የማቴዎስ ወንጌል
5 ሕዝቡንም ባየ ጊዜ ወደ ተራራ ወጣ፤ በዚያ ከተቀመጠ በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ መጡ። 2 ከዚያም ኢየሱስ መናገር ጀመረ፤ እንዲህም ሲል አስተማራቸው፦
3 “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ* ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
4 “የሚያዝኑ ደስተኞች ናቸው፤ መጽናኛ ያገኛሉና።+
5 “ገሮች*+ ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።+
6 “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፤+ ይጠግባሉና።*+
7 “መሐሪዎች ደስተኞች ናቸው፤+ ምሕረት ይደረግላቸዋልና።
8 “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤+ አምላክን ያያሉና።
9 “ሰላም ፈጣሪዎች* ደስተኞች ናቸው፤+ የአምላክ ልጆች ይባላሉና።
10 “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው፤+ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።
11 “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲነቅፏችሁ፣+ ስደት ሲያደርሱባችሁና+ ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።+ 12 በሰማያት የሚጠብቃችሁ ሽልማት ታላቅ ስለሆነ+ ሐሴት አድርጉ፤ በደስታም ፈንጥዙ፤+ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ ስደት አድርሰውባቸው ነበርና።+
13 “እናንተ የምድር ጨው+ ናችሁ፤ ሆኖም ጨው የጨውነት ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን እንዴት መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ከዚህ በኋላ ወደ ውጭ ተጥሎ+ በሰው ከመረገጥ በቀር ለምንም ነገር አያገለግልም።
14 “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ።+ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። 15 ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ* አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፤ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል።+ 16 በተመሳሳይም ሰዎች መልካም ሥራችሁን+ አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ+ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።+
17 “ሕጉን ወይም የነቢያትን ቃል ልሽር እንደመጣሁ አድርጋችሁ አታስቡ። ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም።+ 18 እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይና ምድር ቢያልፉ እንኳ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እስኪከናወኑ ድረስ ከሕጉ አነስተኛዋ ፊደል ወይም የአንዷ ፊደል ጭረት ሳትፈጸም አትቀርም።+ 19 በመሆኑም አነስተኛ ከሆኑት ከእነዚህ ትእዛዛት አንዷን የሚጥስና ሌሎች ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ* ይባላል። እነዚህን ትእዛዛት የሚያከብርና የሚያስተምር ሰው ግን በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ* ይባላል። 20 ጽድቃችሁ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ+ በምንም ዓይነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደማትገቡ+ ልነግራችሁ እወዳለሁ።
21 “በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘አትግደል፤+ ሰው የገደለ ሁሉ ግን በፍርድ ቤት ይጠየቃል’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ ተቆጥቶ ቁጣው የማይበርድለት+ ሁሉ በፍርድ ቤት ይጠየቃል፤ ወንድሙንም ጸያፍ በሆነ ቃል የሚያጥላላ ሁሉ በከፍተኛ ፍርድ ቤት* ይጠየቃል፤ ‘አንተ የማትረባ ጅል’ የሚለው ደግሞ ለእሳታማ ገሃነም* ሊዳረግ ይችላል።+
23 “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ+ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ 24 መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።+
25 “ክስ ከመሠረተብህ ባላጋራ ጋር ወደ ፍርድ ቤት እየሄዳችሁ ሳለ ፈጥነህ ታረቅ፤ አለዚያ ባላጋራህ ለዳኛው፣ ዳኛው ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ዘብ አሳልፎ ይሰጥህና እስር ቤት ልትገባ ትችላለህ።+ 26 እውነት እልሃለሁ፣ የመጨረሻዋን ሳንቲምህን* ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ፈጽሞ ከዚያ አትወጣም።
27 “‘አታመንዝር’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 28 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት+ ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።+ 29 ስለዚህ ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+ 30 እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው።+ መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም* ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።+
31 “በተጨማሪም ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ይስጣት’+ ተብሏል። 32 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና* ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ ምንዝር ለመፈጸም እንድትጋለጥ ያደርጋታል፤ እንዲሁም በዚህ መንገድ የተፈታችን ሴት የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።+
33 “ከዚህም ሌላ በጥንት ዘመን ለነበሩት ‘በከንቱ አትማል፤+ ይልቁንም ለይሖዋ* የተሳልከውን ፈጽም’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 34 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ፈጽሞ አትማሉ።+ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፤ 35 በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግሩ ማሳረፊያ ነችና፤+ በኢየሩሳሌምም ቢሆን አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ነችና።+ 36 በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከፀጉርህ አንዷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ማድረግ አትችልምና። 37 ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤+ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው+ ነው።
38 “‘ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ’+ እንደተባለ ሰምታችኋል። 39 እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ክፉን ሰው አትቃወሙት፤ ከዚህ ይልቅ ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን ደግሞ አዙርለት።+ 40 አንድ ሰው ፍርድ ቤት ሊያቀርብህና እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢፈልግ መደረቢያህንም ጨምረህ ስጠው፤+ 41 እንዲሁም አንድ ባለሥልጣን አንድ ኪሎ ሜትር* እንድትሄድ ቢያስገድድህ* ሁለት ኪሎ ሜትር አብረኸው ሂድ። 42 ለሚለምንህ ስጥ፤ ሊበደርህ የሚፈልገውንም ሰው* ፊት አትንሳው።+
43 “‘ባልንጀራህን ውደድ፤+ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። 44 እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ+ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤+ 45 ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤+ እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል።+ 46 የሚወዷችሁን ብቻ ብትወዱ ምን ብድራት ታገኛላችሁ?+ ቀረጥ ሰብሳቢዎችስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 47 ደግሞስ ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም ብትሉ ምን የተለየ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ የሚያደርጉት ይህንኑ አይደለም? 48 በሰማይ ያለው አባታችሁ ፍጹም* እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።+