ሐጌ
2 በሰባተኛው ወር፣ ከወሩም በ21ኛው ቀን የይሖዋ ቃል በነቢዩ ሐጌ+ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የይሁዳን ገዢ+ የሰላትያልን ልጅ ዘሩባቤልንና+ ሊቀ ካህናቱን የየሆጼዴቅን+ ልጅ ኢያሱን+ እንዲሁም የቀረውን ሕዝብ እባክህ እንዲህ ብለህ ጠይቃቸው፦ 3 ‘የዚህ ቤት* የቀድሞ ክብሩ እንዴት እንደነበረ ያየ ሰው በመካከላችሁ አለ?+ አሁንስ እንዴት ሆኖ ይታያችኋል? ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር ከምንም የማይቆጠር አይደለም?’+
4 “‘አሁን ግን ዘሩባቤል፣ በርታ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘የየሆጼዴቅ ልጅ ሊቀ ካህናቱ ኢያሱ፣ አንተም በርታ።’
“‘እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ፣ በርቱና ሥሩ’+ ይላል ይሖዋ።
“‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 5 ‘ከግብፅ በወጣችሁበት ጊዜ የገባሁላችሁን ቃል አስታውሱ፤+ መንፈሴም በመካከላችሁ ይኖራል።*+ አትፍሩ።’”+
6 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገና ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ።’+
7 “‘ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ፤ በብሔራትም ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ* ነገሮች ይመጣሉ፤+ ደግሞም ይህን ቤት በክብር እሞላዋለሁ’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
8 “‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
9 “‘ይህ ቤት ወደፊት የሚጎናጸፈው ክብር ከቀድሞው የበለጠ ይሆናል’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
“‘በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”
10 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር፣ ከወሩም በ24ኛው ቀን የይሖዋ ቃል ወደ ነቢዩ ሐጌ+ እንዲህ ሲል መጣ፦ 11 “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እባክህ፣ ካህናቱን ስለ ሕጉ እንዲህ ብለህ ጠይቃቸው፦+ 12 “አንድ ሰው በልብሱ እጥፋት የተቀደሰ ሥጋ ቢይዝና ልብሱ ዳቦ፣ ወጥ፣ የወይን ጠጅ፣ ዘይት ወይም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ምግብ ቢነካ፣ የነካው ነገር ቅዱስ ይሆናል?”’”
ካህናቱ “አይሆንም!” ብለው መለሱ።
13 ከዚያም ሐጌ እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ “አስከሬን በመንካቱ* የረከሰ ሰው ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱን ቢነካ የተነካው ነገር ይረክሳል?”+
ካህናቱ “አዎ፣ ይረክሳል” ብለው መለሱ።
14 ሐጌም እንዲህ አለ፦ “‘ይህም ሕዝብ እንዲሁ ነው፤ ይህም ብሔር በፊቴ እንዲሁ ነው’ ይላል ይሖዋ፤ ‘የእጆቻቸውም ሥራ ሁሉ እንዲሁ ነው፤ በዚያ የሚያቀርቡት ማንኛውም ነገር የረከሰ ነው።’
15 “‘አሁን ግን እባካችሁ ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይህን ልብ በሉ፦* በይሖዋ ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት፣+ 16 ያኔ ሁኔታው ምን ይመስል ነበር? አንድ ሰው 20 መስፈሪያ አገኛለሁ ብሎ እህል ወደተከመረበት ቦታ በመጣ ጊዜ 10 መስፈሪያ ብቻ አገኘ፤ ደግሞም አንድ ሰው 50 መለኪያ የወይን ጠጅ ለማግኘት ወደ ወይን መጭመቂያው በመጣ ጊዜ 20 መለኪያ ብቻ አገኘ፤+ 17 እናንተን ይኸውም የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በሚለበልብና በሚያደርቅ ነፋስ፣ በዋግና+ በበረዶ መታሁ፤ ይሁንና አንዳችሁም ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል ይሖዋ።
18 “‘በዛሬው ዕለት ይኸውም በዘጠነኛው ወር፣ ከወሩም በ24ኛው ቀን የይሖዋ ቤተ መቅደስ መሠረት ተጥሏል።+ እባካችሁ ከዚህ ቀን ጀምሮ ይህን ልብ በሉ፦* 19 በጎተራ* ውስጥ የቀረ ዘር አሁንም አለ?+ የወይን ተክሉ፣ በለሱ፣ ሮማኑና የወይራ ዛፉ እስካሁን ድረስ ፍሬ አላፈሩም። ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’”+
20 በወሩ 24ኛ ቀን የይሖዋ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፦+ 21 “ለይሁዳ ገዢ ለዘሩባቤል እንዲህ በለው፦ ‘ሰማያትንና ምድርን አናውጣለሁ።+ 22 የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የብሔራት መንግሥታትንም ብርታት አጠፋለሁ፤+ ሠረገላውንና የሚቀመጡበትን ሰዎች እገለብጣለሁ፤ ፈረሶቹና ጋላቢዎቻቸውም እያንዳንዳቸው በገዛ ወንድማቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።’”+
23 “‘የሰላትያል+ ልጅ አገልጋዬ ዘሩባቤል+ ሆይ’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ‘በዚያ ቀን እወስድሃለሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ደግሞም እንደ ማኅተም ቀለበት አደርግሃለሁ፤ ምክንያቱም የመረጥኩት አንተን ነው’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”