በሐሰተኛ አማልክት ላይ የተነሡ ምሥክሮች
“እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ።”—ኢሳይያስ 43:10
1. እውነተኛው አምላክ ማን ነው? እሱ በአሁኑ ወቅት ከሚመለኩት ብዙ አማልክት የሚልቀው በምን መንገዶች ነው?
እውነተኛው አምላክ ማን ነው? በአሁኑ ወቅት ይህ አንገብጋቢ ጥያቄ በሁሉም ሰው ፊት ተደቅኗል። ሰዎች እጅግ ብዙ የሆኑ አማልክትን ቢያመልኩም ሕይወት ሊሰጠንና አስደሳች የወደፊት ተስፋ ሊያቀርብልን የሚችለው አንድ አምላክ ብቻ ነው። “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን” ሊባልለት የሚቻለው ለአንድ አምላክ ብቻ ነው። (ሥራ 17:28) በእርግጥም የመመለክ መብት ያለው አንድ አምላክ ብቻ ነው። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው ታላቅ የሰማያዊ መዘምራን ቡድን እንዳለው “ጌታችንና አምላካችን [“ይሖዋ” አዓት] ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11
2, 3. (ሀ) ሰይጣን ውሸት በመናገር ይሖዋ ለመመለክ ያለውን መብት የተገዳደረው እንዴት ነው? (ለ) ሔዋን ኃጢአት መሥራቷ በራሷና በልጆቿ ላይ ምን ውጤት አስከተለ? ለሰይጣንስ ምን ጥቅም አስገኘለት?
2 ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ውሸት በመናገር ይሖዋ ለመመለክ ያለውን መብት ተገዳደረ። በእባብ ተጠቅሞ ሔዋን በይሖዋ ሕግ ላይ ብታምፅና ይሖዋ ከከለከለው ዛፍ ብትበላ እንደ አምላክ እንደምትሆን ነገራት። “ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” አላት። (ዘፍጥረት 3:5) ሔዋን እባቡ የተናገረውን አመነችና ከተከለከለው ፍሬ በላች።
3 ሰይጣን በእርግጥ ዋሽቶ ነበር። (ዮሐንስ 8:44) ሔዋን ኃጢአት በሠራችበት ወቅት “እንደ እግዚአብሔር” መሆን የቻለችው መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ራሷ መወሰን በመቻሏ ብቻ ነበር፤ ይህ ደግሞ አምላክ እንዲወስነው መደረግ ያለበት ጉዳይ ነበር። ሰይጣን አትሞቱም ብሎ ቢዋሽም ሔዋን የኋላ ኋላ መሞቷ አልቀረም። ስለዚህ ሔዋን ኃጢአት በመሥራቷ የተጠቀመው ሰይጣን ብቻ ነበር። ሰይጣን ሔዋን ኃጢአት እንድትሠራ ለማግባባት የፈለገው ራሱ አምላክ የመሆን ስውር ዓላማ ስለ ነበረው እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። ሔዋን ኃጢአት ስትሠራ የመጀመሪያ ሰብዓዊ ተከታዩ ሆነች፤ ወዲያውኑም አዳም ከእርሷ ጋር ተባበረ። አብዛኞቹ ልጆቻቸው “በኃጢአት” ከመወለዳቸውም በላይ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ወደቁ፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላም ጠቅላላው ዓለም ከእውነተኛው አምላክ የራቀ ሆነ።—ዘፍጥረት 6:5፤ መዝሙር 51:5
4. (ሀ) የዚህ ዓለም አምላክ ማን ነው? (ለ) በጣም አጣዳፊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?
