የቄሣርን ለቄሣር ማስረከብ
“ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ።”—ሮሜ 13:7
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ክርስቲያኖች ለአምላክና ለቄሣር ያሉባቸውን ግዴታዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት ያለባቸው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉ በፊት የሚያሳስባቸው ነገር ምንድን ነው?
ኢየሱስ በተናገረው መሠረት ለአምላክ የምናስረክባቸው ነገሮችና ለቄሣር ወይም ለመንግሥት የምናስረክባቸው ነገሮች አሉ። ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” ብሏል። በእነዚህ ጥቂት ቃላት ጠላቶቹ አፋቸውን እንዲይዙ ከማድረጉም በላይ ከአምላክ ጋር ባለን ዝምድናና ከመንግሥት ጋር በምናደርገው ግንኙነት ሊኖረን የሚገባውን ሚዛናዊ አመለካከት በአጭሩ ጠቅለል አድርጎ ተናግሯል። ይሰሙት የነበሩት ሰዎች ‘መደነቃቸው’ አያስገርምም!—ማርቆስ 12:17
2 እርግጥ፣ የይሖዋ አገልጋዮች ከሁሉ በፊት የሚያሳስባቸው ነገር የአምላክ የሆኑትን ነገሮች ለአምላክ ማስረከባቸው ነው። (መዝሙር 116:12-14) ይህን ሲያደርጉ ግን ኢየሱስ የተወሰኑ ነገሮችን ለቄሣር ማስረከብ እንዳለባቸው የተናገረውን አይዘነጉም። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸው ቄሣር የሚጠይቃቸውን ነገሮች ለቄሣር ማስረከብ የሚችሉት እስከ ምን ደረጃ እንደሆነ ለመወሰን በጸሎት እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። (ሮሜ 13:7) በዘመናችን ብዙ የሕግ ባለሙያዎች የመንግሥት ሥልጣን ገደብ እንዳለውና በየትም ሥፍራ ያሉ ሰዎችም ሆኑ መንግሥታት የተፈጥሮ ሕግ የሚገዛቸው መሆኑን ተገንዝበዋል።
3, 4. የተፈጥሮ ሕግን፣ አምላክ ለሰዎች የገለጸውን ሕግና ሰብዓዊ ሕግን በተመለከተ ምን ጥሩ ጥሩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ዓለም ሰዎች ሲጽፍ ይህን የተፈጥሮ ሕግ ጠቅሷል፦ “እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም . . . የሚያመካኙት አጡ።” ይህን የተፈጥሮ ሕግ ቢታዘዙ ኖሮ የእነዚህም እምነት የለሾች ሕሊና በትክክለኛው መንገድ ሊመራቸው ይችል ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጨምሮ ተናግሯል፦ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ . . . በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።”—ሮሜ 1:19, 20፤ 2:14, 15
4 የአሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን ዝነኛ የሕግ ባለሙያ የነበሩት እንግሊዛዊው ዊልያም ብላክስቶን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ይህ የተፈጥሮ ሕግ ከሰው ልጅ ጋር [ዘመን] እኩል የኖረና አምላክ ራሱ ያወጣው ሕግ በመሆኑ ከሌላ ከማንኛውም ሕግ የበለጠ ለዚህ ሕግ የመገዛት ግዴታ አለብን። ይህ ሕግ በመላው ዓለም በሚኖሩ ሰዎች ላይ ምንጊዜም ተፈጻሚነት አለው። ይህን ሕግ የሚጻረሩ ሰብዓዊ ሕጎች በሙሉ ምንም ዓይነት ዋጋ አይኖራቸውም።” ብላክስቶን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘውና “አምላክ ለሰዎች ስለገለጸው ሕግ” ሲናገሩም እንዲህ ብለዋል፦ “ሁሉም ሰብዓዊ ሕጎች የተመሠረቱት በእነዚህ ሁለት ሕጎች ማለትም በተፈጥሮ ሕግና አምላክ ለሰዎች በገለጸው ሕግ ላይ ነው፤ ሰብዓዊ ሕጎች በሙሉ ከእነዚህ ሕጎች ጋር እንዲጋጩ ማድረግ አይገባም ማለት ነው።” ይህ በማርቆስ 12:17 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘውና ኢየሱስ ስለ አምላክና ስለ ቄሣር ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው። ቄሣር ከአንድ ክርስቲያን ሊጠብቃቸው በሚችላቸው ነገሮች ረገድ አምላክ ገደብ ማውጣቱን በግልጽ መረዳት ይቻላል። ሳንሄድሪን ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ መስበካቸውን አንዲያቆሙ በማዘዝ ይህን ገደብ ተላልፏል። በመሆኑም ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት ትክክለኛ ምላሽ ሰጥተዋል።—ሥራ 5:28, 29
‘የአምላክ ነገሮች’
5, 6. (ሀ) መንግሥቱ በ1914 መወለዱን ግምት ውስጥ በማስገባት ክርስቲያኖች ከምንጊዜውም በበለጠ ዘወትር በአእምሯቸው ሊይዙት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን የአምላክ አገልጋይ መሆኑን ማስመስከር የሚችለው እንዴት ነው?
