ጥበቃ ለማግኘት ከአምላክ ሕዝቦች አትራቅ
“በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ።”—መዝ. 35:18
1-3. (ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊነታቸው አደገኛ የሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ ማግኘት የሚችሉት ከየት ነው?
ጆ እና ባለቤቱ፣ ለመዝናናት በሄዱበት አካባቢ የተለያዩ ዓይነት ቀለማትና መጠን ያሏቸው ዓሦች በብዛት በሚርመሰመሱበት ባሕር ውስጥ እየዋኙ ነበር። የባሕሩን እንስሳት ይበልጥ ለማየት ስለፈለጉ ጥልቀት ወዳለው የባሕሩ ክፍል መሄድ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የጆ ሚስት ጥልቅ ወደሆነ አካባቢ እየሄዱ እንደሆነ በማስተዋል “በጣም እየራቅን የመጣን ይመስለኛል” አለችው። ጆ ግን “አይዞሽ፣ ወዴት እንደምሄድ አውቃለሁ” በማለት መለሰላት። ሆኖም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ‘ዓሦቹ ሁሉ ወዴት ሄዱ?’ ብሎ ማሰብ ጀመረ። ዓሦቹ ከአካባቢው የጠፉበትን ምክንያት ሲረዳ በጣም ደነገጠ። ጥልቅ ከሆነው የባሕሩ ክፍል አንድ ሻርክ ወደ እሱ እየተምዘገዘገ ሲመጣ ተመለከተ። በዚያ ወቅት ወዴትም ማምለጥ አይችልም ነበር። የሚገርመው ሻርኩ አጠገቡ ከደረሰ በኋላ አቅጣጫውን ቀይሮ ትቶት ሄደ።
2 አንድ ክርስቲያን፣ የሰይጣን ሥርዓት በሚያቀርባቸው እንደ መዝናኛ፣ ሥራና ቁሳዊ ንብረት ባሉ ትኩረት የሚስቡ ነገሮች በጣም ከመማረኩ የተነሳ ጥልቀት ወዳለው ባሕር ውስጥ የመግባት ያህል ሳያውቀው አደገኛ ወደሆነ ሁኔታ ሊገባ ይችላል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ የሆነው ጆ “ይህ አጋጣሚ ጊዜያችንን የምናሳልፈው ከእነማን ጋር እንደሆነ እንዳስብ አድርጎኛል” በማለት ተናግሯል። “አስተማማኝና አስደሳች ከሆነው አካባቢ በሌላ አባባል ከጉባኤው ርቀን መሄድ የለብንም!” ጥልቀት ባለው የባሕሩ ክፍል ውስጥ መዋኘት አደገኛ እንደሆነ ሁሉ ዓለም በሚያቀርባቸው ነገሮች ተስበን ከጉባኤው ከራቅንም ለአደጋ ልንጋለጥ እንችላለን። ጥልቀት ወዳለው አካባቢ እየገባህ እንደሆነ ካስተዋልክ ከአደጋ ነፃ ወደሆነው ቦታ በፍጥነት ተመለስ። እንዲህ ካላደረግህ መንፈሳዊነትህን የማጣት አደጋ ሊያጋጥምህ ይችላል።
3 በዛሬው ጊዜ ዓለም ለክርስቲያኖች አደገኛ ቦታ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5) ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ስለሚያውቅ ንቁ ያልሆኑ ሰዎችን ለመዋጥ እያደባ ነው። (1 ጴጥ. 5:8፤ ራእይ 12:12, 17) ደስ የሚለው ግን ጥበቃ ማግኘት የምንችልበት ዝግጅት ተደርጎልናል። ይሖዋ ለሕዝቡ አስተማማኝ የሆነ መንፈሳዊ መሸሸጊያ ይኸውም የክርስቲያን ጉባኤን አዘጋጅቶላቸዋል።
4, 5. ብዙ ሰዎች ስለ ወደፊት ሕይወታቸው ምን ይሰማቸዋል? ለምንስ?
