በጽኑ አቋምህ ቀጥል
“እኔ ግን በጽኑ አቋሜ እሄዳለሁ።”—መዝሙር 26:11 Nw
1, 2. (ሀ) የሰዎች ጽኑ አቋም የአምላክን ሉዓላዊነት በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ አብይ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጎን መቆማቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
ሰይጣን በዔድን ገነት ባመጸ ጊዜ የአምላክን የመግዛት መብት በተመለከተ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ነው የሚል ክርክር አስነስቷል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) በዚህም የተነሳ የሰዎች ጽኑ አቋም የይሖዋን ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ አብይ ክፍል ሆነ።
2 ምንም እንኳ የይሖዋ ሉዓላዊነት ፍጥረታቱ ባላቸው ጽኑ አቋም ላይ የተመካ ባይሆንም ሰዎችም ሆኑ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ይህን ጥያቄ በሚመለከት ምን አቋም እንደሚወስዱ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ከአምላክ ሉዓላዊነት ጎን መቆማቸውን የሚያሳይ እርምጃ በመውሰድና በዚህ አቋማቸው በመጽናት ነው። አምላክ ደግሞ የሚፈርድላቸው ይህን አቋማቸውን በማየት ነው።
3. (ሀ) ኢዮብና ዳዊት፣ ይሖዋ ምን አይቶ እንዲፈርድላቸው ጠይቀዋል? (ለ) ጽኑ አቋምን በሚመለከት ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?
3 ኢዮብ “ይሖዋ በእውነተኛ ሚዛን ይመዝነኝና ጽኑ አቋሜን ይወቅ” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:6 NW) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊትም “አቤቱ፣ እኔ በየውሃቴ [“በጽኑ አቋሜ፣” NW] ሄጃለሁና ፍረድልኝ፤ በእግዚአብሔርም አምኛለሁና አልናወጥም” በማለት ይሖዋ ጽኑ አቋሙን እንዲያይለት ለምኗል። (መዝሙር 26:1 የ1954 ትርጉም) እኛም ጽኑ አቋማችንን እንደያዝን መቀጠላችን እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም! ሆኖም ጽኑ አቋም ሲባል ምን ማለት ነው? በጽኑ አቋም መሄድ ሲባልስ ምን ማለት ነው? በጽኑ አቋም መሄዳችንን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?
‘በጽኑ አቋሜ ሄጃለሁ’
4. “ጽኑ አቋም” ተብሎ የተተረጎመው ኢንተግሪቲ የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል ምን መልእክት ያስተላልፋል?
4 እዚህ ላይ “ጽኑ አቋም” ተብሎ የተተረጎመው ኢንተግሪቲ የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል ቀና፣ እንከንየለሽ፣ ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይሁን እንጂ ትክክል የሆነውን ማድረግ ማለት ብቻ አይደለም። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን ወይም በሙሉ ልብ ለአምላክ ያደሩ መሆንን ይጨምራል። ሰይጣን “እስቲ እጅህን ዘርግተህ ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል” ብሎ ለአምላክ በተናገረ ጊዜ ኢዮብ ለመጽናት የተነሳሳበትን የልብ ዝንባሌ ጥያቄ ላይ መጣሉ ነበር። (ኢዮብ 2:5) ጽኑ አቋም ተገቢውን እርምጃ ከመውሰድም ባሻገር ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ይጠይቃል።
5. ጽኑ አቋምን መጠበቅ ፍጽምናን እንደማይጠይቅ የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 ሆኖም አንድ ሰው ጽኑ አቋሙን ለመጠበቅ የግድ ፍጹም መሆን አያስፈልገውም። ንጉሥ ዳዊት ፍጽምና የሌለው ሰው ከመሆኑም በላይ በሕይወት ዘመኑ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከባድ ኃጢአቶችን ሠርቷል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት ‘በልቡ ጽኑ አቋም’ የሄደ ሰው እንደነበረ ይናገራል። (1 ነገሥት 9:4 NW) ለምን? ምክንያቱም ዳዊት ይሖዋን ይወድድ ስለነበረ ነው። ልቡን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ሰጥቶ ነበር። ምንም ሳያንገራግር ጥፋቱን ከማመኑም በላይ የተሰጠውን ተግሣጽ ተቀብሎ አካሄዱን አስተካክሏል። በእርግጥም ዳዊት በፍጹም ልቡ ለይሖዋ አምላክ ማደሩና እርሱን መውደዱ በጽኑ አቋም የሚሄድ ሰው መሆኑን ያሳያል።—ዘዳግም 6:5, 6
6, 7. በጽኑ አቋም መሄድ ምን ነገሮችን ይጨምራል?
6 ጽኑ አቋም ለሃይማኖት ያደሩ ከመሆን ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መላ አኗኗራችንን የሚመለከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊት በጽኑ አቋሙ ‘እንደሄደ’ ይናገራል። ዘ ኒው ኢንተርፕሪተርስ ባይብል የተባለው መጽሐፍ “‘መሄድ’ የሚለው ግስ ‘አኗኗርን’ ወይም ‘የአኗኗር ዘይቤን’ ያመለክታል” በማለት ይገልጻል። መዝሙራዊው ‘በመንገዳቸው ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች’ በተመለከተ “ምስክርነቱን የሚጠብቁ፣ በፍጹምም ልብ የሚሹት የተባረኩ ናቸው፤ ዐመፅን አያደርጉም፤ ነገር ግን በመንገዱ ይሄዳሉ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 119:1-3) ጽኑ አቋም ዘወትር የአምላክን ፈቃድ መፈጸምንና በመንገዱ ለመሄድ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል።
7 በጽኑ አቋም መሄድ በችግር ጊዜም እንኳ ቢሆን በታማኝነት ከአምላክ ጎን መቆምን ይጠይቃል። የተለያዩ መከራዎችና ችግሮች ሲደርሱብን መጽናታችን ወይም ይህ ክፉ ዓለም በሚያቀርባቸው ማባበያዎች አለመሸነፋችን በአቋማችን መጽናታችንን ያሳያል። ይህ ደግሞ ይሖዋ እርሱን ለሚሰድበው መልስ እንዲሰጥ ስለሚያስችለው ‘ልቡን ደስ ያሰኘዋል።’ (ምሳሌ 27:11) እንግዲያው እኛም ቁርጥ አቋማችን “እስክሞት ድረስ ከጽኑ አቋሜ ንቅንቅ አልልም” በማለት እንደተናገረው እንደ ኢዮብ መሆን ይኖርበታል። (ኢዮብ 27:5 NW) ሃያ ስድስተኛው መዝሙር በጽኑ አቋማችን ለመሄድ ምን ሊረዳን እንደሚችል ይገልጻል።
‘ኩላሊቴንና ልቤን ፈትን’
8. ዳዊት ይሖዋ ኩላሊቱንና ልቡን እንዲፈትንለት ካቀረበው ልመና ምን ትረዳለህ?
8 ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝ፤ ኩላሊቴንና ልቤን አጥራልኝ” ሲል ጸልዮአል። (መዝሙር 26:2 NW) ኩላሊት የሚገኘው በሰውነታችን ውስጠኛው ክፍል ነው። ኩላሊት በምሳሌያዊ አነጋገር የአንድን ሰው ውስጣዊ ሐሳብና ስሜት ያመለክታል። ምሳሌያዊው ልብም በአጠቃላይ የሰውን ውስጣዊ ሁለንተና ማለትም ዝንባሌውን፣ ስሜቱንና ችሎታውን ይወክላል። ዳዊት ይሖዋ እንዲፈትነው ሲለምን ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን በጥልቀትና በጥንቃቄ እንዲያይለት መጠየቁ ነበር።
9. ይሖዋ ምሳሌያዊ ኩላሊታችንንና ልባችንን የሚያጠራልን እንዴት ነው?
9 ዳዊት ይሖዋ ኩላሊቱንና ልቡን እንዲያጠራለት ለምኗል። ይሖዋ ውስጣችንን የሚያጠራልን እንዴት ነው? ዳዊት “የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለሁ፤ ደግሞም በሌሊት ኩላሊቶቼ ይገሥጹኛል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 16:7 የ1954 ትርጉም) ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ የሰጠው ምክር ወደ ውስጣዊ ማንነቱ ዘልቆ በመግባትና እዚያ በመቀመጥ ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን እንዳስተካከለለት የሚያሳይ ነው። እኛም በቃሉ፣ እርሱ በሚጠቀምባቸው ሰዎችና በድርጅቱ በኩል የምናገኘውን ምክር በአድናቆት የምናሰላስልበትና በውስጣችን እንዲቆይ የምንፈቅድ ከሆነ ውስጣዊ ማንነታችንን ያስተካክልልናል። በዚህ መንገድ እንዲያጠራን ዘወትር ወደ ይሖዋ መጸለያችን በጽኑ አቋም መሄዳችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።
‘ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየም’
10. ዳዊት በአምላክ እውነት እንዲመላለስ የረዳው ምንድን ነው?
10 ዳዊት ቀጥሎ “ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣ በእውነትህም ተመላለስሁ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 26:3) ዳዊት የይሖዋን ምሕረት በደንብ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ ከልብ በመነጨ አድናቆት አሰላስሎበታል። “ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤ ውለታውንም [“ሥራውንም፣” NW] ሁሉ አትርሺ” በማለት ዘምሯል። ከአምላክ ‘ሥራዎች’ መካከል አንዱን በማስታወስ “እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣ ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል። መንገዱን ለሙሴ፣ ሥራውንም ለእስራኤል ሕዝብ አሳወቀ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 103:2, 6, 7) ዳዊት ይህን የተናገረው በሙሴ ዘመን ግብጻውያን በእስራኤላውያን ላይ ስላደረሱት በደል አስቦ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ይሖዋ ሕዝቡን ስለሚያድንበት መንገድ ለሙሴ በነገረው ነገር ላይ በጥልቅ ማሰላሰሉ ልቡን የነካው ከመሆኑም በላይ በአምላክ እውነት ለመመላለስ የወሰደውን ቁርጥ አቋም አጠናክሮለታል።
11. በጽኑ አቋም መሄዳችንን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?
11 የአምላክን ቃል ዘወትር ማጥናታችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን እኛንም በጽኑ አቋማችን እንድንሄድ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት ከእርሷ ጋር የጾታ ብልግና እንዲፈጽም ስታግባባው ጥሏት እንደሸሸ ማስታወሳችን እኛም በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ በማንኛውም ሥፍራ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥመን በአፋጣኝ በመሸሽ ቆራጥ እርምጃ እንድንወስድ እንደሚያበረታታን የታወቀ ነው። (ዘፍጥረት 39:7-12) በዓለም ውስጥ ቁሳዊ ብልጽግና፣ ዝና ወይም ሥልጣን የምናገኝበት አጋጣሚ ቢከፈትልንና ይህ ሁኔታ ቢያጓጓንስ? በግብጽ የሚያገኘውን ክብር የተወው ሙሴ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። (ዕብራውያን 11:24-26) ኢዮብ ያሳየውን ጽናት ሁልጊዜ ማስታወሳችን የጤና እክልም ሆነ ሌሎች ችግሮች ቢደርሱብን እንኳ በታማኝነት ከይሖዋ ጎን ለመቆም ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እንደሚያጠናክርልን ምንም ጥርጥር የለውም። (ያዕቆብ 5:11) ስደት ቢደርስብንስ? እንዲህ ባለው ጊዜ ደግሞ አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ የነበረውን ዳንኤልን ማስታወሳችን ድፍረት እንድናገኝ ያደርገናል!—ዳንኤል 6:16-22
“ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም”
12, 13. ከምን ዓይነት ባልንጀርነት መራቅ ይኖርብናል?
12 ዳዊት በጽኑ አቋሙ እንዲሄድ የረዳውን ሌላ ነገር ሲገልጽ “ከማይረቡ ጋር አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርሁም። የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤ ከዐመፀኞችም ጋር አልቀመጥም” ብሏል። (መዝሙር 26:4, 5) በአጭር አነጋገር ዳዊት ከክፉዎች ጋር አልተቀመጠም። ክፉ ባልንጀርነትን ጠልቷል።
13 እኛስ? በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ፣ በሲኒማ፣ በኢንተርኔት ወይም በሌሎች መንገዶች ከሚቀርቡ ክፉ ሰዎች ጋር ለመቀመጥ እምቢ እንላለን? ከግብዞች ወይም ማንነታቸውን ከሚደብቁ ሰዎች እንርቃለን? በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ አንዳንዶች ስውር ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ወዳጅ መስለው ሊቀርቡን ይችላሉ። በአምላክ እውነት ከማይሄዱ ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንፈልጋለን? ከሃዲዎች ቅን ወይም ምንም ተንኮል የሌላቸው መስለው ለመቅረብ ቢሞክሩም ዋናው ዓላማቸው እኛን ከይሖዋ ማራቅ ነው። በጉባኤ ውስጥ ሁለት ዓይነት ሕይወት የሚመሩ ክርስቲያኖች ቢኖሩስ? እነርሱም ቢሆኑ እውነተኛ ማንነታቸውን ይደብቃሉ። በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ አገልጋይነት እያገለገለ ያለው ጄሰን በወጣትነቱ እንዲህ ያሉ ጓደኞች ነበሩት። እነርሱን በሚመለከት እንዲህ ይላል፦ “አንድ ቀን ከእነዚህ ጓደኞቼ መካከል አንዱ ‘አዲሱ ሥርዓት ሲመጣ መጥፋታችን ስለማይቀር አሁን ምንም አደረግን ምን የሚያመጣው ለውጥ የለም። አንዴ ከሞትን ደግሞ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ ምን እንዳመለጠን እንኳ አናውቅም’ አለኝ። እንዲህ ዓይነቱ አነጋገር አንድ እርምጃ መውሰድ እንዳለብኝ አስገነዘበኝ። እኔ ደግሞ አዲሱ ሥርዓት ሲመጣ መሞት አልፈልግም።” ጄሰን እንዲህ ካሉ ወጣቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አትሳቱ፤ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ከክፉ ባልንጀርነት መራቃችን በእጅጉ አስፈላጊ ነው!
‘ታምራትህን አወራለሁ’
14, 15. ‘የይሖዋን መሠዊያ መዞር’ የምንችለው እንዴት ነው?
14 ቀጥሎ ዳዊት “እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ” በማለት ተናግሯል። ይህን የሚያደርገው ለምንድን ነው? “የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣ ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው” ብሏል። (መዝሙር 26:6, 7) ዳዊት ይሖዋን ማምለክም ሆነ ለእርሱ ያደረ መሆኑን መናገር የሚችለው በሥነ ምግባር ንጹሕ ከሆነ ብቻ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር።
15 በመጀመሪያ በማደሪያው ድንኳን በኋላ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ይከናወኑ የነበሩት ነገሮች በሙሉ “በሰማይ ላለችው መቅደስ ምሳሌና ጥላ” ነበሩ። (ዕብራውያን 8:5፤ 9:23) መሠዊያው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ለመዋጀት ያቀረበውን መሥዋዕት ይሖዋ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን ያመለክታል። (ዕብራውያን 10:5-10) እጃችንን በየዋህነት መታጠብና ‘የይሖዋን መሠዊያ መዞር’ የምንችለው በኢየሱስ መሥዋዕት በማመን ነው።—ዮሐንስ 3:16-18
16. ስለ አምላክ ድንቅ ሥራዎች ለሌሎች መናገራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
16 በቤዛው አማካኝነት ልናገኛቸው ስለምንችላቸው ነገሮች ስናስብ ይሖዋና አንድያ ልጁ ለዋሉልን ውለታ አድናቆት አያድርብንም? እንግዲያው በዚህ የአድናቆት ስሜት በመገፋፋት የአምላክን ተዓምራት ወይም ድንቅ ሥራዎች ለሌሎች እንናገር። እነዚህ ድንቅ ሥራዎች አምላክ በዔድን ገነት ውስጥ ሰውን ከፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሁሉን ነገር እስከሚያድስበት ጊዜ ድረስ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ያመለክታሉ። (ዘፍጥረት 2:7፤ የሐዋርያት ሥራ 3:21) መንግሥቱን የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በመንፈሳዊ አደጋ እንዳይደርስብን ይጠብቀናል! (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይህን ሥራ በትጋት መሥራታችን ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲታየን ከማድረጉም በላይ በአምላክ ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከር እንዲሁም ለይሖዋና ለሰዎች ያለን ፍቅር እንዲጨምር ይረዳናል።
‘የምትኖርበትን ቤት ወደድሁ’
17, 18. ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ምን መሆን ይኖርበታል?
17 መሠዊያው የሚገኝበት የማደሪያው ድንኳን በእስራኤል የይሖዋ አምልኮ ማዕከል ነበር። ዳዊት በዚያ ሥፍራ ደስ እንደሚሰኝ ሲገልጽ “እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣ የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ” በማለት ጸልዮአል።—መዝሙር 26:8
18 ስለ ይሖዋ ትምህርት በሚሰጥባቸው ቦታዎች መሰብሰብ ያስደስተናል? ዘወትር መንፈሳዊ ትምህርት የሚሰጥበት እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች አዳራሽ በየአካባቢው የአምልኮ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል። ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ የአውራጃ፣ የወረዳና ልዩ ስብሰባ እናደርጋለን። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ‘ምስክሩን’ ወይም ማሳሰቢያውን እንማራለን። የይሖዋን ማሳሰቢያዎች ‘እጅግ የምንወድ’ ከሆነ በስብሰባዎች ላይ ዘወትር ለመገኘትና በጥሞና ለማዳመጥ ጉጉት ያድርብናል። (መዝሙር 119:167) ስለ ደኅንነታችን ከሚያስቡልንና በጽኑ አቋማችን መሄዳችንን እንድንቀጥል ከሚያበረታቱን የእምነት ወንድሞቻችን ጋር መሰብሰብ እንዴት የሚያስደስት ነው።—ዕብራውያን 10:24, 25
‘ሕይወቴን አታስወግዳት’
19. ዳዊት ከእነማን ጋር መደመር አልፈለገም?
19 ዳዊት ከአምላክ የእውነት ጎዳና መውጣት የሚያስከትለውን መዘዝ በሚገባ ያውቅ ስለነበር “ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋር፣ ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋር አታስወግዳት። በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤ ቀኝ እጃቸውም ጒቦን ያጋብሳል” በማለት ተማጽኗል። (መዝሙር 26:9, 10) ዳዊት ተንኮል ከሚሸርቡ ክፉ ሰዎች ወይም ከጉቦኞች ጋር መደመር አልፈለገም።
20, 21. የክፉዎችን መንገድ እንድንከተል ሊያደርገን የሚችለው ምንድን ነው?
20 ዛሬ ያለንበት ዓለም ሥነ ምግባር በጎደላቸው ድርጊቶች ተጥለቅልቋል። አብዛኛውን ጊዜ በቴሌቪዥን፣ በመጽሔቶችና በሲኒማ የሚቀርቡት ነገሮች ብልግናን ማለትም ዝሙትን፣ ርኩሰትንና መዳራትን የሚያበረታቱ ናቸው። (ገላትያ 5:19) አንዳንዶች የብልግና ሥዕሎችንና ፊልሞችን ማየትና ጽሑፎችን ማንበብ ሱስ ሆኖባቸዋል። ይህ ደግሞ የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም ይመራል። በተለይ ለዚህ የተጋለጡት ወጣቶች ናቸው። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀጣጥሮ መጫወት በተለመደባቸው አንዳንድ አገሮች የሚኖሩ ወጣቶች ተቀጣጥሮ መጫወት ማንኛውም ወጣት የግድ ማድረግ ያለበት ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ብዙ ወጣቶች ማግባት በማያስችላቸው ዕድሜ ላይ እያሉም ከተቃራኒ ጾታ ፍቅር ይይዛቸዋል። ቀስ በቀስ በውስጣቸው እያየለ የመጣውን የጾታ ፍላጎት ለማርካት ሲሉ ዝሙት እስከ መፈጸም የሚያደርስ ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት ይፈጽማሉ።
21 አዋቂዎችም ቢሆኑ በመጥፎ ተጽዕኖ አይሸነፉም ማለት አይደለም። ሐቀኝነት የጎደለው ንግድ ማካሄድም ሆነ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን የማድረግ ዝንባሌ ጽኑ አቋምን የማላላት አዝማሚያ እንዳለ የሚጠቁሙ ናቸው። ዓለም የሚጓዝበትን ጎዳና መከተል እኛን ከይሖዋ ከማራቅ በስተቀር የሚያስገኘው ጥቅም የለም። ‘ክፉውን የምንጠላና መልካሙን የምንወድ’ በመሆን በጽኑ አቋም መሄዳችንን እንቀጥል።—አሞጽ 5:15
“አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ”
22-24. (ሀ) ከመዝሙር 26 የመደምደሚያ ቃላት ምን የሚያበረታታ ሐሳብ አግኝተሃል? (ለ) የሚቀጥለው ርዕስ ስለ የትኛው ወጥመድ ያብራራል?
22 ዳዊት አምላክን የሚለምነውን ነገር ሲያጠቃልል “እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት [“በጽኑ አቋሜ፣” NW] እጓዛለሁ፤ አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ። እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤ በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ” ብሏል። (መዝሙር 26:11, 12) ዳዊት ጽኑ አቋሙን ጠብቆ ለመኖር ያደረገው ቁርጥ ውሳኔ ምሕረት ለማግኘት ካቀረበው ልመና ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ይህ እንዴት የሚያበረታታ ነው! ኃጢአተኞች ብንሆንም በጽኑ አቋም ለመሄድ እስከቆረጥን ድረስ ይሖዋ ይረዳናል።
23 በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ የአምላክን ሉዓላዊነት ከልብ እንደምንደግፍ እናሳይ። እያንዳንዳችን ይሖዋ ውስጣዊ ሐሳባችንንና ስሜታችንን እንዲመረምርልን እንዲሁም እንዲያጠራልን በጸሎት ልንጠይቀው እንችላለን። የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናት በእርሱ እውነት ላይ ዘወትር ማሰላሰል እንችላለን። በተቻለን መጠን ከመጥፎ ባልንጀሮች እንራቅ፤ እንዲሁም ይሖዋን ለማወደስ ከሚሰበሰቡት ጋር በመሆን እርሱን እንባርክ። ዓለም ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና እንዳያበላሽብን እየተጠነቀቅን የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት እንካፈል። በጽኑ አቋማችን ለመመላለስ የተቻለንን ያህል ጥረት ካደረግን ይሖዋ ሞገስ እንደሚያሳየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
24 በጽኑ አቋም መሄድ ሁሉንም የሕይወት ዘርፍ የሚዳስስ እንደመሆኑ መጠን ስለ አንድ አደገኛ ወጥመድ ማወቅ ይኖርብናል። ይህ ወጥመድ የአልኮል መጠጥን የሚመለከት ነው። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
ታስታውሳለህ?
• የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ፍርድ የሚሰጣቸው በሚያሳዩት ጽኑ አቋም መሠረት መሆኑ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
• ጽኑ አቋም ምንድን ነው? በጽኑ አቋም መሄድስ ምንን ይጨምራል?
• በጽኑ አቋማችን መሄዳችንን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?
• ጽኑ አቋማችንን ለመጠበቅ ስለ የትኞቹ አደገኛ ሁኔታዎች ማወቅና ከእነዚያ መራቅ ይኖርብናል?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ውስጣዊ ሐሳብህን እንዲመረምርልህ ዘወትር ትለምነዋለህ?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሕረት ዘወትር በፊትህ ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተለያየ ፈተና ቢደርስብንም ጽኑ አቋማችንን መጠበቃችን የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኘዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጽኑ አቋምህ መሄድህን እንድትቀጥል በሚረዱህ የይሖዋ ዝግጅቶች ትጠቀማለህ?