የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መስከረም 2020
ከመስከረም 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 23–24
“ብዙኃኑን አትከተሉ”
(ዘፀአት 23:1) “የሐሰት ወሬ አትንዛ። ተንኮል የሚሸርብ ምሥክር በመሆን ከክፉ ሰው ጋር አትተባበር።
የተሟላ መረጃ አለህ?
7 ለጓደኞችህና ለምታውቃቸው ሰዎች ኢ-ሜይሎችን እና የጽሑፍ መልእክቶችን መላክ ያስደስትሃል? አዲስ የወጣ ዜና ስታይ ወይም ለየት ያለ ተሞክሮ ስትሰማ ወሬውን ማንም ሳይቀድምህ ለመናገር ትጓጓለህ? ከሆነ እንዲህ ያለውን ወሬ ለሌሎች ከመላክህ በፊት ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምልከው መረጃ እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ? ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃስ አለኝ?’ እርግጠኛ ያልሆንክበትን መረጃ የምትልክ ከሆነ ሳይታወቅህ ለወንድሞችህ የተሳሳተ መረጃ ልታሰራጭ ትችላለህ። መረጃው ትክክል መሆኑን ከተጠራጠርክ አትላከው፤ እንዲያውም አጥፋው!
8 የሚደርሱንን ኢ-ሜይሎች እና የጽሑፍ መልእክቶች ለሌሎች በችኮላ መላክ ሌላም አደጋ አለው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መስበክ አይችሉም፤ በሌሎች አገሮች ደግሞ ሥራችን ሙሉ በሙሉ ታግዷል። እንደነዚህ ባሉት አገሮች ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች፣ ፍርሃት እንዲያድርብን ወይም ከወንድሞቻችን ጋር በጥርጣሬ ዓይን እንድንተያይ የሚያደርጉ ወሬዎችን ሆን ብለው ይነዛሉ። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኬ ጂ ቢ ተብለው የሚጠሩት የሚስጥር ፖሊሶች፣ ኃላፊነት ያላቸው በርካታ ወንድሞች የይሖዋን ሕዝብ እንደካዱ የሚገልጽ ወሬ አናፈሱ። ብዙዎች ይህን የሐሰት ወሬ በማመናቸው ራሳቸውን ከይሖዋ ድርጅት አገለሉ። ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ደስ የሚለው ነገር፣ ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ተመልሰዋል፤ አንዳንዶቹ ግን ሳይመለሱ ቀርተዋል። እነዚህ ሰዎች ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል። (1 ጢሞ. 1:19) እንዲህ ያለ አሳዛኝ ነገር እንዳይደርስ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? አሉታዊ የሆኑ ወይም ያልተረጋገጡ ዘገባዎችን ከማሰራጨት በመቆጠብ ነው። በቀላሉ ላለመሞኘት ወይም ላለመታለል እንጠንቀቅ። የሰማነውን ሁሉ ከማመናችን በፊት የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት እናድርግ።
(ዘፀአት 23:2) ብዙኃኑን ተከትለህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ከብዙኃኑ ጋር ለመስማማት ስትል የተዛባ ምሥክርነት በመስጠት ፍትሕን አታጣም።
it-1 11 አን. 3
አሮን
አሮን ስህተት በሠራባቸው በሦስቱም ጊዜያት የመጥፎ ድርጊቱ ዋነኛ ጠንሳሽ ተደርጎ አለመገለጹ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ከትክክለኛው ጎዳና የራቀው በሁኔታዎች ወይም በሌሎች ሰዎች ተጽዕኖ ተሸንፎ ሳይሆን አይቀርም። በተለይ መጀመሪያ ጊዜ ስህተት በሠራበት ወቅት “ብዙኃኑን ተከትለህ ክፉ ነገር አታድርግ” ከሚለው ትእዛዝ በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል ይችል ነበር። (ዘፀ 23:2) ያም ቢሆን ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከዚያ በኋላ የአሮን ስም የተነሳው በመልካም ነው፤ የአምላክ ልጅም ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከአሮን ዘር የመጣው ክህነት ሕጋዊ መሆኑን ገልጿል።—መዝ 115:10, 12፤ 118:3፤ 133:1, 2፤ 135:19፤ ማቴ 5:17-19፤ 8:4
(ዘፀአት 23:3) ችግረኛው ሙግት ሲኖረው አታድላለት።
it-1 343 አን. 5
መታወር
ከፍርድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ፍትሕን ማጣመም በመታወር ተመስሏል፤ ሕጉ ጉቦን፣ ስጦታን ወይም አድልዎን አስመልክቶ በርካታ ማስጠንቀቂያዎችን ይዟል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ነገሮች አንድ ዳኛ እንዲታወርና ፍትሐዊ የሆነ ፍርድ እንዳያስተላልፍ ሊያደርጉት ይችላሉ። “ጉቦ አጥርተው የሚያዩ ሰዎችን ዓይን ያሳውራል።” (ዘፀ 23:8) “ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራል።” (ዘዳ 16:19) አንድ ዳኛ ምንም ያህል ጻድቅና አስተዋይ ቢሆንም እንኳ ከባለጉዳዮቹ የሚሰጠው ስጦታ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል። የአምላክ ቃል አንድ ሰው ስጦታ ብቻ ሳይሆን የገዛ ስሜቱም ሊያሳውረው እንደሚችል ይገልጻል፤ እንዲህ ይላል፦ “ለድሃው አታዳላ ወይም ባለጸጋውን ከሌሎች አስበልጠህ አትመልከት።” (ዘሌ 19:15) በመሆኑም አንድ ዳኛ በስሜት ተገፋፍቶ ወይም የብዙኃኑን ተወዳጅነት ለማግኘት በማሰብ በሀብታሞች ላይ ሀብታም በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ሊፈርድባቸው አይገባም።—ዘፀ 23:2, 3
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 23:9) “የባዕድ አገር ሰውን አትጨቁን። እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ስለነበራችሁ የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር ታውቃላችሁ።
“ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ”