4 ያን ጊዜ የነበረው ዓለም በጥፋት ውኃ ተደመሰሰ። (2 ጴጥሮስ 3:6) ከጥፋት ውኃ በኋላ ከይሖዋ የራቀ ሌላ ዓለም ተመሠረተ፤ ይህ ዓለም አሁንም አለ። ይህን ዓለም በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:19) ይህ ዓለም የይሖዋን ሕግ መንፈስና ትርጉም በመጻረር የሰይጣንን ዓላማ ያራምዳል። ሰይጣን የዚህ ዓለም አምላክ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሆኖም ኃይሉ ውስን የሆነ አምላክ ነው። ሰዎችን ደስተኛ ሊያደርጋቸው ወይም ሕይወት ሊሰጣቸው አይችልም፤ ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። ስለዚህ ዓላማ ያለው ሕይወትና የተሻለ ዓለም የሚፈልጉ ሰዎች በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ እውነተኛው አምላክ እንደሆነ ማወቅና ከዚያ በኋላ ደግሞ ፈቃዱን ማድረግን መማር ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 37:18, 27, 28፤ መክብብ 12:13) ስለዚህ የእምነት ሰዎች የሆኑ ወንዶችና ሴቶች ስለ ይሖዋ የሚናገረውን እውነት መመሥከራቸው ወይም ማወጃቸው በጣም አጣዳፊ ነው።
5. ጳውሎስ የጠቀሳቸው ‘እንደ ደመና ያሉ ምሥክሮች’ እነማን ናቸው? ከዘረዘራቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን በስም ጥቀስ።
5 ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንሥቶ እንዲህ ዓይነት ታማኝ ግለሰቦች በዓለም መድረክ ላይ ታይተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ታማኝ ግለሰቦች በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ በብዛት ከዘረዘራቸው በኋላ ‘እንደ ደመና ያሉ ምስክሮች’ በማለት ጠርቷቸዋል። (ዕብራውያን 12:1) በጳውሎስ ዝርዝር ውስጥ በመጀመሪያ የተጠቀሰው የአዳምና የሔዋን ሁለተኛ ልጅ የሆነው አቤል ነበር። በተጨማሪም ከጥፋት ውኃ በፊት ከነበሩት መካከል ሄኖክና ኖኅ ተጠቅሰዋል። (ዕብራውያን 11:4, 5, 7) የአይሁድ ዘር አባት የነበረው አብርሃም ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ተብሎ የተጠራው አብርሃም “የታመነውና እውነተኛው ምስክር” የሆነው የኢየሱስ ቅድመ አያት ሆነ።—ያዕቆብ 2:23፤ ራእይ 3:14
አብርሃም ለእውነት መሠከረ
6, 7. የአብርሃም ሕይወትና ተግባራት ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን የመሠከሩት በምን መንገዶች ነው?
6 አብርሃም የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነበር? በይሖዋ ላይ በነበረው ጠንካራ እምነትና በታማኝነት በመታዘዙ ነው። አብርሃም ዑር የተባለችውን ከተማ ለቅቆ እንዲወጣና ቀሪ ሕይወቱን ራቅ ወዳለ አገር ሄዶ እንዲያሳልፍ ሲታዘዝ ትእዛዙን ፈጽሟል። (ዘፍጥረት 15:7፤ ሥራ 7:2–4) ብዙውን ጊዜ ዘላን ጎሣዎች የዘላንነት ኑሯቸውን ይተዉና በከተማ ውስጥ ያለውን ይበልጥ የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት ይመርጣሉ። ስለዚህ አብርሃም በድንኳን ውስጥ ለመኖር ከተማውን ትቶ ሲወጣ በይሖዋ አምላክ ላይ እንደሚተማመን ጠንካራ ማስረጃ አቅርቧል። ታዛዥነቱ ለሚመለከቱት ሁሉ ራሱን የቻለ አንድ ምሥክርነት ነበር። አብርሃም ባሳየው እምነት ምክንያት ይሖዋ በጣም ባርኮታል። ምንም እንኳ አብርሃም የኖረው በድንኳን ውስጥ ቢሆንም ቁሳዊ ብልጽግና ነበረው። ሎጥና ቤተሰቡ ተማርከው ሲወሰዱ አብርሃም ማራኪዎቹን ተከታትሎ እንዲያስጥላቸው ይሖዋ ረድቶታል። የአብርሃም ሚስት በስተርጅናዋ ወንድ ልጅ ስለ ወለደችለት አብርሃም የዘሩ አባት እንደሚሆን ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽም ሕያው አምላክ እንደሆነ ሰዎች በአብርሃም አማካኝነት ተመልክተዋል።—ዘፍጥረት 12:1–3፤ 14:14–16፤ 21:1–7