5 በተለይ ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ በክርስቶስ መሢሐዊ መንግሥት አማካኝነት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረበት ከ1914 ወዲህ ክርስቲያኖች የአምላክ የሆኑትን ነገሮች ለቄሣር እንዳይሰጡ ይበልጥ መጠንቀቅ አስፈልጓቸዋል። (ራእይ 11:15, 17) በአሁኑ ወቅት የአምላክ ሕግ ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ’ ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ያዛቸዋል። (ዮሐንስ 17:16) ሕይወት ሰጪያቸው ለሆነው አምላክ ራሳቸውን የወሰኑ በመሆናቸው የራሳቸው ንብረት እንዳልሆኑ በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 100:2, 3) ጳውሎስ እንደ ጻፈው “የጌታ ነን።” (ሮሜ 14:8) ከዚህም በላይ አንድ ክርስቲያን ሲጠመቅ የአምላክ አገልጋይ ሆኖ ተሹሟል፤ በመሆኑም ልክ እንደ ጳውሎስ ‘አምላክ ብቁ አገልጋዮች አድርጎናል’ ብሎ መናገር ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 3:5, 6
6 በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ሃይማኖታዊ “አገልግሎቴን አከብራለሁ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 11:13) እኛም እንዲሁ ማድረግ አለብን። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማራን ሆንም አልሆን የአገልግሎት ተልዕኳችንን የሰጠን ይሖዋ ራሱ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (2 ቆሮንቶስ 2:17) አንዳንዶች አቋማችንን የሚመለከት ጥያቄ ሊያነሱ ስለሚችሉ እያንዳንዱ ራሱን የወሰነና የተጠመቀ ክርስቲያን የምሥራቹ አገልጋይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ግልጽና የማያሻማ ማስረጃ ለማቅረብ የተዘጋጀ መሆን አለበት። (1 ጴጥሮስ 3:15) ጠባዩም ለአገልግሎቱ ምሥክርነት የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል። አንድ ክርስቲያን የአምላክ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን ንጹሕ ሥነ ምግባር ያለውና ሌሎች እንዲህ ዓይነት ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው የሚያበረታታ፣ የቤተሰብን አንድነት የሚደግፍ፣ ሐቀኛና ለሕግና ሥርዓት አክብሮት የሚያሳይ መሆን አለበት። (ሮሜ 12:17, 18፤ 1 ተሰሎንቄ 5:15) አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የሚሰጠው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድናና አምላክ ለሰጠው የአገልግሎት ሥራ ነው። የቄሣርን ትእዛዝ ለማክበር ሲል እነዚህን ነገሮች ሊተው አይችልም። እነዚህ ‘የአምላክ ነገሮች’ ናቸው።
‘የቄሣር ነገሮች’
7. የይሖዋ ምሥክሮች ግብር በመክፈል ረገድ ምን ስም አትርፈዋል?
