“የዓለምን መንፈስ” ተቃወሙ
‘ከአምላክ የሆነውን መንፈስ እንጂ፣ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።’—1 ቆሮ. 2:12
1, 2. (ሀ) በብሪታንያ በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ካነሪ የተባሉት ወፎች እንዲኖሩ የሚደረገው ለምን ነበር? (ለ) ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?
በ1911 የብሪታንያ ባለ ሥልጣናት የከሰል ማዕድን ቆፋሪዎችን ሕይወት ለመታደግ የሚረዳ አንድ ሕግ አወጡ። ይህ ሕግ ከሰል በሚወጣበት በእያንዳንዱ ቦታ ካነሪ የተባሉ ሁለት ወፎች እንዲኖሩ ያዝዝ ነበር። እንዲህ ዓይነት ሕግ የወጣው ለምን ነበር? እነዚህ ትናንሽ ወፎች እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ ያሉ መርዛማ ጋዞች በአካባቢው መኖራቸውን ለማወቅ ስለሚረዱ ከሰል በሚወጣበት ጉድጓድ ውስጥ እሳት ቢነሳ የሕይወት አድን ሠራተኞች እነዚህን ወፎች ይዘው ወደ ጉድጓዱ ይገባሉ። አየሩ በመርዛማ ጋዝ መበከል ሲጀምር ወፎቹ የመረበሽ ምልክት ከማሳየታቸውም በላይ ካረፉበት ቦታ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ወፎቹ ላይ የሚታየውን ይህንን የማስጠንቀቂያ ምልክት ማስተዋል በጣም አስፈላጊ ነው። ካርቦን ሞኖክሳይድ ምንም ዓይነት ቀለም እንዲሁም ሽታ የሌለው ጋዝ ሲሆን ቀይ የደም ሕዋሳት ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ኦክስጅን ማድረስ እንዳይችሉ በማድረግ ሕይወትን ያሳጣል። የሕይወት አድን ሠራተኞቹ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ማስጠንቀቂያ ካልተሰጣቸው መርዛማው ጋዝ ወደ ሰውነታቸው እየገባ መሆኑን እንኳ ሳያውቁ ራሳቸውን ሊስቱ እንዲሁም ሊሞቱ ይችላሉ።
2 በመንፈሳዊ ሁኔታም ክርስቲያኖች ከማዕድን ቆፋሪዎቹ ጋር የሚመሳሰል ነገር ያጋጥማቸዋል። እንዴት? ኢየሱስ ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ የመስበኩን ተልእኮ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው ወቅት አደገኛ ወደሆነ ክልል እንደላካቸው ያውቅ ነበር፤ ምክንያቱም ምሥራቹን የሚሰብኩት በሰይጣን ቁጥጥር ሥር በሆነና የዓለም መንፈስ ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ክልል ውስጥ ነው። (ማቴ. 10:16፤ 1 ዮሐ. 5:19) ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱ ሁኔታ በጣም ስላሳሰበው ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ እንዲህ በማለት ወደ አባቱ ጸሎት አቅርቦ ነበር:- “የምለምንህም ከክፉው እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አይደለም።”—ዮሐ. 17:15
3, 4. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል? ይህ ማስጠንቀቂያ የእኛንም ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ፣ በመንፈሳዊ ማንቀላፋት ሞት ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ ተከታዮቹ እንደዚህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገቡ አስጠንቅቋቸዋል። እሱ የሰጠው ማስጠንቀቂያ በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ላይ ለምንኖረው ለእኛም ልዩ ትርጉም አለው። ኢየሱስ “መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ . . . ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠንቅቋቸዋል። (ሉቃስ 21:34-36 NW) ደስ የሚለው ግን ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የተማሯቸውን ነገሮች እንዲያስታውሱ እንዲሁም ንቁዎችና ደፋሮች ሆነው እንዲቀጥሉ አባቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋል።—ዮሐ. 14:26
4 መንፈስ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ እኛንም ይረዳናል? የሚረዳን ከሆነ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? የዓለም መንፈስ ምንድን ነው? ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? የዚህን ዓለም መንፈስ በመቃወም ረገድ ሊሳካልን የሚችለውስ እንዴት ነው?—1 ቆሮንቶስ 2:12ን አንብብ።
ሕይወታችንን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ነው ወይስ የዓለም መንፈስ?
