የሉቃስ ወንጌል
19 ከዚያም ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ገብቶ በዚያ እያለፈ ነበር። 2 በዚያም ዘኬዎስ የተባለ አንድ ሀብታም ሰው የነበረ ሲሆን ይህ ሰው የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ ነበር። 3 እሱም ኢየሱስ የሚባለው ማን እንደሆነ ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ሆኖም አጭር በመሆኑ ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ማየት አልቻለም። 4 ኢየሱስ በዚያ በኩል ያልፍ ስለነበር ዘኬዎስ ሮጦ ወደ ፊት በመሄድ እሱን ለማየት አንድ የሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። 5 ኢየሱስ እዚያ ቦታ በደረሰ ጊዜ ቀና ብሎ ተመለከተውና “ዘኬዎስ፣ ዛሬ ወደ አንተ ቤት ስለምመጣ ቶሎ ውረድ” አለው። 6 በዚህ ጊዜ በፍጥነት ወርዶ ደስ እያለው በእንግድነት ተቀበለው። 7 ሰዎቹ ይህን ባዩ ጊዜ “ኃጢአተኛ ሰው ቤት ሊስተናገድ ገባ” ብለው ሁሉም አጉተመተሙ።+ 8 ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን “ጌታ ሆይ፣ ካለኝ ሀብት ግማሹን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ከሰው የቀማሁትንም* ሁሉ አራት እጥፍ እመልሳለሁ” አለው።+ 9 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ይህም ሰው የአብርሃም ልጅ ስለሆነ ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን መጥቷል። 10 ምክንያቱም የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ነው።”+
11 እነሱም እነዚህን ነገሮች እየሰሙ ሳሉ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ ይህን የተናገረው ኢየሩሳሌም ሲደርሱ የአምላክ መንግሥት ወዲያውኑ የሚገለጥ ስለመሰላቸው ነው።+ 12 ስለዚህ እንዲህ አለ፦ “አንድ መስፍን ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር ሊሄድ ተነሳ።+ 13 ከባሪያዎቹ መካከል አሥሩን ጠርቶ አሥር ምናን* ሰጣቸውና ‘እስክመጣ ድረስ ነግዱበት’ አላቸው።+ 14 የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ስለነበር እሱ ከሄደ በኋላ ‘ይህ ሰው በእኛ ላይ እንዲነግሥ አንፈልግም’ ብለው እንዲነግሩላቸው መልእክተኞች ላኩ።
15 “ከጊዜ በኋላ ንጉሣዊ ሥልጣኑን* ተረክቦ ሲመጣ ገንዘብ* የሰጣቸው ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ለማወቅ አስጠራቸው።+ 16 በመሆኑም የመጀመሪያው ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አሥር ምናን ትርፍ አስገኝቷል’ አለው።+ 17 ጌታው ‘ጎበዝ፣ አንተ ጥሩ ባሪያ! በጣም አነስተኛ በሆነው ነገር ታማኝ ሆነህ ስለተገኘህ በአሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ተሰጥቶሃል’ አለው።+ 18 ሁለተኛው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታዬ፣ ምናንህ አምስት ምናን አስገኝቷል’ አለ።+ 19 ይሄኛውንም ‘አንተም በአምስት ከተሞች ላይ ተሹመሃል’ አለው። 20 ሆኖም ሌላኛው መጥቶ እንዲህ አለ፦ ‘ጌታዬ፣ በጨርቅ ጠቅልዬ የደበቅኩት ምናንህ ይኸውልህ። 21 ይህን ያደረግኩት ጨካኝ ሰው ስለሆንክ ፈርቼህ ነው፤ አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፣ ያልዘራኸውንም የምታጭድ ሰው ነህ።’+ 22 ጌታውም እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ክፉ ባሪያ፣ በራስህ ቃል እፈርድብሃለሁ። ያላስቀመጥኩትን የምወስድ፣ ያልዘራሁትንም የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደሆንኩ ታውቅ ኖሯል ማለት ነው?+ 23 ታዲያ ገንዘቤን* ለምን ለገንዘብ ለዋጮች* አልሰጠህም? እንደዚህ አድርገህ ቢሆን ኖሮ ስመጣ ከነወለዱ እወስደው ነበር።’