4 ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ለባዕድ አገር ሰው አክብሮት እንዲያሳዩ ከማዘዝ ይልቅ ራሳቸውን በእነሱ ቦታ አድርገው እንዲያስቡ አበረታቷቸዋል። (ዘፀአት 23:9ን አንብብ።) እስራኤላውያን “የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር” ያውቃሉ። ዕብራውያኑ፣ ባሪያ ከመሆናቸው በፊትም እንኳ በዘራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት ግብፃውያኑ ያገልሏቸው ነበር። (ዘፍ. 43:32፤ 46:34፤ ዘፀ. 1:11-14) እስራኤላውያን በግብፅ የባዕድ አገር ሰው እያሉ ሕይወት መራራ ሆኖባቸው ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ የባዕድ አገር ሰዎችን ‘እንደ አገራቸው ተወላጅ’ አድርገው እንዲመለከቱ ነግሯቸዋል።—ዘሌ. 19:33, 34
(ዘፀአት 23:20, 21) “በመንገድ ላይ እንዲጠብቅህና ወዳዘጋጀሁት ስፍራ እንዲያመጣህ በፊትህ መልአክ እልካለሁ። 21 የሚልህን ስማ፤ ቃሉንም ታዘዝ። መተላለፋችሁን ይቅር ስለማይል በእሱ ላይ አታምፁ፤ ምክንያቱም እሱ ስሜን ተሸክሟል።
it-2 393
ሚካኤል
1. ከገብርኤል ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሙ የተጠቀሰው ብቸኛው ቅዱስ መልአክ እንዲሁም “የመላእክት አለቃ” ተብሎ የተጠራው ብቸኛው መልአክ ሚካኤል ነው። (ይሁዳ 9) ስሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዳንኤል ምዕራፍ አሥር ላይ ሲሆን እዚህ ጥቅስ ላይ “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ” ተብሎ ተጠርቷል፤ “የፋርስ ንጉሣዊ ግዛት አለቃ” አንድን አነስተኛ ሥልጣን ያለው መልአክ በተቃወመበት ጊዜ ሚካኤል መጥቶ ረድቶታል። ሚካኤል “[የዳንኤል ሕዝብ] አለቃ” እንዲሁም “[ለዳንኤል ሕዝብ] የሚቆመው ታላቁ አለቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዳን 10:13, 20, 21፤ 12:1) ይህም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ውስጥ የመራቸው መልአክ ሚካኤል እንደሆነ ይጠቁማል። (ዘፀ 23:20, 21, 23፤ 32:34፤ 33:2) “የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር” እንደተከራከረ መገለጹ ይህን ሐሳብ ይደግፋል።—ይሁዳ 9
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 23:1-19) “የሐሰት ወሬ አትንዛ። ተንኮል የሚሸርብ ምሥክር በመሆን ከክፉ ሰው ጋር አትተባበር። 2 ብዙኃኑን ተከትለህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ከብዙኃኑ ጋር ለመስማማት ስትል የተዛባ ምሥክርነት በመስጠት ፍትሕን አታጣም። 3 ችግረኛው ሙግት ሲኖረው አታድላለት። 4 “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እሱ ልትመልሰው ይገባል። 5 የሚጠላህ ሰው አህያ ጭነቱ ከብዶት ወድቆ ብታይ ዝም ብለህ አትለፈው። ከዚህ ይልቅ ጭነቱን ከእንስሳው ላይ ለማውረድ እርዳው። 6 “በመካከልህ ያለ ድሃ ሙግት ሲኖረው ፍርድ አታጣምበት። 7 “ከሐሰት ክስ ራቅ፤ እኔ ክፉውን ሰው ጻድቅ እንደሆነ አድርጌ ስለማልቆጥር ንጹሑንና ጻድቁን ሰው አትግደል። 8 “ጉቦ አትቀበል፤ ምክንያቱም ጉቦ አጥርተው የሚያዩ ሰዎችን ዓይን ያሳውራል፤ እንዲሁም የጻድቅ ሰዎችን ቃል ሊያዛባ ይችላል። 9 “የባዕድ አገር ሰውን አትጨቁን። እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ስለነበራችሁ የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር ታውቃላችሁ። 10 “ለስድስት ዓመት መሬትህ ላይ ዘር ዝራ፤ አዝመራውንም ሰብስብ። 11 በሰባተኛው ዓመት ግን መሬትህን አትረሰው፤ እንዲሁ ተወው። በሕዝብህ መካከል ያሉ ድሆች ከዚያ ይበላሉ፤ ከእነሱ የተረፈውንም የዱር አራዊት ይበሉታል። በወይን እርሻህም ሆነ በወይራ ዛፍ እርሻህ እንደዚሁ ታደርጋለህ። 12 “ለስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ሆኖም በሬህና አህያህ እንዲያርፉ እንዲሁም የሴት ባሪያህ ልጅና የባዕድ አገሩ ሰው ጉልበታቸውን እንዲያድሱ በሰባተኛው ቀን ሥራ አትሥራ። 13 “የነገርኳችሁን ነገሮች በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽሙ፤ እንዲሁም የሌሎች አማልክትን ስም አታንሱ፤ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ከአፍህ ሲወጣ ሊሰማ አይገባም። 14 “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓል ታከብርልኛለህ። 15 የቂጣን በዓል ታከብራለህ። በአቢብ ወር በተወሰነው ጊዜ፣ ባዘዝኩህ መሠረት ለሰባት ቀናት ቂጣ ትበላለህ፤ ምክንያቱም ከግብፅ የወጣኸው በዚህ ጊዜ ነው። ማንም ባዶ እጁን ፊቴ አይቅረብ። 16 በተጨማሪም በእርሻህ ላይ በዘራኸው መጀመሪያ በሚደርሰው የድካምህ ፍሬ የመከርን በዓል አክብር፤ ከእርሻህ ላይ የድካምህን ፍሬ በምትሰበስብበት በዓመቱ ማብቂያ ላይ የአዝመራ መክተቻን በዓል አክብር። 17 የአንተ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ በእውነተኛው ጌታ በይሖዋ ፊት ይቅረቡ። 18 “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ከገባበት ከማንኛውም ነገር ጋር አብረህ አታቅርብ። በበዓሎቼም ላይ የሚቀርቡት የስብ መሥዋዕቶች እስከ ጠዋት ድረስ ማደር የለባቸውም። 19 “በምድርህ ላይ የሚገኘውን መጀመሪያ የደረሰውን ምርጥ ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቤት አምጣ። “የፍየል ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል።