7 አብርሃም ሎጥን ለማዳን ከሄደበት ስፍራ ሲመለስ የሳሌም (ቆየት ብሎ ኢየሩሳሌም የተባለችው) ንጉሥ የሆነውን መልከ ጼዴቅን አገኘው፤ እርሱም አብርሃምን ‘የልዑሉ አምላክ ወዳጅ አብራም ይባረክ’ በማለት አቀባበል አደረገለት። በተጨማሪም የሰዶም ንጉሥ አገኘውና ስጦታዎችን ሊሰጠው ፈለገ። አብርሃም ግን ስጦታዎቹን አልቀበልም አለ። ለምን? በረከቶቹን ከማን እንዳገኘ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አልፈለገም። እንዲህ አለ፦ “ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በልዑል እግዚአብሔር እምላለሁ፤ አንተ ‘አብራምን ሀብታም ያደረግሁት እኔ ነኝ’ እንዳትል ሌላው ቀርቶ አንዲት ክር ወይም የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አልወስድም።” (ዘፍጥረት 14:17–24 የ1980 ትርጉም) አብርሃም እንዴት ያለ ግሩም ምሥክር ነበር!
በብሔር ደረጃ የተነሡ ምሥክሮች
8. ሙሴ በይሖዋ ላይ ከፍተኛ እምነት ያሳየው እንዴት ነበር?
8 የአብርሃም ዝርያ የሆነው ሙሴም ጳውሎስ በጠቀሳቸው ምሥክሮች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል። ሙሴ የግብፅን ሀብት ትቶ ወጥቷል፤ ከዚያም የእስራኤልን ልጆች ነፃ ለማውጣት የዓለም ኃያል መንግሥት ገዢ የነበረውን ሰው በድፍረት ፊት ለፊት ተጋፍጧል። ሙሴ ይህን ድፍረት ያገኘው ከየት ነው? ከእምነቱ ነው። ጳውሎስ “[ሙሴ] የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” ብሏል። (ዕብራውያን 11:27) የግብፅ አማልክት በዓይን የሚታዩና በእጅ የሚዳሰሱ ነበሩ። ዛሬም እንኳ ቢሆን ሐውልቶቻቸው የሰዎችን ዓይን ይማርካሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ የማይታይ ቢሆንም ከእነዚህ ሐሰተኛ አማልክት ይበልጥ ለሙሴ እውን ሆኖለት ነበር። ሙሴ ይሖዋ እንዳለና ለአምላኪዎቹ ወሮታ እንደሚከፍል በጭራሽ አልተጠራጠረም። (ዕብራውያን 11:6) ሙሴ ጎላ ብሎ የሚታይ ምሥክር ሆነ።
9. የእስራኤል ብሔር ይሖዋን ማገልገል የነበረበት በምን መንገድ ነበር?
9 ሙሴ እስራኤላውያንን ነፃ ካወጣቸው በኋላ በይሖዋና በያዕቆብ በኩል የአብርሃም ዝርያዎች በሆኑት ሰዎች መካከል የተደረገው ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆነ። በዚሁ ሳቢያም የእስራኤል ብሔር የይሖዋ ልዩ ንብረት ሆኖ ተቋቋመ። (ዘጸአት 19:5, 6) ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔር ደረጃ ምሥክርነት መስጠት አስፈለገ። ከ800 ዓመታት በኋላ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ይህ ብሔር ሕልውና ካገኘበት ጊዜ አንሥቶ የሚሠሩ ናቸው፦ “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፣ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት]።” (ኢሳይያስ 43:10) የዚህ አዲስ ብሔር አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ያገለገሉት እንዴት ነው? በእምነታቸው፣ በታዛዥነታቸውና ይሖዋ ለእነርሱ ሲል ባደረጋቸው ነገሮች አማካኝነት ነው።
10. ይሖዋ ለእስራኤል ሲል ያደረጋቸው ተአምራት የመሠከሩት በምን መንገድ ነው? ይህስ ምን ውጤቶችን አስገኝቷል?
