበዴዎች እንዳያጋጥሟቸው መፍራት አያስፈልጋቸውም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ከተዋጁት ሕዝቦቹ ጋር አብረው እንዲጓዙ አይፈቅድም። ስለዚህ ብሩህ አመለካከትና አስደሳች ተስፋ ይዘው ሊጓዙ ይችላሉ። ኢሳይያስ ይህንን ትንቢት ሲደመድም ምን ብሎ እንደገለጸ ልብ በል፦ “አንበሳም አይኖርበትም፣ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፣ ከዚያም አይገኙም፤ የዳኑት ግን በዚያ ይሄዳሉ፤ እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፣ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ።”—ኢሳይያስ 35:9, 10
21. ከዚህ በፊት የተፈጸመው ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 በዛሬው ጊዜ እንዴት ይፈጸማል ብለን መጠባበቅ አለብን?
21 እንዴት ያለ ድንቅ ትንቢታዊ መግለጫ ነው! ይህን ትንቢት ከእኛ ሁኔታ ወይም ከወደፊቱ ሕይወታችን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለውና ያለፈ ታሪክ የሚገልጽ ውበት የተላበሰ አገላለጽ እንደሆነ አድርገን ብቻ መመልከት አይገባንም። ይህ ትንቢት ባለንበት ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች ላይ በአስደናቂ ሁኔታ በመፈጸም ላይ መሆኑ የተረጋገጠ ሐቅ ነው። ስለዚህ እያንዳንዳችንን የሚነካ ትንቢት ነው። እያንዳንዳችን በደስታ እልል እንድንል የሚገፋፋን ጠንካራ ምክንያት የሚሰጠን ትንቢት ነው። የአሁኑንና የወደፊቱን ሕይወትህን የሚነኩ እነዚህ የትንቢቱ ገጽታዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ተብራርተዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አግሮኖሚስት ዋልተር ሲ ሎደርሚልክ (የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅትን በመወከል) በአካባቢው ካደረጉት ጥናት እንዲህ በማለት ደምድመዋል፦ “ይህ ምድር ከጊዜ በፊት ገነት ነበር።” በተጨማሪም “እስከ ሮማውያን ጊዜ ድረስ” በአየሩ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዳልነበረና “ከጊዜ በፊት ለም የነበረውን ምድር የተካው ‘በረሀ’ ተፈጥሮ ሳይሆን ሰው ሠራሽ መሆኑን” ገልጸዋል።
ታስታውሳለህን?
◻ ኢሳይያስ ምዕራፍ 35 በመጀመሪያ የተፈጸመው መቼ ነበር?
◻ የትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ ምን አስከትሏል?
◻ ይሖዋ ኢሳይያስ 35:5, 6ን የፈጸመው እንዴት ነው?
◻ ከምርኮ የተመለሱ አይሁዳውያን በምድራቸውና በራሳቸው ላይ ምን ለውጦች ደርሰውባቸዋል?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥንት በኤዶማውያን ሥር የነበረችው የፔትራ ከተማ ፍርስራሽ
[ምንጭ]
Garo Nalbandian
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አይሁዳውያን በግዞት ሳሉ አብዛኛው የይሁዳ ምድር እንደ ድብና አንበሳ ያሉ ኃይለኛ አራዊት የሚርመሰመሱበት ምድረ በዳ ሆኖ ነበር
[ምንጭ]
Garo Nalbandian
ድብና አንበሳ፦ Safari-Zoo of Ramat-Gan, Tel Aviv