ሚልክያስ
3 “እነሆ፣ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ እሱም በፊቴ መንገድ ይጠርጋል።*+ እናንተ የምትፈልጉት እውነተኛው ጌታ* በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤+ ደስ የምትሰኙበት የቃል ኪዳኑ መልእክተኛም ይመጣል። እነሆ፣ እሱ በእርግጥ ይመጣል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
2 “ይሁንና እሱ የሚመጣበትን ቀን ሊቋቋም የሚችል ማን ነው? እሱ በሚገለጥበት ጊዜስ ማን ሊቆም ይችላል? እሱ እንደ አንጥረኛ እሳት፣ እንደ ልብስ አጣቢም እንዶድ* ይሆናልና።+ 3 ደግሞም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤+ የሌዊንም ልጆች ያነጻል፤* እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያጠራቸዋል፤ ይሖዋም በጽድቅ መባ የሚያቀርብ ሕዝብ ይኖረዋል። 4 ይሁዳና ኢየሩሳሌም ስጦታ አድርገው የሚያቀርቡት መባ በቀድሞው ጊዜና በጥንት ዘመን እንደነበረው ይሖዋን ደስ ያሰኘዋል።*+
5 “ለመፍረድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞቹ፣+ በአመንዝሮቹ፣ በሐሰት በሚምሉት ሰዎች+ እንዲሁም ቅጥር ሠራተኛውን፣+ መበለቲቱንና አባት የሌለውን ልጅ* በሚያጭበረብሩትና+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰው ለመርዳት ፈቃደኛ በማይሆኑት* ላይ ወዲያውኑ እመሠክርባቸዋለሁ።+ እነዚህ ሰዎች እኔን አልፈሩም” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
6 “እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም።*+ እናንተም የያዕቆብ ልጆች ናችሁ፤ ገና አልጠፋችሁም። 7 ከአባቶቻችሁ ዘመን አንስቶ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ ደግሞም ሥርዓቴን አልጠበቃችሁም።+ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
እናንተ ግን “የምንመለሰው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።
8 “በውኑ ተራ ሰው አምላክን ይሰርቃል? እናንተ ግን እኔን ትሰርቁኛላችሁ።”
እናንተም “የሰረቅንህ እንዴት ነው?” ትላላችሁ።
“በምትሰጡት አሥራትና* መዋጮ ነው። 9 እናንተ በእርግጥ የተረገማችሁ ናችሁ፤* ትሰርቁኛላችሁና፤ አዎ፣ መላው ብሔር እንዲህ ያደርጋል። 10 በቤቴ ውስጥ እህል እንዲኖር አሥራቱን* ሁሉ ወደ ጎተራው አስገቡ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ+ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣*+ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ።”
11 “ለእናንተም ስል፣ በላተኛውን* እገሥጻለሁ፤ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ላይ ያለው የወይን ተክልም ፍሬ አልባ አይሆንም”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
12 “እናንተ የደስታ ምድር ስለምትሆኑ ብሔራት ሁሉ ደስተኞች ብለው ይጠሯችኋል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
13 “በእኔ ላይ ኃይለ ቃል ተናግራችኋል” ይላል ይሖዋ።
እናንተም “በአንተ ላይ የተናገርነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።+
14 “እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አምላክን ማገልገል ዋጋ የለውም።+ ለእሱ ያለብንን ግዴታ በመጠበቃችንና በኃጢአታችን የተነሳ ማዘናችንን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ፊት በማሳየታችን ምን ተጠቀምን? 15 አሁን እብሪተኛ የሆኑ ሰዎችን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ደግሞም ክፉ አድራጊዎች ስኬታማ ሆነዋል።+ እነሱ በድፍረት አምላክን ይፈታተናሉ፤ ከቅጣትም ያመልጣሉ።’”
16 በዚያ ጊዜ ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከባልንጀሮቻቸው ጋር ተነጋገሩ፤ ይሖዋም በትኩረት አዳመጠ፤ ደግሞም ሰማ። ይሖዋንም ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ*+ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።+
17 “የእኔ ልዩ ንብረት*+ በማደርጋቸውም ቀን እነሱ የእኔ ይሆናሉ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “አባት ለሚታዘዝለት ልጁ እንደሚራራ እኔም እራራላቸዋለሁ።+ 18 እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”+