7 የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለበላይ ባለ ሥልጣኖች’ ማለትም ለመንግሥታዊ ገዥዎች መገዛት እንዳለባቸው ያውቃሉ። (ሮሜ 13:1) በመሆኑም ቄሣር ማለትም መንግሥት አግባብነት ያላቸውን ነገሮች እንዲያደርጉ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸው የተጠየቁትን እንዲፈጽሙ ይገፋፋቸዋል። ለምሳሌ ያህል በምድር ላይ በግብር ከፋይነታቸው በጥሩ ምሳሌነት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆኑት ሰዎች መካከል እውነተኛ ክርስቲያኖች ይገኛሉ። በጀርመን ሚውንሽነር ሜርኩር የተባለው ጋዜጣ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በፌዴራል ሪፑብሊኳ ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ሐቀኞችና ከማንም ይበልጥ ግብር በወቅቱ የሚከፍሉ ሰዎች ናቸው።” በኢጣሊያ ላ ስታምፓ የተባለው ጋዜጣ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “[የይሖዋ ምሥክሮች] ከማንም ይበልጥ ለቆሙለት ዓላማ ታማኝ የሆኑ ዜጎች ናቸው፤ ማንም ሰው ሊመኘው የሚችለው ዓይነት አቋም አላቸው። ግብር ላለመክፈል ሲሉ አያጭበረብሩም፤ ወይም የራሳቸውን ጥቅም ከሚነኩ ሕጎች ለመሸሽ አይሞክሩም።” የይሖዋ አገልጋዮች ይህን የሚያደርጉት ‘ለሕሊናቸው ሲሉ’ ነው።—ሮሜ 13:5, 6
8. ለቄሣር የምንሰጠው ነገር በግብር መልክ በሚሰጥ ገንዘብ ብቻ የተወሰነ ነውን?
8 ‘ለቄሣር የሚሰጡት ነገሮች’ ግብር በመክፈል ብቻ የተወሰኑ ናቸውን? አይደሉም። ጳውሎስ ፍርሃትንና አክብሮትን የመሳሰሉ ሌሎች ነገሮችን ጠቅሷል። ጀርመናዊው ምሁር ሃይንሪኽ ሜየር፣ ክሪቲካል ኤንድ ኤክሰጄቲካል ሃንድ ቡክ ቱ ዘ ጎስፕል ኦቭ ማቲው በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[ለቄሣር የሚሰጠው ነገር] . . . ግብር ብቻ ነው ብለን ማሰብ የለብንም፤ ቄሣር አግባብነት ባለው ሥልጣኑ የሚጠይቀው ነገር ሁሉ ሊሰጠው ይገባል።” ታሪክ ጸሐፊው ኢ ደብሊው ባርንስ ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አንድ ክርስቲያን ሊከፍለው የሚገባው ግብር ካለ ይከፍል ነበር፤ “ለአምላክ መሰጠት ያለበትን ነገር ለቄሣር እንዲሰጥ እስካልተጠየቀ ድረስ መንግሥት የሚጠይቅበትን ሌሎች ግዴታዎችም ተቀብሎ ይፈጽማል” ሲሉ ገልጸዋል።
9, 10. አንድ ክርስቲያን ለቄሣር የሚገባውን በማስረከብ ረገድ ምን ዓይነት ስሜት ሊያድርበት ይችላል? ሆኖም የትኞቹን እውነታዎች በአእምሮ መያዝ ይገባል?