10 ይህ ብሔር ከተቋቋመ ከ40 ዓመታት ገደማ በኋላ እስራኤላውያን የተስፋይቱን ምድር ሊወርሱ ተቃረቡ። ሰላዮች ኢያሪኮ የተባለችውን ከተማ ሊሰልሉ ሄዱ፤ የኢያሪኮ ነዋሪ የሆነችው ረዓብ አዳነቻቸው። ለምን? እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በፊታችሁ እንዳደረቀ፣ በዮርዳኖስም ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት፣ በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል። ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም።” (ኢያሱ 2:10, 11) ስለ ይሖዋ ታላላቅ ሥራዎች የተሰራጨው ዜና ረዓብ እና ቤተሰቦቿ ኢያሪኮንና የሐሰት አማልክቶቿን ትተው እንዲወጡና ከእስራአል ሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ይሖዋን እንዲያመልኩት አነሣሣቸው። ይሖዋ በእስራኤል አማካኝነት ትልቅ ምሥክርነት እንደሰጠ አያጠራጥርም።—ኢያሱ 6:25
11. እያንዳንዱ እስራኤላዊ ወላጅ በመመሥከር ረገድ ምን ኃላፊነት ነበረበት?
11 እስራኤላውያን በግብፅ ውስጥ ሳሉ ይሖዋ ሙሴን ወደ ፈርዖን ላከውና “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በግብፃውያን ያደረግሁትን ነገር ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጅህ በልጅ ልጅህም ጆሮች ትነግር ዘንድ፣ ይህችንም ተአምራቴን በመካከላቸው አደርግ ዘንድ የእርሱን የባሪያዎቹንም ልብ አደንድኜአለሁና ወደ ፈርዖን ግባ አለው።” (ዘጸአት 10:1, 2) ታዛዥ እስራኤላውያን የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ለልጆቻቸው ይናገራሉ። ልጆቻቸው በተራቸው ደግሞ ለልጆቻቸው ይናገራሉ፣ እንዲህ እንዲህ እያለም ትውልድ ለትውልድ የይሖዋን ተአምራት ይናገራል። በዚህ መንገድ የይሖዋ ተአምራቶች ሲታወሱ ይኖራሉ። ዛሬም ቢሆን ወላጆች ለልጆቻቸው የመመሥከር ግዴታ አለባቸው።—ዘዳግም 6:4–7፤ ምሳሌ 22:6
12. ይሖዋ ለሰሎሞንና ለእስራኤላውያን የሰጣቸው በረከት ለመመሥከር ያገለገለው እንዴት ነው?