5, 6. መንፈስ ቅዱስ ምን ማድረግ እንድንችል ይረዳናል? ይህን መንፈስ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 አምላክ፣ ሕዝቦቹ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዲያገኙ ዝግጅት ያደረገው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብቻ አልነበረም። የአምላክ መንፈስ በዛሬውም ጊዜ ቢሆን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግና በአገልግሎት ለመካፈል የሚያስችለንን ኃይል በመስጠት ይረዳናል። (ሮሜ 12:11፤ ፊልጵ. 4:13) ከዚህም በላይ “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች የሆኑትን እንደ ፍቅር፣ ደግነትና ጥሩነት የመሳሰሉ መልካም ባሕርያት እንድናፈራ ያስችለናል። (ገላ. 5:22, 23) ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ፣ መንፈስ ቅዱስን ለማይፈልጉ ሰዎች ይህን መንፈስ አይሰጣቸውም።
6 እንግዲያው፣ ‘መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ?’ የሚለውን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህንን መንፈስ ለማግኘት ማድረግ የምንችላቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ይናገራል። ልንወስደው የምንችለው አንዱ ቀላልና አስፈላጊ እርምጃ አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠን መለመን ነው። (ሉቃስ 11:13ን አንብብ።) ሌላው ጠቃሚ እርምጃ ደግሞ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ምክር ማጥናትና በተግባር ላይ ማዋል ነው። (2 ጢሞ. 3:16) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ ሁሉ የአምላክን መንፈስ ያገኛል ማለት አይደለም። ሆኖም ቅን ልብ ያለው አንድ ክርስቲያን የአምላክን ቃል ሲያጠና በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃል ላይ የሚንጸባረቀውን ስሜትና አመለካከት ማስተዋል ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ ኢየሱስን ወኪሉ አድርጎ እንደሾመው እንዲሁም መንፈሱን የሚሰጠን በእሱ በኩል እንደሆነ አምነን መቀበላችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ቈላ. 2:6) በመሆኑም ኢየሱስ በተወው ምሳሌና በትምህርቶቹ መሠረት ሕይወታችንን መምራት ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:21) ክርስቶስን ለመምሰል ይበልጥ ጥረት ባደረግን መጠን የዚያኑ ያህል መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን።
7. የዓለም መንፈስ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
7 ከዚህ በተቃራኒ ግን የዓለም መንፈስ ሰዎች የሰይጣንን ባሕርያት እንዲያንጸባርቁ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል። (ኤፌሶን 2:1-3ን አንብብ።) የዓለም መንፈስ በተለያየ መንገድ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህ መንፈስ፣ የሰው ልጆች የአምላክን መመሪያዎች እንዲጥሱ እንደሚያነሳሳቸው በዛሬው ጊዜ በዙሪያችን የምንመለከታቸው ነገሮች በግልጽ ያሳያሉ። ሰዎች ‘የሥጋን ምኞት’ እንዲከተሉ፣ “የዓይን አምሮት” እንዲያድርባቸውና “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” እንዲኖራቸው ያደርጋል። (1 ዮሐ. 2:16 NW) የዓለም መንፈስ እንደ ዝሙት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ቅናት፣ ቁጣና ስካር ያሉት የሥጋ ሥራዎች ምንጭ ነው። (ገላ. 5:19-21) እንዲሁም ቅዱስ የሆነውን ነገር የሚጻረር የክህደት አስተሳሰብን ያስፋፋል። (2 ጢሞ. 2:14-18) በመሆኑም አንድ ሰው የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት በፈቀደ መጠን የሰይጣንን ባሕርያት የበለጠ ማንጸባረቁ አይቀርም።
8. እያንዳንዳችን ምን ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል?