9 መንግሥት የአምላክ መብት የሆኑትን ነገሮች ሳይጋፋ ምን ነገሮችን መጠየቅ ይችላል? አንዳንዶች በግብር መልክ ከሚሰጠው ገንዘብ ሌላ ምንም ነገር ለቄሣር መሰጠት እንደሌለበት ይሰማቸዋል። ለቲኦክራሲያዊ ሥራ ሊያውሉት የሚችሉትን ጊዜ ሊወስድባቸው የሚችል ማንኛውም ዓይነት ነገር ለቄሣር መሰጠት እንደሌለበት ሆኖ ይሰማቸዋል። ሆኖም ‘ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አሳባችንንና ኃይላችን መውደድ’ ያለብን ቢሆንም ይሖዋ ጊዜያችንን ቅዱሱን አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችንም ለማከናወን እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። (ማርቆስ 12:30፤ ፊልጵስዩስ 3:3) ለምሳሌ ያህል፣ ያገቡ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛቸውን ደስ ማሰኘት የሚችሉበት ጊዜ መመደብ እንዳለባቸው ተመክረዋል። እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ማድረግ ስህተት አይደለም፤ ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ‘የጌታ ነገር’ ሳይሆን ‘የዓለም ነገር’ እንደሆነ ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 7:32-34፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ጋር አወዳድር።
10 በተጨማሪም ክርስቶስ ተከታዮቹ ግብር ‘እንዲከፍሉ’ ፈቅዷል። ግብር ለመክፈል ለይሖዋ የወሰንነውን ጊዜ መጠቀም እንደሚኖርብን ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም መላ ሕይወታችን ለይሖዋ የተወሰነ ነው። በአንድ አገር ውስጥ አንድ ሠራተኛ ከሚያገኘው ገቢ ላይ 33 በመቶ የሚሆነውን ለመንግሥት የሚገብር ከሆነ (በአንዳንድ አገሮች የግብሩ መጠን ከዚህ ይበልጣል) ይህ ማለት አንድ ሠራተኛ በየዓመቱ በአማካይ የአራት ወር ደሞዙን ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት ያስገባል ማለት ነው። በሌላ አባባል አንድ ሠራተኛ የሥራ ዘመኑ ሲያበቃ ከሥራ ዘመኑ ውስጥ በአማካይ ወደ 15 ዓመት ገደማ የሚሆነውን ጊዜ ያሳለፈው “ቄሣር” የሚጠይቀውን ግብር በመክፈል ነው ማለት ነው። የትምህርትንም ሁኔታ ተመልከቱ። አብዛኞቹ አገሮች ወላጆች ልጆቻቸውን ምን ያህል ዓመት ማስተማር እንዳለባቸው የሚደነግግ ሕግ አላቸው። ማስተማር የሚኖርባቸው ዓመት ከአገር ወደ አገር ይለያያል። በአብዛኞቹ አገሮች የትምህርቱ ዘመን ረዘም ያለ ጊዜ የሚሸፍን ነው። እርግጥ ነው፣ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ጠቃሚ ነው፤ ሆኖም አንድ ልጅ ከሕይወት ዘመኑ ምን ያህሉን በትምህርት ማሳለፍ እንዳለበት የሚወስነው ቄሣር ነው፤ ክርስቲያን ወላጆች ደግሞ የቄሣርን ውሳኔ ያከብራሉ።
የውትድርና አገልግሎት ግዴታ
11, 12. (ሀ) በብዙ አገሮች ውስጥ ቄሣር ምን ጥያቄ ያቀርባል? (ለ) የጥንት ክርስቲያኖች ለውትድርና አገልግሎት ምን አመለካከት ነበራቸው?
11 በአንዳንድ አገሮች ቄሣር የሚያቀርበው ሌላው ጥያቄ የውትድርና አገልግሎት ግዳጅ ነው። በ20ኛው መቶ ዘመን የውትድርና አገልግሎት ግዴታ በዜጎች ላይ የሚጣለው በአብዛኞቹ አገሮች በጦርነት ጊዜያት ሲሆን በሰላም ጊዜም የውትድርና አገልግሎት ግዴታ የደነገጉ አንዳንድ አገሮች አሉ። በፈረንሳይ ይህ ግዳጅ ለብዙ ዓመታት የደም ግብር ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል። ይህ ማለት እያንዳንዱ ወጣት ሕይወቱን ለአገሩ ለመሠዋት ፈቃደኛ መሆን አለበት ማለት ነው። ይህ አገልግሎት ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎች ሊፈጽሙ የሚችሉት ግዴታ ነውን? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱ ነበር?
12 የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ጥሩ ዜጎች ለመሆን ይጥሩ የነበረ ቢሆንም እምነታቸው ሌላውን ሰው እንዲገድሉ ወይም ሕይወታቸውን ለአገራቸው መሥዋዕት እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውም ነበር። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ተርቱሊያንንና ኦሪገንን ጨምሮ የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ክርስቲያኖች የሰውን ሕይወት እንዳያጠፉ ይከለከሉ እንደነበረ ገልጸዋል። በሮማ ሠራዊት ውስጥ እንዳይሳተፉ ያገዳቸው ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ነበር።” ፕሮፌሰር ሲ ጄ ካዱ ዘ ኧርሊ ቸርች ኤንድ ዘ ወርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ቢያንስ እስከ ማርኩስ ኦሪሊየስ ዘመን ድረስ [161-180 እዘአ] ከተጠመቀ በኋላ ወታደር የሆነ አንድም ክርስቲያን አልነበረም።”
13. አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና አባላት የውትድርና አገልግሎትን በተመለከተ የጥንት ክርስቲያኖች የነበራቸው ዓይነት አመለካከት የሌላቸው ለምንድን ነው?
13 በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባሎች ይህን የመሰለ አመለካከት የሌላቸው ለምንድን ነው? በአራተኛው መቶ ዘመን በተካሄደው ሥር ነቀል ለውጥ የተነሣ ነው። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ካውንስልስ የተባለው የካቶሊክ ጽሑፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በአረማውያን ንጉሠ ነገሥቶች አገዛዝ ሥር የነበሩ . . . ብዙ ክርስቲያኖች ከውትድርና አገልግሎት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ድርጊቶችን ከመፈጸም እንዲታቀቡ የሚያደርጉ ሃይማኖታዊ እምነቶች ነበሯቸው፤ በመሆኑም ቆራጥ አቋም በመውሰድ መሣሪያ አንታጠቅም ይሉ ነበር፤ አለዚያም በገዛ ፈቃዳቸው የውትድርና ሥራቸውን ይተዉ ነበር። [በ314 እዘአ አርልስ ውስጥ የተካሄደው] ሲኖዶስ ቆስጠንጢኖስ ያደረጋቸውን ለውጦች ግምት ውስጥ በማስገባት ክርስቲያኖች በጦርነት የማገልገል ግዴታ አለባቸው የሚል መግለጫ አወጣ፤ . . . ይህ የሆነው ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች ወዳጅ በሆነ ገዥ አማካኝነት ከመንግሥት ጋር ሰላም (በላቲን ኢን ፓቼ) ስለ ፈጠረች ነው።” በራሳቸው ሕሊና ተገፋፍተው በጦር ሠራዊት ውስጥ አናገለግልም ያሉ አንዳንድ ሰዎች ቢኖሩም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በዚህ ረገድ የኢየሱስን ትምህርት እርግፍ አድርገው በመተዋቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንጎቻቸው በአገራቸው የጦር ሠራዊት ውስጥ እንዲያገለግሉ ሲያበረታቱ ኖረዋል።
14, 15. (ሀ) በአንዳንድ አገሮች ክርስቲያኖች ከውትድርና አገልግሎት ነፃ የመሆን መብት የሚጠይቁት ምንን መሠረት በማድረግ ነው? (ለ) ከዚህ ግዳጅ ነፃ የመሆን መብት በሌለባቸው አገሮች አንድ ክርስቲያን የውትድርና አገልግሎትን በተመለከተ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ እንዲችል የሚረዱት የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?