ከመስከረም 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 25–26
“የማደሪያ ድንኳኑ ዋነኛ ዕቃ”
(ዘፀአት 25:9) የማደሪያ ድንኳኑንም ሆነ በውስጡ የሚቀመጡትን ቁሳቁሶች ሁሉ እኔ በማሳይህ ንድፍ መሠረት ትሠሯቸዋላችሁ።
it-1 165
የቃል ኪዳኑ ታቦት
ንድፍና አሠራር። ሙሴ የማደሪያ ድንኳኑን እንዲሠራ ይሖዋ ባዘዘው ወቅት በመጀመሪያ የሰጠው የታቦቱን ንድፍና አሠራር ነበር፤ ምክንያቱም በማደሪያ ድንኳኑም ሆነ በመላው የእስራኤል ሰፈር ውስጥ የነበረው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዕቃ ታቦቱ ነበር። ታቦቱ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል እንዲሁም ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል (111 × 67 × 67 ሴንቲ ሜትር) ነበር። የተሠራው ከግራር እንጨት ሲሆን ውስጡም ሆነ ውጭው በንጹሕ ወርቅ ተለብጦ ነበር። “በዙሪያው” ባለጌጥ የሆነ “የወርቅ ክፈፍ” ተሠርቶለታል። የታቦቱ መክደኛ ደግሞ በእንጨት ተሠርቶ በወርቅ የተለበጠ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሠራ ነበር፤ ርዝመቱና ወርዱም ከታቦቱ ጋር እኩል ነበር። በመክደኛው ላይ ከተጠፈጠፈ ወርቅ የተሠሩ ሁለት ኪሩቦች ነበሩ፤ አንዱ ኪሩብ በአንዱ ጫፍ፣ ሌላኛው ኪሩብ ደግሞ በሌላኛው ጫፍ ትይዩ ሆነው የተሠሩ ሲሆን ፊታቸው ወደ መክደኛው ያጎነበሰ ነው፤ ክንፎቻቸውን ደግሞ ወደ ላይ በመዘርጋት ታቦቱን በክንፎቻቸው ይከልሉታል። (ዘፀ 25:10, 11, 17-22፤ 37:6-9) መክደኛው “የስርየት ስፍራ” ወይም “የስርየት መክደኛ” ተብሎም ተጠርቷል።—ዘፀ 25:17፤ ዕብ 9:5 ግርጌ፤ የስርየት መክደኛ የሚለውን ተመልከት።
(ዘፀአት 25:21) መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ትገጥመዋለህ፤ የምሰጥህንም ምሥክር በታቦቱ ውስጥ ታስቀምጠዋለህ።
it-1 166 አን. 2
የቃል ኪዳኑ ታቦት
የቃል ኪዳኑ ታቦት ማስታወሻ ሆነው የሚያገለግሉ ቅዱስ ነገሮች የሚቀመጡበት ቅዱስ ሣጥን ነበር፤ በውስጡ የሚቀመጡት ዋነኞቹ ነገሮች የምሥክሩ ሁለት ጽላቶች ወይም አሥርቱ ትእዛዛት ነበሩ። (ዘፀ 25:16) ‘መና የያዘው የወርቅ ማሰሮና ያቆጠቆጠችው የአሮን በትርም’ ታቦቱ ውስጥ ተቀምጠው ነበር፤ ሆኖም የሰለሞን ቤተ መቅደስ ከመገንባቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ከታቦቱ እንዲወጡ ተደርጓል። (ዕብ 9:4፤ ዘፀ 16:32-34፤ ዘኁ 17:10፤ 1ነገ 8:9፤ 2ዜና 5:10) ሙሴ ልክ ከመሞቱ በፊት ለሌዋውያኑ ካህናት ‘የሕጉን መጽሐፍ’ የሰጣቸው ሲሆን መጽሐፉን በታቦቱ ውስጥ እንዲያስቀምጡ ከማዘዝ ይልቅ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በአምላካችሁ በይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በዚያ በእናንተ ላይ ምሥክር ሆኖ ያገለግላል።”—ዘዳ 31:24-26
(ዘፀአት 25:22) እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ። በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ እስራኤላውያንን በተመለከተ የማዝህንም ሁሉ አሳውቅሃለሁ።
it-1 166 አን. 3
የቃል ኪዳኑ ታቦት
ከአምላክ መገኘት ጋር ተያያዥነት ነበረው። የቃል ኪዳኑ ታቦት በኖረበት ዘመን ሁሉ ከአምላክ መገኘት ጋር ተያያዥነት ነበረው። ይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል ገብቶ ነበር፦“እኔም በዚያ እገለጥልሃለሁ፤ ከመክደኛውም በላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ። በምሥክሩ ታቦት ላይ በሚገኙት በሁለቱ ኪሩቦች መካከል ሆኜ . . . የማዝህንም ሁሉ አሳውቅሃለሁ።” “እኔ ከመክደኛው በላይ በደመና ውስጥ [እገለጣለሁ]።” (ዘፀ 25:22፤ ዘሌ 16:2) ሳሙኤል ይሖዋ “ከኪሩቤል በላይ” እንደተቀመጠ ጽፏል (1ሳሙ 4:4)፤ በመሆኑም ኪሩቦቹ የይሖዋ ‘ሠረገላ ምስል’ ነበሩ። (1ዜና 28:18) በተጨማሪም “ሙሴ ከአምላክ ጋር ለመነጋገር ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ከምሥክሩ ታቦት መክደኛ በላይ ድምፅ ሲያነጋግረው ይሰማ ነበር፤ እሱም ከሁለቱ ኪሩቦች መካከል ያነጋግረው ነበር።” (ዘኁ 7:89) ከጊዜ በኋላም ኢያሱና ሊቀ ካህናቱ ፊንሃስ በታቦቱ ፊት ሆነው ለይሖዋ ጥያቄ አቅርበዋል። (ኢያሱ 7:6-10፤ መሳ 20:27, 28) ሆኖም ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ገብቶ ታቦቱን የሚያየው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ እሱም ይህን የሚያደርገው ይሖዋን ለማነጋገር ሳይሆን በዓመት አንድ ጊዜ የስርየትን ቀን ሥርዓት ለመፈጸም ነው።—ዘሌ 16:2, 3, 13, 15, 17፤ ዕብ 9:7
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 25:20) ኪሩቦቹ ሁለቱን ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይከልሉታል፤ እነሱም ትይዩ ይሆናሉ። የኪሩቦቹ ፊት ወደ መክደኛው ያጎነበሰ ይሆናል።
it-1 432 አን. 1
ኪሩብ
በምድረ በዳ በተሠራው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ የኪሩብ ምስል ያለባቸው ዕቃዎች ነበሩ። በታቦቱ መክደኛ ሁለት ጫፎች ላይ ከተጠፈጠፈ ወርቅ የተሠሩ ሁለት ኪሩቦች ነበሩ። ኪሩቦቹ ትይዩ ሆነው የተሠሩ ሲሆን አምልኮ የሚያቀርቡ በሚመስል መንገድ ፊታቸው ወደ ታቦቱ መክደኛ ያጎነበሰ ነበር። ሁለቱም ኪሩቦች ሁለት ክንፍ ነበራቸው፤ ጥበቃ የሚያደርጉ በሚመስል መንገድ ክንፎቻቸውን ወደ ላይ በመዘርጋት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይከልሉታል። (ዘፀ 25:10-21፤ 37:7-9) በተጨማሪም ቅድስቱን ከቅድስተ ቅዱሳኑ የሚለየው መጋረጃና የማደሪያ ድንኳኑ ውስጠኛ ጨርቆች ኪሩቦች ተጠልፈውባቸው ነበር።—ዘፀ 26:1, 31፤ 36:8, 35
