ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ
15 አሁን ደግሞ ወንድሞች፣ የነገርኳችሁን ምሥራች ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፤+ ይህ ምሥራች እናንተም የተቀበላችሁትና የቆማችሁለት ነው። 2 በተጨማሪም እኔ የነገርኳችሁን ምሥራች አጥብቃችሁ የምትይዙ ከሆነ በምሥራቹ ትድናላችሁ፤ አለዚያ አማኝ የሆናችሁት በከንቱ ነው ማለት ነው።
3 እኔ የተቀበልኩትን ከሁሉ በላይ የሆነውን ነገር ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ይኸውም ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤+ 4 ደግሞም ተቀበረ፤+ ቅዱሳን መጻሕፍት+ እንደሚሉትም በሦስተኛው ቀን+ ተነሳ፤+ 5 ለኬፋ*+ ከዚያም ለአሥራ ሁለቱ ታየ።+ 6 በኋላ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች የታየ+ ሲሆን አንዳንዶቹ በሞት ቢያንቀላፉም አብዛኞቹ ግን አሁንም ከእኛ ጋር አሉ። 7 ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤+ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ።+ 8 በመጨረሻ ደግሞ እንደ ጭንጋፍ ለምቆጠር ለእኔ ተገለጠልኝ።+
9 እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ።+ 10 ሆኖም አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው። አምላክ ለእኔ ያሳየው ጸጋም ከንቱ ሆኖ አልቀረም፤ እንዲያውም ከሁሉም የበለጠ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ይሁንና ይህን ያደረገው ከእኔ ጋር ያለው የአምላክ ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። 11 እንግዲህ እኔም ሆንኩ እነሱ የምንሰብከው በዚህ መንገድ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት በዚህ መንገድ ነው።
12 ታዲያ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ እየተሰበከ ከሆነ+ ከእናንተ መካከል አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? 13 የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሳም ማለት ነዋ! 14 ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ ስብከታችን ከንቱ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። 15 ከዚህም በተጨማሪ ሙታን በእርግጥ የማይነሱ ከሆነ አምላክ ክርስቶስን ከሞት ስላላስነሳው፣ ክርስቶስን አስነስቶታል+ ብለን ስንመሠክር ሐሰተኞች የአምላክ ምሥክሮች ሆነን ተገኝተናል ማለት ነው።+ 16 ምክንያቱም ሙታን የማይነሱ ከሆነ ክርስቶስም ከሞት አልተነሳም ማለት ይሆናል። 17 ክርስቶስ ካልተነሳ ደግሞ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም ከነኃጢአታችሁ ትኖራላችሁ።+ 18 ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው በሞት ያንቀላፉትም ጠፍተው ቀርተዋል ማለት ነው።+ 19 በክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ለዚህ ሕይወት ብቻ ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን።
20 ይሁንና ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል።+ 21 ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል+ ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው።+ 22 ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ+ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉና።+ 23 ሆኖም እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤+ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።+ 24 ከዚያም ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን አጥፍቶ መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ በሚያስረክብበት ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል።+ 25 አምላክ ጠላቶችን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግለት ድረስ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ይገባዋልና።+ 26 የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል።+ 27 አምላክ “ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዝቶለታልና።”+ ሆኖም ‘ሁሉም ነገር ተገዝቷል’+ ሲል ሁሉንም ነገር ያስገዛለትን እንደማይጨምር ግልጽ ነው።+ 28 ይሁንና ሁሉም ነገር ከተገዛለት በኋላ ወልድ ራሱ ሁሉን ነገር ላስገዛለት ራሱን ያስገዛል፤+ ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን ነው።+