14 በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ብዙሐኑን መከተል አለባቸውን? የለባቸውም። አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ከውትድርና አገልግሎት ግዴታ ነፃ በሚሆኑበት አገር የሚኖር ከሆነ ሃይማኖታዊ አገልጋይ እንደ መሆኑ መጠን በውትድርና አገልግሎት ለማገልገል እንዳይገደድ ሊጠይቅ ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) ዩናይትድ ስቴትስንና አውስትራሊያን ጨምሮ በርካታ አገሮች በጦርነት ወቅትም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ሰጥተዋል። በተጨማሪም በሰላም ዘመን ወታደራዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ባለባቸው ብዙ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ አገልጋዮች መሆናቸው እውቅና አግኝቶ ከዚህ ግዳጅ ነፃ የመሆን መብት አግኝተዋል። ይህም በመሆኑ ሕዝባዊ አገልግሎታቸውን በመስጠት ሰዎችን መርዳታቸውን መቀጠል ችለዋል።
15 አንድ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ከዚህ ግዳጅ ነፃ መሆን በማይችሉበት አገር ውስጥ የሚኖር ከሆነስ? በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን በመጠቀም የራሱን ውሳኔ መውሰድ ይኖርበታል። (ገላትያ 6:5) የቄሣርን ሥልጣን ግምት ውስጥ በማስገባት ለይሖዋ ማስረከብ ያለበት ነገር ምን እንደሆነ በጥንቃቄ ይመረምራል። (መዝሙር 36:9፤ 116:12-14፤ ሥራ 17:28) የአንድ እውነተኛ ክርስቲያን መለያ ምልክት በሌሎች አገሮች የሚኖሩትንም ሆነ የሌሎች ጎሣዎች አባላት የሆኑትን ጨምሮ ለእምነት ባልደረቦቹ በሙሉ ፍቅር ማሳየት እንደሆነ ያስታውሳል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ጴጥሮስ 2:17) በተጨማሪም እንደ ኢሳይያስ 2:2-4፤ ማቴዎስ 26:52፤ ሮሜ 12:18፤ 14:19፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4 እና ዕብራውያን 12:14 ባሉት ጥቅሶች ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች አይዘነጋም።
የሲቪል አገልግሎት
16. በአንዳንድ አገሮች ቄሣር የውትድርና አገልግሎትን ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ከውትድርና አገልግሎት ነፃ የሆነ ምን አገልግሎት እንዲፈጽሙ ይጠይቃል?
16 ይሁን እንጂ ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ከወታደራዊ ግዳጅ ነፃ እንዲሆኑ ባይፈቅዱም እንኳ አንዳንድ ግለሰቦች በውትድርና አገልግሎት ላለመካፈል የሚወስዱትን አቋም የሚቀበሉ መንግሥታት አሉ። ከእነዚህ አገሮች መካከል ብዙዎቹ እንዲህ ዓይነት አቋም ያላቸውን ግለሰቦች የውትድርና አገልግሎት እንዲሰጡ ላለማስገደድ አንዳንድ ዝግጅቶች አድርገዋል። በአንዳንድ አገሮች ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የሆነ ነገር ማከናወንን የመሳሰሉ ሥራዎችን የሚጠይቀው የሲቪል አገልግሎት ከውትድርና ጋር ግንኙነት የሌለው ብሔራዊ አገልግሎት ተደርጎ ይታያል። አንድ ራሱን የወሰነ ክርስቲያን በእንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት መሳተፍ ይችላልን? አሁንም ቢሆን አንድ ራሱን ወስኖ የተጠመቀ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ምርኩዝ አድርጎ የራሱን ውሳኔ መውሰድ ይኖርበታል።
17. በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከውትድርና አገልግሎት ነፃ የሆነ የሲቪል አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረ የሚያሳይ ምን ምሳሌ አለ?