12 እስራኤላውያን ታማኝ በነበሩበት ወቅት ይሖዋ የሰጣቸው ከፍተኛ በረከት በአካባቢያቸው ለነበሩት ብሔራት ምሥክር ሆኗል። ይሖዋ እንደሚሰጣቸው ቃል የገባላቸውን በረከቶች በዝርዝር ከተረከላቸው በኋላ ሙሴ “የምድር አሕዛብም ሁሉ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ” አዓት] ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል” ብሏል። (ዘዳግም 28:10) ሰሎሞን ባሳየው እምነት ምክንያት ጥበብና ሀብት ተለግሶታል። በግዛት ዘመኑ ሕዝቡ በጣም በልጽጎና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ሰላም አግኝቶ ነበር። ይህን ወቅት በተመለከተ “ከአሕዛብም ሁሉ፣ ጥበቡንም ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር” የሚል እናነባለን። (1 ነገሥት 4:25, 29, 30, 34) ሰሎሞንን ከጎበኙት ሰዎች መካከል ጎላ ብላ የምትታየው የሳባ ንግሥት ነበረች። ይሖዋ ለሕዝቡና ለንጉሡ የለገሰውን በረከት ራሷ ከተመለከተች በኋላ “በአምላክህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ” አዓት] ፊት ንጉሥ እንድትሆን በዙፋኑ ላይ ያስቀምጥህ ዘንድ የወደደህ አምላክህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት] ብሩክ ይሁን፤ አምላክህ እስራኤልን ለዘላለም ያጸናቸው ዘንድ ወድዷቸዋልና” ብላለች።—2 ዜና መዋዕል 9:8
13. እስራኤላውያን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ የመሠከሩት በምን አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም? እኛስ በአሁኑ ጊዜ ከዚህ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
13 እስራኤላውያን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ የመሠከሩት ሐዋርያው ጳውሎስ በጠቀሰው ነገር ሳይሆን አይቀርም። በሮም ውስጥ ላለው የክርስቲያን ጉባኤ ስለ ሥጋዊ እስራኤላውያን ሲያብራራ “የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው” ብሏል። (ሮሜ 3:1, 2) ከሙሴ ጀምሮ አንዳንድ ታማኝ እስራኤላውያን ይሖዋ ከእስራኤል ጋር የነበረውን ግንኙነትም ሆነ ምክሮቹን እንዲሁም ሕጎቹንና ትንቢቶቹን በመንፈስ ተነሣስተው ጽፈዋል። እነዚህ የጥንት ጸሐፊዎች በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት አንድ አምላክ ብቻ እንዳለና ስሙ ይሖዋ እንደሆነ በአሁኑ ወቅት ያለነውን እኛን ጨምሮ ከእነርሱ በኋላ ለሚመጡት ትውልዶች ሁሉ መሥክረዋል።—ዳንኤል 12:9፤ 1 ጴጥሮስ 1:10–12
14. ለይሖዋ ከመሠከሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የተሰደዱት ለምንድን ነው?
14 እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት እምነት ሳያሳዩ መቅረታቸውና ይሖዋ ወደ ራሱ ሕዝብ ምሥክሮችን መላኩ በጣም ያሳዝናል። ከእነዚህ ምሥክሮች ውስጥ ብዙዎቹ ስደት ደርሶባቸዋል። ጳውሎስ አንዳንዶች “መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ” ብሏል። (ዕብራውያን 11:36) በእርግጥም ታማኝ ምሥክሮች ነበሩ! ብዙውን ጊዜ ስደት ይመጣባቸው የነበረው እንደነሱው ይሖዋ የመረጠው ብሔር አባላት ከነበሩ ሰዎች መሆኑ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! (ማቴዎስ 23:31, 37) እንዲያውም የሕዝቡ ኃጢአት በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት በ607 ከዘአበ ይሖዋ ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲያጠፉና በሕይወት የተረፉትን አብዛኞቹን እስራኤላውያን ማርከው እንዲወስዷቸው ባቢሎናውያንን አመጣባቸው። (ኤርምያስ 20:4፤ 21:10) ይህ ለይሖዋ ስም በብሔር ደረጃ ይሰጥ የነበረው ምሥክርነት መጨረሻ ነበርን? በፍጹም አልነበረም።
ለአማልክት የቀረበላቸው ፈተና
15. እስራኤላውያን በባቢሎን ውስጥ በግዞት በነበሩበት ወቅት እንኳ ምሥክርነት የተሰጠው እንዴት ነው?
