ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ
6 ወንድሞች፣ አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት* መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።+ ይሁንና አንተም ፈተና ላይ እንዳትወድቅ+ ለራስህ ተጠንቀቅ።+ 2 አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ፤+ በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።+ 3 አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ+ ራሱን እያታለለ ነው። 4 ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤+ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር+ ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል። 5 እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማልና።+
6 ከዚህም በተጨማሪ ቃሉን በመማር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ይህን ትምህርት* ከሚያስተምረው ሰው ጋር መልካም ነገሮችን ሁሉ ይካፈል።+
7 አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል፤+ 8 ምክንያቱም ለሥጋው ብሎ የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳል፤ ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል።+ 9 ካልታከትን* ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።+ 10 እንግዲያው ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ* እስካገኘን ድረስ ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ።
11 በራሴ እጅ እንዴት ባሉ ትላልቅ ፊደላት እንደጻፍኩላችሁ ተመልከቱ።
12 በሥጋ ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ* እንድትገረዙ ሊያስገድዷችሁ ይሞክራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በክርስቶስ የመከራ እንጨት* ሳቢያ ስደት እንዳይደርስባቸው ነው። 13 እነሱ እንድትገረዙ የሚፈልጉት በእናንተ ሥጋ ለመኩራራት ብለው ነው እንጂ የተገረዙት ራሳቸውም እንኳ ሕጉን አይጠብቁም።+ 14 ይሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመከራ እንጨት* ካልሆነ በስተቀር በሌላ ነገር ፈጽሞ መኩራራት አልፈልግም፤+ በእሱ የተነሳ፣ በእኔ አመለካከት ዓለም ሞቷል፤* በዓለም አመለካከት ደግሞ እኔ ሞቻለሁ።* 15 መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤+ ከዚህ ይልቅ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።+ 16 ይህን የሥነ ምግባር ደንብ በመከተል በሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ይኸውም በአምላክ እስራኤል+ ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።
17 የኢየሱስ ባሪያ መሆኔን የሚያሳይ መለያ ምልክት በሰውነቴ ላይ ስላለ+ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ።
18 ወንድሞች፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን። አሜን።