ምዕራፍ 11
በኢንተርኔት ጓደኝነት ብመሠርት ምን ችግር አለው?
ከሰዎች ጋር ለማውራት በምን መልኩ መገናኘት ትመርጣለህ?
□ ፊት ለፊት
□ በስልክ
□ በኮምፒውተር
ከማን ጋር ማውራት ይቀልሃል?
□ ከክፍልህ ልጆች
□ ከቤተሰብህ አባላት
□ ከክርስቲያን ባልንጀሮችህ
በነፃነት ማውራት እንደምትችል የሚሰማህ የት ስትሆን ነው?
□ በትምህርት ቤት
□ በቤት
□ በጉባኤ ስብሰባዎች
ለመጀመሪያው ጥያቄ የሰጠኸውን መልስ እስቲ መለስ ብለህ እየው። መልስህ ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት ከማውራት ይልቅ በኮምፒውተር አማካኝነት ማውራት እንደምትመርጥ የሚያሳይ ነው? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በርካታ ወጣቶች ጓደኝነት ለመመሥረትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት የሚመርጡት ኢንተርኔትን ነው። ኢሌን የተባለች አንዲት ወጣት “በዓለም ዙሪያ ከሚኖሩና በምንም መንገድ ልናገኛቸው ከማንችላቸው ሰዎች ጋር መገናኘት መቻል በጣም ደስ የሚል ነገር ነው” ብላለች። የ19 ዓመቷ ታሚ ደግሞ ወጣቶች ኢንተርኔትን የሚመርጡበትን ሌላውን ምክንያት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች የሚወዱህ ዓይነት ሰው ሆነህ ለመቅረብ ያመችሃል። ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት በምትገናኝበት ጊዜ ግን ካልወደዱህ ምንም ማድረግ አትችልም።”
እስቲ አሁን ደግሞ ለሁለተኛውና ለሦስተኛው ጥያቄ የሰጠኸውን መልስ ተመልከት። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከምታገኛቸው ክርስቲያኖች ጋር ከማውራት ይልቅ ከክፍልህ ልጆች ጋር ማውራት የሚቀልህ ከሆነ ሊገርምህ አይገባም። የ18 ዓመቷ ዮርዳኖስ እንዲህ ብላለች፦ “በትምህርት ቤት እንደ አንተ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሰዎች የማግኘት አጋጣሚህ ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ ከእነሱ ጋር መቀራረብ ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል።”
ከላይ ከተመለከትናቸው ነጥቦች አንጻር አብረውህ ከሚማሩት ልጆች ጋር በኢንተርኔት ለማውራት ብትፈልግ የሚያስደንቅ አይሆንም። ታሚ በአንድ ወቅት እንዲህ ታደርግ ነበር። “አብረውኝ የሚማሩት ልጆች በሙሉ በኢንተርኔት ስለ ተለያዩ ነገሮች ያወሩ ስለነበር እኔ ብቻ መለየት አልፈለግሁም” ብላለች።a የ20 ዓመቷ ናርዶስ ከጓደኞቿ ጋር ለመገናኘት የሚያስችላት ድረ ገጽ ከፍታለች። “ቴክኖሎጂ እየተራቀቀ መጥቷል። አዳዲስ የመገናኛ መንገዶች ተፈጥረዋል። ኢንተርኔት ከእነዚህ አንዱ ሲሆን እኔም ወድጄዋለሁ” ብላለች።
አደጋዎቹን ግምት ውስጥ አስገባ
አንዳንድ ወጣቶች ጓደኝነት ለመመሥረትም ሆነ ከዚያ በኋላ ለመገናኘት የሚቀላቸው ኢንተርኔት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ናርዶስ “ኢንተርኔት፣ ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት ብታወራ ኖሮ የማይኖርህን ዓይነት ድፍረት ይሰጥሃል” ብላለች። ታሚ በዚህ ትስማማለች። “ዓይናፋር ከሆንክ በኢንተርኔት ስታወራ፣ ምን እንደምትል አስቀድመህ ለማሰብ አጋጣሚ ታገኛለህ” ብላለች።
ይሁን እንጂ በኢንተርኔት ከሰዎች ጋር መገናኘት አደጋዎች አሉት፤ እነዚህን አደጋዎች ችላ ብሎ ማለፍ ደግሞ ሞኝነት ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አደገኛ በሆነ አካባቢ ዓይንህን በጨርቅ ሸፍነህ ትጓዛለህ? ታዲያ ኢንተርኔት የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ሳታውቅ በጭፍን በኢንተርኔት መጠቀም ተገቢ ይመስልሃል?