4 ከአምላክ የራቀው ማኅበረሰብ፣ የሰዎች አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ደኅንነት እንዲጠበቅ ማድረግ የሚችለው በተወሰነ መጠን ብቻ ነው። ወንጀል፣ ዓመፅና የኑሮ ውድነት ሌላው ቀርቶ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንኳ ብዙ ሰዎች አካላዊ ደኅንነታቸው አደጋ ላይ እንደወደቀ እንዲሰማቸው አድርገዋቸዋል። ከዕድሜ መግፋትና ከጤና ማጣት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሁሉም ሰው ላይ ይደርሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ፣ ቤት፣ ጥሩ ገቢ እንዲሁም በአንጻራዊ ሁኔታ ጥሩ ጤንነት ያላቸው ሰዎች እነዚህን ነገሮች እንዳያጡ ይሰጋሉ።
5 ብዙዎች ስሜታዊ ደኅንነት ማግኘትም የሕልም እንጀራ ሆኖባቸዋል። ጋብቻና የቤተሰብ ሕይወት ሰላምና እርካታ እንደሚያስገኝላቸው ተስፋ ያደረጉ በርካታ ሰዎች የጠበቁት ነገር አለመሳካቱ የሚያሳዝን ነው። ከመንፈሳዊ ደኅንነት አንጻር ሲታይም ወደ አብያተ ክርስቲያናት አዘውትረው የሚሄዱ አብዛኞቹ ሰዎች የሚሰጣቸው መመሪያ ትክክለኛነት አጠራጣሪ ስለሆነባቸው ግራ ተጋብተዋል። ለዚህም በዋነኝነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የሃይማኖት መሪዎቻቸው የሚከተሉት ምግባረ ብልሹ አኗኗርና የሚያስተምሩት ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጭ ትምህርት ይገኙበታል። በዚህም የተነሳ ብዙዎች፣ የሳይንሱ መስክ በሚያስገኘው እድገት ላይ ተስፋ ከማድረግ እንዲሁም ለሌሎች መልካም ማድረግና ጥሩ ሥነ ምግባር ማሳየት መሻሻል እንደሚያስገኝ ከመጠበቅ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ይሰማቸዋል። ከዚህ አንጻር በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች በስጋት የተዋጡ መሆናቸው ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ እምብዛም ማሰብ አለመፈለጋቸው አያስገርምም።
6, 7. (ሀ) አምላክን የሚያገለግሉ ሰዎች ነገሮችን የሚያዩበት መንገድ እሱን ከማያገለግሉት ሰዎች የተለየ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥለን ምን እንመለከታለን?
6 የክርስቲያን ጉባኤ አባል የሆኑት ሰዎች ነገሮችን የሚያዩበት መንገድ የጉባኤው አባል ካልሆኑት ሰዎች ምንኛ የተለየ ነው! አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎችና የሚደርሱባቸው ችግሮች በይሖዋ ሕዝቦች ላይም የሚደርሱ ቢሆንም የምንሰጠው ምላሽ ግን ፈጽሞ የተለየ ነው። (ኢሳይያስ 65:13, 14ን እና ሚልክያስ 3:18ን አንብብ።) ለምን? የሰው ልጅ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የወደቀው ለምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አጥጋቢ መልስ ያገኘን ከመሆኑም ሌላ የሕይወትን ውጣ ውረዶችና ችግሮች እንዴት መቋቋም እንደምንችል ተምረናል። በዚህም ምክንያት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከሚገባው በላይ አንጨነቅም። የይሖዋ አምላኪዎች በመሆናችን ጤናማና ቅዱስ ጽሑፋዊ ካልሆነ አስተሳሰብ፣ ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ድርጊቶችና ከሚያስከትሉት መዘዝ ጥበቃ እናገኛለን። በዚህም የተነሳ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሌሎች ሰዎች የሌላቸው ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት አለን።—ኢሳ. 48:17, 18፤ ፊልጵ. 4:6, 7
7 አንዳንድ ምሳሌዎችን መመልከታችን ይሖዋን ከማያገለግሉ ሰዎች በተቃራኒ የእሱ አገልጋዮች የሚሰማቸውን የደኅንነት ስሜት ለማስተዋል ይረዳናል። እነዚህ ምሳሌዎች አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን እንድንመረምር እንዲሁም አምላክ ለእኛ ጥቅም ብሎ የሰጠንን ምክር ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ እንችል እንደሆነ እንድናመዛዝን ሊረዱን ይችላሉ።—ኢሳ. 30:21
‘እግሬ ሊሰናከል ጥቂት ቀረኝ’
8. የይሖዋ አገልጋዮች ምንጊዜም ምን ማድረግ ነበረባቸው?