8 እርግጥ ነው፣ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ ሆነን መኖር አንችልም። እያንዳንዱ ግለሰብ ‘ሕይወቴን እንዲመራልኝ የምፈልገው መንፈስ ቅዱስ ነው ወይስ የዓለም መንፈስ?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለበት። በአሁኑ ጊዜ በዓለም መንፈስ እየተመሩ ያሉ ሰዎች ከዚህ ተጽዕኖ ተላቅቀው መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸውን እንዲመራላቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን በአንድ ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ይመሩ የነበሩ ሰዎች በዓለም መንፈስ ሊሸነፉ ይችላሉ። (ፊልጵ. 3:18, 19) የዓለምን መንፈስ እንዴት መቃወም እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶችን አስተውሉ
9-11. የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እያሳደረብን እንደሆነ የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
9 ቀደም ሲል የተጠቀሱት በብሪታንያ የሚገኙ የከሰል ማዕድን ቆፋሪዎች፣ ካነሪ የተባሉት ወፎች የሚያሳዩትን ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመመልከት መርዛማ ጋዝ መኖሩን ማወቅ ይችሉ ነበር። አንድ የማዕድን ቆፋሪ፣ ወፏ ካረፈችበት ቦታ ላይ ስትወድቅ ከተመለከተ ሕይወቱን ለማዳን ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይገነዘባል። በመንፈሳዊ ሁኔታስ የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እያሳደረብን መሆኑን የሚጠቁሙ አንዳንድ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
10 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በተማርንበትና ሕይወታችንን ለይሖዋ በወሰንበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን በጉጉት እናነብ ነበር። እንዲሁም አዘውትረን ከልብ የመነጨ ጸሎት እናቀርብ ነበር። በበረሃ አካባቢ የሚገኝ የውኃ ምንጭ የተጠማን ሰው እንደሚያስደስተው ሁሉ እኛም እያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ በመንፈሳዊ እንደሚያድሰን ስለምናውቅ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ያስደስተን ነበር። እነዚህን ነገሮች ማድረጋችን የዓለም መንፈስ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ለመላቀቅ እንዲሁም ይህ መንፈስ እንደገና ተጽዕኖ እንዳያደርግብን ለመከላከል እንድንችል ረድቶናል።
11 አሁንስ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጥረት እናደርጋለን? (መዝ. 1:2) አዘውትረን ከልብ በመነጨ ስሜት ወደ ይሖዋ እንጸልያለን? በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በየሳምንቱ በመገኘት በስብሰባዎቹ እንደምንደሰት እናሳያለን? (መዝ. 84:10) ወይስ ከእነዚህ ጥሩ ልማዶች መካከል አንዳንዶቹን ትተናቸዋል? እውነት ነው፣ ጊዜያችንን የሚሻሙና ኃይላችንን የሚያሟጥጡ የተለያዩ ኃላፊነቶች ይኖሩብን ይሆናል፤ በመሆኑም ሁልጊዜ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖረን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ከዚህ በፊት የነበሩንን ጥሩ ልማዶች ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እየተውናቸው ከሆነ ይህንን ያደረግነው የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ስላሳደረብን ይሆን? አሁንስ፣ ቀደም ሲል የነበሩንን ጥሩ ልማዶች እንደገና ማዳበር እንድንችል ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ ፈቃደኞች ነን?
‘ሸክም እንዳይበዛባችሁ ተጠንቀቁ’
12. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? ለምንስ?
