ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ
“እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፣ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ [“በይሖዋ፣” አዓት] የተተከለች ናት።”—ዕብራውያን 8:1, 2
1. አምላክ ለኃጢአተኛው የሰው ዘር ምን ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጓል?
ይሖዋ አምላክ ለሰው ልጆች ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሣ የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ አንድ መሥዋዕት አዘጋጅቷል። (ዮሐንስ 1:29፤ 3:16) ይህም የበኩር ልጁን ሕይወት ከሰማይ ማርያም ወደምትባል አንዲት ድንግል አይሁዳዊት ማኅፀን ማዛወር የሚጠይቅ ነበር። የይሖዋ መልአክ ማርያም የምትጸንሰው ልጅ “ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ” እንደሚባል በግልጽ ነግሯት ነበር። (ሉቃስ 1:34, 35) የማርያም እጮኛ ለነበረው ዮሴፍ፣ ኢየሱስ የሚፀነሰው በተአምራዊ መንገድ እንደሆነና እርሱም ‘ሕዝቡን ከኃጢአታቸው እንደሚያድናቸው’ ተነግሮት ነበር።—ማቴዎስ 1:20, 21
2. ኢየሱስ ዕድሜው 30 ዓመት ገደማ ሲሆን ምን አደረገ? ለምንስ?
2 ኢየሱስ እያደገ ሲሄድ በተዓምራዊ መንገድ እንደተወለደ ከሚገልጹት ከእነዚህ እውነታዎች አንዳንዶቹን ተረድቶ መሆን አለበት። ሰማያዊ አባቱ በምድር ላይ ሊሠራው የሚገባ ሕይወት አድን ሥራ እንደሰጠው ያውቅ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ የ30 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ለመጠመቅ የአምላክ ነቢይ ወደነበረው ወደ ዮሐንስ መጣ።—ማርቆስ 1:9፤ ሉቃስ 3:23
3. (ሀ) ኢየሱስ “መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም” ሲል ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ኢየሱስ ተከታዮቹ ለሚሆኑት ሁሉ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
3 ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ይጸልይ ነበር። (ሉቃስ 3:21) ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም፣ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ” ሲል እንደጠቆመው ከዚህ ጊዜ አንሥቶ በመዝሙር 40:6-8 ላይ የሚገኙትን ቃላት በሕይወቱ ውስጥ ሠርቶባቸዋል። (ዕብራውያን 10:5) ኢየሱስ በዚህ መንገድ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ዘወትር የእንስሳት መሥዋዕት እየቀረበ እንዲቀጥል አምላክ ‘እንደማይፈልግ’ መረዳቱን አሳይቷል። ከዚህ ይልቅ መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበውን ፍጹም ሰብዓዊ አካል አምላክ እንዳዘጋጀለት ተገንዝቦ ነበር። ይህም የእንስሳት መሥዋዕት የማቅረቡ አስፈላጊነት እንዲያከትም የሚያደርግ ነበር። ኢየሱስ ለአምላክ ፈቃድ ራሱን ለማስገዛት ያለውን ልባዊ ፍላጎት ሲገልጽም እንዲህ በማለት ጸሎቱን ቀጥሏል፦ “በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፣ አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ።” (ዕብራውያን 10:7) ኢየሱስ በዚያ ዕለት ያሳየው ድፍረትና ራስ ወዳድነት የሌለበት አምልኮታዊ ፍቅር ወደፊት ደቀ መዛሙርቱ ለሚሆኑ ሁሉ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!—ማርቆስ 8:34
4. ኢየሱስ ራሱን ሲያቀርብ አምላክ እንደተስማማ ያሳየው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ሲጠመቅ ያቀረበውን ጸሎት አምላክ እንደተቀበለው አሳይቷልን? ኢየሱስ ከመረጣቸው ሐዋርያት አንዱ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፣ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም፣ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ፦ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።”—ማቴዎስ 3:16, 17፤ ሉቃስ 3:21, 22
5. የቤተ መቅደሱ መሠዊያ ጥላ የሆነው ለምን ነገር ነው?