በኢንተርኔት ጓደኞች ለማግኘት መሞከር ምን አደጋዎች እንዳሉት እንመልከት። ከማታውቃቸው ሰዎች ጋር በኢንተርኔት የማውራት ልማድ የነበራት ኢሌን “መጥፎ ከሆኑ ሰዎች ጋር የመገናኘትህ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው” ብላለች። አክላም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ በኢንተርኔት ማውራት ጀምራችሁ ደቂቃ እንኳ ሳትቆዩ ግለሰቡ የብልግና ወሬ ያነሳል፤ ወይም ‘ድንግል ነሽ? በአፍ የፆታ ግንኙነት ትፈጽሚያለሽ?’ እንደሚሉ ያሉ ጥያቄዎች ያቀርባል። እንዲያውም አንዳንዶች ሳይበርሴክስ [በኢንተርኔት የብልግና ወሬ በማውራት የፆታ ስሜትን ማርካት] እንድትፈጽሙ ይጋብዟችኋል።”
የምታወሩት ከምታምኑት ጓደኛችሁ ጋር ቢሆንስ? እንደዚያም ቢሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ጆአን “‘ንጹህ ጓደኛዬ ነው’ ከምትሉት ተቃራኒ ፆታ ያለው ሰው ጋርም እንኳ ለረጅም ሰዓት ልታወሩ ትችላላችሁ። መልእክት በመለዋወጥ የምታሳልፉት ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ ከግለሰቡ ጋር ይበልጥ እየተቀራረባችሁ ትሄዳላችሁ፤ ለማንም የማትናገሩትን ነገር የማውራት አጋጣሚያችሁ የሰፋ ይሆናል።”
‘ማንነታቸውን የሚደብቁ ሰዎች’
ንጉሥ ዳዊት ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ላለመግጠም መጠንቀቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ ያውቅ ነበር። “አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር አልተቀመጥኩም፤ ማንነታቸውን ከሚደብቁ ሰዎች ጋርም አልገጥምም” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 26:4 NW
በኢንተርኔት በምትጠቀምበት ወቅት ዳዊት የጠቀሳቸው ዓይነት ሰዎች አጋጥመውህ ያውቃሉ? በኢንተርኔት ላይ ሰዎች ‘ማንነታቸውን የሚደብቁት’ ለምን ሊሆን ይችላል? ․․․․․
በሌላ በኩል ግን በኢንተርኔት ስትጠቀም ማንነትህን የምትደብቀው አንተ ትሆን? ቻት ሩም የመጠቀም ልማድ የነበራት አቢጋኤል “ከሰዎች ጋር መነጋገር ከጀመርኩ በኋላ ከምናወራው ነገር ጋር የሚስማማ ባሕርይ እንዳለኝ ለማስመሰል እሞክራለሁ” ብላለች።
ሊያ የተባለች ወጣት የፈጸመችው የማታለል ድርጊት ከዚህ የተለየ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ጎረቤት ጉባኤ ካለ አንድ ልጅ ጋር አዘውትረን በኢንተርኔት እናወራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ አንዳችን ለሌላው ያለንን ‘የፍቅር’ ስሜት መግለጽ ጀመርን። ወላጆቼ በአጠገቤ ሲያልፉ በኮምፒውተሩ ላይ ከእሱ ጋር የምንጻጻፍበትን ገጽ እደብቀው ስለነበር ምን እያደረግኩ እንዳለ ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። የ13 ዓመቷ ልጃቸው ለ14 ዓመት ልጅ የፍቅር ግጥም እየጻፈች ነው ብለው ጨርሶ አልጠረጠሩም። ይህ በሐሳባቸውም እንኳ አልነበረም።”
ራስህን ከአደጋ መጠበቅ
በኢንተርኔት ከሰዎች ጋር ማውራት ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ አይካድም። ለምሳሌ ያህል፣ አዋቂዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት በኢንተርኔት ይጠቀማሉ። አንተም እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ራስህን ከአደጋ ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላለህ? የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት።
● ኢንተርኔት ስትጠቀም ብዙ ጊዜ እንዳታጠፋ ራስህን ተቆጣጠር፤ እንዲሁም እንቅልፍን ጨምሮ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች የምታውለውን ጊዜ እንዳይሻማብህ ተጠንቀቅ። ብራያን የተባለ ወጣት “አብረውኝ የሚማሩ አንዳንድ ልጆች ኢንተርኔት ሲጠቀሙ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ እንደቆዩ ይናገራሉ” ብሏል።—ኤፌሶን 5:15, 16
● ከምታውቃቸው አሊያም ማንነታቸውን ማጣራት ከምትችለው ሰዎች ጋር ብቻ ተነጋገር። ጥሩ ሥነ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በቀላሉ የሚታለሉ ወጣቶችን ለማጥመድ ኢንተርኔትን ሲያስሱ ይውላሉ።—ሮም 16:18
● በኢንተርኔት አማካኝነት ስትገበያይ ጠንቃቃ ሁን። ለሌሎች የግል መረጃዎችን በምትሰጥበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። አለበለዚያ ልትጭበረበር ወይም ከዚያ ለከፋ ችግር ልትጋለጥ ትችላለህ።—ማቴዎስ 10:16
● ለጓደኞችህ ፎቶህን በምትልክበት ወቅት ‘ይህንን ፎቶ የሚያይ ሰው በእውነት የአምላክ አገልጋይ መሆኔን ሊጠራጠር ይችላል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።—ቲቶ 2:7, 8
● ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት ስትነጋገር እንደምታደርገው ሁሉ በኢንተርኔት ስታወራም ጨዋታው ተቀይሮ “የማይገቡ ነገሮች” ከተነሱ ውይይቱ እንዲቋረጥ አድርግ።—ኤፌሶን 5:3, 4
● ምንጊዜም በኢንተርኔት ስትጠቀም እውነቱን ለመደበቅ አትሞክር። ከወላጆችህ ‘ማንነትህን የምትደብቅ’ ከሆነ አንድ ችግር አለ ማለት ነው። ካሪ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ወጣት “ከእናቴ የምደብቀው ምንም ነገር የለም። ኢንተርኔት ስጠቀም የማደርገውን ነገር ሁሉ አሳያታለሁ” ብላለች።—ዕብራውያን 13:18
“መታገሥህ የሚክስ ይሆንልሃል!”