15 በባቢሎን ውስጥ በግዞት እያሉ እንኳ የዚህ ብሔር ታማኝ አባላት የይሖዋን አምላክነትና ኃይል ከመመሥከር ወደ ኋላ አላሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል በድፍረት የናቡከደነፆርን ሕልም ተርጉሟል፣ ለብልጣሶር በግድግዳ ላይ የተጻፈለትን ጽሑፍ አብራርቷል፤ በተጨማሪም ዳርዮስ ጸሎትን በተመለከተ ያወጣውን ትእዛዝ ለመፈጸም ፈቃደኛ በመሆን አቋሙን አላላላም። ሦስቱ ዕብራውያን ለአንድ የተቀረጸ ምስል አንሰግድም ባሉ ጊዜ ለናቡከደነፆር አስደናቂ ምሥክርነት ሰጥተዋል።—ዳንኤል 3:13–18፤ 5:13–29፤ 6:4–27
16. ይሖዋ እስራኤላውያን ወደ ገዛ ምድራቸው እንደሚመለሱ አስቀድሞ የተነበየው እንዴት ነው? እስራኤላውያን የሚመለሱበት ዓላማስ ምን ነበር?
16 ሆኖም ይሖዋ በእስራኤል ምድር ላይ እንደገና በብሔር ደረጃ ምሥክርነት እንዲሰጥ ዓላማ ነበረው። በባቢሎን ውስጥ በግዞት በነበሩ አይሁዳውያን መካከል ትንቢት ይናገር የነበረው ሕዝቅኤል ባድማ የሆነችውን ምድር በተመለከተ ይሖዋ የወሰነውን ነገር ሲጽፍ “እኔም የእስራኤልን ቤት ሰዎች ሁሉ ሁሉንም አበዛባችኋለሁ፣ በከተሞችም ሰዎች ይኖሩባቸዋል ባድማዎቹም ስፍራዎች ይሠራሉ” ብሏል። (ሕዝቅኤል 36:10) ይሖዋ ይህን የሚያደርገው ለምንድን ነው? በአንደኛ ደረጃ ለራሱ ስም እንዲመሠከር ሲል ነው። በሕዝቅኤል አማካኝነት “የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም” ብሏል።—ሕዝቅኤል 36:22፤ ኤርምያስ 50:28
17. በኢሳይያስ 43:10 ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምንድን ነው?
17 ነቢዩ ኢሳይያስ እስራኤላውያን የይሖዋ ምሥክርና ባሪያው እንደሆኑ የሚገልጹትን የኢሳይያስ 43:10 ቃላት በመንፈስ ተነሣስቶ የጻፈው እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ እንደሚመለሱ ትንቢት በተናገረበት ወቅት ነው። በኢሳይያስ ምዕራፍ 43 እና 44 ላይ ይሖዋ የእስራኤል ፈጣሪ፣ መሥራች፣ አምላክ፣ ቅዱስ፣ አዳኝ፣ ተቤዥ፣ ንጉሥና ሠሪ እንደሆነ ተገልጿል። (ኢሳይያስ 43:3, 14, 15፤ 44:2) እስራኤላውያን እንዲማረኩ የፈቀደው በተደጋጋሚ ጊዜያት በዚህ መልክ ሳያከብሩት በመቅረታቸው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉም እንኳ ሕዝቡ ነበሩ። ይሖዋ “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፣ አንተ የእኔ ነህ” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 43:1) እስራኤላውያን በባቢሎን ውስጥ ያሳለፉት የግዞት ኑሮ ማክተም ነበረበት።
18. እስራኤላውያን ከባቢሎን ነፃ መውጣታቸው ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ያረጋገጠው እንዴት ነው?