24 “ከዚያም በዚያ ቆመው የነበሩትን ሰዎች ‘ምናኑን ውሰዱበትና አሥር ምናን ላለው ስጡት’ አላቸው።+ 25 እነሱ ግን ‘ጌታ ሆይ፣ እሱ እኮ አሥር ምናን አለው’ አሉት። እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ 26 ‘እላችኋለሁ፣ ላለው ሁሉ ተጨማሪ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ሰው ላይ ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።+ 27 በተጨማሪም በእነሱ ላይ እንድነግሥ ያልፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡና በፊቴ ግደሏቸው።’”
28 ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ጉዞውን በመቀጠል ወደ ኢየሩሳሌም አቀና። 29 ደብረ ዘይት በተባለው ተራራ+ ወደሚገኙት ወደ ቤተፋጌ እና ወደ ቢታንያ በተቃረበ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ላካቸው፤+ 30 እንዲህም አላቸው፦ “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደሩ ከገባችሁም በኋላ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ ውርንጭላ ታስሮ ታገኛላችሁ። ፈታችሁ ወደዚህ አምጡት። 31 ይሁን እንጂ ማንም ሰው ‘የምትፈቱት ለምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ ‘ጌታ ይፈልገዋል’ ብላችሁ ንገሩት።” 32 የተላኩትም ሄደው ልክ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት።+ 33 ውርንጭላውን እየፈቱ ሳሉ ግን ባለቤቶቹ “ውርንጭላውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። 34 እነሱም “ጌታ ይፈልገዋል” አሉ። 35 ከዚያም ውርንጭላውን ወደ ኢየሱስ ወሰዱት፤ መደረቢያቸውንም በውርንጭላው ላይ ጣል አድርገው ኢየሱስን በላዩ አስቀመጡት።+
36 እየተጓዘም ሳለ መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር።+ 37 ከደብረ ዘይት ተራራ ቁልቁል ወደሚወስደው መንገድ እንደተቃረበ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደቀ መዛሙርቱ ባዩአቸው ተአምራት መደሰትና አምላክን በታላቅ ድምፅ ማወደስ ጀመሩ፤ 38 እንዲህም ይሉ ነበር፦ “በይሖዋ* ስም ንጉሥ ሆኖ የሚመጣ የተባረከ ነው! በሰማይ ሰላም፣ በአርያም ላለውም ክብር ይሁን!”+ 39 በሕዝቡ መካከል የነበሩ አንዳንድ ፈሪሳውያን ግን “መምህር፣ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው እንጂ” አሉት።+ 40 እሱ ግን መልሶ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ እንኳ ድንጋዮች ይጮኻሉ” አላቸው።
41 ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረበ ጊዜም ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት፤+ 42 እንዲህም አለ፦ “አንቺ፣ አዎ አንቺ ራስሽ፣ ሰላም የሚያስገኙልሽን ነገሮች ምነው ዛሬ በተረዳሽ ኖሮ፤ አሁን ግን ከዓይኖችሽ ተሰውረዋል።+ 43 ምክንያቱም ጠላቶችሽ በሾለ እንጨት በዙሪያሽ ቅጥር ቀጥረው አንቺን የሚከቡበትና ከሁሉም አቅጣጫ የሚያስጨንቁበት ጊዜ ይመጣል።+ 44 አንቺንና በውስጥሽ የሚኖሩትን ልጆችሽን ፈጥፍጠው ከአፈር ይደባልቃሉ፤+ በአንቺ ውስጥም ሳያፈርሱ እንደተነባበረ የሚተዉት ድንጋይ አይኖርም፤+ ምክንያቱም በአንቺ ላይ ምርመራ የተካሄደበትን ጊዜ አልተገነዘብሽም።”
45 ከዚያም ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በዚያ የሚሸጡትን ያስወጣ ጀመር፤+ 46 እንዲህም አላቸው፦ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’+ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት።”+
47 እሱም በየዕለቱ በቤተ መቅደሱ ማስተማሩን ቀጠለ። ሆኖም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት እንዲሁም የሕዝቡ መሪዎች ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፤+ 48 ይሁንና ሕዝቡ ሁሉ እሱን ለመስማት ከአጠገቡ ስለማይለይ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገባቸው።+