(ዘፀአት 25:30) ገጸ ኅብስቱን በጠረጴዛው ላይ ሁልጊዜ በፊቴ ታስቀምጣለህ።
it-2 936
ገጸ ኅብስት
በማደሪያ ድንኳኑ ወይም በቤተ መቅደሱ ቅድስት ውስጥ ባለው ጠረጴዛ ላይ አሥራ ሁለት ዳቦዎች ይቀመጡ የነበረ ሲሆን በሰንበት ቀናት ዳቦዎቹ በትኩስ ዳቦ ይቀየሩ ነበር። (ዘፀ 35:13፤ 39:36፤ 1ነገ 7:48፤ 2ዜና 13:11፤ ነህ 10:32, 33) ገጸ ኅብስት ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ አገላለጽ በቀጥታ ሲተረጎም “የፊት ዳቦ” ማለት ነው። ‘ፊት’ የሚለው ቃል መገኘትን ሊያመለክት ይችላል (2ነገ 13:23)፤ በመሆኑም ገጸ ኅብስቱ ለይሖዋ ሁልጊዜ እንደሚቀርብ መባ ሆኖ በይሖዋ ፊት ይቀመጣል። (ዘፀ 25:30) ገጸ ኅብስቱ ‘የሚነባበረው ዳቦ’ (2ዜና 2:4) እና “በአምላክ ፊት የቀረበ ኅብስት” (ማር 2:26፤ ዕብ 9:2) ተብሎም ተጠርቷል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 25:23-40) “በተጨማሪም ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ትሠራለህ። 24 በንጹሕ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ትሠራለታለህ። 25 ዙሪያውንም አንድ ጋት ስፋት ያለው ጠርዝ ታበጅለታለህ፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ። 26 አራት የወርቅ ቀለበቶች ትሠራለታለህ፤ ከዚያም ቀለበቶቹን አራቱ እግሮቹ በሚገኙባቸው አራት ማዕዘኖች ላይ ታደርጋቸዋለህ። 27 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ በጠርዙ አጠገብ ይሆናሉ። 28 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ትለብጣቸዋለህ፤ ጠረጴዛውንም በእነሱ አማካኝነት ትሸከማለህ። 29 “ለመጠጥ መባ ማፍሰሻ የሚያገለግሉትን ሳህኖቹን፣ ጽዋዎቹን፣ ማንቆርቆሪያዎቹንና ጎድጓዳ ሳህኖቹን ትሠራለህ። ከንጹሕ ወርቅ ትሠራቸዋለህ። 30 ገጸ ኅብስቱን በጠረጴዛው ላይ ሁልጊዜ በፊቴ ታስቀምጣለህ። 31 “ከንጹሕ ወርቅ መቅረዝ ትሠራለህ። መቅረዙም ወጥ ከሆነ ወርቅ ተጠፍጥፎ የተሠራ ይሁን። የመቅረዙ መቆሚያ፣ ግንድ፣ ቅርንጫፎች፣ አበባ አቃፊዎች፣ እንቡጦችና የፈኩት አበቦች ወጥ ሆነው የተሠሩ ይሆናሉ። 32 በመቅረዙ ጎንና ጎን ስድስት ቅርንጫፎች ይኖራሉ፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ከአንዱ ጎን፣ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች ደግሞ ከሌላው ጎን የወጡ ይሆናሉ። 33 በአንዱ በኩል ባሉት ቅርንጫፎች በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ፤ በሌላኛው በኩል ባሉት ቅርንጫፎችም በእያንዳንዳቸው ላይ የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ ሦስት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። ስድስቱ ቅርንጫፎች ከመቅረዙ ግንድ የሚወጡት በዚህ መንገድ ይሆናል። 34 በግንዱ ላይም የአልሞንድ አበባ የሚመስሉ አራት የአበባ አቃፊዎችን ከእንቡጦቹና ከፈኩት አበቦች ጋር እያፈራረቅክ ትሠራለህ። 35 ከግንዱ በሚወጡት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥር አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ በቀጣዮቹ ሁለት ቅርንጫፎች ሥርም እንዲሁ አንድ እንቡጥ ይኖራል፤ ከግንዱ የሚወጡት ስድስቱም ቅርንጫፎች በዚሁ መንገድ ይሠራሉ። 36 እንቡጦቹና ቅርንጫፎቻቸው እንዲሁም የመቅረዙ ሁለመና ንጹሕ ከሆነ አንድ ወጥ ወርቅ ተጠፍጥፈው የተሠሩ ይሆናሉ። 37 ሰባት መብራቶች ትሠራለታለህ፤ መብራቶቹ በሚለኮሱበት ጊዜ ከፊት ለፊቱ ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ። 38 መቆንጠጫዎቹና መኮስተሪያዎቹ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ይሁኑ። 39 ቁሳቁሶቹ ሁሉ ከአንድ ታላንት ንጹሕ ወርቅ ይሠሩ። 40 በተራራው ላይ ተገልጦልህ ባየኸው ንድፍ መሠረት ተጠንቅቀህ ሥራቸው።
ከመስከረም 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 27–28
“ከካህናቱ ልብስ ምን ትምህርት እናገኛለን?”
(ዘፀአት 28:30) ኡሪሙንና ቱሚሙን በፍርድ የደረት ኪሱ ውስጥ ታስቀምጣቸዋለህ፤ አሮን በይሖዋ ፊት ለመቅረብ በሚገባበት ጊዜ በልቡ ላይ መሆን አለባቸው፤ አሮን በይሖዋ ፊት በሚቀርብበት ጊዜ ለእስራኤላውያን ፍርድ መስጫውን ዘወትር በልቡ ላይ ይሸከም።
it-2 1143
ኡሪምና ቱሚም
በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ኡሚምና ቱሚም ዕጣ መጣያ እንደሆኑ ያምናሉ። የጄምስ ሞፋት ትርጉም በዘፀአት 28:30 ላይ “ቅዱስ ዕጣ መጣያዎች” በማለት ጠርቷቸዋል። አንዳንዶች እነዚህ ዕጣ መጣያዎች ሦስት እንደሆኑና አንዱ ላይ “አዎ፣” አንዱ ላይ ደግሞ “አይደለም” ተብሎ እንደተጻፈ ሦስተኛው ግን ምንም እንዳልተጻፈበት ይናገራሉ። ጥያቄ ከቀረበ በኋላ ዕጣው ሲወጣ መልሱ ይገኛል፤ ምንም ያልተጻፈበት ዕጣ መጣያ ከወጣ ግን መልሱ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል። ሌሎች ደግሞ ኡሪምና ቱሚም በአንድ በኩል ነጭ፣ በአንድ በኩል ደግሞ ጥቁር የሆኑ ሁለት ጠፍጣፋ ድንጋዮች እንደሆኑ ያስባሉ። ድንጋዮቹ ሲጣሉ ሁለት ነጭ ከወጣ መልሱ “አዎ” እንደሆነ፣ ሁለት ጥቁር ከወጣ መልሱ “አይደለም” እንደሆነ፣ ነጭና ጥቁር ከወጣ ደግሞ መልሱ የለም ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ። በአንድ ወቅት ሳኦል ፍልስጤማውያን ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት መቀጠል ይኖርበት እንደሆነ ለማወቅ በካህኑ አማካኝነት ሲጠይቅ መልስ አላገኘም ነበር። ከሰዎቹ መካከል አንዳንዶቹ ኃጢአት እንደሠሩ ስለተሰማው “የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ በቱሚም አማካኝነት መልስ ስጠን!” በማለት ልመና አቅርቧል። ሳኦልና ዮናታን ከሰዎቹ መካከል ተለዩ፣ ከዚያም ከሁለቱ ማን እንደሆነ ለመለየት ዕጣ ተጣለ። በዚህ ዘገባ ላይ “በቱሚም አማካኝነት መልስ ስጠን!” በማለት ሳኦል ያቀረበው ልመና በሁለቱ ላይ ከተጣለው ዕጣ ጋር ግንኙነት ያለው ቢመስልም ሁለቱ የተለያዩ ነገሮች ሳይሆኑ አይቀሩም።—1ሳሙ 14:36-42
