ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ
1 በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ+ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና+ እሱ የገለጠው ራእይ* ይህ ነው። ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ+ በምልክቶች ገለጠለት፤ 2 ዮሐንስም አምላክ ስለሰጠው ቃልና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰጠው ምሥክርነት ይኸውም ስላያቸው ነገሮች ሁሉ መሥክሯል። 3 የዚህን ትንቢት ቃል ጮክ ብሎ የሚያነብ ደስተኛ ነው፤ እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፉትን ነገሮች የሚጠብቁት ደስተኞች ናቸው፤+ የተወሰነው ጊዜ ቀርቧልና።
4 ከዮሐንስ፣ በእስያ አውራጃ ለሚገኙ ለሰባቱ ጉባኤዎች፦+
“ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው”+ እንዲሁም በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት+ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን፤ 5 በተጨማሪም “ታማኝ ምሥክር፣”+ “ከሙታን በኩር”+ እና “የምድር ነገሥታት ገዢ”+ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ለወደደንና+ በገዛ ደሙ አማካኝነት ከኃጢአታችን ነፃ ላወጣን፣+ 6 ነገሥታት*+ እንዲሁም ለአምላኩና ለአባቱ ካህናት+ ላደረገን ለእሱ ክብርና ኃይል ለዘላለም ይሁን። አሜን።
7 እነሆ፣ ከደመናት ጋር ይመጣል፤+ ዓይኖች ሁሉ፣ የወጉትም ያዩታል፤ በእሱም የተነሳ የምድር ነገዶች ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ።+ አዎ፣ ይህ በእርግጥ ይሆናል። አሜን።
8 “እኔ አልፋና ኦሜጋ፣*+ ያለው፣ የነበረውና የሚመጣው፣ ሁሉን ቻይ ነኝ” ይላል ይሖዋ* አምላክ።+
9 የኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ+ ከእናንተ ጋር የመከራው፣+ የመንግሥቱና+ የጽናቱ+ ተካፋይ የሆንኩ እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ፣ ስለ አምላክ በመናገሬና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሬ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ነበርኩ። 10 በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ፤ ከኋላዬም እንደ መለከት ያለ ኃይለኛ ድምፅ ሰማሁ፤ 11 እንዲህም አለኝ፦ “የምታየውን በመጽሐፍ ጥቅልል ላይ ጽፈህ በኤፌሶን፣+ በሰምርኔስ፣+ በጴርጋሞን፣+ በትያጥሮን፣+ በሰርዴስ፣+ በፊላደልፊያና+ በሎዶቅያ+ ለሚገኙት ለሰባቱ ጉባኤዎች ላከው።”
12 እኔም እያናገረኝ ያለው ማን እንደሆነ ለማየት ዞር አልኩ፤ በዚህ ጊዜም ሰባት የወርቅ መቅረዞች ተመለከትኩ፤+ 13 በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስል አየሁ፤+ እሱም እስከ እግሩ የሚደርስ ልብስ የለበሰና ደረቱ ላይ የወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር። 14 በተጨማሪም ራሱና ፀጉሩ እንደ ነጭ ሱፍ፣ እንደ በረዶም ነጭ ነበር፤ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤+ 15 እግሮቹም እቶን ውስጥ እንደጋለ የጠራ መዳብ ነበሩ፤+ ድምፁም እንደ ውኃ ፏፏቴ ነበር። 16 በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ይዞ ነበር፤+ ከአፉም በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ረጅም ሰይፍ+ ወጣ፤ ፊቱም በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሐይ ነበር።+ 17 ባየሁት ጊዜ እንደሞተ ሰው ሆኜ እግሩ ሥር ወደቅኩ።
እሱም ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፦ “አትፍራ። እኔ የመጀመሪያውና+ የመጨረሻው ነኝ፤+ 18 ሕያው የሆነውም እኔ ነኝ፤+ ሞቼም ነበር፤+ አሁን ግን ለዘላለም እኖራለሁ፤+ የሞትና የመቃብር* ቁልፎችም አሉኝ።+ 19 ስለዚህ ያየሃቸውን ነገሮች፣ አሁን እየተከናወኑ ያሉትንና ከእነዚህ በኋላ የሚፈጸሙትን ነገሮች ጻፍ። 20 በቀኝ እጄ ላይ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብት እንዲሁም የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ቅዱስ ሚስጥር ይህ ነው፦ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱን ጉባኤዎች መላእክት* ያመለክታሉ፤ ሰባቱ መቅረዞች ደግሞ ሰባቱን ጉባኤዎች ያመለክታሉ።+