የጥናት ርዕስ 10
መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ
ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ተከተል’
“ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።”—ሉቃስ 9:23
ዓላማ
ይህ ርዕስ፣ ሁላችንም ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል ምን ትርጉም እንዳለው እንድናስብ ይረዳናል። በተለይ ደግሞ በቅርቡ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ታማኝነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ሊረዳቸው ይችላል።
1-2. አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላ የትኞቹን በረከቶች ያገኛል?
ተጠምቆ የይሖዋን ቤተሰብ መቀላቀል በጣም ያስደስታል። ይህን ውድ መብት ያገኙ ሁሉ፣ መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ይሖዋ በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ እንደሚስማሙ ጥያቄ የለውም፦ “በቅጥር ግቢዎችህ ይኖር ዘንድ የመረጥከውና ያቀረብከው ሰው ደስተኛ ነው።”—መዝ. 65:4
2 ይሖዋ ወደ ቅጥር ግቢዎቹ የሚያስገባው ሁሉንም ሰው አይደለም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ የሚቀርበው ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንደሚፈልጉ ወደሚያሳዩ ሰዎች ነው። (ያዕ. 4:8) ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ስትጠመቅ ወደ ይሖዋ ልዩ በሆነ መንገድ ትቀርባለህ። ከተጠመቅክ በኋላ ይሖዋ ‘ማስቀመጫ እስክታጣ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልህ’ መተማመን ትችላለህ።—ሚል. 3:10፤ ኤር. 17:7, 8
3. ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ ክርስቲያኖች ምን ከባድ ኃላፊነት አለባቸው? (መክብብ 5:4, 5)
3 እርግጥ ነው፣ ጥምቀት የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው። ይህን እርምጃ ከወሰድክ በኋላ ፈተና ወይም መከራ ቢያጋጥምህም እንኳ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። (መክብብ 5:4, 5ን አንብብ።) የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንደመሆንህ መጠን የኢየሱስን አርዓያ እና ትእዛዛቱን የቻልከውን ያህል በጥብቅ ለመከተል ጥረት ታደርጋለህ። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጴጥ. 2:21) ይህ ርዕስ በዚህ ረገድ ይረዳሃል።
ፈተና እና መከራ ቢያጋጥምህም ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ተከተል’
4. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “የመከራ እንጨት” ይሸከማሉ ሲባል ምን ማለት ነው? (ሉቃስ 9:23)
4 ከተጠመቅክ በኋላ ሕይወትህ አልጋ በአልጋ አይሆንም። እንዲያውም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ “የመከራ እንጨት” እንደሚሸከሙ በግልጽ ተናግሯል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ “በየዕለቱ” ነው። (ሉቃስ 9:23ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ሲል ተከታዮቹ ሁልጊዜ መከራ እንደሚደርስባቸው መግለጹ ነበር? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ፣ ተከታዮቹ ብዙ በረከቶች ቢያገኙም ተፈታታኝ ሁኔታዎችም እንደሚያጋጥሟቸው መግለጹ ነበር። አንዳንዶቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ደግሞ በጣም ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ።—2 ጢሞ. 3:12
5. ኢየሱስ መሥዋዕት የሚከፍሉ ሰዎች ምን በረከት እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል?
5 እስካሁንም ቤተሰቦችህ ተቃውመውህ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ስትል አንዳንድ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገህ ይሆናል። (ማቴ. 6:33) ከሆነ፣ ይሖዋ በታማኝነት ያከናወንከውን ሥራ እንደተመለከተ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዕብ. 6:10) ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በሕይወትህ ተመልክተህ ይሆናል፦ “ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።” (ማር. 10:29, 30) ያገኘሃቸው በረከቶች መሥዋዕት ካደረግካቸው ነገሮች በእጅጉ እንደሚበልጡ ምንም ጥያቄ የለውም።—መዝ. 37:4
6. ከተጠመቅክ በኋላ ‘ከሥጋ ምኞት’ ጋር መታገልህን መቀጠል የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
6 ከተጠመቅክ በኋላም ‘ከሥጋ ምኞት’ ጋር መታገል ይኖርብሃል። (1 ዮሐ. 2:16) ምክንያቱም የአዳም ዘር እንደመሆንህ መጠን ከተጠመቅክ በኋላም ኃጢአተኛ ነህ። አንዳንድ ጊዜ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ብሏል፦ “በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በሰውነቴ ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮም 7:22, 23) የኃጢአት ዝንባሌ ያለህ መሆኑ ተስፋ ሊያስቆርጥህ ይችላል። ሆኖም ራስህን ለይሖዋ በወሰንክበት ወቅት ለእሱ በገባኸው ቃል ላይ ማሰላሰልህ ፈተናን ለመቋቋም ያለህን ቁርጠኝነት ያጠናክረዋል። ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ፈተና ሲያጋጥምህ ይረዳሃል። እንዴት?
7. ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ለእሱ ምንጊዜም ታማኝ ለመሆን የሚረዳህ እንዴት ነው?
7 ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ራስህን ትክዳለህ። ይህም ሲባል ይሖዋን የሚያሳዝኑ ፍላጎቶችንና ምኞቶችን እንቢ ትላለህ ማለት ነው። (ማቴ. 16:24) ስለዚህ ፈተና ሲያጋጥምህ ‘ምን ላድርግ?’ የሚለውን ለመወሰን ብዙ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግህም። ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ፣ ይኸውም ለይሖዋ ያለህን ታማኝነት መጠበቅ እንደሆነ አስቀድመህ ወስነሃል። ይሖዋን ለማስደሰት ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ይዘህ ትቀጥላለህ። እንደ ኢዮብ ትሆናለህ ሊባል ይችላል። ኢዮብ በጣም ከባድ መከራ ቢደርስበትም “ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ቁርጥ አቋሙን ገልጿል።—ኢዮብ 27:5
8. ራስህን ስትወስን ባቀረብከው ጸሎት ላይ ማሰላሰልህ ፈተናን ለማሸነፍ የሚረዳህ እንዴት ነው?
8 ለይሖዋ ራስህን ስትወስን ባቀረብከው ጸሎት ላይ ማሰላሰልህ ማንኛውንም ፈተና ለማሸነፍ ብርታት ይሰጥሃል። ለምሳሌ ባለትዳር የሆነች ሴት ታሽኮረምማለህ? በፍጹም! እንዲህ ያለውን ነገር እንደማታደርግ ቀድሞውንም ወስነሃል። መጀመሪያውኑም ተገቢ ያልሆነ ስሜት በልብህ ውስጥ እንዲያቆጠቁጥ ስለማትፈቅድ እንዲህ ያለው ስሜት ሥር ከሰደደ በኋላ ለማስወገድ መታገል አያስፈልግህም። ‘ከክፉዎች መንገድ ፈቀቅ ትላለህ።’—ምሳሌ 4:14, 15
9. ራስህን ስትወስን ባቀረብከው ጸሎት ላይ ማሰላሰልህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስቀደም የሚረዳህስ እንዴት ነው?
9 አዘውትረህ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ እንቅፋት የሚሆን ሥራ ብታገኝስ? አሁንም ቢሆን ‘ምን ላድርግ?’ ብለህ ግራ አትጋባም። እንዲህ ያለውን ሥራ እንደማትቀበል ሥራውን ከማግኘትህ ከረጅም ጊዜ በፊት ወስነሃል። በመሆኑም መጥፎ ውሳኔ ካደረግክ በኋላ ውሳኔው ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ አትታገልም። ኢየሱስ አባቱን ለማስደሰት ቁርጠኛ እንደነበረ ሁሉ አንተም ራስህን የወሰንክለትን አምላክ የሚያሳዝንን ማንኛውንም ነገር ወዲያውኑ አጥብቀህ ትቃወማለህ።—ማቴ. 4:10፤ ዮሐ. 8:29
10. ይሖዋ ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ እንድትከተል’ የሚረዳህ እንዴት ነው?
10 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የሚያጋጥምህ መከራና ፈተና ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ለመከተል’ ያለህን ቁርጠኝነት ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጥሃል። እንዲህ ስታደርግ ይሖዋ እንደሚረዳህ መተማመን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮ. 10:13
ኢየሱስን ያለማቋረጥ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?
