የማቴዎስ ወንጌል
28 ከሰንበት ቀን በኋላ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን* ጎህ ሲቀድ መግደላዊቷ ማርያምና ሌላዋ ማርያም መቃብሩን ለማየት መጡ።+
2 እነሆም የይሖዋ* መልአክ ከሰማይ ስለወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ተከሰተ፤ መልአኩም መጥቶ ድንጋዩን አንከባለለውና በላዩ ተቀመጠ።+ 3 መልኩ እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበር።+ 4 ጠባቂዎቹ እሱን ከመፍራታቸው የተነሳ ተንቀጠቀጡ፤ እንደ በድንም ሆኑ።
5 ሆኖም መልአኩ ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ።+ 6 አስቀድሞ እንደተናገረው ከሞት ስለተነሳ እዚህ የለም።+ ኑና አስከሬኑ አርፎበት የነበረውን ስፍራ እዩ። 7 ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል።+ እዚያም ታዩታላችሁ’ በሏቸው። እነሆ ነግሬአችኋለሁ።”+
8 ስለዚህ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ተውጠው ከመታሰቢያ መቃብሩ በፍጥነት በመውጣት ወሬውን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።+ 9 ወዲያውም ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡና እግሩን ይዘው ሰገዱለት።* 10 ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” አላቸው።
11 ሴቶቹ በመንገድ ላይ ሳሉ ከጠባቂዎቹ አንዳንዶቹ+ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው። 12 የካህናት አለቆቹም ከሽማግሌዎቹ ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ በርከት ያሉ የብር ሳንቲሞች* በመስጠት 13 እንዲህ አሏቸው፦ “‘ሌሊት ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው አስከሬኑን ሰረቁት’ በሉ።+ 14 አትጨነቁ፤ ወሬው ወደ አገረ ገዢው ጆሮ ከደረሰ ሁኔታውን እናስረዳዋለን።”* 15 እነሱም የብር ሳንቲሞቹን ተቀብለው እንደታዘዙት አደረጉ፤ ይህም ታሪክ እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁዳውያን ዘንድ በስፋት ይወራል።
16 ይሁንና የኢየሱስ 11 ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ለመገናኘት በገሊላ ወደሚገኘው፣ እሱ ወደነገራቸው ተራራ ሄዱ።+ 17 ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤* አንዳንዶች ግን ተጠራጠሩ። 18 ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ አላቸው፦ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።+ 19 ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤+ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣+ 20 ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።+ እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ* መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”+