12 የዓለምን መንፈስ ለመቃወም ከላይ የተመለከትናቸውን እርምጃዎች ከመውሰድ በተጨማሪ ምን ማድረግ እንችላለን? ኢየሱስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ምክር ከመስጠቱ በፊት፣ ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ አንዳንድ አደጋዎች አስጠንቅቋቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል:- “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት፣ እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል።”—ሉቃስ 21:34, 35 NW
13, 14. ምግብና መጠጥን በተመለከተ የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው?
13 እስቲ ኢየሱስ ስለሰጠው ማስጠንቀቂያ አስብ። በምግብና በመጠጥ መደሰትን ማውገዙ ነበር? አልነበረም! ኢየሱስ፣ ሰሎሞን የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ያውቅ ነበር:- “ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።” (መክ. 3:12, 13) ያም ቢሆን የዓለም መንፈስ ከምግብና ከመጠጥ ጋር በተያያዘ ሰዎች ራስን ያለመግዛት ዝንባሌ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግም ኢየሱስ ያውቅ ነበር።
14 ከልክ በላይ መብላት ወይም መጠጣት የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ አስተሳሰባችን በዓለም መንፈስ እንዳልተመረዘ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን:- ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በጽሑፎቻችን ላይ ሆዳምነትን የሚመለከት ምክር ሳነብ ምን እርምጃ እወስዳለሁ? የቀረበው ሐሳብ ለእኔ ጠቃሚ እንዳልሆነ ወይም ከልክ በላይ ጥብቅ እንደሆነ በማሰብ ምክሩን በቸልታ አልፈዋለሁ? ወይም ለድርጊቴ ምክንያት አቀርባለሁ?a የአልኮል መጠጥ የምንጠጣ ከሆነ ልከኛ እንድንሆን እንዲሁም ‘ከስካር’ እንድንርቅ የተሰጠውን ምክር በተመለከተስ ምን አመለካከት አለኝ? እነዚህ ምክሮች እኔን አይመለከቱኝም ብዬ በማሰብ አቅልዬ እመለከታቸዋለሁ? ሌሎች የአልኮል መጠጥ የመጠጣት ልማዴ እንዳሳሰባቸው ቢነግሩኝ ሐሳባቸውን ላለመቀበል አንገራግራለሁ ወይም ወደ መቆጣት አዘነብላለሁ? በዚህ ረገድ የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሌሎች አቅልለው እንዲመለከቱት አበረታታለሁ?’ በእርግጥም፣ አንድ ሰው ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እንዳደረገበት ወይም እንዳላደረገበት ይጠቁማል።—ከሮሜ 13:11-14 ጋር አወዳድር።
ጭንቀት አንቆ እንዳይዛችሁ ተጠንቀቁ
15. ኢየሱስ የትኛውን የሰው ልጆች ዝንባሌ በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
15 የዓለምን መንፈስ ለመቃወም የሚረዳን ሌላው አስፈላጊ እርምጃ ደግሞ ጭንቀትን ከመቆጣጠር ጋር የተያያዘ ነው። ኢየሱስ፣ ፍጽምና የጎደለን ፍጥረታት በመሆናችን ለዕለታዊ ፍላጎታችን የመጨነቅ ዝንባሌ እንዳለን ያውቅ ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ “አትጨነቁ” የሚል ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 6:25) አምላክን ማስደሰት፣ ያሉብንን ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች መወጣትና ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉት አስፈላጊ ጉዳዮች እንደሚያሳስቡን የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 7:32-34) ታዲያ ኢየሱስ ከሰጠው ማስጠንቀቂያ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
16. የዓለም መንፈስ በብዙ ሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
16 ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል ዝንባሌን የሚያበረታታው የዓለም መንፈስ ብዙዎች ጤንነታቸውን ሊጎዳ በሚችል ጭንቀት እንዲዋጡ ያደርጋቸዋል። ዓለም፣ ገንዘብ አስተማማኝ መጠጊያ እንደሆነና የሰው ማንነት የሚለካው በግለሰቡ መንፈሳዊ ባሕርያት ሳይሆን በንብረቱ ብዛትና ጥራት ላይ እንደሆነ ሊያሳምነን ይሞክራል። እንደዚህ ባለው ፕሮፖጋንዳ የተታለሉ ሰዎች ሀብት ለማግኘት የሚባዝኑ ሲሆን አዲስ የመጣውን እንዲሁም ትልቅና በጣም ዘመናዊ የሆነውን ዕቃ ለማግኘት ስለሚፈልጉ ሁልጊዜ ይጨነቃሉ። (ምሳሌ 18:11) ለቁሳዊ ነገሮች እንዲህ ያለ የተዛባ አመለካከት መያዝ አንድ ሰው በጭንቀት እንዲዋጥ የሚያደርገው ሲሆን ይህም መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል።—ማቴዎስ 13:18, 22ን አንብብ።
17. ጭንቀት አንቆ እንዳይዘን ምን ማድረግ እንችላለን?
17 “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ” የሚለውን የኢየሱስ ምክር መታዘዛችን ጭንቀት አንቆ እንዳይዘን ለመከላከል ያስችለናል። ኢየሱስ እንዲህ ካደረግን የሚያስፈልጉን መሠረታዊ ነገሮች እንደሚጨመሩልን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ማቴ. 6:33) በዚህ ተስፋ ላይ እምነት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ የአምላክን ጽድቅ በማስቀደም ማለትም ከገንዘብ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ትክክለኛ ስለሆነው አካሄድ አምላክ ያወጣቸውን መመሪያዎች በመታዘዝ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ከንግድ ሥራችን ጋር በተያያዘ የምንከፍለው ግብር እንዲቀንስልን በማሰብ የሐሰት መዝገብ አናዘጋጅም እንዲሁም “በትናንሽ” ነገሮችም እንኳ አንዋሽም። ያለብንን ዕዳ በመክፈል ረገድ “ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’ . . . ይሁን” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንታዘዛለን፤ ከገንዘብ ነክ ነገሮች ጋር በተያያዘ የገባነውን ቃል ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። (ማቴ. 5:37፤ መዝ. 37:21) አንድ ሰው በእነዚህ ጉዳዮች ሐቀኛ መሆኑ ሀብታም ባያደርገውም የአምላክን ሞገስና ንጹሕ ሕሊና ያስገኝለታል፤ ከዚህም በላይ ጭንቀቱን በእጅጉ ይቀንስለታል።
18. ኢየሱስ ምን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል? እሱን በመምሰል የምንጠቀመውስ እንዴት ነው?
18 የአምላክን መንግሥት ማስቀደም፣ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መለየትን ይጨምራል። በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ጥራት ያለው ልብስ የለበሰባቸው ወቅቶች ነበሩ። (ዮሐ. 19:23) ከጥሩ ወዳጆቹ ጋር በመሆን ይመገብ ነበር፤ ወይን ጠጅ የጠጣባቸው ጊዜያትም አሉ። (ማቴ. 11:18, 19) ይሁን እንጂ ንብረት እንዲሁም መዝናኛ በሕይወቱ ውስጥ እንደ ቅመም ነበሩ እንጂ ዋነኛውን ቦታ የሚይዙ ነገሮች አልነበሩም። የኢየሱስ ምግብ የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ ነበር። (ዮሐ. 4:34-36) የኢየሱስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ሕይወት በጣም አስደሳች ይሆንልናል! ግፍ የደረሰባቸውን ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን በማጽናናት ደስታ እናገኛለን። የጉባኤያችን አባላት ፍቅር ያሳዩናል እንዲሁም ይደግፉናል። በተጨማሪም የይሖዋን ልብ ደስ እናሰኛለን። ቅድሚያ ልንሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠን ሀብትና መዝናኛ ጌታ አይሆኑብንም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ለማገልገል የሚረዱን ባሪያዎች ይሆናሉ። እንዲሁም የአምላክን መንግሥት በመደገፉ ሥራ በቅንዓት የምንካፈል ከሆነ በዓለም መንፈስ የመሸነፋችን አጋጣሚ ጠባብ ይሆናል።
‘የመንፈስን ነገር’ ማሰባችሁን ቀጥሉ
19-21. ‘የመንፈስን ነገር’ ማሰባችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?