17 በግዳጅ የሚፈጸም አገልግሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም የነበረ ይመስላል። አንድ የታሪክ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ከይሁዳ ነዋሪዎች ይሰበሰብ ከነበረው ግብርና መዋጮ ሌላ በግዳጅ የሚፈጸም ሥራ [በሕዝብ ባለ ሥልጣኖች ትእዛዝ ያለ ክፍያ የሚከናወን ሥራ] ነበር። ይህ በምሥራቁ ዓለም የነበረ ጥንታዊ ሥርዓት ሲሆን የግሪክና የሮማ ባለ ሥልጣኖችም ይጠቀሙበት ነበር። . . . አዲስ ኪዳንም ይሁዳ ውስጥ በግዳጅ ይፈጸሙ የነበሩ ሥራዎችን የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ይጠቅሳል፤ ይህም በግዳጅ ይፈጸም የነበረው ሥራ ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበረ ያመለክታል። ከዚህ ልማድ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የቀሬናው ስምዖን የኢየሱስን መስቀል [የመከራ እንጨት] እንዲሸከም ወታደሮች አስገድደዋል (ማቴዎስ 5:41፤ 27:32፤ ማርቆስ 15:21፤ ሉቃስ 23:26)።”
18. የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ ከውትድርና እንዲሁም ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ነፃ በሆኑ በየትኞቹ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶች ይሳተፋሉ?
18 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶች እንዲሳተፉ በመንግሥት ወይም በአካባቢው ባለ ሥልጣኖች ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ሥራው ጉድጓድ እንደ መቆፈር ወይም መንገድ እንደ መሥራት ያለ አንድ የተወሰነ ሥራ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቋሚነት የሚከናወን ሥራ ይሆናል። ለምሳሌ መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ወይም ደግሞ ሆስፒታሎችን ለመጠገን በሚካሄዱ ሥራዎች በየሳምንቱ መሳተፍ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ የሲቪል አገልግሎት ለማኅበረሰቡ የሚጠቅምና ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ወይም የይሖዋ ምሥክሮችን ሕሊና በምንም መንገድ የማይነካ እስከሆነ ድረስ ብዙውን ጊዜ የተጠየቅነውን እናደርጋለን። (1 ጴጥሮስ 2:13-15) ይህን ማድረግ ብዙውን ጊዜ ግሩም የሆነ ውጤታማ ምሥክርነት ለመስጠት ከማስቻሉም በላይ አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ፀረ መንግሥት ናቸው በማለት በሐሰት የሚወነጅሉ ሰዎችን አፍ ያስይዛል።—ከማቴዎስ 10:18 ጋር አወዳድር።
19. አንድ ክርስቲያን ለተወሰነ ጊዜ ወታደራዊ ያልሆነ ብሔራዊ አገልግሎት እንዲፈጽም ቄሣር ጥያቄ ቢያቀርብለት ጉዳዩን መመልከት ያለበት እንዴት ነው?
19 ሆኖም አንድ ክርስቲያን ለተወሰነ ጊዜ በአንድ የሲቪል አስተዳደር የሚካሄድ ብሔራዊ አገልግሎት ክፍል የሆነ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጥ መንግሥት ቢጠይቀው ምን ማድረግ ይችላል? አሁንም ቢሆን ክርስቲያኖች ስለዚህ ጉዳይ በቂ እውቀት ባካበተ ሕሊናቸው ተጠቅመው የራሳቸውን ወሳኔ መውሰድ አለባቸው። “ሁላችንም . . . በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለን።” (ሮሜ 14:10) ቄሣር አንድ ነገር እንዲፈጽሙ ያዘዛቸው ክርስቲያኖች ነገሩን በጸሎት መመርመርና በጉዳዩ ላይ በሚገባ ማሰላሰል ይኖርባቸዋል።a በተጨማሪም በጉባኤው ውስጥ ከሚገኙ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር ጉዳዩን አንስቶ መወያየት ጥሩ ነው። ከዚህ በኋላ የግል ውሳኔ መውሰድ ይገባል።—ምሳሌ 2:1-5፤ ፊልጵስዩስ 4:5
20. አንድ ክርስቲያን ወታደራዊ ያልሆነ ብሔራዊ የሲቪል አገልግሎትን በተመለከተ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዲችል የትኞቹ ጥያቄዎችና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዱት ይችላሉ?
20 ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ በሚያመዛዝኑበት ጊዜ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ጳውሎስ ‘ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች መገዛትና መታዘዝ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን መሆን፣ እንዲሁም ገሮችና ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የምናሳይ መሆን’ እንዳለብን ተናግሯል። (ቲቶ 3:1, 2) እንደዚሁም ክርስቲያኖች የተጠየቁትን የሲቪል ሥራ በሚገባ ይመረምራሉ። ሥራውን ከተቀበሉ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን መጠበቅ ይችላሉን? (ሚክያስ 4:3, 5፤ ዮሐንስ 17:16) ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነውን? (ራእይ 18:4, 20, 21) ይህን ሥራ መፈጸማቸው ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን ለመወጣት የሚያደርጉትን ጥረት የሚያደናቅፍ ወይም ከልክ በላይ የሚገታ ነውን? (ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25) በሌላ በኩል ደግሞ የተጠየቀውን አገልግሎት እየሰጡ መንፈሣዊ ዕድገት ማድረግና ምናልባትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሳተፍ ይችላሉን?—ዕብራውያን 6:11, 12
21. ወታደራዊ ያልሆነ ብሔራዊ የሲቪል አገልግሎትን በተመለከተ አንድ ወንድም የደረሰበት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ጉባኤው ወንድምን እንዴት ሊመለከተው ይገባል?
21 ክርስቲያኑ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው እውነተኛ መልስ የተጠየቀው ብሔራዊ የሲቪል አገልግሎት “ጥሩ ሥራ” እንደሆነና ባለ ሥልጣኖቹን በመታዘዝ ሥራውን ሊፈጽመው እንደሚችል ሆኖ እንዲሰማው የሚያደርግ ከሆነስ? ይህ ግለሰቡ ራሱ በይሖዋ ፊት የሚወስደው ውሳኔ ነው። የተሾሙ ሽማግሌዎችና ሌሎች ክርስቲያኖች የዚህን ወንድም ሕሊና ሙሉ በሙሉ ሊያከብሩና እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም ጥሩ አቋም ያለው ክርስቲያን እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። አንድ ክርስቲያን ይህን የሲቪል አገልግሎት ሊፈጽም እንደማይችል ሆኖ ከተሰማውም አቋሙ ሊከበርለት ይገባል። ይህም ክርስቲያን ቢሆን ጥሩ አቋም ይዞ የሚቀጥል ስለሆነ ፍቅራዊ ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 10:29፤ 2 ቆሮንቶስ 1:24፤ 1 ጴጥሮስ 3:16
22. ምንም ዓይነት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙን ምን ማድረጋችንን እንቀጥላለን?
22 ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን “ክብር ለሚገባው ክብር” መስጠታችንን አናቆምም። (ሮሜ 13:7) ትክክለኛ የሆነን ሥርዓት እናከብራለን፤ እንዲሁም ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ዜጎች ለመሆን እንጥራለን። (መዝሙር 34:14) አልፎ ተርፎም ክርስቲያናዊ ሕይወታችንንና ሥራችንን የሚመለከቱ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ጥያቄ በሚቀርብላቸው ጊዜ “ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ” እንጸልያለን። የቄሣርን ነገሮች ሁሉ ለቄሣር በማስረከባችን “እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን” መኖር እንደምንችል እናምናለን። (1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2) ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክን ነገሮች ሁሉ በሚገባ ለአምላክ በማስረከብ የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የሆነውን የመንግሥቱን ምሥራች መስበካችንን እንቀጥላለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ አንድ ክርስቲያን ከቄሣርና ከይሖዋ ጋር ያለው ግንኙነት ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ይበልጥ የሚያሳስበው ነገር ምንድን ነው?
◻ ለቄሣር ፈጽሞ ልንሰጠው የማንችለውና ለይሖዋ ልንሰጠው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
◻ ለቄሣር ልንሰጠው የሚገባን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ የውትድርና አገልግሎትን ግዴታ በተመለከተ ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዱን ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
◻ ወታደራዊ ያልሆነ ብሔራዊ የሲቪል አገልግሎት እንድንሰጥ ብንጠየቅ ልናስብባቸው የሚገቡን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ ይሖዋንና ቄሣርን በተመለከተ ምን ማድረጋችንን እንቀጥላለን?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያት “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ተናግረዋል