የዳዊት መዝሙር።
א [አሌፍ]
37 በክፉዎች አትበሳጭ፤
ወይም በክፉ አድራጊዎች አትቅና።+
2 እንደ ሣር በፍጥነት ይደርቃሉ፤+
እንደለመለመ ተክልም ይጠወልጋሉ።
ב [ቤት]
3 በይሖዋ ታመን፤ መልካም የሆነውንም አድርግ፤+
በምድር ላይ ኑር፤ ለሰዎችም ታማኝ ሁን።+
4 በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤
እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።
ג [ጊሜል]
5 መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤+
በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል።+
6 ጽድቅህን እንደ ንጋት ብርሃን፣
የአንተንም ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል።
ד [ዳሌት]
7 በይሖዋ ፊት ዝም በል፤+
እሱንም በተስፋ ተጠባበቅ።
የጠነሰሰውን ሴራ
በተሳካ ሁኔታ እየፈጸመ ባለ ሰው አትበሳጭ።+
ה [ሄ]
8 ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው፤+
ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ።
9 ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤+
ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ።+
ו [ዋው]
10 ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤+
በቀድሞ ቦታቸው ትፈልጋቸዋለህ፤
እነሱ ግን በዚያ አይገኙም።+
11 የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤+
በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።+
ז [ዛየን]
12 ክፉ ሰው በጻድቁ ላይ ያሴራል፤+
በእሱ ላይ ጥርሱን ያፋጫል።
13 ይሖዋ ግን ይስቅበታል፤
የሚጠፋበት ቀን እንደሚደርስ ያውቃልና።+
ח [ኼት]
14 ክፉዎች የተጨቆነውንና ድሃውን ለመጣል፣
እንዲሁም ቀና የሆነውን መንገድ የሚከተሉትን ለማረድ
ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ ደጋናቸውንም ይወጥራሉ።
15 ሆኖም ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤+
ደጋኖቻቸው ይሰበራሉ።
ט [ቴት]
16 ብዙ ክፉ ሰዎች ካላቸው የተትረፈረፈ ሀብት ይልቅ
ጻድቅ ሰው ያለው ጥቂት ነገር ይሻላል።+
17 የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፤
ይሖዋ ግን ጻድቃንን ይደግፋል።
י [ዮድ]
18 ይሖዋ ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች የሕይወት ጎዳና ያውቃል፤
ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል።+
19 በአደጋ ወቅት ለኀፍረት አይዳረጉም፤
በረሃብ ዘመን የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራቸዋል።
כ [ካፍ]
20 ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤+
የይሖዋ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይከስማሉ፤
እንደ ጭስ ይበናሉ።
ל [ላሜድ]
21 ክፉ ሰው ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤
ጻድቅ ሰው ግን ለጋስ ነው፤ ደግሞም ይሰጣል።+
22 አምላክ የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤
እሱ የረገማቸው ግን ይጠፋሉ።+
מ [ሜም]
23 ይሖዋ በሰው መንገድ ደስ ሲሰኝ፣+
አካሄዱን ይመራለታል።+
24 ቢወድቅም እንኳ አይዘረርም፤+
ይሖዋ እጁን ይዞ ይደግፈዋልና።+
נ [ኑን]
25 በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤
ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣+
ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም።+
26 ሁልጊዜ ሳይሰስት ያበድራል፤+
ልጆቹም በረከት ያገኛሉ።
ס [ሳሜኽ]
27 ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፤+
ለዘላለምም ትኖራለህ።
28 ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፤
ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም።+
ע [አይን]
ምንጊዜም ጥበቃ ያገኛሉ፤+
የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል።+
29 ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤+
በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።+
פ [ፔ]
30 የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤
ምላሱም ስለ ፍትሕ ያወራል።+
31 የአምላኩ ሕግ በልቡ አለ፤+
በሚሄድበት ጊዜም እግሮቹ አይብረከረኩም።+
צ [ጻዴ]
32 ክፉ ሰው ጻድቁን ለመግደል
በዓይነ ቁራኛ ይከታተለዋል።
33 ይሖዋ ግን በክፉው እጅ አይጥለውም፤+
ወይም ለፍርድ በሚቀርብበት ጊዜ ጥፋት አያገኝበትም።+
ק [ኮፍ]
34 ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤ መንገዱንም ተከተል፤
እሱም ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ምድርንም ትወርሳለህ።
ክፉዎች ሲጠፉ+ ታያለህ።+
ר [ረሽ]
35 ጨካኝ የሆነውን ክፉ ሰው፣
በበቀለበት መሬት ላይ እንደለመለመ ዛፍ ተንሰራፍቶ አየሁት።+
36 ይሁንና ሕይወቱ በድንገት አለፈ፤ በቦታውም አልነበረም፤+
አጥብቄ ፈለግኩት፤ ላገኘው ግን አልቻልኩም።+
ש [ሺን]
37 ነቀፋ የሌለበትን ሰው ልብ በል፤
ቀና የሆነውንም ሰው+ በትኩረት ተመልከት፤
የዚህ ሰው የወደፊት ሕይወት ሰላማዊ ይሆናልና።+
38 ኃጢአተኞች ሁሉ ግን ይጠፋሉ፤
ክፉዎች ምንም ተስፋ አይኖራቸውም።+
ת [ታው]
39 ጻድቃን መዳን የሚያገኙት ከይሖዋ ነው፤+
በጭንቅ ጊዜ መሸሸጊያቸው እሱ ነው።+
40 ይሖዋ ይረዳቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም።+
እሱን መጠጊያ ስላደረጉ፣
ከክፉዎች ይታደጋቸዋል፤ ደግሞም ያድናቸዋል።+