19 ሐሳብ ከተግባር ይቀድማል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሳያስቡት እንዳደረጉት የሚገልጹትን ነገር እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ሥጋዊ አስተሳሰብ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ አስተሳሰባችንን መጠበቅ ያለውን አስፈላጊነት በተመለከተ ማሳሰቢያ የሰጠው ለዚህ ነው። ጳውሎስ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ በሥጋዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 8:5 NW
20 ታዲያ አስተሳሰባችንንም ሆነ ተግባራችንን የዓለም መንፈስ እንዳይቆጣጠረው ምን ማድረግ እንችላለን? በአእምሯችን ውስጥ የሚመመላለሱትን ሐሳቦች በመቆጣጠር ዓለም የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን የምንችለውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለአብነት ያህል፣ መዝናኛ በምንመርጥበት ጊዜ የሥነ ምግባር ብልግና ወይም ዓመፅ ከሚታይባቸውና አእምሯችንን ከሚያቆሽሹ ፕሮግራሞች መራቅ አለብን። ቅዱስ ወይም ንጹሕ የሆነው የአምላክ መንፈስ በቆሸሸ አእምሮ ውስጥ እንደማይኖር መገንዘብ አለብን። (መዝ. 11:5፤ 2 ቆሮ. 6:15-18) ከዚህም በተጨማሪ አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ በመጸለይ፣ በማሰላሰልና በስብሰባዎች ላይ በመገኘት የአምላክ መንፈስ አስተሳሰባችንን እንዲመራው መፍቀድ ይኖርብናል። አዘውትረን በክርስቲያናዊው የስብከት ሥራ በመካፈል ከዚህ መንፈስ ጋር የሚስማማ እርምጃ እንወስዳለን።
21 እንግዲያው የዓለምን መንፈስና ይህ መንፈስ የሚያስፋፋቸውን የሥጋ ምኞቶች መቃወም እንደሚኖርብን ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን የዓለምን መንፈስ ለመቃወም የምናደርገው ጥረት የሚያስቆጭ አይደለም፤ ምክንያቱም ጳውሎስ እንደተናገረው “የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።”—ሮሜ 8:6
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሆዳምነት ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ነገር ነው፤ ሆዳም የሚባለው አልጠግብ ባይ ወይም ስግብግብ የሆነ ሰው ነው። በመሆኑም አንድ ግለሰብ ሆዳም መሆኑ የሚታወቀው በክብደቱ ሳይሆን ለምግብ ባለው አመለካከት ነው። መካከለኛ ሰውነት ያለው እንዲያውም ቀጭን የሆነ ሰውም እንኳ ሆዳም ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ከመጠን በላይ መወፈር በሕመም ምክንያት ሊመጣ አሊያም ከቤተሰብ ሊወረስ ይችላል። አንድ ሰው ወፍራምም ይሁን ቀጭን ሆዳም የሚያስብለው ከምግብ ጋር በተያያዘ ስግብግብነት የተጠናወተው መሆኑ ነው።—በኅዳር 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄ” ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
• የዓለም መንፈስ በየትኞቹ መንገዶች ተጽዕኖ ሊያደርግብን ይችላል?
• የዓለምን መንፈስ መቃወም የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ ሥራ ወይም ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳችሁ በፊት መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልዩ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አእምሯችን ንጹሕ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ፣ ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ሐቀኞች መሆን እንዲሁም በምግብና በመጠጥ ረገድ ልከኞች መሆን ይኖርብናል