11. ኢየሱስን ያለማቋረጥ መከተል የምትችልበት አንዱ ግሩም መንገድ የትኛው ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 ኢየሱስ ቀናተኛ ነበር፤ እንዲሁም ወደ ይሖዋ አዘውትሮ በመጸለይ ከእሱ ጋር ተቀራርቦ ኖሯል። (ሉቃስ 6:12) አንተም ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ያለማቋረጥ ለመከተል ከሚረዱህ ነገሮች አንዱ ወደ ይሖዋ እንድትቀርብ የሚረዱህን ነገሮች የማድረግ ልማድ ማዳበር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል” ይላል። (ፊልጵ. 3:16) አልፎ አልፎ፣ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን ቅዱስ አገልግሎት ለማስፋት ጥረት ስላደረጉ ወንድሞችና እህቶች የሚገልጽ ተሞክሮ ትሰማ ይሆናል። ምናልባት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተካፍለው ወይም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለ ግብ ማውጣት የምትችል ከሆነ እባክህ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ሕዝቦች አገልግሎታቸውን ለማስፋት ይጓጓሉ። (ሥራ 16:9) ይሁንና በአሁኑ ወቅት እንዲህ ለማድረግ ሁኔታህ የማይፈቅድልህ ቢሆንስ? እንዲህ ማድረግ ከቻሉ ክርስቲያኖች እንደምታንስ ሊሰማህ አይገባም። የክርስቲያኖች ሩጫ ጽናት ይጠይቃል። (ማቴ. 10:22) ዋናው ነገር አቅምህና ሁኔታህ በሚፈቅድልህ መጠን ይሖዋን ማገልገልህ እንደሆነ አትርሳ። ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ያለማቋረጥ መከተል የምትችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ይህ ነው።—መዝ. 26:1
12-13. ቅንዓትህ መቀዝቀዝ ከጀመረ ምን ማድረግ ትችላለህ? (1 ቆሮንቶስ 9:16, 17) (“ከውድድሩ አትውጣ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
12 ይሁንና ጸሎትህ ተደጋጋሚ፣ አገልግሎትህ ደግሞ አሰልቺ እየሆነ እንደመጣ ቢሰማህስ? መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የምታገኘው ደስታ እየቀነሰ ቢመጣስ? ከተጠመቅክ በኋላ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ‘የይሖዋን መንፈስ አጥቻለሁ’ የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩል። ፍጹም ስላልሆንክ ስሜትህ ሊለዋወጥ ይችላል። ቅንዓትህ መቀዝቀዝ ከጀመረ በሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ላይ አሰላስል። ጳውሎስ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ቢያደርግም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ተነሳሽነቱ ሊቀንስ እንደሚችል ተገንዝቧል። (1 ቆሮንቶስ 9:16, 17ን አንብብ።) “ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል” ብሏል። በሌላ አባባል፣ ጳውሎስ ስሜቱ ቢለዋወጥም እንኳ አገልግሎቱን ለማከናወን ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር።
13 አንተም ፍጹም ባልሆነው ስሜትህ ላይ ተመሥርተህ ውሳኔ ከማድረግ ተቆጠብ። ተነሳሽነት ባይኖርህም እንኳ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ትክክለኛውን ነገር ማድረግህን ከቀጠልክ ውሎ አድሮ ተነሳሽነትህ ሊጨምር ይችላል። እስከዚያው ድረስ ግን ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዘህ መቀጠልህ ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ያለማቋረጥ እንድትከተል ይረዳሃል። የምታሳየው ጽናት የእምነት አጋሮችህንም ያበረታታቸዋል።—1 ተሰ. 5:11
“ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ . . . ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ”
14. ራስህን ምን ብለህ መጠየቅ ይኖርብሃል? ለምንስ? (2 ቆሮንቶስ 13:5)
14 ከተጠመቅክ በኋላ ዘወትር ራስህን መመርመርህም ይጠቅምሃል። (2 ቆሮንቶስ 13:5ን አንብብ።) አልፎ አልፎ ሕይወትህንና ልማዶችህን መለስ ብለህ በመቃኘት ‘በየዕለቱ እየጸለይኩ ነው? መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብኩና እያጠናሁ ነው? በስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ? እንዲሁም በአገልግሎት ላይ እካፈላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። እነዚህን የአምልኮህን ዘርፎች ይበልጥ አስደሳች ማድረግ የምትችልባቸውን መንገዶች ለመፈለግ ሞክር። ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦ ‘መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለሌሎች ማብራራት እችላለሁ? አገልግሎቴን ይበልጥ አስደሳች ማድረግ የምችልበት መንገድ ይኖር ይሆን? በጸሎቴ ላይ የምፈልገውን ነገር ለይቼ እጠቅሳለሁ? ጸሎቴ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደምታመን ያሳያል? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኛለሁ? በስብሰባዎች ላይ ይበልጥ በትኩረት ማዳመጥና የማደርገውን ተሳትፎ ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?’
15-16. ከአንድ ወንድም ተሞክሮ ፈተናን ስለመቋቋም ምን ትምህርት አግኝተሃል?
15 ድክመቶችህን በተመለከተ ራስህን በሐቀኝነት መመርመርህም ጠቃሚ ነው። ሮበርት የተባለ ወንድም ይህን ነጥብ ጥሩ አድርጎ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “የ20 ዓመት ወጣት ሳለሁ በሳምንት ውስጥ የተወሰነ ሰዓት እሠራ ነበር። አንድ ቀን ከሥራ በኋላ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ቤቷ እንድመጣ ጋበዘችኝ። ቤት ብቻችንን ሆነን ‘ጥሩ ጊዜ እንደምናሳልፍ’ ነገረችኝ። መጀመሪያ ላይ ሰበብ ለማቅረብ ሞከርኩ፤ በኋላ ግን ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለጽኩላትና ምክንያቱን አብራራሁላት።” ሮበርት ፈተናውን ተቋቁሟል፤ ይህም የሚያስመሰግነው ነው። በኋላ ላይ ግን ሁኔታውን መለስ ብሎ ሲያጤነው የተሻለ ምላሽ መስጠት ይችል እንደነበር ተሰምቶታል። እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “የሰጠሁት ምላሽ፣ ዮሴፍ ለጶጢፋር ሚስት የሰጠውን ምላሽ ያህል ፈጣንም ሆነ ቁርጥ ያለ አልነበረም። (ዘፍ. 39:7-9) እንዲያውም እንቢ ማለት ያን ያህል ከብዶኝ የነበረ መሆኑ ገርሞኛል። ይህ አጋጣሚ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ማጠናከር እንዳለብኝ እንድገነዘብ ረዳኝ።”
16 አንተም ልክ እንደ ሮበርት ራስህን መመርመርህ ሊጠቅምህ ይችላል። አንድን ፈተና ተቋቁመህ ብታልፍም እንኳ ‘እንቢ ለማለት ምን ያህል ጊዜ ወስዶብኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ማስተካከያ ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ ራስህን አትኮንን። ድክመት እንዳለብህ ማወቅህ በራሱ ጠቃሚ ነው። ስለ ጉዳዩ ጸልይ፤ እንዲሁም በይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመመራት ያለህን ቁርጠኝነት ለማጠናከር እርምጃ ውሰድ።—መዝ. 139:23, 24
17. ሮበርት ታማኝ መሆኑ የይሖዋን ስም ያስከበረው እንዴት ነው?
17 የሮበርት ተሞክሮ በዚህ አላበቃም። እንዲህ ብሏል፦ “የሥራ ባልደረባዬ ግብዣዋን እንደማልቀበል ከነገርኳት በኋላ ‘ፈተናውን አልፈሃል’ አለችኝ። እኔም ምን ማለቷ እንደሆነ ጠየቅኳት። እሷም፣ በፊት የይሖዋ ምሥክር የነበረ ጓደኛዋ ሁሉም ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ሁለት ዓይነት ሕይወት እንደሚመሩና አቋማቸውን ለማላላት አጋጣሚ ካገኙ ዓይናቸውን እንደማያሹ ነግሯት እንደነበር ነገረችኝ። ስለዚህ ያለው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ እኔን እንደምትፈትነኝ ነግራው ነበር። በዚህ ጊዜ፣ የይሖዋን ስም በማስከበሬ በጣም ተደሰትኩ።”
18. ከተጠመቅክ በኋላ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል? (“ግሩም ርዕሶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
18 ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ስትጠመቅ፣ ምንም ይምጣ ምን ስሙን ማስቀደስ እንደምትፈልግ ታሳያለህ። ይሖዋ የሚያጋጥሙህን መከራዎችና የምትቋቋማቸውን ፈተናዎች እንደሚያስተውል እርግጠኛ ሁን። ታማኝነትህን ለመጠበቅ የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል። በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሚሰጥህ ተማመን። (ሉቃስ 11:11-13) በይሖዋ እርዳታ፣ ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ያለማቋረጥ መከተል ትችላለህ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ክርስቲያኖች “የመከራ እንጨት በየዕለቱ” የሚሸከሙት እንዴት ነው?
ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ለመከተል’ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ራስህን ስትወስን ባቀረብከው ጸሎት ላይ ማሰላሰልህ ታማኝነትህን ለመጠበቅ የሚረዳህ እንዴት ነው?
መዝሙር 89 ስማ፣ ታዘዝ፤ ትባረካለህ