5 አምላክ የኢየሱስ አካል መሥዋዕት ሆኖ እንዲቀርብ መስማማቱ በመንፈሳዊ አባባል በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ከነበረው የሚበልጠው መሠዊያ እውን እንደሆነ ያሳያል። እንስሳት ይቀርቡበት የነበረው መሠዊያ፣ አምላክ የኢየሱስን ሰብዓዊ ሕይወት እንደ መሥዋዕት አድርጎ ለመቀበል የነበረውን “ፈቃድ” ወይም ዝግጅት ለሚያመለክተው መንፈሳዊ መሠዊያ ጥላ ነበር። (ዕብራውያን 10:10) ሐዋርያው ጳውሎስ ለመሰል ክርስቲያኖች “መሠዊያ አለን፣ ከእርሱም ሊበሉ ድንኳኒቱን [ወይም ቤተ መቅደሱን] የሚያገለግሉ መብት የላቸውም” ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (ዕብራውያን 13:10) በሌላ አባባል እውነተኛ ክርስቲያኖች አብዛኞቹ አይሁዳውያን ካህናት ከናቁት ከፍተኛ የኃጢአት ማስተሠሪያ መሥዋዕት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
6. (ሀ) ኢየሱስ ሲጠመቅ እውን የሆነው ነገር ምንድን ነበር? (ለ) መሲሕ ወይም ክርስቶስ ማለት ምን ማለት ነው?
6 ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱ አምላክ መላውን የመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት ማቋቋሙን የሚያመለክት ሲሆን በዚህ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት ሆኖ የሚያገለግለው ኢየሱስ ነው። (ሥራ 10:38፤ ዕብራውያን 5:5) ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ በመንፈስ አነሣሽነት ይህ ታላቅ ክንውን የተፈጸመው ‘ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት’ መሆኑን ለይቶ አመልክቷል። (ሉቃስ 3:1-3) የጢባርዮስ ቄሣር አሥራ አምስተኛ ዓመት የሞላው በ29 እዘአ ሲሆን ይህም ልክ ንጉሥ አርጤክስስ የኢየሩሳሌም ቅጥር እንዲሠራ ትእዛዝ ካወጣበት ጊዜ የጀመሩት 69 የዓመታት ሳምንታት ወይም 483 ዓመታት የተጠናቀቁበት ጊዜ ነበር። (ነህምያ 2:1, 5-8) በትንቢቱ መሠረት ‘አለቃው መሲሕ’ የሚመጣው ልክ በዚሁ ዓመት ነበር። (ዳንኤል 9:25) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ብዙ አይሁዳውያን ይህን ያውቁ ነበር። ሉቃስ “ሕዝቡ” የመሲሕን ወይም የክርስቶስን መምጣት “ይጠባበቅ ነበር” በማለት ዘግቧል። መሲሕና ክርስቶስ የሚሉት የማዕረግ ስሞች “የተቀባ” የሚል ተመሳሳይ ትርጉም ካላቸው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የመጡ ናቸው።—ሉቃስ 3:15 የ1980 ትርጉም
7. (ሀ) አምላክ ‘ቅድስተ ቅዱሳኑን’ የቀባው መቼ ነበር? ይህስ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ሌላ ምን ነገር አግኝቷል?
7 ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት የአምላክ ሰማያዊ መኖሪያ በታላቁ የመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ ‘ቅድስተ ቅዱሳን’ እንዲሆን ተቀብቷል ወይም ተለይቷል። (ዳንኤል 9:24) ‘በሰው ሳይሆን በይሖዋ የተተከለው እውነተኛው ድንኳን [ወይም ቤተ መቅደስ]’ ሥራውን ጀመረ። (ዕብራውያን 8:2) ከዚህም በተጨማሪ ሰው የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ ዳግም ተወልዷል። (ከዮሐንስ 3:3 ጋር አወዳድር።) ይህም አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ልጁ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም” ንጉሥና ሊቀ ካህን ሆኖ እንዲያገለግል ወደ ሰማያዊ ሕይወት ይመልሰዋል ማለት ነው።—ዕብራውያን 6:20፤ መዝሙር 110:1, 4
በሰማይ የሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን
8. የአምላክ ሰማያዊ ዙፋን ምን አዲስ መልክ ይዟል?
8 ኢየሱስ በተጠመቀበት ዕለት የአምላክ ሰማያዊ ዙፋን አዲስ መልክ ይዟል። አምላክ የዓለምን ኃጢአት ለማስተሠረይ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት በመሥዋዕትነት እንዲቀርብ ማድረጉ ከሰው ኃጢአተኛነት ጋር ሲነጻጸር የአምላክ ቅድስና ምን ያህል ከፍ ያለ መሆኑን የሚያጎላ ነው። በተጨማሪም አምላክ የሚቀርበውን መማጸኛ ወይም የሥርየት መለመኛ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ ምሕረቱን በጉልህ የሚያንጸባርቅ ነው። በመሆኑም በሰማይ የሚገኘው የአምላክ ዙፋን ሊቀ ካህናቱ ጥላነት ባለው መንገድ ኃጢአትን ለማስተሠረይ በዓመት አንድ ጊዜ የእንስሳ ደም ይዞ ይገባበት እንደነበረው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ሆኗል።
9. (ሀ) በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳን መካከል የነበረው መጋረጃ ምን ያመለክታል? (ለ) ኢየሱስ የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ መጋረጃ አልፎ የገባው እንዴት ነው?
9 ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየው መጋረጃ የኢየሱስን ሥጋዊ አካል የሚያመለክት ነበር። (ዕብራውያን 10:19, 20) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ በተመላለሰበት ወቅት ወደ አባቱ እንዳይሄድ ያገደው ነገር ይህ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:50) ኢየሱስ ሲሞት “የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።” (ማቴዎስ 27:51) ይህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንዳይገባ ያገደው ነገር እንደተወገደ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። ከሦስት ቀናት በኋላ ይሖዋ አምላክ አንድ አስገራሚ ተአምር ፈጸመ። ኢየሱስን ሥጋና ደም ያለው ሟች ሰው አድርጎ ሳይሆን “ለዘላለም የሚኖር” ክብራማ መንፈሳዊ ፍጡር አድርጎ ከሞት አስነሣው። (ዕብራውያን 7:24) ከአርባ ቀናት በኋላ ኢየሱስ ወደ ሰማይ በማረግ ‘በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይታይ ዘንድ’ ወደ እውነተኛይቱ “ቅድስተ ቅዱሳን” ገብቷል።—ዕብራውያን 9:24
10. (ሀ) ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ የመሥዋዕቱን ዋጋ ካቀረበ በኋላ ምን ነገር ተፈጸመ? (ለ) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ መቀባታቸው ለእነርሱ ምን ትርጉም አለው?
10 ኢየሱስ የዓለምን ኃጢአት ለማስተሠረይ ያፈሰሰውን ደም ዋጋ አምላክ ተቀብሎታልን? በእርግጥ ተቀብሎታል። ልክ ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ ከ50 ቀናት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ይህን የሚያረጋግጥ ነገር ተፈጽሟል። በኢየሩሳሌም አንድ ላይ ተሰብስበው በነበሩት 120 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ የአምላክ መንፈስ ቅዱስ ፈሰሰ። (ሥራ 2:1, 4, 33) በዚህ ወቅት እንደ ሊቀ ካህናታቸው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ የመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ ‘መንፈሳዊ መሥዋዕትን የሚያቀርቡ ቅዱሳን ካህናት’ ሆነው እንዲያገለግሉ ተቀቡ። (1 ጴጥሮስ 2:5) ከዚህም በላይ እነዚህ ቅቡዓን አንድ አዲስ ብሔር ማለትም መንፈሳዊ እስራኤላውያንን ያቀፈ የአምላክ “ቅዱስ ሕዝብ” ሆነው ተቋቋሙ። ከዚህ ጊዜ ወዲህ በኤርምያስ 31:31 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ስለ “አዲስ ቃል ኪዳን” የሚናገረውን የመሳሰሉት በእስራኤል ላይ የተነገሩ መልካም ትንቢቶች ሁሉ እውነተኛ ‘የአምላክ እስራኤል’ በሆነው በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።—1 ጴጥሮስ 2:9፤ ገላትያ 6:16
የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሌሎች ገጽታዎች
11, 12. (ሀ) የካህናቱ አደባባይ ኢየሱስን በሚመለከት ለምን ነገር ጥላ ነበር? ቅቡዓን ተከታዮቹንስ በሚመለከት ምን ትርጉም ነበረው? (ለ) በመታጠቢያው ሰን የተመሰለው ምንድን ነው? እርሱስ ዛሬ እየተሠራበት ያለው እንዴት ነው?
11 ምንም እንኳ ቅድስተ ቅዱሳኑ የአምላክ ዙፋን የሚገኝበትን “ሰማይ” የሚያመለክት ቢሆንም ሌሎቹ የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ገጽታዎች በሙሉ በምድር ላይ ከሚገኙ ነገሮች ጋር የተያያዙ ናቸው። (ዕብራውያን 9:24) በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ መሠዊያውን እንዲሁም ካህናቶቹ ቅዱስ አገልግሎት ከማከናወናቸው በፊት የሚታጠቡበትን የውኃ ማጠራቀሚያ ትልቅ ሰን የያዘው የውስጠኛው የካህናት አደባባይ ይገኝ ነበረ። በአምላክ የመንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ እነዚህ ነገሮች ምን ያመለክታሉ?
12 የውስጠኛው የካህናት አደባባይ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጽምና ያለው ሰብዓዊ የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን ከኃጢአት ነጻ እንደነበር ለማመልከት የቆመ ነው። የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ባላቸው እምነት መሠረት እንደ ጻድቃን ይቆጠራሉ። በዚህ መንገድ አምላክ ከኃጢአት ነፃ እንደሆኑ አድርጎ ሊያያቸው ይችላል። (ሮሜ 5:1፤ 8:1, 33) ስለዚህ ይህ አደባባይ እያንዳንዱ የቅዱሳን ካህናቱ አባላት እንደ ጻድቅ ሆነው በመቆጠር በአምላክ ፊት ያገኙትን ቦታ ያመለክታል። ያም ሆኖ ግን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ፍጹማን ያልሆኑና ኃጢአት ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች ናቸው። በአደባባዩ መካከል የሚገኘው የውኃ ማጠራቀሚያ ሰን ሊቀ ካህናቱ ቅዱሳን ካህናቱን ደረጃ በደረጃ ለማንጻት የሚጠቀምበትን የአምላክ ቃል ያመለክታል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለዚህ የማንጻት ሂደት ራሳቸውን በማስገዛታቸው አምላክን የሚያስከብርና ሌሎችም ወደ ንጹሕ አምልኮው እንዲመጡ የሚስብ ግርማ አግኝተዋል።—ኤፌሶን 5:25, 26፤ ከሚልክያስ 3:1-3 ጋር አወዳድር።
ቅድስት
13, 14. (ሀ) የቤተ መቅደሱ ቅድስት ኢየሱስንና ቅቡዓን ተከታዮቹን በሚመለከት ምን ትርጉም አለው? (ለ) የወርቅ መቅረዙ ምን ያመለክታል?
13 የቤተ መቅደሱ የመጀመሪያው ክፍል ከአደባባዩ የተሻለ ሁኔታን የሚያመለክት ነው። ፍጹም ሰው የነበረውን ኢየሱስ ክርስቶስን በሚመለከት ወደ ሰማይ ለመመለስ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሆኖ እንደገና መወለዱን የሚያሳይ ትርጉም አለው። ቅቡዓን ተከታዮችም በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ ባላቸው እምነት መሠረት እንደ ጻድቃን ከተቆጠሩ በኋላ የአምላክ መንፈስ በእነርሱ ላይ በዚህ ለየት ያለ መንገድ ይሠራል። (ሮሜ 8:14-17) “ከውኃና [ጥምቀታቸውን ያመለክታል] ከመንፈስ” መንፈሳዊ የአምላክ ልጆች ሆነው ‘ዳግመኛ ይወለዳሉ።’ እስከ ሞት ድረስ በታማኝነት ከጸኑ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በመሆን ለሰማያዊ ሕይወት ከሞት የመነሣት ተስፋ ያገኛሉ።—ዮሐንስ 3:5, 7፤ ራእይ 2:10
14 በምድራዊ ቤተ መቅደስ ቅድስት ውስጥ ያገለግሉ የነበሩትን ካህናት ከቤተ መቅደሱ ውጪ የነበሩ አምላኪዎች አያዩአቸውም ነበር። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች የማያገኙትን ወይም ሙሉ በሙሉ የማይረዱትን መንፈሳዊ ሁኔታ ያገኛሉ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የነበረው የወርቅ መቅረዝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያገኙትን የእውቀት ብርሃን ያመለክታል። በመብራቶቹ ውስጥ እንደሚጨመረው ዘይት ሁሉ የአምላክ ቅዱስ መንፈስም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብርሃን እንዲፈነጥቅ አድርጓል። ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ ያገኙትን እውቀት ለራሳቸው ብቻ ይዘው አይቀመጡም። ከዚህ ይልቅ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። . . . መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት የተናገረውን ኢየሱስን ይታዘዛሉ።—ማቴዎስ 5:14, 16
15. በገጸ ኅብስት ገበታው ላይ በሚገኘው ኅብስት የተመሰለው ምንድን ነው?
15 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚህ የእውቀት ብርሃን መመላለሳቸውን ለመቀጠል በገጸ ኅብስት ገበታው ላይ በሚገኘው ኅብስት ከተመሰለው ማዕድ ዘወትር መመገብ ይኖርባቸዋል። ዋነኛው የመንፈሳዊ ምግባቸው ምንጭ የአምላክ ቃል ሲሆን ይህንኑ በየዕለቱ ለማንበብና ባነበቡት ላይ ለማሰላሰል ይጥራሉ። ኢየሱስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያው’ አማካኝነት ‘ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ’ እንደሚያቀርብላቸው ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 24:45) ይህ “ባሪያ” በየትኛውም ወቅት በምድር ላይ የሚገኙትን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን በጠቅላላ የሚያመለክት ነው። ክርስቶስ ይህን የቅቡዓን ቡድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ ለማሳወቅና በዚህ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ኑሮ ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል ስለሚቻልበት መንገድ ወቅታዊ መመሪያ ለመስጠት ተጠቅሞበታል። በዚህ ምክንያት ቅቡዓን ክርስቲያኖች እነዚህን ከመሰሉት መንፈሳዊ ዝግጅቶች በሙሉ በአድናቆት ይመገባሉ። ይሁን እንጂ የመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሕልውና የአምላክን እውቀት ወደ አእምሮና ልባቸው በማስገባት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ኢየሱስ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች አምላክ የገለጠውን ፈቃዱን ለመፈጸም በየዕለቱ የሚያደርጉት ጥረት እርካታ ይሰጣቸዋል።
16. በዕጣኑ መሠዊያ ላይ በሚቀርበው አገልግሎት የተመሰለው ምንድን ነው?
16 ካህኑ በቅድስት ውስጥ በሚገኘው የዕጣን መሠዊያ ላይ ጠዋትና ማታ ለአምላክ ያጥን ነበር። በተመሳሳይ ወቅትም ካህናት ያልሆኑ አምላኪዎች በቤተ መቅደሱ የውጨኛው አደባባይ ቆመው ወደ አምላክ ይጸልዩ ነበር። (ሉቃስ 1:8-10) መጽሐፍ ቅዱስ ‘ዕጣን’ “የቅዱሳን ጸሎት” እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 5:8) መዝሙራዊው ዳዊት “ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበለኝ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 141:2) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ ይሖዋ በጸሎት ለመቅረብ ያገኙትን መብት እንደ ውድ ሀብት ይንከባከቡታል። ከልብ የሚንቆረቆሩ ጸሎቶች ጣፋጭ ሽታ እንዳለው ዕጣን ናቸው። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎችን ለማስተማር በአንደበታቸውም በመጠቀም አምላክን ያወድሳሉ። በተለይ መከራዎችን ተጋፍጠው መጽናታቸውና ፈታኝ ሁኔታዎችን በንጹሕ አቋም መወጣታቸው አምላክን የሚያስደስት ነው።—1 ጴጥሮስ 2:20, 21
17. ሊቀ ካህናቱ በስርየት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የመግባቱ ትንቢታዊ ጥላ ፍጻሜ ምንድን ነው?
17 የእስራኤል ሊቀ ካህናት በስርየት ቀን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ገብቶ ፍም በያዘው የወርቅ ጥና ላይ ዕጣን ማጨስ ነበረበት። ይህን ማድረግ የነበረበት የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን ደም ከማምጣቱ በፊት ነበር። በዚህ ትንቢታዊ ጥላ ፍጻሜ መሠረት ሰው የነበረው ኢየሱስ ሕይወቱን ለኃጢአታችን ዘላቂ መሥዋዕት አድርጎ በይሖዋ አምላክ ፊት ከማቅረቡ በፊት ንጹሕ አቋሙን ሙሉ በሙሉ ጠብቋል። በዚህ መንገድ አንድ ፍጹም ሰው ሰይጣን ምንም ዓይነት ፈተና ቢያመጣበትም በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ሊገኝ እንደሚችል አሳይቷል። (ምሳሌ 27:11) ኢየሱስ ፈተና በገጠመው ጊዜ “ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት።” (ዕብራውያን 5:7) በዚህ መንገድ ይሖዋ ጻድቅና መብት ያለው የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን አስመስክሯል። አምላክ ኢየሱስን ከሞት በማስነሣትና የማይጠፋ ሰማያዊ ሕይወት በማጎናጸፍ መልሶ ክሶታል። ኢየሱስ ይህ ከፍተኛ ቦታ ከተሰጠው በኋላ ወደ ምድር በመጣበት ሁለተኛ ዓላማ ላይ ያተኩራል፤ ይኸውም ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኛ ሰዎችን ከአምላክ ጋር ማስታረቅ ነው።—ዕብራውያን 4:14-16
የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የተጎናጸፈው ታላቅ ክብር
18. ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱን ታላቅ ክብር ያላበሰው እንዴት ነው?