8 ከሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ መመልከት እንደምንችለው ይሖዋን ለማገልገልና ለመታዘዝ የመረጡ ሰዎች ይህን ለማድረግ ከማይፈልጉ ጋር የቀረበ ወዳጅነት ላለመመሥረት ይጠነቀቁ ነበር። ይሖዋም በእሱ አገልጋዮችና በሰይጣን ተከታዮች መካከል ጠላትነት እንደሚኖር ጠቁሞ ነበር። (ዘፍ. 3:15) የአምላክ ሕዝቦች መለኮታዊ መመሪያዎችን በጥብቅ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ በማድረጋቸው አኗኗራቸው በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች የተለየ ነበር። (ዮሐ. 17:15, 16፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) እንዲህ ያለ አቋም መያዝ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የጥበብ እርምጃ መሆኑን የተጠራጠሩበት ጊዜ ነበር።
9. የመዝሙር 73ን ጸሐፊ ግራ ያጋባው ሁኔታ ምን ነበር?
9 ያደረጉት ውሳኔ ጥበብ የተንጸባረቀበት መሆኑን ከተጠራጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች አንዱ የመዝሙር 73 ጸሐፊ ሲሆን ይህ ሰው ከአሳፍ ዝርያዎች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። መዝሙራዊው፣ አምላክን ለማገልገል የሚጥሩ ሰዎች መከራና ችግር ሲያጋጥማቸው ክፉዎች ግን በአብዛኛው የተሳካላቸው፣ ደስተኞችና ባለጸጎች መስለው የሚታዩት ለምን እንደሆነ ጠይቋል።—መዝሙር 73:1-13ን አንብብ።
10. መዝሙራዊው ያነሳቸውን ጥያቄዎች ልታስብባቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
10 መዝሙራዊው ያነሳቸው ዓይነት ጥያቄዎች በአእምሮህ ተፈጥረውብህ ያውቃሉ? ከሆነ በጥፋተኝነት ስሜት ልትዋጥ ወይም እምነትህ እየተዳከመ እንደሆነ ሊሰማህ አይገባም። ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ የተጠቀመባቸውን ጨምሮ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ተሰምቷቸው ያውቃል። (ኢዮብ 21:7-13፤ መዝ. 37:1፤ ኤር. 12:1፤ ዕን. 1:1-4, 13) በእርግጥም ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ‘አምላክን ማገልገልና መታዘዝ ከሁሉ የተሻለ አካሄድ ነው?’ የሚለውን ጥያቄ በቁም ነገር ሊያስቡበትና መልሱን አምነው ሊቀበሉት ይገባል። ይህ ጥያቄ ሰይጣን በኤደን ገነት ካነሳው ጥያቄ ጋር ግንኙነት አለው። ከሉዓላዊ ገዥነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ አንድምታው ይሄ ነው። (ዘፍ. 3:4, 5) በመሆኑም ሁላችንም መዝሙራዊው ያነሳውን ጉዳይ መመርመራችን የተገባ ነው። ጉራቸውን የሚነዙ ክፉ ሰዎች የተሳካላቸው ስለሚመስሉ ልንቀናባቸው ይገባል? በዚህ ‘ተሰናክለን’ ይሖዋን ማገልገላችንን በመተው የእነሱን ጎዳና ልንከተል ይገባል? ሰይጣን የሚፈልገው እንዲህ እንድናደርግ መሆኑ የታወቀ ነው።
11, 12. (ሀ) መዝሙራዊው ጥርጣሬውን ማስወገድ የቻለው እንዴት ነው? ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) አንተስ መዝሙራዊው የደረሰበት ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ የረዳህ ምንድን ነው?