ጓደኞች ለማግኘት መፈለግህ ያለ ነገር ነው። የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ከሌሎች ጋር መሆን ያስደስታቸዋል። (ዘፍጥረት 2:18) በመሆኑም ጓደኞች የማፍራት ፍላጎት ቢኖርህ ሊገርምህ አይገባም፤ የተፈጠርከው እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንዲኖርህ ተደርገህ ነው! መጠንቀቅ የሚኖርብህ እንዴት እንደምትመርጣቸው ብቻ ነው።
ጓደኞችህን በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መሠረት የምትመርጥ ከሆነ በጣም ጥሩ ጓደኞች እንደምታገኝ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አንዲት የ15 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋንና አንተን የሚወዱ ጓደኞች ማግኘት አስቸጋሪ ነው። እንዲህ ዓይነት ጓደኞች ስታገኝ ግን መታገሥህ የሚክስ ይሆንልሃል!”
ቃላት አይጎዱም ያለው ማን ነው? ሐሜት እንደ ሰይፍ ሊወጋ ይችላል። ታዲያ ከሐሜት መራቅ የምትችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
ቁልፍ ጥቅስ
“ከሆኑ ሰዎች ጋር አልተቀመጥኩም፤ ማንነታቸውን ከሚደብቁ ሰዎች ጋርም አልገጥምም።”—መዝሙር 26:4 NW
ጠቃሚ ምክር
ኢንተርኔት ስትጠቀም ጊዜው ከመቼው እንደሚበር አታውቀውም! ስለዚህ የምታቆምበትን ጊዜ ወስን፤ ከዚያም የወሰንከውን ጊዜ አክብር። አስፈላጊ ከሆነ ጊዜው ሲደርስ ምልክት እንዲሰጥህ ሰዓትህን ሙላው።
ይህን ታውቅ ነበር?
መጥፎ ዓላማ ያለው ሰው ስለ አንተ ከኢንተርኔት ላይ ጥቂት መረጃዎችን ምናልባትም የአንተንና የትምህርት ቤትህን ስም እንዲሁም የስልክ ቁጥርህን ማወቅ ከቻለ በቀላሉ ያገኝሃል።
ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች
በሳምንት ውስጥ ኢንተርኔት በመጠቀም የማጠፋው ጊዜ ከ ․․․․․ መብለጥ የለበትም፤ ይህንን ውሳኔዬን ለማክበር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ኢንተርኔት እየተጠቀምኩ ሳለሁ የማላውቀው ሰው ቢያናግረኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․
ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․
ምን ይመስልሃል?
● በኢንተርኔት አማካኝነት ከሰዎች ጋር መነጋገር ፊት ለፊት ከማውራት ጋር ሲነጻጸር ምን ጥቅሞችና ጉዳቶች አሉት?
● በኢንተርኔት ስታወራ ያልሆንከውን ሆነህ መቅረብ ቀላል የሚሆነው ለምንድን ነው?
● ኢንተርኔት ስትጠቀም ብዙ ጊዜ እንዳታጠፋ ራስህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
● ኢንተርኔት ለየትኞቹ ጠቃሚ ዓላማዎች ሊውል ይችላል?
[በገጽ 103 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከማላውቃቸው ወይም በአካል ብንገናኝ ኖሮ ጓደኛ ከማላደርጋቸው ሰዎች ጋር በኢንተርኔት አልነጋገርም።”—ጆኣን
[በገጽ 100 እና 101 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አደገኛ በሆነ አካባቢ ዓይንሽን በጨርቅ ሸፍነሽ ትጓዣለሽ? ታዲያ ኢንተርኔት የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ሳታውቂ በጭፍን ኢንተርኔት መጠቀም ተገቢ ይመስልሻል?