18 ይሖዋ “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። (ሐጌ 2:9) ኢየሱስ የማይጠፋ ሕይወት ያለው ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኖ ከሞት እንዲነሣ በማድረግ ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ከፍተኛ ክብር እንዲላበስ አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ “ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን” ለማምጣት በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ይገኛል። (ዕብራውያን 5:9) ይህን ዓይነት ታዛዥነት በማሳየት ቀዳሚ የሆኑት በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት 120 ደቀ መዛሙርት ናቸው። የራእይ መጽሐፍ የእነዚህ የእስራኤል መንፈሳዊ ልጆች ቁጥር በመጨረሻ 144,000 እንደሚሞላ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 7:4) ከእነርሱ መካከል ብዙዎቹ ከሞቱ በኋላ በሰው ዘር ተራ መቃብር ውስጥ ሆነው ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ የሚገኝበትን ጊዜ መጠበቅ አስፈልጓቸው ነበር። በዳንኤል 4:10-17, 20-27 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ትንቢታዊ የዘመን ስሌት ኢየሱስ በጠላቶቹ መካከል መግዛት የሚጀምርበት ጊዜ 1914 እንደሆነ ይጠቁማል። (መዝሙር 110:2) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከአሥርተ ዓመታት በፊት ይህን ዓመት በጉጉት ሲጠባበቁ ቆይተዋል። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና እርሱን ተከትለው የመጡት ሌሎች ወዮታዎች በእርግጥም ኢየሱስ በ1914 እንደ ነገሠ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ሆነዋል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ‘ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ’ ስለደረሰ ኢየሱስ “ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” የሚለውን ቃል በሞት አንቀላፍተው ለሚገኙት ቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱ ይፈጽምላቸዋል።—1 ጴጥሮስ 4:17፤ ዮሐንስ 14:3
19. የ144,000ዎቹ ቀሪዎች ወደ ሰማያዊው ቅድስተ ቅዱሳን የሚገቡት እንዴት ነው?
19 የቅዱሳን ካህናቱ 144,000 አባላት በሙሉ ግንባራቸው ታትሞ ወደ ሰማያዊ ቤታቸው አልተሰበሰቡም። የእነርሱ ቀሪዎች እስከ ዛሬም ድረስ በመንፈሳዊ ሁኔታ ከአምላክ ቅዱስ መኖሪያ ‘በመጋረጃ’ ማለትም በሥጋዊ አካላቸው ተጋርደው በቅድስት ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች እምነታቸውን ጠብቀው ሲሞቱ የማይጠፋ ሕይወት ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት በመሆን በቅጽበት ከሞት ተነሥተው በሰማይ ከሚገኙቱ የ144,000 አባላት ጋር ይቀላቀላሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:51-53
20. የቅዱሳን ካህናቱ ቀሪዎች በአሁኑ ጊዜ ምን ወሳኝ ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
20 በሰማይ ካለው ከታላቁ ሊቀ ካህናት ጋር እነዚህን የሚያክሉ ካህናት በማገልገላቸው የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ተጨማሪ ክብር አግኝቷል። እስከዚያው ድረስ ግን ከቅዱሳን ካህናቱ መካከል ገና በምድር ላይ ያሉት ጠቃሚ ሥራ እያከናወኑ ነው። በሐጌ 2:7 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው በዚህ የስብከት ሥራ አማካኝነት በፍርድ መልእክቶቹ ‘አሕዛብን እያናወጠ ነው።’ የዚያኑ ያህል ደግሞ ‘የአሕዛብ የተመረጠ ዕቃ’ ተብለው የተጠሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ አምላኪዎች ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ እየጎረፉ ነው። እነዚህ ሰዎች በፈጣሪ የአምልኮ ዝግጅት ውስጥ ምን ቦታ ይኖራቸዋል? ታላቁ የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ወደፊትስ ምን ክብር ያገኛል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? እነዚህን ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ ኢየሱስ በ29 እዘአ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
◻ ከ29 እዘአ ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለው የትኛው ዝግጅት ነው?
◻ ቅድስቱና ቅድስተ ቅዱሳኑ ምን ያመለክታሉ?
◻ ታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ከፍተኛ ክብር የተጎናጸፈው እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በ29 እዘአ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት ታላቁ የአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሥራውን ጀመረ