11 መዝሙራዊው ያደረበትን ጥርጣሬ ለማስወገድ የረዳው ምንድን ነው? የጽድቅን ጎዳና ከመከተል ወደኋላ ሊል ጥቂት ቀርቶት እንደነበር ቢናገርም “ወደ አምላክ መቅደስ” ሲገባ ማለትም በአምላክ የመገናኛ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲገናኝ እንዲሁም በአምላክ ዓላማ ላይ ሲያሰላስል አመለካከቱ ተለወጠ። በዚህ ጊዜ መዝሙራዊው የክፉዎችን ዕጣ መቋደስ እንደማይፈልግ ግልጽ ሆነለት። በሕይወታቸው ውስጥ ባደረጉት ምርጫና በተከተሉት ጎዳና የተነሳ “በሚያዳልጥ ስፍራ” ላይ የተቀመጡ ያህል እንደሆኑ ተገነዘበ። መዝሙራዊው፣ ይሖዋን በመተው ብልግና የሚፈጽሙ ሁሉ “በቅጽበት” እንደሚጠፉ፣ እሱን የሚያገለግሉ ግን ድጋፉን እንደሚያገኙ አስተዋለ። (መዝሙር 73:16-19, 27, 28ን አንብብ።) ይህ አባባል እውነት መሆኑን አንተም ሳትመለከት አትቀርም። ብዙዎች መለኮታዊ ሕግጋትን ችላ በማለት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማሟላት መኖር አስደሳች እንደሆነ ቢሰማቸውም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ከሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ማምለጥ አይችሉም።—ገላ. 6:7-9
12 መዝሙራዊው ካጋጠመው ነገር ሌላስ ምን ትምህርት እናገኛለን? መዝሙራዊው በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሲሆን የደኅንነት ስሜት የተሰማው ከመሆኑም በላይ ጥበብ አግኝቷል። ይሖዋ ወደሚመለክበት ቦታ ሲሄድ ነገሮች ወለል ብለው የታዩት ሲሆን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ ጀመረ። ዛሬም በተመሳሳይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር የሚሰጡን ሰዎችና ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት እንችላለን። በእርግጥም ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ትእዛዝ መስጠቱ የተገባ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ማበረታቻ የሚያገኙ ከመሆኑም ሌላ በጥበብ ጎዳና ለመሄድ ይነቃቃሉ።—ኢሳ. 32:1, 2፤ ዕብ. 10:24, 25
ወዳጆቻችሁን በጥበብ ምረጡ
13-15. (ሀ) ዲና ምን አጋጠማት? ይህስ ምን ትምህርት ይሰጠናል? (ለ) ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር ጓደኝነት መመሥረት ጥበቃ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
13 የያዕቆብ ልጅ የሆነችው የዲና ታሪክ ከዓለማዊ ጓደኞች ጋር መግጠም የሚያስከትለውን ከባድ ችግር ከሚያሳዩ ምሳሌዎች አንዱ ነው። ስለ ዲና የሚገልጸው የዘፍጥረት ዘገባ፣ ይህች ወጣት ቤተሰቧ በሚኖርበት አካባቢ ካሉ ከነዓናውያን ሴቶች ጋር ጊዜ የማሳለፍ ልማድ እንደነበራት ይናገራል። ከነዓናውያን የይሖዋ አምላኪዎች የሚመሩባቸውን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አይከተሉም ነበር። ከዚህ በተቃራኒ የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች ካገኙት ነገር መመልከት እንደሚቻለው የከነዓናውያን አኗኗር ምድሪቱ በጣዖት አምልኮ፣ በሥነ ምግባር ብልግና፣ ወራዳ በሆነ የፆታ አምልኮ እንዲሁም በዓመፅ እንድትሞላ አድርጎ ነበር። (ዘፀ. 23:23፤ ዘሌ. 18:2-25፤ ዘዳ. 18:9-12) ዲና ከእነዚህ ሰዎች ጋር መግጠሟ ያስከተለውን መዘዝ እስቲ እንመልከት።