29 አለዚያማ ለመሞት ብለው በመጠመቅ ምን የሚያተርፉት ነገር ይኖራል?+ ሙታን ፈጽሞ የማይነሱ ከሆነ እነሱም ለመሞት ብለው የሚጠመቁበት ምን ምክንያት አለ? 30 እኛስ ሁልጊዜ ለአደጋ ተጋልጠን የምንኖረው ለምንድን ነው?+ 31 እኔ በየቀኑ ሞትን እጋፈጣለሁ። ወንድሞች፣ ይህ እውነት መሆኑን የጌታችን የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሆናችሁት በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክህት አረጋግጥላችኋለሁ። 32 እንደ ሌሎች ሰዎች* በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር ከታገልኩ፣+ እንዲህ ማድረጌ ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ሙታን የማይነሱ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ።”+ 33 አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል* ያበላሻል።+ 34 ጽድቅ የሆነውን በማድረግ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአት መሥራትን ልማድ አታድርጉ፤ አንዳንዶች ስለ አምላክ አያውቁምና። ይህን የምላችሁ ላሳፍራችሁ ብዬ ነው።
35 ይሁንና አንድ ሰው “ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው? ከሞት የሚነሱትስ ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው?” ይል ይሆናል።+ 36 አንተ ማስተዋል የጎደለህ! የምትዘራው መጀመሪያ ካልሞተ ሕያው ሊሆን አይችልም። 37 ደግሞም ስንዴም ሆነ ሌላ ዓይነት እህል ስትዘራ የምትዘራው ዘሩን እንጂ በኋላ የሚያድገውን አካል አይደለም፤ 38 ሆኖም አምላክ የፈለገውን አካል ይሰጠዋል፤ ለእያንዳንዱም ዘር የራሱን አካል ይሰጠዋል። 39 ሥጋ ሁሉ አንድ ዓይነት አይደለም፤ በመሆኑም የሰው ሥጋ አለ፣ የከብት ሥጋ አለ፣ የወፎች ሥጋ አለ እንዲሁም የዓሣ ሥጋ አለ። 40 በተጨማሪም ሰማያዊ አካላት አሉ፤+ ምድራዊ አካላትም አሉ፤+ ሆኖም የሰማይ አካላት የራሳቸው ክብር አላቸው፤ የምድር አካላት ደግሞ ሌላ ዓይነት ክብር አላቸው። 41 ፀሐይ የራሷ ክብር አላት፤ ጨረቃ ደግሞ ሌላ ዓይነት ክብር አላት፤+ ከዋክብትም ሌላ ዓይነት ክብር አላቸው፤ እንዲያውም የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል።
42 ስለዚህ የሙታን ትንሣኤም እንደዚሁ ነው። የሚዘራው የሚበሰብስ ነው፤ የሚነሳው የማይበሰብስ ነው።+ 43 የሚዘራው በውርደት ነው፤ የሚነሳው በክብር ነው።+ የሚዘራው በድካም ነው፤ የሚነሳው በኃይል ነው።+ 44 የሚዘራው ሥጋዊ አካል ነው፤ የሚነሳው መንፈሳዊ አካል ነው። ሥጋዊ አካል ካለ መንፈሳዊ አካልም አለ። 45 ስለዚህ “የመጀመሪያው ሰው አዳም ሕያው ሰው* ሆነ” ተብሎ ተጽፏል።+ የኋለኛው አዳም ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።+ 46 ይሁንና የመጀመሪያው መንፈሳዊው አይደለም። የመጀመሪያው ሥጋዊው ነው፤ የኋለኛው ደግሞ መንፈሳዊው ነው። 47 የመጀመሪያው ሰው ከምድር የተገኘና ከአፈር የተሠራ ነው፤+ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ከሰማይ ነው።+ 48 ከአፈር የተሠሩት ከአፈር እንደተሠራው ናቸው፤ ሰማያዊ የሆኑትም ከሰማይ እንደመጣው ናቸው።+ 49 ከአፈር የተሠራውን ሰው መልክ እንደመሰልን ሁሉ+ የሰማያዊውንም መልክ እንመስላለን።+
50 ይሁን እንጂ ወንድሞች ይህን እነግራችኋለሁ፦ ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም፤ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። 51 እነሆ፣ አንድ ቅዱስ ሚስጥር እነግራችኋለሁ፦ በሞት የምናንቀላፋው ሁላችንም አይደለንም፤ ነገር ግን ሁላችንም እንለወጣለን፤+ 52 የመጨረሻው መለከት በሚነፋበት ወቅት ድንገት፣ በቅጽበተ ዓይን* እንለወጣለን። መለከት ይነፋል፤+ ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሳሉ፤ እኛም እንለወጣለን። 53 ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሊለብስ ይገባዋልና፤+ ይህ ሟች የሆነው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋል።+ 54 ሆኖም ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስና ይህ ሟች የሆነው የማይሞተውን ሲለብስ “ሞት ለዘላለም ተዋጠ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል።+ 55 “ሞት ሆይ፣ ድል አድራጊነትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?”+ 56 ለሞት የሚዳርገው መንደፊያ ኃጢአት ነው፤+ ለኃጢአት ኃይል የሚሰጠው ደግሞ ሕጉ ነው።+ 57 ሆኖም አምላክ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ድል ስለሚያጎናጽፈን የተመሰገነ ይሁን!+
58 ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤+ አትነቃነቁ፤ እንዲሁም ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ አለመሆኑን አውቃችሁ+ ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።+