(ዘፀአት 28:36) “ከንጹሕ ወርቅም የሚያብረቀርቅ ጠፍጣፋ ወርቅ ሠርተህ ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ‘ቅድስና የይሖዋ ነው’ ብለህ ትቀርጽበታለህ።
it-1 849 አን. 3
ግንባር
የእስራኤል ሊቀ ካህናት። የእስራኤል ሊቀ ካህናት የሚያስረው ጥምጣም ከፊት ለፊቱ ማለትም ከግንባሩ በላይ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ እንደ ማኅተም የተቀረጸበት ጠፍጣፋ ወርቅ ነበረው፤ ይህ ወርቅ ‘ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳይ ቅዱስ ምልክት’ ተብሎም ተጠርቷል። (ዘፀ 28:36-38፤ 39:30) ሊቀ ካህናቱ እስራኤላውያን ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ ዋነኛ ወኪል ስለሆነ ኃላፊነቱን በሚወጣበት ጊዜ ቅዱስ መሆን ይጠበቅበታል፤ በተጨማሪም ይህ ጽሑፍ ሁሉም እስራኤላውያን ለይሖዋ ከሚያቀርቡት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ምንጊዜም ቅዱስ መሆን እንዳለባቸው ያስታውሳቸዋል። ከዚህም ሌላ የአምላክን ቅድስና የሚያስከብረውን የክህነት አገልግሎት እንዲያከናውን በይሖዋ ለተመረጠው ለታላቁ ሊቀ ካህናት ለኢየሱስ ክርስቶስ ተስማሚ ተምሳሌት ነው።—ዕብ 7:26
(ዘፀአት 28:42, 43) እርቃናቸውን የሚሸፍኑበት የበፍታ ቁምጣም ትሠራላቸዋለህ። ቁምጣውም ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ ይሆናል። 43 በደል እንዳይሆንባቸውና እንዳይሞቱ አሮንና ወንዶች ልጆቹ ወደ መገናኛ ድንኳኑ በሚገቡበት ጊዜ ወይም ቅዱስ በሆነው ስፍራ ለማገልገል ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ እነዚህን ልብሶች መልበስ አለባቸው። ይህ ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለሚመጡት ዘሮቹ ዘላለማዊ ደንብ ነው።
ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ይሖዋን ማክበር
17 ለይሖዋ አምልኮ ስናቀርብ ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ መመላለሳችን ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መክብብ 5:1 “ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትሄድ እግርህን ጠብቅ” ይላል። ሙሴም ሆነ ኢያሱ በተቀደሰ ቦታ ላይ በቆሙ ጊዜ ጫማቸውን እንዲያወልቁ ታዘው ነበር። (ዘፀ. 3:5፤ ኢያሱ 5:15) ይህንን ማድረጋቸው አክብሮት እንዳላቸው የሚያሳይ ነበር። እስራኤላውያን ካህናት “ሰውነትን የሚሸፍን” የበፍታ ሱሪ መልበስ ነበረባቸው። (ዘፀ. 28:42, 43) እንዲህ ማድረጋቸው በመሠዊያው አጠገብ በሚያገለግሉበት ጊዜ ሰውነታቸው እንዳይጋለጥ ለማድረግ ይረዳል። የካህኑ ቤተሰብ አባላት በሙሉ ክብር ባለው መንገድ በመመላለስ ረገድ አምላክ ያወጣውን መሥፈርት ማሟላት ነበረባቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 28:15-21) “የፍርዱን የደረት ኪስ የጥልፍ ባለሙያ እንዲሠራው ታደርጋለህ። የደረት ኪሱ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ መሠራት ይኖርበታል። 16 ለሁለት በሚታጠፍበትም ጊዜ ቁመቱ አንድ ስንዝር፣ ወርዱ ደግሞ አንድ ስንዝር የሆነ ካሬ ይሁን። 17 የከበሩ ድንጋዮችን በአራት ረድፍ በማቀፊያ ውስጥ ታደርግበታለህ። በመጀመሪያው ረድፍ ሩቢ፣ ቶጳዝዮንና መረግድ ይደርደር። 18 በሁለተኛው ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና ኢያስጲድ ይደርደር። 19 በሦስተኛው ረድፍ ለሼም፣ አካትምና አሜቴስጢኖስ ይደርደር። 20 በአራተኛውም ረድፍ ክርስቲሎቤ፣ ኦኒክስና ጄድ ይደርደር። በወርቅ አቃፊዎችም ውስጥ ይቀመጡ። 21 ድንጋዮቹም የእስራኤልን ወንዶች ልጆች ስሞች ማለትም 12ቱን በየስማቸው የሚወክሉ ይሆናሉ። ለ12ቱም ነገዶች ልክ ማኅተም በሚቀረጽበት መንገድ ለእያንዳንዳቸው በየስማቸው ይቀረጽላቸው።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
በእስራኤል ሊቀ ካህን የደረት ኪስ ላይ የነበሩት የከበሩ ድንጋዮች የተገኙት ከየት ነው?
እስራኤላውያን ከግብፅ ወጥተው በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት አምላክ በሊቀ ካህኑ ልብስ ላይ የደረት ኪስ እንዲሠሩ አዝዟቸው ነበር። (ዘፀአት 28:15-21) በደረት ኪሱ ላይ የነበሩት የከበሩ ድንጋዮች ሰርዲዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፣ በሉር፣ ሰንፔር፣ አልማዝ፣ ያክንት፣ ኬልቄዶን፣ አሜቴስጢኖስ፣ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያስጴድ ናቸው። ይሁንና እስራኤላውያን እነዚህን የከበሩ ድንጋዮች ማግኘት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበራቸው?
በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች የከበሩ ድንጋዮችን እንደ ውድ ሀብት ይቆጥሯቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለመገበያያነት ይጠቀሙባቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቶቹ ግብፃውያን በጣም ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች ማለትም በዛሬው ጊዜ ኢራንና አፍጋኒስታን ተብለው ወደሚጠሩት ቦታዎች ምናልባትም እስከ ሕንድ ድረስ በመሄድ የከበሩ ድንጋዮችን ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። እንዲሁም በግብፅ ካሉ የማዕድን ማውጫ ቦታዎች የተለያየ ዓይነት ያላቸው በርካታ የከበሩ ድንጋዮችን ያወጡ ነበር። የግብፅ ነገሥታት ድል አድርገው በያዟቸው አካባቢዎች ያሉ የማዕድን ማውጫ ቦታዎችን በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ኢዮብ፣ በእሱ ዘመን የነበሩ ሰዎች ውድ የሆኑ ማዕድናትን ለማግኘት ጉድጓድ ይቆፍሩና ከመሬት በታች መተላለፊያ ያበጁ የነበረው እንዴት እንደሆነ ገልጿል። ኢዮብ፣ ከመሬት ተቆፍረው ከሚወጡት ማዕድናት መካከል ሰንፔርንና ቶጳዝዮንን ለይቶ ጠቅሷል።—ኢዮብ 28:1-11, 19
በዘፀአት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ፣ እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው ሲወጡ የግብፃውያንን ውድ ንብረቶች ‘በዝብዘው እንደወሰዱ’ ይናገራል። (ዘፀአት 12:35, 36) በመሆኑም እስራኤላውያን በሊቀ ካህኑ የደረት ኪስ ላይ የተደረጉትን የከበሩ ድንጋዮች ያገኙት ከግብፅ ሊሆን ይችላል።
(ዘፀአት 28:38) በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ አሮንም አንድ ሰው ቅዱስ ከሆኑ ነገሮች ይኸውም እስራኤላውያን ቅዱስ ስጦታ አድርገው በሚያቀርቧቸው ጊዜ ከሚቀድሷቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ለሚፈጽመው ስህተት ተጠያቂ ይሆናል። በይሖዋም ፊት ተቀባይነት እንዲያገኙ ዘወትር በግንባሩ ላይ መሆን ይኖርበታል።
it-1 1130 አን. 2
ቅድስና
እንስሳትና ሰብሎች። በኩር የሆኑ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች ለይሖዋ የተቀደሱ ተደርገው ስለሚቆጠሩ ሊዋጁ አይገባም ነበር። መሥዋዕት ሆነው ከቀረቡ በኋላ የተወሰነው ክፍል ቅዱስ ለሆኑት ካህናት ይሰጣል። (ዘኁ 18:17-19) የፍሬ በኩራት እና አሥራትም መሥዋዕትና ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የተለዩ ስጦታዎች ሆነው የቀረቡ በመሆናቸው ቅዱስ ነበሩ። (ዘፀ 28:38) ለይሖዋ የተቀደሱ ነገሮች በሙሉ ቅዱስ በመሆናቸው ቀላል ተደርገው ሊታዩ አሊያም ደግሞ ለተራ ወይም ቅዱስ ላልሆነ አገልግሎት ሊውሉ አይገባም አበር። ስለ አሥራት የሚገልጸው ሕግ ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ከስንዴ ሰብሉ አሥራት አድርጎ የሚሰጠውን ከለየ በኋላ እሱ ወይም ከቤተሰቡ አባላት መካከል አንዱ ባለማወቅ ከተለየው ስንዴ ወስዶ ምግብ ለማብሰል ወይም ለሌላ ዓላማ ቢጠቀምበት ግለሰቡ የተቀደሱ ነገሮችን በተመለከተ የወጣውን የአምላክ ሕግ በመተላለፍ በደል ይጠየቃል። ሕጉ ግለሰቡ ከመንጋው መካከል እንከን የሌለበትን አውራ በግ መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ እንዲሁም የዋጋውን 20 በመቶ ጨምሮ ለቅዱሱ ስፍራ ካሳ እንዲሰጥ ያዛል። ይህም ለይሖዋ የተሰጡ ቅዱስ ነገሮች በታላቅ አክብሮት ሊያዙ እንደሚገባ ያሳያል።—ዘሌ 5:14-16
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 27:1-21) “ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱም አምስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር እንጨት ትሠራለህ። መሠዊያው አራቱም ጎኖቹ እኩል፣ ከፍታው ደግሞ ሦስት ክንድ መሆን አለበት። 2 በአራቱ ማዕዘኖቹ ላይ ቀንዶች ትሠራለታለህ፤ ቀንዶቹም የመሠዊያው ክፍል ይሆናሉ፤ መሠዊያውንም በመዳብ ትለብጠዋለህ። 3 አመዱን ማስወገጃ ባልዲዎችን፣ አካፋዎችን፣ ሳህኖችን፣ ሹካዎችንና መኮስተሪያዎችን ትሠራለህ፤ ዕቃዎቹንም ሁሉ ከመዳብ ትሠራቸዋለህ። 4 ለመሠዊያው እንደ መረብ አድርገህ የመዳብ ፍርግርግ ትሠራለታለህ፤ በፍርግርጉ በአራቱም ማዕዘኖቹ ላይ አራት የመዳብ ቀለበቶችን ትሠራለታለህ። 5 ፍርግርጉንም ከመሠዊያው ጠርዝ ወደ ታች ወረድ አድርገህ ታስቀምጠዋለህ፤ ፍርግርጉም መሠዊያው መሃል አካባቢ ይሆናል። 6 ለመሠዊያው የሚሆኑ መሎጊያዎችን ከግራር እንጨት ትሠራለህ፤ በመዳብም ትለብጣቸዋለህ። 7 መሎጊያዎቹም ቀለበቶቹ ውስጥ ይገባሉ፤ መሠዊያውን በምትሸከሙበትም ጊዜ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ጎኖቹ በኩል ይሆናሉ። 8 መሠዊያውንም ባዶ ሣጥን አስመስለህ ከሳንቃ ትሠራዋለህ። ልክ ተራራው ላይ ባሳየህ መሠረት ይሠራ። 9 “የማደሪያ ድንኳኑን ግቢ ትሠራለህ። በስተ ደቡብ በኩል የሚገኘው፣ ፊቱ በደቡብ አቅጣጫ ያለው የግቢው ጎን በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ይኖሩታል፤ የአንዱ ጎን ርዝመት 100 ክንድ ይሆናል። 10 ግቢው 20 ቋሚዎችና ከመዳብ የተሠሩ 20 መሰኪያዎች ይኖሩታል። በቋሚዎቹ ላይ ያሉት ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎቻቸው ደግሞ ከብር የተሠሩ ይሆናሉ። 11 በስተ ሰሜን በኩል በሚገኘው ጎን ያሉት መጋረጃዎችም ርዝመታቸው 100 ክንድ ይሆናል፤ እንዲሁም 20 ቋሚዎችና ለቋሚዎቹ የሚሆኑ ከመዳብ የተሠሩ 20 መሰኪያዎች ይኖራሉ፤ በቋሚዎቹም ላይ ማንጠልጠያዎችና ማያያዣዎች ይኖራሉ። 