14 “ከአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረ” እንደሆነ የተገለጸው ሴኬም ዲናን “ባያት ጊዜ ይዞ በማስገደድ ደፈራት።” (ዘፍ. 34:1, 2, 19) እንዴት የሚያሳዝን ነገር ነው! ዲና እንዲህ ዓይነት ነገር ይደርስብኛል ብላ አስባ የምታውቅ ይመስልሃል? ዲና በአካባቢው የሚገኙት ወጣቶች ምንም ጉዳት እንደማያደርሱባት በማሰብ ከእነሱ ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ፈልጋ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጣም ተሞኝታለች።
15 ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? ከማያምኑ ሰዎች ጋር ጊዜ እያሳለፍን ምንም ጉዳት አይደርስብንም ብለን ማሰብ አንችልም። ቅዱሳን መጻሕፍት “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ይላሉ። (1 ቆሮ. 15:33) በሌላ በኩል ደግሞ እምነትህን ከሚጋሩ እንዲሁም እንደ አንተ የላቀ የሥነ ምግባር አቋም ካላቸውና ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ጥበቃ ያስገኝልሃል። እንዲህ ያሉት ጥሩ ወዳጆች ጥበብ የተሞላበት እርምጃ እንድትወስድ ያበረታቱሃል።—ምሳሌ 13:20
“ታጥባችሁ ነጽታችኋል”
16. ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ስለሚገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ብሏል?
16 ብዙዎች ራሳቸውን ከሚያረክሱ ድርጊቶች እንዲያነጹ የክርስቲያን ጉባኤ ረድቷቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለነበረው ጉባኤ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ሲጽፍ በዚያ የሚገኙት ክርስቲያኖች ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ሲሉ ስላደረጓቸው ለውጦች ገልጾ ነበር። አንዳንዶቹ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ሌቦች፣ ሰካራሞችና እንደነዚህ ያሉትን ተግባራት የሚፈጽሙ ነበሩ። ሆኖም ጳውሎስ “ታጥባችሁ ነጽታችኋል” ብሏቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብብ።
17. ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት መኖራቸው ሕይወታቸውን የለወጠው እንዴት ነው?
17 እምነት የሌላቸው ሰዎች፣ ሊከተሉት የሚችሉት አስተማማኝ መመሪያ የላቸውም። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው አመለካከት ይመሩ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበሩት ክርስቲያኖች አማኞች ከመሆናቸው በፊት እንዳደረጉት በዙሪያቸው ያሉትን ሰዎች ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗር ይከተሉ ይሆናል። (ኤፌ. 4:14) በሌላ በኩል ግን ሰዎች ስለ አምላክ ቃልና ዓላማ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታቸው አኗኗራቸውን ለውጠው የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንዲችሉ ኃይል ይሰጣቸዋል፤ እርግጥ ነው፣ ይህ እንዲሆን የተማሩትን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ቆላ. 3:5-10፤ ዕብ. 4:12) በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑ ብዙዎች የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ከመማራቸውና የተማሩትን ተግባራዊ ከማድረጋቸው በፊት ልቅ የሆነ አኗኗር ይከተሉ እንደነበር ሊነግሩህ ይችላሉ። ያም ሆኖ ሕይወታቸው ደስታም ሆነ እርካታ የራቀው ነበር። ሰላማዊ ሕይወት መምራት የጀመሩት ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ኅብረት ሲፈጥሩና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር ሲጀምሩ ነው።
18. አንዲት ወጣት ምን አጋጥሟታል? ይህስ ምን ያረጋግጣል?
18 ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ጥበቃ የሚያገኙበትን የክርስቲያን ጉባኤ ትተው ሄደው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ዓይነት ውሳኔ በማድረጋቸው አሁን ክፉኛ ይጸጸታሉ። ታንያa የምትባል አንዲት እህት ከልጅነቷ ጀምሮ እውነትን ታውቅ የነበረ ቢሆንም 16 ዓመት ሲሆናት “ዓለም የሚያቀርባቸውን ማራኪ ነገሮች ለማግኘት” ስለፈለገች ከጉባኤ ራቀች። ይህን ማድረጓ ካስከተላቸው መዘዞች መካከል ያልተፈለገ እርግዝናና ጽንስ ማስወረድ ይገኙበታል። አሁን እንዲህ ትላለች፦ “ከጉባኤ ርቄ ያሳለፍኳቸው ሦስት ዓመታት በስሜቴ ላይ ፈጽሞ የማይጠፋ ጠባሳ ትተዋል። ሁልጊዜ የሚረብሸኝ ነገር በሆዴ የነበረውን ልጄን መግደሌ ነው። . . . ለአጭር ጊዜም ቢሆን እንኳ ዓለምን ‘ቀምሰው ለማየት’ ለሚመኙ ወጣቶች የምሰጣቸው ምክር ቢኖር ‘ፈጽሞ አትሞክሩት!’ የሚል ነው። ዓለም መጀመሪያ ላይ የሚጥም ሊሆን ይችላል፤ በኋላ ላይ ግን እሬት እሬት ይላል። ዓለም ሕይወታችንን ከማመሰቃቀል ውጪ የሚፈይድልን ነገር የለም። እኔ ስለቀመስኩት አውቀዋለሁ። ከይሖዋ ድርጅት ፈጽሞ አትውጡ! ደስታ የሚያስገኘው ብቸኛው የሕይወት ጎዳና ይህ ነው።”
19, 20. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ጥበቃ ታገኛለህ? እንዴትስ?
19 ጥበቃ ከምታገኝበት ከክርስቲያን ጉባኤ ብትወጣ ምን ሊያጋጥምህ እንደሚችል ለአንድ አፍታ አስብ። ብዙዎች እውነትን ከመቀበላቸው በፊት የነበራቸውን ትርጉም የለሽ ሕይወት ገና ሲያስቡት ዝግንን ይላቸዋል። (ዮሐ. 6:68, 69) ከክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ጋር ተቀራርበህ ከኖርክ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ካለው የተመሰቃቀለና በመከራ የተሞላ ሕይወት ተጠብቀህ መኖር ትችላለህ። ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ ጋር ጊዜ ማሳለፍህና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ መገኘትህ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች መከተል የጥበብ አካሄድ መሆኑን ሁልጊዜ የሚያስታውስህ ከመሆኑም ሌላ በእነዚህ መሥፈርቶች መሠረት እንድትኖር ያበረታታሃል። አንተም እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን “በታላቅ ጉባኤ መካከል አመሰግንሃለሁ” እንድትለው የሚያነሳሳህ በቂ ምክንያት አለህ።—መዝ. 35:18
20 እርግጥ ነው፣ ሁሉም ክርስቲያኖች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው መመላለስ አስቸጋሪ እንደሆነ የሚሰማቸው ጊዜ ይኖራል። በዚህ ወቅት ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚጠቁማቸው ሰው ማግኘታቸው ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። አንተም ሆንክ ሌሎች የጉባኤው አባላት እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የሚቀጥለው ርዕስ ወንድሞቻችሁን ‘ማጽናናትና ማነጻችሁን መቀጠል’ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ያብራራል።—1 ተሰ. 5:11
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሟ ተቀይሯል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• መዝሙር 73ን የጻፈው ግለሰብ ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
• ከዲና ተሞክሮ ምን እንማራለን?
• ጥበቃ የምታገኘው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ነው እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከአደጋ ነፃ በሆነው አካባቢ ዋኝ፤ በሌላ አባባል ከክርስቲያን ጉባኤ አትራቅ!