18 እንዲያውም ይሖዋ የእስራኤልን ከባቢሎን ነፃ መውጣት ለአማልክት የቀረበ ፈተና አደረገው። የአሕዛብን ሐሰተኛ አማልክት ለራሳቸው ምሥክሮችን እንዲያቀርቡ ተገዳደራቸውና እስራኤልን ምሥክሩ አድርጎ አቆመ። (ኢሳይያስ 43:9, 12) እስራኤልን ከግዞት ነፃ ባወጣበት ወቅት የባቢሎን ጣዖታት ጨርሶ አማልክት እንዳልሆኑና እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አረጋግጧል። (ኢሳይያስ 43:14, 15) ይህ ድርጊት ከመፈጸሙ ከ200 ዓመታት ገደማ በፊት ፋርሳዊው ቂሮስን በስሙ ጠርቶ አይሁዳውያንን ነፃ ለማውጣት የሚጠቀምበት ባሪያው እንደሆነ በመግለጽ የአምላክነቱን ተጨማሪ ማስረጃ አቀረበ። (ኢሳይያስ 44:28) እስራኤል ነፃ ትወጣለች። ለምን? ይሖዋ ማብራሪያ ሲሰጥ ‘[እስራኤላውያን] ምስጋናዬን ይናገራሉ’ ብሏል። (ኢሳይያስ 43:21) ሁኔታው መመሥከር የሚችሉበት ተጨማሪ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።
19. እስራኤላውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ቂሮስ ያቀረበላቸው ጥሪና ታማኝ አይሁዳውያን ከምርኮ መልስ ያደረጓቸው ነገሮች ምን ምሥክርነት ሰጥተዋል?
19 አስቀድሞ እንደተተነበየው ጊዜው ሲደርስ ፋርሳዊው ቂሮስ ባቢሎንን ድል አደረጋት። ቂሮስ አረማዊ ቢሆንም አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ እንዲወጡ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ እንዲህ በማለት የይሖዋን አምላክነት አውጅዋል፦ “ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፣ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፣ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ” አዓት] ቤት ይሥራ።” (ዕዝራ 1:3) ብዙ አይሁዳውያን የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለዋል። ረጅም ጉዞ አድርገው ወደ ተስፋይቱ ምድር ተመለሱና የቀድሞው ቤተ መቅደስ ይገኝ በነበረበት ስፍራ መሠዊያ ሠሩ። ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮችና ኃይለኛ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም በመጨረሻ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመሥራት ቻሉ። ይህ ሁሉ የተፈጸመው ይሖዋ ራሱ “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም” በማለት በተናገረው መሠረት ነው። (ዘካርያስ 4:6) እነዚህ ክንውኖች ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ተጨማሪ ማስረጃ ሆነዋል።
20. እስራኤላውያን ድክመት ቢኖርባቸውም በጥንቱ ዓለም ስለ ይሖዋ ስም በመመሥከራቸው ረገድ ምን ሊባል ይችላል?
20 በዚህ መንገድ የእስራኤል ብሔር ፍጹም ያልሆነና አንዳንዴም ዓመፀኝነት የሚታይበት ቢሆንም ይሖዋ እስራኤልን እንደ ምሥክሩ አድርጎ መጠቀሙን ቀጠለ። በቅድመ ክርስትና ዘመን ይህ ብሔር ከቤተ መቅደሱና ከክህነቱ ጋር የዓለም የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ሆኖ ነበር። ይሖዋ ከእስራኤል ጋር በሚዛመድ መልኩ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያደረጋቸውን ነገሮች የሚያነብ ሁሉ አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለና ስሙም ይሖዋ እንደሆነ በጭራሽ አይጠራጠርም። (ዘዳግም 6:4፤ ዘካርያስ 14:9) ይሁን እንጂ ለይሖዋ ስም ከዚህ የበለጠ ምሥክርነት መሰጠት ነበረበት፤ ይህ ጉዳይ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።
ታስታውሳለህን?
◻ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አብርሃም የመሠከረው እንዴት ነው?
◻ ሙሴ ታማኝ ምሥክር እንዲሆን ያስቻለው የትኛው ጎላ ብሎ የሚታይ ባሕርይ ነው?
◻ እስራኤላውያን ስለ ይሖዋ በብሔር ደረጃ የመሠከሩት በምን መንገዶች ነው?
◻ እስራኤል ከባቢሎን ነፃ መውጣቷ ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነበር?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃም ባሳየው እምነትና ታዛዥነት ለይሖዋ አምላክነት ጉልህ ምሥክርነት ሰጥቷል