12 በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በግቢው ወርድ ልክ 50 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ አሥር ቋሚዎችና አሥር መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል። 13 በስተ ምሥራቅ አቅጣጫ በፀሐይ መውጫ በኩል ያለው የግቢው ወርድ 50 ክንድ ነው። 14 በአንዱ በኩል 15 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል። 15 በሌላኛውም በኩል 15 ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ይኖራሉ፤ ሦስት ቋሚዎችና ሦስት መሰኪያዎችም ይኖሯቸዋል። 16 “የግቢው መግቢያ ከሰማያዊ ክር፣ ከሐምራዊ ሱፍ፣ ከደማቅ ቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ የበፍታ ድር ተሸምኖ የተሠራ 20 ክንድ ርዝመት ያለው መከለያ ይኑረው፤ አራት ቋሚዎችና ለቋሚዎቹ የሚሆኑ አራት መሰኪያዎችም ይኑሩት። 17 በግቢው ዙሪያ ያሉት ቋሚዎች በሙሉ ከብር የተሠሩ መቆንጠጫዎችና ከብር የተሠሩ ማንጠልጠያዎች ይኖሯቸዋል፤ መሰኪያዎቻቸው ግን ከመዳብ የተሠሩ ይሆናሉ። 18 ግቢው ርዝመቱ 100 ክንድ፣ ወርዱ 50 ክንድ ሆኖ በቀጭኑ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ የተሠሩ 5 ክንድ ከፍታ ያላቸው መጋረጃዎች ይኖሩታል፤ ከመዳብ የተሠሩ መሰኪያዎችም ይኑሩት። 19 በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት የሚውሉት ቁሳቁሶችና ዕቃዎች በሙሉ እንዲሁም የድንኳኑ ካስማዎችና የግቢው ካስማዎች በሙሉ ከመዳብ የተሠሩ ይሆናሉ። 20 “አንተም መብራቶቹ ያለማቋረጥ እንዲበሩ ለመብራት የሚሆን ተጨቅጭቆ የተጠለለ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ እስራኤላውያንን ታዛቸዋለህ። 21 አሮንና ወንዶች ልጆቹ መብራቶቹ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ በምሥክሩ አጠገብ ካለው መጋረጃ ውጭ ከምሽት አንስቶ እስከ ጠዋት ድረስ በይሖዋ ፊት እንዲበሩ ያደርጋሉ። ይህ እስራኤላውያን በትውልዶቻቸው ሁሉ የሚፈጽሙት ዘላቂ ደንብ ነው።
ከመስከረም 28–ጥቅምት 4
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 29–30
“ለይሖዋ የሚሰጥ መዋጮ”
(ዘፀአት 30:11, 12) ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 12 “የሕዝብ ቆጠራ በማካሄድ የእስራኤልን ልጆች በምትቆጥርበት ጊዜ ሁሉ እያንዳንዱ ሰው በቆጠራው ወቅት ለይሖዋ ስለ ሕይወቱ ቤዛ መስጠት አለበት። ይህን የሚያደርጉት በሚመዘገቡበት ጊዜ መቅሰፍት እንዳይመጣባቸው ነው።
it-2 764-765
ምዝገባ
በሲና። በይሖዋ ትእዛዝ መሠረት የመጀመሪያው ምዝገባ የተካሄደው እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር በሲና በሰፈሩበት ወቅት ነበር። በዚህ ሥራ ሙሴን ለማገዝ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ መሪ ተመርጦ ነበር፤ እነዚህ መሪዎች የየነገዳቸውን ምዝገባ የመከታተል ኃላፊነት ነበረባቸው። ለወታደራዊ አገልግሎት ብቁ የሆኑ ዕድሜያቸው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ወንዶች ተመዝግበው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሕጉ የተመዘገቡት በሙሉ በማደሪያው ድንኳን ለሚቀርበው አገልግሎት ግማሽ ሰቅል (1.10 የአሜሪካ ዶላር) ግብር እንዲከፍሉ ያዝዝ ነበር። (ዘፀ 30:11-16፤ ዘኁ 1:1-16, 18, 19) የተመዘገቡት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 603,550 ነበር፤ ይህ ቁጥር በምድሪቱ ውስጥ ርስት የማይኖራቸውን ሌዋውያንን አይጨምርም። ሌዋውያን ለቤተ መቅደሱ ግብር መክፈልም ሆነ ወደ ሠራዊቱ መቀላቀል አይጠበቅባቸውም ነበር።—ዘኁ 1:44-47፤ 2:32, 33፤ 18:20, 24
(ዘፀአት 30:13-15) የተመዘገቡት ሁሉ የሚሰጡት ይህን ነው፦ እንደ ቋሚ መለኪያ ሆኖ በሚያገለግለው በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት ግማሽ ሰቅል ይሰጣሉ። አንድ ሰቅል ሃያ ጌራ ነው። ለይሖዋ የሚሰጠው መዋጮ ግማሽ ሰቅል ነው። 14 ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኗቸው የተመዘገቡት ሁሉ ለይሖዋ መዋጮ ይሰጣሉ። 15 ለሕይወታችሁ ማስተሰረያ እንዲሆን ለይሖዋ መዋጮ በምትሰጡበት ጊዜ ባለጸጋው ከግማሽ ሰቅል አብልጦ፣ ችግረኛውም ከግማሽ ሰቅል አሳንሶ አይስጥ።
it-1 502
መዋጮ
ሕጉ አንዳንድ መዋጮዎች እንዲሰጡ ያዝዝ ነበር። ሙሴ እስራኤላውያንን በቆጠረበት ወቅት ዕድሜው 20 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ወንድ ሁሉ ስለ ሕይወቱ ቤዛ የሚሆን “በቅዱሱ ስፍራ ሰቅል መሠረት ግማሽ ሰቅል [1.10 ዶላር ገደማ]” ብር መስጠት ነበረበት። ይህ ገንዘብ ለሕይወታቸው ማስተሰረያ እንዲሆን እንዲሁም “በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት” እንዲውል “ለይሖዋ መዋጮ” ሆኖ ይሰጥ ነበር። (ዘፀ 30:11-16) የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የሆነው ጆሴፈስ እንደጻፈው (ዘ ጁዊሽ ዎር VII, 218 [vi, 6]) ይህ “የተቀደሰ ግብር” ከዚያ በኋላ በየዓመቱ ይከፈል ነበር።—2ዜና 24:6-10፤ ማቴ 17:24፤ ግብር የሚለውን ተመልከት።
(ዘፀአት 30:16) ለሕይወታችሁ ማስተሰረያ በመሆን በይሖዋ ፊት ለእስራኤላውያን እንደ መታሰቢያ ሆኖ እንዲያገለግል ለማስተሰረያ የቀረበውን የብር ገንዘብ ከእስራኤላውያን ወስደህ በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ ለሚቀርበው አገልግሎት ትሰጠዋለህ።”
ይህን ያውቁ ኖሯል?
በኢየሩሳሌም በነበረው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚከናወነው አገልግሎት የሚያስፈልገው ገንዘብ ይገኝ የነበረው እንዴት ነው?
በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚካሄዱት አብዛኞቹ አገልግሎቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘው ከሕዝቡ ከሚሰበሰብ ግብር ሲሆን በዋነኝነት ደግሞ ከሁሉም ሰው ከሚጠበቅ አሥራት ነበር። ሆኖም ሌሎች የግብር ዓይነቶችም ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የመገናኛው ድንኳን በተሠራበት ወቅት “ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት” ወይም መዋጮ እንዲሆን ግማሽ ሰቅል ብር ከእያንዳንዱ የተመዘገበ እስራኤላዊ እንዲሰበስብ ይሖዋ ለሙሴ ነግሮት ነበር።—ዘፀአት 30:12-16
ከዚያ ጊዜ በኋላ እያንዳንዱ አይሁዳዊ መጠኑ የተወሰነ ዓመታዊ የቤተ መቅደስ ግብር መክፈሉ ልማድ የሆነ ይመስላል። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን ከዓሣው አፍ በተገኘው ሳንቲም ይህን ግብር እንዲከፍል አዝዞት ነበር።—ማቴዎስ 17:24-27
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 29:10) “ከዚያም ወይፈኑን በመገናኛ ድንኳኑ ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ወንዶች ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።
it-1 1029 አን. 4
እጅ
እጅ መጫን። በአንድ ሰው ወይም በአንድ ነገር ላይ እጅ መጫን ለተለያየ ዓላማ ያገለግል ነበር። በጥቅሉ ሲታይ እጅ መጫን አንድን ሰው ወይም አንድን ነገር መምረጥን ወይም በሆነ መንገድ እውቅና መስጠትን ያመለክታል። የክህነት ሥርዓቱ በተቋቋመበት ወቅት አሮንና ልጆቹ መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው ወይፈንና በሁለቱ በጎች ላይ እጃቸውን ጭነው ነበር፤ ይህም እነዚህ እንስሳት መሥዋዕት የተደረጉት አሮንና ልጆቹ ለይሖዋ አምላክ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ሲባል መሆኑን እውቅና እንደሰጡ ያመለክታል። (ዘፀ 29:10, 15, 19፤ ዘሌ 8:14, 18, 22) ሙሴ በአምላክ ትእዛዝ መሠረት ኢያሱ እሱን እንዲተካ ሲሾመው እጁን በኢያሱ ላይ ጭኖበት ነበር፤ ከዚያም ኢያሱ እስራኤልን በተገቢው መንገድ መምራት እንዲችል ‘በጥበብ መንፈስ ተሞላ።’ (ዘዳ 34:9) አንዳንድ ሰዎች በረከት እንዲያገኙ ለማድረግም እጅ ይጫንባቸው ነበር። (ዘፍ 48:14፤ ማር 10:16) ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ሰዎችን ሲፈውስ ዳስሷቸዋል ወይም እጁን ጭኖባቸዋል። (ማቴ 8:3፤ ማር 6:5፤ ሉቃስ 13:13) አንዳንድ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበሉት ሐዋርያት እጃቸውን ሲጭኑባቸው ነበር።—ሥራ 8:14-20፤ 19:6
(ዘፀአት 30:31-33) “አንተም ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ‘በትውልዶቻችሁ ሁሉ ይህ ምንጊዜም ለእኔ ቅዱስ የቅብዓት ዘይት ይሆናል። 32 ይህ ማንም ሰው ሰውነቱን የሚቀባው አይደለም፤ እንዲሁም በተመሳሳይ መንገድ በመቀመም እንዲህ ያለ ቅባት ማዘጋጀት የለባችሁም። ይህ የተቀደሰ ነገር ነው። ለእናንተም ምንጊዜም የተቀደሰ ይሆናል። 33 ይህን የመሰለ ቅባት የሚሠራና ያልተፈቀደለትን ሰው የሚቀባ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረግ።’”
it-1 114 አን. 1
ቅቡዕ፣ መቀባት
ይሖዋ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ላይ የቅብዓት ዘይት የሚቀመምበትን መንገድ ገልጾ ነበር። ዘይቱ የሚዘጋጀው ምርጥ የሆኑ ነገሮችን ማለትም ከርቤ፣ ጣፋጭ ቀረፋ፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ጠጅ ሣር፣ ብርጉድና የወይራ ዘይት ልዩ በሆነ መንገድ በማዋሃድ ነበር። (ዘፀ 30:22-25) ማንኛውም ሰው ይህን ውህድ አዘጋጅቶ ቅዱስ ላልሆነ ወይም ላልተፈቀደ ዓላማ ቢጠቀምበት በሞት ይቀጣ ነበር። (ዘፀ 30:31-33) ይህም በቅዱሱ ዘይት በመቀባት የሚሰጥ ሹመት ያለውን የላቀ ቦታና ቅድስና ያሳያል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 29:31-46) “ለክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርበውን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ። 32 አሮንና ወንዶች ልጆቹ የአውራውን በግ ሥጋና በቅርጫቱ ውስጥ ያለውን ቂጣ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ይበሉታል። 33 እነሱን ካህናት አድርጎ ለመሾምና ለመቀደስ ማስተሰረያ ሆነው የቀረቡትን ነገሮች ይበላሉ። ሆኖም እነዚህ ነገሮች የተቀደሱ ስለሆኑ ያልተፈቀደለት ሰው ሊበላቸው አይችልም። 34 ለክህነት ሹመት ሥርዓቱ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው ሥጋና ቂጣ ተርፎ ያደረ ካለ የተረፈውን በእሳት አቃጥለው። የተቀደሰ ስለሆነ መበላት የለበትም። 35 “እኔ ባዘዝኩህ ሁሉ መሠረት ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ በዚሁ መንገድ ታደርግላቸዋለህ። እነሱን ካህናት አድርገህ ለመሾም ሰባት ቀን ይፈጅብሃል። 36 ለማስተሰረያ እንዲሆን የኃጢአት መባ የሚሆነውን በሬ በየዕለቱ ታቀርባለህ፤ ለመሠዊያውም ማስተሰረያ በማቅረብ መሠዊያውን ከኃጢአት ታነጻዋለህ፤ መሠዊያውን ለመቀደስም ቀባው። 37 መሠዊያውን ለማስተሰረይ ሰባት ቀን ይፈጅብሃል፤ እጅግ ቅዱስ መሠዊያ እንዲሆንም ቀድሰው። መሠዊያውን የሚነካ ማንኛውም ሰው ቅዱስ መሆን አለበት። 38 “በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው እነዚህን ይሆናል፦ አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት የበግ ጠቦቶችን በየቀኑ ሳታቋርጥ ታቀርባለህ። 39 አንደኛውን የበግ ጠቦት ጠዋት ላይ ታቀርበዋለህ፤ ሌላኛውን የበግ ጠቦት ደግሞ አመሻሹ ላይ ታቀርበዋለህ። 40 ተጨቅጭቆ በተጠለለ አንድ አራተኛ ሂን ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አንድ አሥረኛ የላመ ዱቄትና ለመጠጥ መባ የሚሆን አንድ አራተኛ ሂን የወይን ጠጅ ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋር ይቅረብ። 41 ሁለተኛውንም የበግ ጠቦት ልክ ማለዳ ላይ ከምታቀርባቸው ጋር ተመሳሳይ ከሆኑ የእህልና የመጠጥ መባዎች ጋር አመሻሹ ላይ ታቀርበዋለህ። ይህን ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ይኸውም ለይሖዋ በእሳት የሚቀርብ መባ አድርገህ ታቀርበዋለህ። 42 ይህም እኔ እናንተን ለማነጋገር ራሴን በምገልጥበት በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ በይሖዋ ፊት ዘወትር የሚቀርብ የሚቃጠል መባ ይሆናል። 43 “እኔም በዚያ ራሴን ለእስራኤላውያን እገልጣለሁ፤ ያም ስፍራ በክብሬ የተቀደሰ ይሆናል። 44 መገናኛ ድንኳኑንና መሠዊያውን እቀድሰዋለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እቀድሳቸዋለሁ። 45 እኔም በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ። 46 እነሱም በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ። እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ።